Thursday, May 27, 2010

የውሸት ትንሽ የለውም ቁጥር ፳፱

ውድ አንባብያን
ለተነገረው ሁሉ መልስ መስጠት፧ ለተባለው ውሸት ሁሉ ማስተባበያ  ማቅረብ ፧ አስፈላጊ ባይሆንም አንዳንዱን ግን ዝም ብሎ  ማለፍ አላስፈላጊ እየሆነ  እያገኘነው ነው። ባለፈው ደጋግመን እንዳልነው ሁሉ በውሸት የተናቀ  እንጂ የተከበረ  እስካሁን አላየንም። መዋሸት ደግሞ  እየበዛ  ሲሄድ ህክምና የሚያስፈልገው፧ ጸሎት የሚደረግለት ጠበል የሚሞከርለት ይሆናል። ሲዳማዎች ሲተርቱ "አህያ  ከመሞቱ መጎተቱ" ይሉ ነበር። በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተከሰተው ችግር እዚህ የደረሰው በኛ አመለካከት መብት በመደፈሩ የአንባገነንነት ሥራ  በመለመዱ ጥቂቶች ብዙሃኑን አፍነን ከቤተክርስቲያን አባረን በራሳችን ደንብ በጥቂቶቻችን ውሳኔ  ሕዝቡን እንነዳዋላን ካልሆነም እናባርረዋለን ከሚል ክርስቲያናዊ ካልሆነ የጥቅምና  የፖለቲካ መንደርደሪያ  በመነሳቱ ነው። ታዲያ  ጥሉ የእምነት ሳይሆን የጥቅምና የፖለቲካ የመብት መከበርና ያለመከበር አባላትን የማክበርና የመናቅ ብሎም በቤተክርስቲያኑ ንዋይ ላይ ተመርኩዞ ሌላውን በመጫን ሙሉ ቁጥጥር ለማድረግ የሚደረግ ፍልሚያ  መሆኑ ግልጽ ነው። ዛሬ ካህናትን የሚያባርረው ቦርድ በካህናቱ ላይ ሕጸጽ አግኝቶባቸው ሳይሆን የምንለውን አይፈጽሙም የቦርዱን አስተዳደር ትእዛዝ ሳይሆን የሚከተሉት የወንጌሉን ትእዛዝ ነው በሚል እንደሆነ ይታወቃል። ወንድሞቼ ከኢትዮጵያ  በ DV ከመጡ ዓመት ያልሞላቸው ባልዬው ብቻ እየሰራ  ያለ ገና  ያልተቌቌሙ ቤተሰቦች ልጅ ወልደው ለክርስትና  ማስነሻ ቦርዱ የወሰነውን  $150 መክፈል አንችልም እባካችሁ አስተያየት አድርጉልን ባይሆን ከመጪው ሳምንት ደሞዜ ላይ $50 ለመክፈል ቃል ልግባ ብሎ ባልዬው ካህኑን በለመናቸው መሰረት አባታችን ሄደው ቦርዱን ሲማጸኑ የቦርድ አባላቱ ግን " አንዴ  የተወሰነ  ነገር ስለሆነ $150 ሳታስከፍል እንዳታነሳ"  በመባለቸው ካህኑም በሁኔታው ተበሳጭተው "መልካም ልጆቼ፧ ክርስትና  ለማንሳት ወደማያስከፍሉት አባት እመራቸዋለሁ" በማለታቸው ከስራ እንዲባረሩ ያበቃቸውን ወንጀል የዘረዘረው ደብዳቤ ይጠቅሳል። ክሱም "ክርስና በማንሳት ገቢ እንዳናገኝ ክርስትና የሚያስነሱትን ወደ ሌላ  ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልከሃል"  የሚል ነበር ። ይህ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ለናንተ እንተውና፧ የሃይማኖት ጉዳይ ነውን? ለሚለው ግን መረዋ በግል የገንዘብ የንግድ እንጂ የክርስቲያን ስራ  አለመሆኑን   ያምናል።

እሩቅ ሳንሄድ ባለፈው እሑድ  22 MAY 2010  በመቅደሱ ፊት ቆሞ የፍርድ ቤት ውሳኔ  በሚል የቦርዱ ምክትል ሊቀ መንበር ባነበበው ጽሁፍ ላይ  "ምስክሮች ከተደመጡ በኋላ ክቡር ፍርድ ቤቱ በቤተክርስቲያኗ ላይ የተደረጉት ማገጃዎች እንዲነሱና በከሳሾች በአቶ  ተኮላ መኮንንና  በአቶ  ጸሐይ ጽድቅ ቤተማርያም የተመሰረተው ክስ ደግሞ ቀደም ሲል በአቶ  ዳግም ካሳሁን እና በወ/ሮ ጥሩ አየር ፍስሀ በቤተክርስቲያናችን ላይ የተመሰረተን ክስ ውድቅ ወዳደረገው ወደ 192nd (DISTRICT COURT)  ፍርድ ቤት እንዲዘዋወር ( እንዲመለስ ወስኗል)። ይህም የተደረገበት ምክንያት የሁለቱ ክሶች ከሳሾች ስም ዝርዝር ይለያይ እንጂ ክሶቹ ተመሳሳይ ስለሆኑ ነው።" ውድ ምእመናን ማታለል ሌላ  ነገር ሆኖ ፍርድ ቤት ያላለውን መናገር ደግሞ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን መረዋ ሊያስጠነቅቃቸው ይወዳለል።

ለነገሩማ በሚመጣው ወር ማለትም  በ 6/ 25 / 2010 9:00 AM ላይ በ 101 DISTRICT  COURT, JUDGE MARTIN  LOWY የቀጠሩት የጠበቃዎች CONFERENCE  መኖሩን ብንነግራቸው አቶ ሙሉአለም ይቅርታ  ዋሽቻለሁ የሚሉ ይመስላችኌል? መዋሸት መሳሳት ብቻ  ሳይሆን ሆን ተብሎ  ከተደረገ ደግሞ የሚያስቀጣበት ሰዓት እንዳለም መታወቅ ይኖርበታል። ወንድሞች  እድሜ  ይስጠን እንጂ ሁሉንም ወደፊት የምናየው ጉዳይ  ይመስለናል።
ከላይ እንዳነበባችሁት እኝሁ ምክትል ሊቀመንበራችን "በቤተክርስቲያኗ ላይ የተደረጉት ማገጃዎች እንዲነሱ ፍርድ ቤቱ ............ ወስኗል" ይሉናል። ለነገሩ ገንዘብን አስመልክቶ የነበረው እገዳ ከመነሳቱ በስተቀር ዳኛው የፍርድ ቤቱ እገዳ ተሻሽሏል አሉ እንጂ ተነስቷል አላሉም። ውሳኔው የቦርድ አባላት

1 አማንያንን  ከቤተክርስቲያን ለማባረር ለመከልከል እንደማይችሉ
2 DOCUMENTS ማጥፋት እንደማይችሉ
3 ፖሊስ መቅደስ ውስጥ ማስገባት እንደማይችሉ የተወሰነ  መሆኑን ለምን ይክዳሉ

መጀመሪያስ ቢሆን የከሳሾች ክስ አታባርሩንም፧ ለጸሎት የሚመጣን መከልከል አትችሉም፧ ፖሊስ መቅደሱ ውስጥ ማስገባት አትችሉም  የሚል  አልነበረምን?

ወንድሞቼ የቦርድ አባላት ምእመናን   ላይ መቀለድ ትችሉ ይሆናል፤ በፍርድ ቤት ወሳኔ ላይ ግን ባትቀልዱ መልካም ነው። ይህ ደግሞ ወደ መጥፎ ሁኔታ  ያመራል ብለን እንሠጋለን። ያኔ  ማንንም መውቀስ አትችሉም ምላስን ብቻ  እንጂ። የፍርድ ቤቱን  ውሳኔም ሆነ    ም/ ሊቀመንበሩ ያነበቡትን ደብዳቤ የሚከተለውን የድሕረ  ገጽ አድራሻ በመጫን ከተለጠፈበት ከቤተክርስቲያኑ ድሕረ  ገጽ ማንበብ ትችላላችሁ።





ስለእውነት የተባለውን እንዳለ አቅርቦ ለምእመናን የመንገር ሃላፊነት ያለበት ቦርድ ዛሬም በቤተክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ቆሞ ያልተባለ መናገሩ ያሳዝናል። ያሳፍራልም። ቀደም ባለው ጊዜ እንደተናገርነው ቤተክርስቲያኑን ወደ ስደት ሲኖዶስ ለመውሰድ እየተመቻቸ፧ ሰባክያን ከዚሁ ከስደት ሲኖዶስ እየተጋበዙ እየመጡ ለመሆኑ በተከታታይ ያያችሁት ጉዳይ ነው። ሰባኪዎቹም ለይስሙላም ሆነ ከልብ የቦርድ አባላት ገንዘብ ላይ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ አማንያን የሌለው ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን ሊባል እንደማይችል መናገራቸውንም የሰማነው ጉዳይ ነው። አንድ ነገር እዚህ ላይ ለመናገር የምንወደው ለጥቅም የተነሳ ማንም ግለሰብ ከማንም ጋር ሊስማማ  እንደማይችል ነው። 
ይህንን የቤተክርስቲያን ችግር በሰላም ለመፍታት የተነሱትን ግለሰቦች ስም የማጥፋት ዘመቻም ወደ አሳፋሪ  ሁኔታ እየሄደ ያለ  ይመስለናል። ማንም የማንንም ሥም ማጥፋት ይችላል የሚል አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ሁኔታዎች ወደ መጥፎ  እየሄዱ ነውና  ቢያስቡበት መልካም ነው።
በተረፈ ባለፈው ወር ተደርጎ በነበረው የምእመናን ስብሰባ  የተመረጡ የኮሚቴ አባላት ቦርዱ ሊያነጋግራቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ የቦርዱን ውሳኔ  ትክክል አለመሆን ተቀብለው ያወጡትን መግለጫ መረዋ ከዚህ በታች ያቀርባል።

መልካሙን ያሰማን

           


የተባበሩት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመፍትሄ ኮሚቴUNITED ST. MICHAEL CHURCH RESOLUTION COMMITTEE
4509 Beaus Way, Garland, TX 75043 (972) 226-1728



05-23-10

ውድ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን።

በ 5-8-10 ባደረግነው ስብሰባ ላይ በሰጣችሁን ኃላፊነትና ውክልና የአስተዳደር ቦርዱን ለማነጋገር ሞክረን ሳይሳካልን ቀርቷል። እስክ 5-18-10 በደብዳቤ መልስ እንዲሰጡን የጊዜ ገደብ ስንሰጣቸው፣ በቃል ደግሞ ሁለት ቀን ጨምረንላቸው፣ በስልክም፣ በግንባር በማነጋገርም የምእመናኑን ጥያቄ ለማቅረብ ተማፅነን ነበር። ይህ እንዲህ እንዳለ፣ በ 5-23-10 የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ስብሰባ ከመጥራታችን በፊት፣ በ 5-22-10 ከዚህ ጋር አያይዘን የምናቀርበውን የመልስ ደብዳቤ ከቦርዱ ደረሰን።

ለአስተዳደር ቦርዱ ግልፅ ውይይት ፍቃደኝነት ለመስጠት ብለን የስብሰባውን አቋም የሚገልጽ መግለጫ አዘግይተን ዛሬ ከዚህ መሸኛ ደብዳቤ ጋር ለናንተ በትህትና እናቀርባለን።

በሚቀጥሉት ሁለት ወይንም ሶስት ሳምንታት ኮሚቴው እስከ አሁን የወሰደውን ተግባር የሚገመግምና ለወደፊቱ በምን ዓይነት መልኩ ችግሩን ለማስወገድ የሚቻልበት እቅድ ለመንደፍ አጠቃላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስብሰባ እንጠራለን። ቦታውንና ጊዜውን ቀደም ብለን እናስታውቃችኋለን።

1ኛ፡ አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ                                          ሊቀመንበር
2ኛ፡ አቶ ግርማቸው አድማሴ                                       ም/ሊቀመንበር
3ኛ፡ አቶ ብርሃነማርቆስ ታደሰ                                      ፀሐፊ
4ኛ፡ አቶ ሳሙኤል ደንቢ ፈረደ                                    ቃለ ጉባኤና የEቅድ ሥራ
5ኛ፡ ዲ/ን አርአያ ኃይለመስቀል                                    የኃይማኖት Aማካሪ
6ኛ:  አቶ ንጉሤ ጀንበሩ                                              የፍትሕና የሕግ Aማካሪ
7ኛ፡ አቶ ቢራቱ ዎዳ                                                  የፍትሕና የሕግ አማካሪ
8ኛ፡ አቶ ደመላሽ ደበበ                                               የሕዝብ ግንኙነት
9ኛ፡ ወ/ሮ በየነች መኮንን                                            የሕዝብ ግንኙነት


የተባበሩት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመፍትሄ

UNITED ST. MICHAEL CHURCH RESOLUTION COMMITTEE
4509 Beaus Way, Garland, TX 75043 (972) 226-1728
tadesse1@aol.com

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አሀዱ Aምላክ Aሜን።

5-13-10

ለተከበራችሁ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የቦርድ አባላት።

የአክብሮት መንፈሳዊ ሰላምታችንን እናቀርባለን።

ቤተክርስቲያናችን ውስጥ በተፈጠረው ችግር በግምት ቁጥራቸው ወደ 200 የሚጠጉ ምእመናን ግንቦት 1 ቀን 2002 ዓም (May 8, 2010) ተሰብስበው ከተወያዩ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ የቦርድ አባላት ጋር ተነጋግሮ የደረሰበትን ውጤት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሚያቀርብለትን ኮሚቴ በመሰየም ጉዳዩን እንድንከታተል በመጨረሻው ስማችን የተዘረዘረውን መርጦ ተለያይቷል።

የቤተ ክርስቲያኑን ችግር በቦርድ አባላት ላይ ብቻ ጥሎ በጎን ሆኖ መመልከት ክርስቲያናዊ አሰራር ያለመሆኑን ያመነበት ጉባኤ ሲልከን እኛም አቅማችን የፈቀደውን ያህል ለመርዳት ፈቃደኞች መሆናችንን አረጋግጠናል።

ስለዚህ፤ ምንም እንኳን ለችግሩ ከማንም የበለጠ የቦርዱ አባላት ኃላፊነትና ግዴታ መሆኑን ብንረዳም እኛም አደራ ለጣለብን ምእመናን በሰጠን የጊዜ ገደብ ውስጥ መልስ ለመስጠት እንድንችል ከግንቦት 11 ቀን 2002 ዓም (May 18, 2010) በፊት በጋራ ለመሰባሰብ ቀንና ሰዓቱ ቀደም ብሎ እንዲገለጽልን እናሳስባለን።

ቅዱስ ሚካኤል ሰላሙን ይስጠን።

አባላት፡ ተፈራወርቅ አሰፋ                                                       የኮሚቴ ሰብሳቢ
ግርማቸው አድማሴ
ንጉሴ ጀንበሩ
ብርሃነማርቆስ ታደሰ
ደመላሽ ደበበ
በየነች መኮንን
ዲ/ን አርአያ ኃይለመስቀል
ቢራቱ ዎዳ
ሳሙኤል ደንቢ ፈረጃ













የተባበሩት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመፍትሄ
UNITED ST. MICHAEL CHURCH RESOLUTION COMMITTEE
4509 Beaus Way, Garland, TX 75043 (972) 226-1728
tadesse1@aol.com

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አሀዱ አምላክ Aሜን።

5-11-10

መግለጫ

ቅዳሜ አንደ አውሮፓ ዘመን Aቆጣጠር ግንቦት 8 ቀን 2010 (አንደ Iትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 1 ቀን 2002), በደብል ትሪ ሆቴል ሪቻርድሰን፡ ቴክሳስ በግምት ወደ 200 የሚጠጉ የቅዱስ ሚካኤል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታይ ምእመናን፣ በቅርቡ በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ክርስቲያናዊ እምነትን የማያንፀባርቅ በAማኝ ወጣቶች፣ እናቶችና አባቶች ላይ የደረሰውን አሳፋሪ ተግባር በመቃወም ቤተክርስቲያናችን አሁን ካለችበት አስከፊ ተግባር ተላቃ የአማኞች ቤትነቷን ለማረጋገጥ የምንችልበትን በጋራ ለመሻት የተደረገ ስብሰባ ነበር።

ይህ ስብሰባ ወይንም ጉባኤ ምእመናኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ክርስቲያናዊ ገንቢ ሃሳብ የሰጡበት ሲሆን፣ ለወደፊት የአባላት መብት ተከብሮ ሰላምና ፍቅር ተመስርቶ ሕዝቡ ኃይማኖቱንና ባህሉን ተከትሎ አንዴት አንደሚኖርም በሰፊው ተወያይቷል።

ይህንንም ሃሳብ ከግብ ለማድረስ በተለያየ መልክ ተደራጅተው ያሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ለሰላም፤ ለAንድነትና ለኃይማኖት መስፋፋት ተገቢውን ሚና በመጫወት ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጉባኤው አሳስቧል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ የስብሰባው ታዳሚ መሠረታዊ የሆኑትን የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ችግሮች ካጤነ በኋላ በመፍትሔ ሃሳብ ላይ በማተኮር የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል።

ተሰብሳቢው የሚከተሉትን የAቋም ውሳኔዎች አሳልፎ ለተመረጠው ኮሚቴ ሙሉ የውክልና መብት ሰጥቶታል።

1ኛ. ሁለት መሠረታዊ ሂደቶችን የተከተለ መፍትሔ

ሀ. ልዩነት ከመፈጠሩ በፊት የነበረው የAባላት መብት አንዲከበር
ለ. ሁሉን አቀፍ የሆነ ጊዜአዊ የአመራር ኮሚቴ አሁን ባለው ምትክ Eዲቋቋም

2ኛ. የአቋም መግለጫውም፤

ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ እረፍት የምናገኝበት፤ እምነታችንን የምናጠነክርበት፣ ባህላችንን ለልጆቻችን የምናስተምርበት፤ መፈቃቀርን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትን የምናሳይበት ቦታ ሆና ቆይታ ነበር። በተደጋጋሚ በሽማግሌዎች ችግሮችን ለመፍታት ተሞክሮ የአስተዳደር ቦርድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ መፍትሄ ለማግኘት አልተቻለም። በአሁኑ ወቅት ግን የቤተክርስቲያኑ Aካሄድ ያሳሰባቸው ጥያቄ አለን ሲሉ በፖሊስ የሚወገዱበት፣ አባል ለመሆን የማመልከቻ ተከፍሎ ቦርድ ከፈቀደ ብቻ መቀላቀል የሚቻልበት፤ ክርስቲያን ሆኖ ለመጠመቅ እንኳን ክፍያ የሚጠየቅበት ሆኗል።

ሀ. እኛ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ምእመናን፣ በቤተክርስቲያናችን ከእምነታችን ውጭ በአስተዳደር ቦርዱ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እጅጉን ያሳዘነን ሲሆን ለዚህም ቦርዱ ይቅርታ እንዲጠይቅ።

ለ. የሚደረገው የአባላትን ቁጥር በዘዴ የመቀነስ፣ ቦርዱ ያልተስማማውን የማባረር ሁኔታዎች በአስቸኳይ ቆመው ቤተክርስቲያናችንን ወደነበረበት ይመለስና ፈቃደኛ የሆነው ሁሉ አባል የሚሆንበት ሁኔታ እንዲመቻች።

ሐ. ሳንወያይበት የተቀየረው መተዳደሪያ ደንብ ወደነበረበት ተመልሶ፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት ተደርጎ ሁሉም የሚያምንበት ደንብ እንዲሆን ለማድረግ ሁኔታዎች እንዲመቻቹና አዲስ ምርጫ በአስቸኳይ እንዲደረግ።

የተሰብሳቢውን ሃሳብ ተረድቶ ወደ መፍትሔው ተግባራዊነት የሚመራ ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ የሚከተሉትን የኮሚቴ አባላትን መስርቷል።

ቅዱስ ሚካኤል ሰላሙን ይስጠን። አሜን።

1ኛ፡ አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ                                         ሊቀመንበር
2ኛ፡ አቶ ግርማቸው አድማሴ                                      ም/ሊቀመንበር
3ኛ፡ አቶ ብርሃነማርቆስ ታደሰ                                     ፀሐፊ
4ኛ፡ አቶ ሳሙኤል ደንቢ ፈረጃ                                   ቃለ ጉባኤና የእቅድ ሥራ
5ኛ፡ ዲ/ን አርአያ ኃይለመስቀል                                   የኃይማኖት አማካሪ
6ኛ፡ አቶ ንጉሤ ጀንበሩ                                            የፍትሕና የሕግ Aማካሪ
7ኛ፡ አቶ ቢራቱ ዎዳ                                                የፍትሕና የሕግ አማካሪ
8ኛ፡ አቶ ደመላሽ ደበበ                                             የሕዝብ ግንኙነት
9ኛ፡ ወ/ሮ በየነች መኮንን                                         የሕዝብ ግንኙነት 2

Wednesday, May 19, 2010

ለመብታችሁ የቆማችሁ እንኴን ደስ ያላችሁ ቁጥር ፳፰

ፍርድ ቤት እንዴት ዋለ? ይላል የአገራችን ሰው። አዲስ እሱን የሚመለከት ነገር እንዳለ  ለመጠየቅ ሲያስብ ነው ይህንን  የሚለው። እናንተም በፊናችሁ የትላንቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ  እንዴት ነበር?  ብላችሁ ብትጠይቁ ያገኛችሁት መልስ የተለያየ  ሊሆን ይችላል። የስኴር በሽታ ይዞት አንድ እገሩ ስለተቆረጠ ሰው ሁኔታ የተለያየ  ሰዎች ሲያወሩ የተለያየ  ነገር ቢናገሩ አይገርምምና። "አንደኛው የሚያሳዝን ነው አንድ እገሩን ቆረጡት" ሲል ሌላው ደግሞ  በፊናው " እግዜር ይመስገን ሁለት እግሩ ሳይቆረጥ ቀረ" ብሎ እንደሚናገረው አይነት መሆኑን ለመጠቆም ያክል ነው። መረዋ በበኩሉ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር፤ ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችልና የግለሰቦች የማምለክ መብት በጥቂት ጉልበተኞች ሊነጠቅ አለመቻሉን ነው።

በትላንትናው እለት ሁለት ነገር የተከናወነ  ሲሆን አንደኛው በይግባኙ ቀጠሮ አስፈላጊው የመልስና የመከራከሪያ ነጥቦች ለፍርድ ቤቱ በጠበቃው ተቀነባብሮ መግባቱን ስንነግራችሁ ውጤቱን ወደፊት በሚደርስ ሰዓት የምንሰማው  ነውና መረዋም ጉዳዩን ተከታትሎ   የሚዘግብ   መሆኑን  ቃል ይገባል። በተረፈ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይደርሱ ተወስኖባቸው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል ሁለት ግለሰቦች መስርተውት የነበረው ክስ የፍትሕ ቀኑ ደርሶ  የተፈጠረውን ለመመስከር የደረሰባቸውን በደል ለዳኛው ለማሳየት እድል በማግኘታቸው ማንም ለመብት እቆማለሁ የሚል ግለሰብ ሊደሰትበት የሚገባ ጉዳይ እንደነበረ ልናወሳችሁ እንወዳለን። 

ምንም ነገር ሳያደርጉ ለመጸለይ ከመጡበት ቤተክርስቲያን በፖሊስ ታስረው የወጡት እናት ከምስክር ወንበር ላይ ሆነው የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ  ሁኔታው እየታወሳቸው ያለቅሱ የነበሩት እሳቸው ብቻ  ሳይሆኑ ያዳምጣቸው  የነበረው  ሁሉ እንደነበር መናገርም እውነት ነው። በቀኑ የነበረውን ሁኔታ  እነደገና በቴሌቪዥን እንዳየነው በድጋሜ ፍርድ ቤት ሲታይ በእውነት ይህ የተደረገው እኛ  ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው? የሚያሰኝም  ነበር።  ወንድሞቼ  ሽማግሌዎቻችን የት ደረሱ? የሚል ቢያጋጥማችሁ አትገረሙ።
የተለያዩ ምስክሮችን ያቀረቡት የከሳሽ ጠበቃ  ከተጠበቀው በላይ ጉዳዩን እንዳጠኑት በግልጽ ያሳይ ነበር።
በእለቱ የቦርዱን ውሳኔ ትክክለኝነት ለመናገር በምስክርነት ቀርበው የነበሩት ዶክተሩና አቶ አበራ  ምን ብለው እንደመሰከሩ ወደፊት የፍርድቤቱን የቃል በቃል ግልባጭ  (TRANSCRIPT)  ስናገኝ ቃል በቃል እንደምናቀርብ ቃል እየገባን በሁኔታው እራሳቸው እንኴን ደስተኛ እንዳልነበሩ ግን  መናገር ሃቅ ይሆናል።

ይህ ክስ ከተጀመረ  በኋላ  ለጠበቃ ገንዘብ ከቤተክርስቲያኑ ካዝናም ሆነ ባንክ አላወጣንም ያሉት እነዚህ ግለሰቦች የተናገሩት እውነት መሆን አለመሆኑን በሂደት ወደፊት የምናየው ሲሆን ለጊዜው ገንዘብ ለማውጣታቸው የቀረበ  ማስረጃ  ባለመኖሩ የገንዘቡ እገዳ  ሲነሳላቸው የቀረው እገዳ  ግን ጉዳዩ ወደፊት በሰፊው እስኪታይ ድረስ እንዲቆይ መወሰኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን።

በውሳኔው መሰረትም

1  ማንም አማኝ ከቤተክርስቲያን ሊወገድ እንደማይችል የእምነት መብቱ የተጠበቀ  መሆኑን የቦርድ አባላትም ይህንን መብት   መጋፋት እንደማይችሉ የተወሰነ  መሆኑን።

2   ምንም አይነት የቤተክርስቲያኑ ዶሲዎች እንዳይነኩ እንዳይጠፉ

3  ፖሊሶች በምንም አይነት ወደ መቅደሱ እንዳይደርሱ መወሰኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን።

ለራስ መብት መቆም ማለት የሌላውንም መብት ማስከበር ነውና  በቦርድ አባላት ውሳኔ  ተገፎ  የነበረው (THE FIRST AMENDMENT RIGHT ) የመጀመሪያው የአሜሪካን ሕገ መንግስት ማሻሻያ መብት ማንም ሊጋፋው የማይችል መሆኑን የቦርድ ባለስልጣኖችም እንዲገነዘቡት መደረጉ ለሁላችንም የወደፊት ተስፋ  ነው።

ትግላችን የመብት ጉዳይ ነው

ፍትሕ ባለበት አንባገነኖች አይነግሱም  


Tuesday, May 11, 2010

የተጠራው ስብሰባ በጥሩ መንገድ ተጠናቀቀ ቁጥር ፳፯

ምእመናን እንዴት ከረማችሁ።

ባለፈው ቅዳሜ የቤተክርስቲያናችን ችግር ያሳሰባቸው ግለሰቦች ጠርተውት የነበረው ስብሰባ  ከ 300 ያላነሰ  የኦርቶዶክስ አማንያን የተሳተፉበትና ለመጀመሪያ ጊዜ ሥነ ስርዓት የታየበት: መደማመጥና መግባባት የሰፈነበት እንደነበረ ከስፍራው በመገኘት ለመመስከር እድል ማግኘታችንን ልናወሳችሁ እንወዳለን። ተሰብሳቢው ምእመናን በቤተክርስቲያናችን አካባቢ የተደረገው ድርጊት ያስቆጣቸው መሆኑን ባንድ ቃል ከመስማማታቸውም በላይ፤ ወደፊት ለሚደረገው ሁሉ በሙሉ ልብ ተሳታፊ ለመሆን ቆርጠው መነሳታቸውንና ቤተክርስቲያኑን ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ መግባባት እንዲሰፍን፤ መከባበር ጎልቶ እንዲታይ ሙሉ ጥረት ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ልንነግራችሁም እንወዳለን። በስብሰባው ላይ በቀረበ ጥያቄና  መልስ ደግሞ 22 የቤተክርስቲያን አባላት ከቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ቦርዱ በመወሰኑ፤ በሁኔታው የተበሳጩ የመብታቸው መረገጥ ያንገበገባቸው ግለሰቦች በትናንትናው እሁድ ቦርዱ በፖሊስ ሊያባርራቸው መወሰኑን ለማስቆም ወደ ፍርድ ቤት ሄደው አርብ እለት ከፍርድ ቤት የማገጃ ወረቀት ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ማገጃ  መሰረት

ማናቸውም ለጸሎት የሚመጡ ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን መግባት እንዳይከላከሉ  ወስኗል። ይህንን ውሳኔም ፖሊስ እንዲያውቀው መደረጉም ለተሰብሰቢው ተነግሯል፡


2   የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ለቤተክርስቲያኑ አስፈላጊ የቀን ተቀን ወጭዎች ሌላ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ  እንደተደረገበትም  ለተሰብሳቢው ተነግሯል ፤


3  የቤተክርስቲያኑ ዶሲዎችና በኮምፒውተር ያሉ ሰነዶች በተለያየ መንገድ የተያዙ  ማናቸውም መረጃዎች እንዳይጠፉ  እንዳይቀደዱ እንዳወረወሩ ፍርድ ቤቱ ማዘዙን ግለሰቦቹ  ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቱ ጊዜዊ እገዳ ውሳኔ ሲነበብ ተሰብሳቢው ዳር እስከዳር በጭብጨባ ድጋፉን እንደሰጠም መናገር እንወዳለን።

ውድ የኦርቶዶክስ ቤተሰቦች  

አሁንም መረዋ ትናንት ይል እንደነበረው በክስ የቤተክርስቲያን ፍቅርና  ሰላም ይመለሳል የሚል እምነት እንደሌለው እየገለጸ፤ አማራጭ አጥተው ወደ ሕግ የሄዱትን  ግን ሙሉ ለሙሉ አክሄዳቸውን የሚቀበልና ለምን እንዳደረጉት እንደሚገባው መናገር ይወዳል። በልመና እስካሁን መቆየቱ የባሰ  ችግር እንጂ ሰላም አላመጣምና።

ቤተክርስቲያን እንዴት ይከሰሳል?
ብለው ለሚጠይቁ ግለሰቦች እናንተም በበኩላችሁ
ፖሊስ እንዴት መቅደስ እንዲገባ ተደረገ?
ብላችሁ ልትጠይቌቸው ይገባል። ሁላችንም እንደምናምነው   ቤተክርስቲያን ይቅርና ትምሕርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንኴን ፖሊስ የመግባት መብት የለውም ብለን እንከራከር የነበርን ግለሰቦች እንዴት ዛሬ  መቅደሱን በ k9 የፖሊስ  አድምበታኞች  እናስደፍራለን?  

ስለመብት እንሞታለን የሚል ግለሰብስ እንዴት የሌላውን የመጸለይ መብት ሊጋፋ  ይነሳል?

ስለ ሃይማኖት አላውቅም ማለት ሌላ ነገር ሆኖ  እያለ በእምነት ፖለቲካ  ማካሄድ ደግሞ ሌላ ስህተት አይደለምን?
ባለፈው እሁድ ቦርዱ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የበተነውን ወረቀት ያየ  ደግሞ ቦርዱ እምነትን ወደ ጎን ትቶ ፖለቲካ  እያካሄደ  ለመሆኑ ግልጽ መረጃ እየሰጠ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት  አጸዳኋቸው  ያለንን የመሃበረ ቅዱሳንን አባላት  ዛሬም       "ጆሮ ቆራጭ " መጣብህ  አይነት  እያነሳ  ሊያስፈራራን መሞከሩን ስናይ አዘንን እንጂ አልተገረምንም። ይልቅስ ቦርዶቹ የምእመናንን ግፊት ተቀብለው  የስደት ሲኖዶስ አንቀበልም ማለታቸውን ስናነብ  ሃሌ ሉያ ማለታችን ልንነግራቸው እንወዳለን።

በማያያዝ ሃይማኖትን የዘር መለያያ ለማድረግ፤ አማራ ትግሬ በማለት መንግስትንና  እምነትን ለማጠላለፍ መሞከራቸው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል። ነገሩ የውሸት ውንጀላ ነው እንጂ ቢሆን እንኴን እነሱ የተለያየ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ሆነው ለማምለክ እንደሚመጡ ሁሉ ሌላውም የመንግስት ደጋፊ የመደገፍ መብት እንዳለውና ለአምልኮ  መምጣትም እንደሚችል መቀበል ነበረባቸው። አማራ የሆነ መብት ካለው ደግሞ ኦሮሞም ትግሬም ኤርትራዊም ሆኖ  ባንድ የማምለክ መብቱ ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ነው እንላለን።  ስለሚካኤል በፖለቲካ  ሳይሳካልን  ሲቀር ሕዝቡን በእምነት አንከፋፍለው።

በመጨረሻም በዚሁ በቅዳሜው ስብሰባ  የነበረው ሕዝብ ባንድ ቃል ቤተክርስቲያናችን ወደነበረበት ለመመለስ ተስማምቶ ለዚህም ሕጉ ወደነበረበት እንዲመለስ። አባላት ካለምንም ገደብ ይከፍሉ የነበረውን እየከፈሉ መመዝገብ እንዲችሉ እንዲደረግ ይህንን በስራ ሊተረጉሙ የሚችሉ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው የስልጣን ሱስ ያላናወዛቸው ግለሰቦችን ማሳተፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንዲሆን፤ ይህንንም በስራ  ለመተግበር ከቦርዱ ጋር እሚያቀናጁ 9 ምእመናን ያለበት ኮሚቴ አቌቁመው የስብሰባው ፍጻሜ  ሆኗል።

ተሰብሳቢዎቹ ያላግባብ የተሰናበቱት ካህናት ወደ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ጥረት እንዲደረግ አሳስበው፤ ለዚህም ቦርዱ የመቻቻል መርህ ቢከተል የተሻለ  እንደሚሆን አሳስቧል። ክርስቲያን የሆነውን የኦርቶዶክስ አማኝ አይደለህም የማለት ችሎታውም ብቃቱም የሌለው ቦርድ እራሱን እንዲያስተውልና  ወደሰላም እንዲመለስ ጥረት ቢያደረግ ይሻላል  በማለትም ስምምነት ላይ ደርሷል።

ቦርዱ ያባረራቸውን ካህን እርዳታ አስመልክቶ ቀደም ሲል  ለዚሁ ጉዳይ ተሰብስቦ  የነበረው ቡድን ያቌቌመው ሌላ ኮሚቴ ስራውን እየሰራ  መሆኑ ተነግሮ  በተለይም የካህኑን የመኖሪያ  ፈቃድ ለማደናቀፍ ቦርዱ የሚያደርገውን አሳፋሪ ተግባር እንዲያቆም ጥያቄ  ለማቅረብ መታሰቡን ከስፍራው የነበሩ ግለሰቦች ገለጻ ሰጥተዋል። ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ ትብብራችንና  እርዳታችንን እንድናሳይ መረዋም በበኩሉ ጥሪ ያደርጋል። ቤተክርስቲያን ስደተኛን ትደግፋለች እንጂ ስደተኛ ለመፍጠር አትተባበርምና።

የጅምሩን ፍጻሜ  ያሳምርልን

አሜን
  

Tuesday, May 4, 2010

የተገፋ እንጂ የገፋ ይጸድቃል ብላችሁ እንዳታስቡ ቁጥር ፳፮

ውድ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አባላት።

በሰራችሁት ቤተክርስቲያን እንደ እንግዳ፤ በመጠየቃችሁ እንደ ወንጀለኛ፤ ለመብት በመቆማችሁ እንደ ከሃዲ፤የተቆጠራችሁ። ከመቅደስ በፖሊስ ተገፍታችሁ በፌሮ እጃችሁ ለተጠፈረው፤ ለእስራት ለተጋረዳችሁ። ለፈጣሪ እንጂ ለሰው አናጎበድድም በማለታችሁ ለተወገዛችሁ ከሥራ ለተባረራችሁ አባቶች። ለሁላችሁም ምስጋና ይድረሳችሁ።

እነሆኝ ለቅሶአችሁ የገባቸው በደላችሁ የተሰማቸው ምእመናን በዝምታ የሚደረግ የለምና ተሰብስበን መወያየት አለብን ብለው ለፊታችን ቅዳሜ ስብሰባ መጥረታቸውን ሰምተናልና ሁላችሁም በስብሰባው ላይ እንድትገኙ መረዋም ጥሪውን ያቀርባል።

በዝምታ ያተረፍነው ነገር ቢኖር ንቀትን ብቻ ነው።
ሁሉም ለመብቱ የመታገል ግዴታ  አለበት።

ቤተክርስቲያን የመንፈሳዊ ቦታ  እንጂ የፍራቻ ቦታ መሆን አይኖርበትም።

ሰው ማምለክ  የሚችለው መጀመሪያ መብቱ ሲጠበቅ ብቻ ነው።
ኑ በስብሰባው መታሰር አይኖርም።
ኑ በስብሰባው መታፈን አያጋጥማችሁም።



ለመወያየት እንጂ ለመጣላት መሰብሰብ አያስፈልግምና ለመጣላት ለመሳደብ እቅድ ያላችሁ እባካችሁ አትምጡ።



ቀኑ



5-8-2010



ሰዓት



4፡00 P M



ቦታ



Double Tree Hotel Dallas


Richardson


1981 North Central Expressway,


Richardson


TX ,75080

972 808 5386

Sunday, May 2, 2010

ቤተክርስቲያናችን የፖለቲካ መፋለሚያ ሜዳ እየሆነ ነው ቁጥር ፳፭

ውድ የቅዱስ ሚካኤል አማንያን። እስካሁን ትእግስቱን ያደላችሁ ፈጣሪ አምላክ አሁንም ትእግስቱን ይስጣችሁ። በአማንያንና እምነት በማያስፈራቸው መካከል ፤ አንገታቸውን በደፉና የልብ ልብ በተሰማቸው መካከል ያለውን ልዩነት እያየን ያለን   ይመስለናል። ፈሪሃ  እግዚአብሔር ያደረበት በክርስቶስ አምላክነት የሚያምን ሰው የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪዎች ምእመናትን በፖሊስ አስከብበው አምልኮ ለማድረግ እየሞከሩ ነው ብላችሁ ስትነግሩት ለማመን የሚቸገር የኦርቶዶክስ አማኝ ቢያጋጥማችሁ የእምነት ጥንካሬውን ያሳይ እንደሁ እንጂ ጥርጣሬ እንዳይመስላችሁ።

በዛሬው እለት አቶ አበበ የቦርዱ ጸሐፊ በመላከ ሳህል አወቀ  ላይ የተደረገውን ወሳኔ አስመልክቶ ለመባረር ያደረሳቸውን ጥፋት ለመተንተን በቤተክርስቲያኑ መንበር ላይ ወጥተው ሊናገሩ ሲሞክሩ ነገሩ ያንገሸገሻቸው እናቶች ጥያቄ አለን እያሉ ሲናገሩ አቶ ሙሏለምና አቶ አበራ ፊጣ ከውጭ ሆነው ትእዛዝ ይጠባበቁ የነበሩትን ፖሊሶች ከነጫማቸው እየመሩ ወደቤተክርስቲያን በማስገባት እናቶች እግዚኦታቸውን በጉልበት እንዲያቆሙ አድርገዋል። እግዚኦታ አናቆምም ያሉት እናት ታስረው ወደ ፖሊስ መኪና ሲወሰዱም ያዓይን ምስክር ነበርን። በሌላ ወገን እኝሁ አቶ  ሙሉዓለም የቦርዱ  ም/ ሊቀመንበር ፖሊሶችን እየመሩ ወደ ትምህርት ቤቱ በመሄድ አቶ ቴዎድሮስንና አቶ  መንግስቱን ከቤተክርስቲያኑ እንዲያባረሩላቸው ከመጠየቃቸውም በላይ ሁለተኛ ወደ ቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ፖሊሶች እንዲያስፈርሟቸው ማድረጋቸውን ለመረዳት ችለናል።

ትላንት ለኛ አልተገዙም ያሉትን ካህናት ያባረሩ የቦርድ አባላት፤ ዛሬ እናቶችን በልጆቻችን ፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ ማጎሳቆልና ማሳሰር፤ የማይፈልጉትን እየመረጡ እንዳትመጣ እያሉ ማስፈራራትንና ማስፈረምን ተያይዘዋል። ሕግ አክባሪ የሆነው ምእመን በሁኔታው እያዘነ በተለይ እናቶች ነጠላቸውን እያነጠፉ እናት እንደሞተበት እንባቸውን ሲያነቡ ያየ  ያለሁት በእውነት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው ወይ? ብሎ  ቢጠይቅ እውነት አለው።

የሁሉንም እንባ የሚቀበል ፈጣሪያችን የናቶችንና ያባቶችን በተለይም የወጣቶቹን እንባ  እንደሚሰማ  ምንም ጥርጥር የለንም።
ስለሆነም በተደረገው ሳንደናገጥ ባንድ ላይ መቆም ያለብን አሁን ነው። ድል የመቱ የመሰላቸው ፖለቲከኞች እንደ ልማዳቸው እየተሳሳቱ መሆኑን ለማሳየት ባንድ ላይ ሆነን በሕግ ከመታገል ሌላ  ምንም አማራጭ እንደሌለ መገንዘብ የግድ ይሏል። የሽማግሌዎችን የስራ ውጤት እስካሁን ጠበቅን ካሁን በኋላ አማራጩ ሕጋዊ ብቻ መሆን አለበት። አባል መሆን ብቻ ነው የሚያዋጣው ለሚሉት መልሰ: ቤተክርስቲያን አትድረሱ እያለ  በፖሊስ የሚያባርር የቤተክርስቲያን አመራር አባል የማይፈልገውን አባል $50 ከፍሎ  ማመልከቻ  ቢያስገባ ይፈቅዱለታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለናል።  ያውም ከዓመት በኋላ ለሚሰጥ የመምረጥና  የመመረጥ መብት። በ ፩ ዓመት ውስጥ በዚህ ቤተክርስቲያን ላይ ምን ያክል በደል ሊያደርሱ እንደሚችሉም መመልከት የማይችል ወይም የነሱን ሥራ የሚያጸድቅ ብቻ  ነው ዓመት መጠበቅ አለብን የሚለን።

አባት ሽምግሌዎችን አይተናል አልተንቀሳቀሱም። የቦርዱ አመራሮች አሁን በፖሊስ እስከተመኩ ድረስ እኛ ደግሞ በሕግ መብታችንን ለማስገበር መነሳት አማራጭ የሌለው ነው እንላለን።

ቀጣዩን  እርምጃ  ሰሞኑን እናሳውቃችኋለን። በፖሊስ ታስረው ለነበሩ እናት ከልብ ሐዘናችንን እየገለጽን ክርስቶስ ለቅሶአቸውን እንደሚሰማ እንዳይጠራጠሩ አብረን በጸሎት እናበረታታለን።

ክርስቶስ ልባቸው የደነደነውን ያስብ። መንፈስ ቅዱስን ያውርድላቸው።

አሜን