Wednesday, April 28, 2010

የወንጌል ቃል የሚያስፈራው በእምነት ደካማ የሆነን ብቻ ነው። ቁጥር ፳፬

እውነትን ማጣመም ይቻል ይሆናል። መግደልና መቅበር ግን አስቸጋሪ ነው። የተለያየ ውሸትን በመወርወር አንዱ ይለጠፍና  ይቀር ይሆናል ብለው በሚያልሙ የቤተክርስቲያን መሰባሰብና  ሕዝቡ በሰላም ማምለኩ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣቱ እንቅልፍ በሚነሳቸው ግለሰቦች ዛሬም እንደትላንቱ የሸር ቱሻ እየገመዱ የሞቀ ቤት እያፈረሱ ይገኛሉ። አለቆቻቸው የቤተክርስቲያን ቦርድ ተመራጮች የበደል አለንጋቸውን እያወናጨፉ እነዚህን ግለሰቦች እንዲጮሁና እንዲናከሱ ትእዛዝም እንዳሰተላለፉላቸው ከድርጊታቸው መገንዘብ ይቻላል።

ውድ የቤተክርስቲያን አባላት። ባለፈው ቅዳሜ ከቤተክርስቲያን እንዲሰናበቱ የተደረጉትና  በቤተክርስቲያን አካባቢ እንኴን ዝር እንዳይሉ ቦርዱ ፖሊስ ጠርቶ ያስፈረማቸው ካህን ስለሁኔታው ሲናገሩ ያዳመጡ ግለሰቦች እንደነገሩን ከስራ  እንደተባረሩ ሲነገራቸው "መባረሬ መልካም ለእምነቴ የምከፍለው የጸጋ ዋጋ ነውና ቅር  አልሰኝም  ነገር ግን የቤተሰቤን የሕጋዊ ወረቀት ሂደት ( IMMIGRATION PROCESESSE) አስመልክቶ እያለቀ ያለ ነገር በመሆኑ ተባበሩኝ"  ብለው ቢማጸኑ እንኴን እንቢኝ እንደተባሉ  ስንሰማ እንደ ስደተኛነታችን ወላጅ እንደመሆናችን ከልብ አዝነናል። ውድ አንባብያን። እዚህ አገር ስደተኞችንም  ሆነ  የመኖሪያ ወረቀት የሌላቸውን ግለሰቦች  የሚረዱት የተለያዩ  ቤተክርስቲያናቶች መሆናቸው እየታወቀ፡ የኛ የቤተክርስቲያን መሪነን ባዮች ግን ፈቃድ ለማግኘት የተቃረቡትን አባት ከነልጆቻቸው ወደአገራቸው ለመመለስ ሽር ጉድ ማለታቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። ልጅ ያላችሁ ቤተሰብ የሆናችሁ የመኖሪያ  ወረቀት ችግር የነበረባችሁ ሁሉ ሊሰማችሁ ይገባል። ባገራችን ወንጀለኛ እንኴን ነፍሱን የሙጥኝ የሚለው ቤተክርስቲያን ተጠግቶ  እንደነበር እየተረሳን የመጣ ይመስላል::

አንድ ግለሰብ እዚህ አሜሪካን አገር ያሉ የስፓኒሽ ተወላጆችና  የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ ተጋዳዎች በአሜሪካ  ውስጥ ወደ 12 ሚሊዮን የሚደርስ የመኖሪያ  ወረቀት የሌለውን ግለሰብ የመኖሪያ  ወረቀት እንዲሰጠው መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ ሲያጨናንቁ እያየን እያለ፡ የኛ የቤተክርስቲያን መሪዎች ግን የካህኑን የመኖሪያ  ወረቀት ጉዳይ አስመልክቶ ለኢሚግሬሽን ደብዳቤ  በመጻፍ ለማጨናገፍ  ይጣደፋሉ። ይህ ደግሞ  "ፈጣሪ አንዱን ኢትዮጵያዊ አግኝቶ ምን ላድርግልህ?  ጠይቀኝና እፈጽምልሃለሁ  ያደረኩልህን እጥፍ ደግሞ  ለጔደኛህ አደርግለታለሁ ቢለው አንድ ዓይኔን  አውጣልኝ"  አለው የሚለውን ቀልድ ያስታውሷል አለን። አልሳቅንም ፈዘን ቀረን እንጂ።

ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች እያነሱ የመጡት ጥያቄ አባል እንሁንና  ከውስጥ መቀየር ይቻላል የሚል ነው። የረሱት ነገር ቢኖር

ትላንት አትናገሩም የተባሉት እኮ  አባላት ነበሩ።
ትላንት በፖሊስ የተባረሩት እኮ  አባላት ነበሩ።
ትላንት የስብሰባ  ወረቀት አስፈርመው ስብሰባ  የተከለከሉት አባላት ነበሩ።
ትላንት በስብሰባ ላይ የተሰደቡት አባላት ነበሩ።
በተጨማሪ ቀይረንዋል ባሉት ሕግ  2.1 መሰረት አንድ ክፍያ  ለ ስድስት ወር ያቆመ ግለሰብ አባል ለመሆን $50  ከፍሎ ማመልከቻ  ማስገባት እንዳለበት ጠቅሶ ማመልከቻው በቦርዱ ከጸደቀለት የመምረጥና  የመመረጥ መብት የሚኖረው ከአንድ ዓመት በኋላ መሆ ኑን ይጠቅሳል። ዓመት አይደለም ሁለት ወር ያልሞላው ቡድንም ያደረሰውን በደል እያየነው ነው።

እንደ ባንክ ብድር በፊርማቸው ብቻ  ስብሰባ  ያስጠሩ የነበረ  ዶክተር ሰሎሞን ለስብሰባ ሲመጡ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ያየ አባል በመሆን ካመት በኋላ  ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ እንዴት ሊያሳምነን ይችላል?

የተመረጡትን የቦርድ አባላት ያሰተዋወቁ የአማካሪ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ  ሰይፉ ካሳ ስብሰባውን ለመካፈል ሲመጡ አትገቡም ተብለው በመመለሳቸው እንዳዘኑ ይገባናል። የተባረሩት ግን የቀድሞውን ሊቀመንበር ይደግፋሉ በሚል እንጂ አባል ስላልሆኑ ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ?

ለመሆኑ አባል ቢኮንስ በፖሊስ አትድረሱ እያሉ ካላባረሩን በስተቀር የሚቀርብን ምን ይሆን? ጽድቅ ከበጎ ምግባርና  ከእምነት እንጂ አባል በመሆን የሚገኝ የሚመስላቸው ካሉ መመከር ያስፈልጋቸዋል።

ለናሙና አዲሱ መተዳደሪያ  ሕግ የሚለውን እናንሳላችሁ።

2.6 .................... ኮረም  ሁለት ጊዜ ካልሞላ ለውሳኔ  የቀረበው ጉዳይ ቦቦርዱ ውሳኔ ይወሰናል"
ትርጉም የራሳችን ።
በተገኘው ሰው ይወሰናል ቢል ይገባን ነበር በቦርዱ ይወሰናል ነው የሚለው። ታዲያ የአባላትን ሳይሆን የፈላጭ ቆራጭ ቦርድ ስልጣንን ለሚያጠናክር አካል ድጋፍ ለመስጠት ነው አባል የምንሆነው?
ለመሆኑ መተዳደሪያ ደንቡ እንዴት ተቀየረ? ማን ተወያየበት?
ሁላችንም በ40ቀን በ 80 ቀን ስንጠመቅ የቤተክርስቲያኑ አባል እንደሆንን እንዴት እንዘነጋለን።
በክርስቲያን መርህና እምነት ሳይሆን በፖሊስ ብዛት   እገዛለሁ የሚል የቤተክርስቲያን ቦርድ አካል ለመሆን ከሆነ  ጥረቱ ክርስቲያናዊ እሚሆነው እምኑ ላይ ነው?
በኛ እምነት ተሰባስበን መወያየት ተወያይተን መፍትሄ ላይ መድረስ አለብን እንላለን።
ነገ  በሺህ ግለሰቦች አስተዋጽኦ የተሰራው ቤተክርስቲያ 125 ባልሞሉ አባላት ተሸጠ ቢባል እንዳናዝን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዛውም ሁሉም ሳይስማሙበት።


SENBETE የሚለው ብሎግ እንደተለመደው  ቆንጆ  ስድብ አዝሎ  ወጥቷልና  እባካችሁ አንብቡላቸው። የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባየሁ ነው እንዲሉ።




   

Sunday, April 25, 2010

በጠበበው ደጅ ግቡ ..... " ማቶዎስ ም 7 ቁ 13 ቁጥር ፳፫

የማቴዎስ ወንጌል
 ምእራፍ  7 ቁጥር  13 በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው። 
14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
15 የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።
16 ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?
17 እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።
18 መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።
19 መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
20 ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።

የማቴዎስ ወንጌል
 ምእራፍ 5 ቁጥር 11 ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
12 ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።

13 እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
14 እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
15 መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
16 መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።

ወንድሞችና  እህቶች የቤተክርስቲያን አባላት።   ከዚህ በላይ ያሉትን ጥቅሶች ማንም አልነገረንም በሚካኤል ስም እንመሰክራለን ነገር ግን የገጠመንን የቤተክርስቲያን ችግር አሰብንና እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ እናገላብጥ ብለን ስናገላብጥ ያገኘነውን እንዳለ  አቀረብነው። ስለ እውነት ቃሉ ልባችንን ነካው። የናንተንም ይነካው ይሆናል  ብለን እንዳለ  አቀረብነው። መላከ ሳህልን በቅዳሜ እለት ከቤተክርስቲያን ያባረረው ቦርድ ያባረረው ካህኑን ብቻ  ሳይሆን ሁላችንንም ነው። በፖሊስ ታጅበው ሁለተኛ ቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ የተነገራቸው አባት ጥፋታቸው ቦርዱን እንደ እግዚአብሐር አላመልክም  ማለታቸው ብቻ ነው። የቤተክርስቲያንችን መተዳደሪያ ደንብ አንድም ሰው ቤተክርስቲያን መጥቶ  የማምለክ መብቱ አይገፈፍም እያለ  6 የቦርድ አባላት ብቻቸውን ወስነው የሃገሩን ሕግ የማያውቁትን ካሕን አስፈራርተው ማባረራቸው የሚያሳዝን ነው። ተናጋሪው አቶ  አበበ ጤፉም ሆኑ እንደስእል የተቀመጡት ሊቀመንበር የቤተክርስቲያኑን ትግል ወደፊት ወስደውታል። ካሁን በኋላ  የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ በመጠቀም ሁላችንም ላይ አደጋ  እንዳይፈጥሩ መዘጋጀት የግድ ይላል።

ሕግ የማያውቁ ሕግ አስፈጻሚዎች የሆኑ የቦርድ አባላት በካሕኑ ቤተሰብ ላይ የወሰዱት ብያኔ  እነሱ ላይ እንደሚዞር ምንም ጥርጥር የለንም። ከኋላ  ሆነው ይህ እንዲደረግ ይጥሩ የነበሩ ግለሰቦችም እራሳቸውን ቢገመግሙ መልካም ነው እነላለን። የተደረገው ድርጊት አንድም የመንፈስ ነገር የለበትምና። በሕዝብ ገንዘብ አባላትን ማጎሳቆል መቆም አለበት። ለዚህም ፈሪሃ  እግዚአብሔር ያደረበት ሁሉ መጠየቅ ያለበት ይመስለናል።

ቀሲስ መስፍን ከሰበካ በኋላ  ያለቀ  ባትሪ ሆኛለሁና ካሁን በኋላ  አልቀጥልም ብሎ  መሰናበቱን ስንሰማ  በድጋሜ ሐዘን ተሰማን። 
ወንድሞች በዛሬ  ደስተኛ የነበሩት የቆዩት ካህን ከነልጃቸው ሊሆኑ ይችል ይሆናል። ዛሬ የሚጨፍሩ ነገ  እንደሚያዝኑ ግን ምንም አንጠራጠርም። ቦርዱ የፖሊስ መአት ያሰለፈው ለምን ነበር?  ቤተክርስቲያን በክርስቶስ እንጂ በፖሊስ ትጠበቃለችን?  ወንድሞ ቼ የፖሊሱን ጋጋታ አይታችሁ "እኔ  ቤተክርስቲያን እንጂ ፖሊስ ጣቢያ አልሳለምም "ብላችሁየ የተመለሳችሁ ስንቶቻችሁ ናችሁ? 
ይህንን የጠየቅነው የተመለሰውን ሕዝብ በማየታችን ነው። ነገ ወረቀት የሌላቸው አዲስ የመጡ ቢኖሩ ፖሊስ ፍራቻ ወደቤተክርስቲያን እንዳይደርሱ እየተደረገ ነው። በነገራችን ላይ ሁላችንም እንዴት የመኖሪያ ፈቃድ እንዳገኘን እንተዋወቃለን።
ፖለቲከኞች ዛሬ ተሸነፉ እንጂ አላሸነፉም።
የቦርድ አባላት በሚያስደንቅ ሁኔታ  ዛሬ ተሸነፉ እንጂ አላሸነፉም።
የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ዛሬ  ተሸነፉ እንጂ አላሸነፉም።
ያሸነፉት ሚካኤል ፍርዱን ይስጥ ያሉት ናቸው። አምላክ ልጁን እንደሰጠን ሁሉ ዛሬም ሁለቱን ልጆቹን አሳልፎ ሰጠን። መከተልና ክርስቲያናዊ ግዳጅ መወጣት የሁላችንም ፋንታ ነው።
ባለፈው አጠቃላይ ስብሰባ አቶ  ሰይፉ ካሳና ዶክተር ሰሎሞን ስብሰባውን ለመካፈል መጥተው መከልከላቸውን ስንሰማ አልተደሰትንም። በሰፈሩት ቁና  ማለት እንችል ነበር ግን ቤተክርስቲያን ሆነብን።

ትግላችን በተጠናከረ  መንገድ ይቀጥላል።ቤተክርስቲያን የአማንያን ትሆናለች።
     

Tuesday, April 20, 2010

ያረገዘ መውለዱ አይቀር ፳፪

አርግዛለች አሉ ድባብ የፈረንጂ፡
ለኔም ይደርሰኛል አንድ እግር ካንድ እጅ።

ያለው አዝማሪ ምን ችግር አጋጥሞት እንደዚያ እንዳለ ለመተንበይ የሚያስቸግር አይደለም። ዳላስ ላይ ደግሞ ለየት አለና

እደግ እደግ ብለን የተከልነው ቀጋ፡
ዘንበል ዘንበል አለ እኛኑ ሊወጋ።

ብለው የሚያዜሙ አጋጥመውን እንደ ጥንቱ እኛም በፊናችን

አራት እግር አንድ ራስ መንቀል አቅቷችሁ፡
ለብልቦ ለብልቦ አቃጥሎ  ይፍጃችሁ።

ብለን ለሚያንጎራጉሩት መልስ ሰጠናቸው። የእሑዱን የቤተክርስቲያን ስብሰባ እንዴት ነበር? ብለው ለጠየቁን ደግሞ ከዚህ በፊት እትማችን እንዳልነው እኛ ከቁልቌል ወተት አንጠብቅምና ምን ተባለ? ከማለት ይልቅ የሚባለውን ገምግመን አማራጩ ሌላ  መሆን አለበት ካልን ውሎ  አደረ። ስብሰባውን በታዛቢነት ተከታተልን እንጂ ለውጥ ያመጣል ብለን ከጅምሩም አስበነው አናውቅም። በመወያየት ሰላም እንፈጥራለን ይሉ የነበሩ ግለሰቦች በደረሰባቸው ተናደው፡ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን እየለቀቁ ሲወጡ ስናይ ያልነው ተፈጻሚነት አገኘ አልን እንጂ ምነው? በደህና  አላልንም። ይህ ገርሞን ሳያበቃ "፳ ዓመት የደከምኩበት ቤተክርስቲያን የበሩ ቁልፍ ተነፈግኝ ካሁን በኋላ ስብሰባ ውስጥ አታዩኝም " ብለው እንባ  እየተናነቃቸው ለአባላት አቤቱታቸውን ያቀረቡት የቀድሞው የቤተክርስቲያኑ ያስተዳደር ቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት ግለሰብ ስብሰባውን እረግጠው ሲወጡ የተከተሏቸው አንድ የወልቃይት እናት ብቻ እንደነበሩ ስንመለከት ደግሞ   "ሲያልቅ አያምር በሰፈሩት ቁና ........" ማለታችን አልቀረም። የብዙ ጊዜ ጔደኛቸውና የስትራተጂ አማካሪያቸው እንኴን አልተከተሏቸውም። አይገርማችሁም? 

"እኔ ገንዘብ ባይኖረኝም የሰላም እንቅልፍ እተኛለሁ"  ያሉት ዶክተር ማ እንቅልፍ እንደተነሳ  ባይናገሩም የተረበሻችሁ አላችሁ ለማለትና በአሽሙር ግለሰቦችን ለመልከፍ  የተጠቀሙበት እንደነበረ  ለመገመት አልተቸገርንም። ያም ሆነ ይህ ስብሰባው አጣሪ ኮሚቴው እየፈራና እየቸረ ያቀረበው ገለጻ ሙሉ በሙሉ ሳይሰማ የስብሰባው ፍጻሜ ሆነ። የአጣሪው ኮሚቴ አባል የሆኑት የሁለት ልጆች እናት እንዳይናገሩ መብታቸውን የከለከሏቸው የቅርብ ጔደኛቸው የነበሩ ግለሰብ መሆናቸውን ስናይ እሳቸው ካዘኑት በላይ አዘንን።  ምነው ወንድሜ ምን ነካዎ  ብንላቸው ደስ ባለን ነበር። ነገር ግን አናንተ እነማን ናችሁ ተብሎ ድብድብ ቢነሳስ ብለን ፈራን። ዘንድሮ  ደግሞ የፈራ የእናቱ ልጅ ነው የሚለውን የጥንቱን አባባል መለስ ብለን ማሰብ ወደናል። ቤተክርስቲያናችን የደረሰበት እጣ ከሌላው ቦታ  የተለየ  አይደለም። አሁንም ፖለቲካና እምነት የተቀላቀለባቸው የፖለቲካ  መስመራቸው ግብ አልመታ ሲል በጸሎት እንደመለመን አርፎ የተቀመጠውን አማኝ በመበታተን ሲከፋው ያምጻል ግራ  ሲጋባ ከኛ ጎን ይሰለፋል ብለው የሚያልሙ ካልሆነም ከተበተነ የሚታፈስ አይጠፋም ብለው የሚዘገን የሚጠብቁ ግለሰቦች ሕልም እንደሆነ ከተገነዘብን እንደ ሰነበትን ደጋግመንም የተናገርን ይመስለናል። ሲኖዶስን እንደጠላት መፈረጅ አይደለም የኦርቶዶክስ እምነት እንዴት ቢከለስ ፈረንጅኛ ቅርጽ ይኖረዋል ብለው የሚመኙ ቡድኖች የሚቀምሩት ለመሆኑም ሂደቱን በመያት መናገር ይቻላል እንላለን። ለምን ግለሰቦች ያለውን ችግር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ዝምታን ወደዱ?  ብለን ስንጠይቅ ቀልደኛው ባልደረባችን "አሁንስ እነሱም እንዳይውጣባቸው የሚፈሩት ነገር ያለ ይመስላል"  ብሎን አረፈ ። ለጥርጣሬው መንደረደሪያ ይኑረው እንጂ መረጃ  እንደሌለው ይገባናል።

ባለፈው ስብሰባ የታዘብነው ሌላ ነገር ቢኖር ገንዘብ ጠፋ  አልጠፋ ለማለት ሁሉንም የምንፈልገውን ዶሴዎች ቦርዱ እንድናይ እድል አልሰጠንም ሆኖም በጥቅሉ የጠፋ  ገንዘብ የለም ብለው ሁኔታውን እያብራሩ   ባሉበት  ወቅት ከዚህ ውጭ መናገር አትችሉም ገንዘብ አልጠፋም ብላችኋል በቃ አትናገሩም ብለው የሚያዋክቧቸውን ግለሰቦች ስንመለከት ነው። ትላንት ባገራችን እናትና  አባት ይጋደል የነበረበትን ሁኔታ  አስታወሰን። የተናጋሪዎቹን መብት ይጋፉ የነበሩት ቤተዘመዶች ነበሩና። ለካ እምነትም ፖለቲካ  ነው ብሎ የኔ ቢጤ ግለሰብ ቢወናበድ ምን ይገርመናል። ትላንት የውሸት መታወቂያ  አንግቶ ቤቱን የለቀቀ ስደተኛ ተጋዳይ ቁርባንን እንደመሸሸጊያ እያደረገው ይሆን?  ያለን ሌላው ግለሰብ አፍ አፉን አልነው እንጂ መንደርደሪያ እንደነበረው የሚክድ ከመሃከላችን አንዳችም ግለስብ አልነበረም።

ውድ አንባብያን ባለፈው የነበረው ስብሰባ  ያናደዳቸው ግለሰቦች ስብሰባውን እየረገጡ ሲወጡ ይውጡ ተዋቸው ይሉ የነበሩ ግለሰቦች ያላወቁት ነገር ለደስታ አይደለም ለሐዘንም ሰው እንደሚያስፈልግ ነው። 30 ዓመት በፖለቲካ ሕብረተሰቡን ማሰባሰብ ያልቻለ ተቃዋሚም ይሁን ደጋፊ የፖለቲካ  ቡድን ሰውን በማለያየት ወደ ስልጣን መምጣት ይቻላል ብሎ  የሚያስብ ከሆነ ለሱ "መጽሐፍ ቅዱስ"  ሳይሆን  መጽሐፍ ገላጭ ሊያስፈልገው ነው።

ለማንኛውም በውይይት መፈታት ይቻላል ብላችሁ ያለፈውን ቀን ጠብቃችሁ በውጤቱ የተናደዳችሁ አማንያን ልታደርጉ የምትችሉት ነገር ቢኖር ተነስታችሁ በሕግ መታገል ብቻ ይሆናል ብለን እናምናለን። በፍርድ ቤት  ወሳኔ አንድ መሆን አይቻልም ብንልም ያለው አማራጭ እየጠበበ ምን ይሆናሉ? አሸነፍናቸው ገደል ይግቡ የሚሉትን ግለሰቦች በውይይት ማሳመን አዳጋች ነውና።  የፖለቲካ  አመለከታታችሁ ከኛ ከተለየ እናባርራችኋለን ብለው እያባረሩ ያሉትን ገንዘብ ሳይከፍሉ ገንዘብ የሚቆጥሩትን ቡድኖች መቌቌሚያ  ሌላ  መንገድ ይኖራል ብለን ማመን አቁመናልና። የተለያዩ  ሽማግሌዎች የጀመሩት የማስማማት ጥረት የት እንደደረስ ባናውቅም ካሁን በኋላ  አክብረው ያናግሯቸዋል ብሎ  የሚጠብቅ ካለ የዋህ ብቻ ነው እንላለን። ውድ ወንድሞች ለመብት መታገል አኩሪ ነው። እበላ ባይ መሆን ግን አንድም ክርስቲያናዊ ካልሆነም ፖለቲካዊ ካልያም ሰላማዊ አያደርግም። በመፍራት ሰላም አይመጣም ሰላም በእምነትና በትግል እንጂ። የሚፈራውስ ማን ነው? የሚፈራውስ ለምን? ማለት ደግሞ ለእውነታው መንገድ ይቀዳል። እኔ  በደህና  ግዜ ተምሬ የገንዘብ ችግር የለብኝም ያሉት ግለሰብ የገንዘብ ሳይሆን የእምነት ችግር እንዳለባቸው በግልጽ ይፋ  አደረጉት "ሃብታም ይጸድቃል ከማለት ይልቅ ግመል .............."  ያስታውሷል። እንካ  ስላንቲያ  ውስጥ መግባት ደግሞ የእልፍኝ ሳይሆን የማድቤት ያረገዋልና ሳንናገር እንለፈው።

ወንድሞችና እህቶች ዲያብሎስም ባንድ ወቅት መልአክ እንደነበረ  አንርሳ።
 መልከም ሰንብቱ።

Saturday, April 10, 2010

{ሰበር ዜና } የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል !! ቁጥር ፳፩

"ያረገዘ  መውለዱ አይቀርም ይሉ ነበር አንድ የአብማ  ወይዘሮ "


እኛ እንኴን ቀጠሯችን በሌላ እርእስ  ነበር።  የሆነ ሆኖ "በእለተ ቀኑ በአለእግዚአብሔር ቸር ወሬ እንድንሰማ አደረገን" የሚሉ አባላት አነጋግረን ስላጋጠማቸው  ደስታቸው ደስ ለሚላቸው አማንያን መናገሩን እኛም አመንንበት። በእለተ ቀኑ የተሰማው ቸር ወሬ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?  ለቤተክርስቲያኑ አባላት መብት መታገል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው  የሚሉት አባላት ክስ መስርተው ባለፈው ዳኛው "ቦርዱ ሕግ የመቀየር መብት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አለው የሚል የሚያሻማ ሐረግ በመኖሩ የቀየሩት በግልጽ አባላትን ለማባረር የቤተክርስቲያኑን ንብረት ለመቆጣጠር እንደሆነ ቢገባኝም ድርጊቱ በመብታቸው ዙሪያ ነው በማለት"የወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ከሳሾች ይግባኝ በማለታቸው ነው።  

የይግባኙን ዶሴዎች የተመለከተው THE  TEXAS 5TH DISTRICT APPEALE COURT OF DALLAS በ 04-07-10 ፋይሎችንና የተቀረጹ የክርክሩን የድምጽ ካሴቶች በማዳመጥ "እውነት ነው ይግባኙ መታየት አለበት ብሎ"  በመስማማቱ የመጀመሪያው የጠበቆች ክርክር በ 05-18-10 እንዲሰማ መቀጠሩንም እኛም ተከታትለን እንደደረስንበት ልንነግራችሁ እንወዳለን። 


ውድ የቤተክርስቲያን አባላት። ክርክር መጥፎ እንደሆነ በተለይም ክርክሩ በቤተክርስቲያን አካባቢ ሲሆን ይበልጥ እንደሚጎዳ መረዋ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል። ማንም አሸነፈ እንደማይሆን  የምንጎዳው ደግሞ ሁላችንም ነን ብለንም ነበር። .............የገደለው ባሌ የሞተው ወንድሜ.............አይነት። ግና ከቦርድ ተመራጮች ወገን የምናየውና የምንሰማው ትንሽ እያስከፋን እየመጣ መሆኑን ሳንናገር ብናልፍ በራሳችን ላይ መዋሸት ይሆናል። በተለያየ ወቅት ሊያናግሯቸው የመጡትን ሁሉ ገንዘብ ተበድሮ መመለስ እንዳቃተው ተበዳሪ ምክንያት እያበዙ ከውይይት ሲሸሹ መመልከታችንንም መደበቅ አንወድም። አንድን መንፈሳዊ አባትን "ካድሬ ቄስ" ብሎ የሚጠራ የቦርድ አባል ዞር ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት እንላለን። ሰሞኑን ደግሞ ባለፈው እንደነገርናችሁ በቤተክርስቲያኑ ተከስቶ የነበረውን የካሕናት ችግር ላይ ቦርዱ በወገነኝነት ያጠፋውን ሳይሆን ያላጠፋውን ለመገሰጽ እንዳሰቡ ስንሰማ ጊዜው ሲደርስ የምንለው ብዙ ነገር መኖሩንና የተደገሰው ድግስ እንደሰማነው እውነት ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የአባላትን ተሳትፎ በሰፊው የሚጠይቅ እርምጃ ለመውሰድ መረዋ መነሳቱን በቅድሚያ ማሳሰብ እንወዳለን።

ውድ አንባብያን ኒቆዲመሶች በብዛት እንዳሉ እናውቃለን የጴጥሮሶች እጦት እንዳለ ግን የተገነዘብን አልመሰለንም። ቼ ጉቤራን መፍጠር ቀላል ይሆን ይሆናል ትልቁ ችግር ማርቲን ሉተርን መፍጠር ላይ ነው።  ይሁዳ መሆን ያጔጔ ይሆናል የሚከብደው እነደ አቡነ  ጴጥሮስ እራስን መሰዋት ነው። ሃገር ወዳዶች ነን ማለት ይቀል ይሆናል፤ የሚከብደው ከዘር ማነቆ አስተሳሰብ መውጣቱ ነው። ፖለቲከኛ መሆን ፈቃድ የማይጠየቅበት ክፍት ስራ ነው፡ የሚከብደውና እውቀት የሚጠይቀው የመነፈሳዊ አባት መሆንና መንፈሳዊ ተግባር ማሳየት ነው።

በዳግም ትንሳኤ ቦርዱ ምን እንደሚል መተንበይ ተቸግረናል በትንሳኤው እለት ሊቀመንበሩ ያነበቡት እስካሁን ምን እንደሆነ አልገባንምና።

እንዴው ለፈገግታ ያክል አንዱ አንባቢያችን የላኩልንን ቀልድ እናካፍላችሁ። ከአረብ አገር ወደ አሜሪካ የመጡ ቤተሰቦች የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነውን ልጃቸውን አብዱል ከሪምን ትምህርት ቤት አስገቡት። በመጀመሪያው ቀን አስተማሪው የልጁን ስም ጠየቀው ልጁም ስሙን ተናገረ መምህሩም ስምህ ስለረዘመ ብሎም ለአሜሪካዊ ጔደኞችህ መጥራት እንዳይከብዳቸው ከዛሬ ጀምሮ ዊልያም እያልን እንጠራሃለን አለው። ቀኑን ሙሉ ሁሉም ዊልያም እያለ ሲጠራው ዋለ። የትምህርቱ ቀን አለቀና እቤት ሲደርስ እናቱ አብዱል ከሪም ብላ  ስትጠራው እማየ የለም ዊልያም ብለሽ ጥሪኝ አላት በሁኔታው የተናደደችው እናት ትላንትና  አሜሪካ  መጣህና የኛ ስም አስጠላህ ብላ ገረፈችው። አባቱም እንዲሁ ሁኔታውን ሰምቶና ተናዶ ልጁን እንደ እናትየው ደበደበው። በማግስቱ ወጣቱ ትምህርት ቤት ሲሄድ ስሙን ያወጣለት አስተማሪ በልጁ አካል ላይ ያለውን ሰንበር ተመልክቶ ምን ሆንክ? ብሎ ሲጠይቀው  ወጣቱ ምን አለ  መሰላችሁ ሁለት አረቦች አሜሪካዊ መሆኔን በስሜ ሲያረጋግጡ  ተባብረው ደበደቡኝ አለ አሉ። ፈገግታ መልካም ነው እህቶቼና ወንድሞቼ። ሁላችንንም ከሃዘን ይሰውረን።

ቸር አሰምቶ በቸር ይግጠመን

Wednesday, April 7, 2010

ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከበረት ውጭ ታሳድራለች። ፳

ውድ አንባብያን እንኴን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ብለን ከሳምንት ዝምታ በኋላ በድጋሜ የመልካም  ምኞታችንን ስንገልጽላችሁ ዓመት በዓሉን በሰላም ከቤተሰቦቻችሁ ጋር እንዳሳለፋችሁ  በመተማመን ነው።  የትንሳኤ በዓል ለማክበር የተሰበሰበውን ሕዝብ ብዛት በማየት ያልተደነቀ ሰው ነበር ብሎ መናገር ይከብዳል። እውነትም የምእመናኑ ብዛት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ከመሰጠቱ ባሻገር ሁኔታውን የተመለከተ ያለሁት አገር ቤት ነው አሜሪካ? ብሎ ቢጠይቅ አይፈረድበትም። ማኅሌት የቆሙት ካህናት ሌሊቱን ሙሉ ደከመን ሳይሉ ሰርጓ እንዳማረላት ሙሽራ እየተውረገረጉ  ሲወርቡ ያየ ሰው ለመቀላቀል ቢነሽጠው  በተቀመጠበት ማሸበሽብ ቢጀምር ሁሉም አበጀህ ይለው እንደነበር መናገር ማጋነንም አይሆንም።

ታዲያ ሁኔታዎች እንደዚህ ባማሩበት የክርስቶስን ትንሳኤ በደሰታ በምናከብርበት ወቅት አስደንጋጭ ሁኔታ ተፈጠረ። መቅደሱ ውስጥ የነበሩት ካህን የድምጽ ማጉሊያውን በመጠቀም በሕግ አምላክ እያሉ ወደ ተሰበሰቡት ካህናት በመምጣት ታምረ ማርያሙ ሲነበብ መቅድሙ ታልፏልና መደረግ የለበትም በሕግ አምላክ በሕግ አምላክ ማለታቸውን ቀጠሉ። ለነገሩ ድጔው አልቦ መቅድም ወአልቦ መልክአ ስእል  ማለቱን ሰሞነኛው ቄስ የተረዱት አልነበረም። በትንሳኤ ቀን በሚደረግ ስርአት ላይ እንደ 33 የእመቤታችን በአላትና እንደተቀሩት እለተ ሰንበቶች   እንደማያስገድድ ደግሞ ለሳቸው እንግዳ ቢሆንባቸው አልተደነቅንም። በመቅደስ ውስጥ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አገልግሎት የሚሰጥ ካህን  አይደለም ማንም የመንፈሳዊ አባት በሕግ አምላክ ማለት ከጀመረ የእምነት ክስረት አለበት ብለን ብናስብ ትክክለኛ አመለካከት ይመስለናል። መገዘትን ያክል ስልጣን ያለው ካህን በሕግ አምላክ አለ ማለት ጠመንጃውን አስቀምጦ በቆመጥ ሊዋጋ  እንደሚነሳ  ወታደር ተምሳሊት አይነት መሆኑ ነውና።

ጥፋት አልተደረገም እንጂ ተደርጎ ቢሆን እንኴን ዲያቆናቱን በመላክ ወይንም ቀርቦ በሹክሹክታ እርስ በርሳቸው በመነጋገር መተራረም   ሲቻል ካልሆነም በሌላ  ጊዜ መወያየት ተገቢ ሆኖ ሳለ ምእመናን እስኪደናገጡ እናቶች በእንባ እስኪራጩ ድረስ ሕዝቡን ማስደንገጥ አሳፋሪ ነው ከማለት ሌላ ምን ማለት ይቻላል። የቄሳር ሕግ በቄሳር ስፍራ እንጂ በቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ለመጠቀም መሞከርስ ምን ማለት ነው?

ሁኔታውን የታዘበው ቀልደኛው ወንድማችን ማታ ላይ ምን አለን  መሰላችሁ። ጥፋቱ የጮሁት ካህን ሳይሆን እኝህ መንፈሳዊ አባት የማያውቁትን ማህሌት ያሳመሩት የድጔ የቅኔ የአቌቋም እውቀታቸውን በሚገባ  ያሳዩት የሌላው ካህን ጥፋት ነው። እሳቸው እውቀታቸውን ባያሳዩ  ኖሮ በሕግ አምላክን ባልሰማን ነበር። እኔም እንዳንተ አቌቋም ድጔ ባልማር ቅኔ ባልችል አዋቂ እኮ ነኝ ብለው ታምረ  ማርያም እንደሚያውቁ ለማሳየት በሕግ አምላክ ቢሉ ለምን ተገረማችሁ ብሎን አረፈ ። እንዴውም ከቅዳሴው በኋላ ወደ መጨረሻ እልል በይ ይል የነበረው ካህን እሱም የመዘመር እውቀት እንዳለው ለማሳየት ያደረገውን ጥረት አላስተዋላችሁምን? ብሎን አረፈ። ቀጠለና ይህ ያዘምር የነበረው ካህን የድምጽ ማጉያውን እኔ ስዘምር ትቀንሳላችሁ ብሎ  በመክሰሱ ለድምጽ ማጉያው የድምጽ መቀነሻና መጨመሪያው ቁልፍ ተሰርቶለት እንደተቆለፈ የነገረንም በዚሁ ወቅት ነበር። ወንድሞቼ ጽድቅ በጩኸት አይገኝም።

ስለ ቁልፍ መቀየር ካነሳን ዘንዳ የቤተክርስቲያኑ ቁልፍ $4000 በላይ ወጥቶበት በቁጥር የሚከፈት እንዲሆን መደረጉን እስካሁን ሰምታችኋል ብለን እናስባለን። ካሁን በኋላ ቤተክርስቲያኑን የሚከፍቱት ፈቃድ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ይሆናሉ። የቤተክርስቲያኑን ኮምፒውተር ደግሞ እውቀት ያላቸው ዶክተር ከባለቤታቸው ጋር መረከባቸውን ስንሰማ አልተገረምንም።ነገ ደግሞ  ቤተክርስቲያን የሚያስቀድስ ሁሉ እንደስብሰባ አባልነቱ እየተጣራ  እንዲገባ  የሚደረግበት ሰዓት ይመጣል ብንል ትንቢት አይሆንም። የሁኔታዎችን አካሄድ ግንዛቤ  ውስጥ በማስገባት  ስለመጭው መናገራችን እንጂ።

ነገርን ነገር አነሳውና የድሮ  ቀልድ ታወሰን ሚስት የባሏን ኪስ ስትፈትሽ አንድ አይደለም 4 የራሷን ፎቶግራፍ አገኘች። ወደ ባሏ ሆደችና እንደምትወደኝ ገባኝ አንድ አይደለም 4 ፎቶዬን በኪስህ ይዘህ እንደምትጔዝ ደረስኩበት አለችው። እሱም አዎ "ችግር በገጠመኝ ቁጥር ፎቶሽን በማየት የገጠመኝ ችግር አነስተኛ ሆኖ እንዲታየኝ  ይረዳኛል" አለ  ይባላል።
በነገራችን ላይ እንዴው ሁኔታዎቹን ስናስብ የድሮ ግጥም ትዝ አለን

እናት አባት ቢሞት ባገር ይለቀሳል
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል። ይባል ነበር።

እኛም ሌላ ጥያቄ  እናንሳ። ምእመን ሲያጠፋ  በንስሐ አባት  በምእመን በሽማግሌ ይወቀሳል። ታዲያ  ባለው ሁኔታ ያጠፋ ካህን ሲያጋጥም በመጀመሪያ ማጥፋቱን የሚያየው አካል ማነው? የሚገስጠውስ ማን ይሆን?  ትክክል መሰራቱን የሚቆጣጠረው የትኛው አካል ይሆን? መልሱን ለናንተ  እንተዋለን።

ችግሩ እየሰፋ መጥቶ የት እንደደረስን ለመታዘብ እድል እንዲሰጣችሁ በሚል የሚከተለውን vidio እንድትመለከቱት መረዋ ይጋብዛል።

http://www.youtube.com/watch?v=xaYl8KZNKco&feature=related


በሌላ  በኩል በያዝነው ወር በ17 በሚደረገው አጠቃላይ ስብሰባ ቦርዱ አንድ አይነት አቌም ይዞ  እንዳልመጣ መስማታችንን ስንነግራችሁ ሁኔታው ያስፈራቸው የቦርድ አባላት በግል አባላትን እያነጋገሩ የተለመድ የፖለቲካ ቅስቀሳ እያኪያሄዱ መሆኑን ልንነግራቸሁ እንወዳለን። ለእውነት የቆመ ክርስቲያን ነገሮችን እንዳመጣጣቸው ይቀበላል እንጂ በቅድሚያ ተሰብስቦ ምን ብለን እንዋሽ አይልም።
በሚቀጥለው እትማችን  Senbete የተባለው ብሎግ ያወጣውን ጽሑፍ አስመልክቶ በመረጃ  የተደገፈ የራሳችንን ግንዛቤ በሰፊው እናቀርብላችኌለን። እስከዚያው ድረስ ሰላም ሁኑ።