Saturday, July 17, 2010

ስብሰባው እንደጠረጠርነው ካለውጤት ተበተነ ቁጥር ፴፯

በዛሬ  እለት ተጠርቶ  የነበረው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ስብሰባ ምልአተ  ጉባኤ  አልሞላም ተብሎ ስብሰባው መበተኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን። መረዋ መቼም ቢሆን ቦርዱ ቅንነት ያለበት የምእመናን ስብሰባ እንዲደረግ ያደርጋል ብሎ ተጠራጥሮ  ስለማያውቅ ለሁኔታው አዲስ አልሆንም። እንዴውም ጥርጣሬውን የበለጠ አጠናከረው ማለት እውነት ይሆናል።   እንደ ቦርድ አባላቱ አባባል የተመዘገበው የአባላት ቁጥር 328 አካባቢ መሆኑ ሲነገር ለስብሰባው የተገኘው ምእመናን  ቁጥር ግን ወደ  65 አካባቢ እንደነበር ስንነግራችሁ ይህ ቁጥር ደግሞ በሆቴል ተሰብስቦ የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ አሳስቦናል ካለው ከሁለት ጊዜ  ስብስብ እጅጉን አንሶ  መገኘቱን ስናይ የሞራል ድጋፍ ሆኖናል የቦርዱን ደጋፊዎች ደግሞ እንደሚስደነግጥ  እርግጠኞች ነን። ለምን  ምእመናት አልተገኙም ለሚለው ብዙ ማለት ቢቻልም የቦርዱ አባላት ግን በነደፉት መተዳደሪያ ደንባቸው 2.6 ላይ እንደሚለው (....... if  the a meeting is  called but fails for lack of a quorum two times,  the matter under consideration may be determined by the Board of  Trustees in its discretion.......) ስብሰባ  ተጠርቶ በምልአተ ጉባኤ አለመሙላት ሁለት ጊዜ  ከተበተነ ለውይይት ሊቀርብ የታሰበው ጉዳይ ቦርዱ በመሰለው ይወሰናል..... ትርጉም የራሳችን የሚለውን ተጠቅሞ ለመወሰን የታቀደ  እንደሆነ ለመገመት ግን ጊዜ  አልወሰደብንም።

በተለያየ  ሰዓት እንደ ዳላስ አየር  የሚቀያየረው  "የአባላት ቁጥር  ከመቼው  300  ገባ?   ብለው የጠየቁ ተሰብሳቤዎች እንደነበሩ ስንነግራችሁ ከተሰብሳቢዎቹ መሃከል በቦርዱ በተደነገገው መተዳደሪያ  ደንብ 9.1 (........... For a purpose reasonabel to the member's interests as  a member, any  member of the church may:
(i)      inspect and copy the records of member's names and address during usual church hours upon resonable written notice to the Secretary;........................ ) እንደ  አባል የአባላትን ጥቅም አስመልክቶ ማንም የቤተክርስቲያኑ አባል ምናልባት:
(ለቤተክርስቲያኑ ጸሃፊ በቂ ጊዜ  የሚሰጥ ደብዳቤ  ጽፎ  በማስገባት በስራ  ሰዓት የአባላትን ዝርዝር ስምና  አድራሻ የመመርመር ብሎም የመገልበጥ መብት ይኖረዋል....... )
የሚለውን በመጥቀስ የአባላት ዝርዝር እንዲያሳዮቸው መጠየቃቸውን ልናወሳችሁ እንወዳለን። ይህንን  ጉዳይ አስመልክቶ ቦርዱ ፍርድ ቤት ድረስ የተከራከረበት ጉዳይ በመሆኑ በቀላሉ ሕግ አክብረው ያሳዩናል  ብለው ከጠበቁ የዋህነት ያለ ይመስለናል።  በተለይም ስብሰባው ሆን ተብሎ የተዘጋጀ እንደነበረ  ከብሎጋቸው የተጻፈውን አጀንዳ ማየቱ ጠቃሚ ይመስለናል።

ያም ሆነ ይህ

ተው አትነካኩን አትፍጁን በነገር
እኛም ትኋን በልቶን  አልተኛንም ነበር

ያለው ባንሳሳት የወገራ  ሰው ነበር መሰል።

ጊዜ ያመጣውን ጊዜ  እስኪመልሰው
........... ተጫወተ  በሰው።  ያለው ዘፋኝ ግን ስሙን ዘነጋነው።

በጉልበት የተነጠቀ  መብታችን በሕግ ይከበራል። እኛ ከሕግና  ከእምነት ውጭ ጉልበት የለንም።

Sunday, July 4, 2010

ውግዘቱ ባልከፋ ቁጥር ፴፮

እንዴት ሰነበታችሁ ውድ አንባብያን

በዛሬው እለት በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ስርአተ  ቅዳሴ  የተሳተፋችሁ በመላ  የሰማችሁት አዲስ ነገር እንዳለ ይገባናል። ይኸውም የቦርዱ ጸሃፊ ከቅዳሴ  በኋላ ተነስተው የተናገሩት በየብሎጉ ላይ የሚጻፈው ስድብ የቤተክርስቲያንን ሽማግሎዎች የሚዘልፈው ስም የሚያጠፋው ሁሉ መቆም እንዳለበትና ይህም በየብሎጉ የተጻፈው የቦርዱ ጽሑፍ  እንዳልሆነ  የሚያስተባብል ነበር ክርስቲያኖች የልባቸው ሲነካና ሲደሰቱ ሃሌ ሉያ ይላሉና  መረዋም ሃሌ ሉያ  ሊል ይወዳል። እነዚህ በስድብ የተካኑ የቦርዱ ደጋፊ ብሎጎች ያትሙትና  ያወጡት የነበረው ብዙው ከቦርዱ ብቻ  ሊያገኙ የሚችሉትን ዶክሜንቶች እንደነበረ  ያደባባይ ሚስጥር  ስለነበረ ዛሬ ሁኔታው ወዳላሰቡበት መንገድ እየሄደባቸው በመሆኑ እራሳቸውን ሊያሸሹ ቢሞክሩ አንደንቅም። እንዴውም ባለፈው በክራውን ፕላዛ ተደርጎ  በነበረ  የምእመናን ስብሰባ  ላይ አንድ ግለሰብ "ይህንን በየብሎጉ የሚጻፉ አሳፋሪ ጽሑፎችን ቦርዱ እስካሁን ያላስተባበለው ከመሆኑን በላይ ጸሃፊዎቹ በጽሑፋቸው እንደ ቦርድ እንጂ እንደ ውጭ ታዛቢ አለመዘገባቸው የቦርዱ አበጃችሁ ባይነት ማስረጃ  መሆኑን ተናግረው ነበር።" ተናጋሪው "ባገራችን ሙት ክቡር እንደሆነና  አሁን ግን የሙታንን ስም እየጠሩ ለማስፈራሪያ መጠቀማቸው ያሳዘናቸው መሆኑንም "መናገራቸውን እናስታውሳለን። እነሆ ሁለት ሳምንት ባልሞላ  ጊዜ  ውስጥ የቦርዱን ጆሮ  ስቦ ማስተባበያ  መስጠት ላይ ከደረሱ የስብስቡ ሃይል እየሰራ  ነው ብለን እያመንን ነው።

በተጨማሪም ቦርዱ በያዝነው ወር በ 17 በጠራው ስብሰባ  ላይ ምንም እንኴን አጀንዳ  ነው ብለው የሚያቀርቡት ገንዘብን አስመልክቶ  ኦዲት አድርገናል ለማለትና  ለክስ መከላከያ  መሆኑ ቢገባንም። ከቁጥጥራቸው  ውጭ ሆኖ  የብሎግና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ባባላት ቢነሱ ተናግረናል ለማለትና  ባጭር ለመቅጨት የታሰበ  እቅድ  መሆኑን ለማወቅም  ምሑርነትን   አልጠየቀንም።

በተጨማሪም ካህኑ የስድብ ብሎግን አስመልክቶ  ማውገዛቸውን ስናዳምጥ ያልነው ነገር ቢኖር "ውግዘቱ ባልከፋ። ክርስቲያን ምእመናን ማባረራቸው አግባብ አይደለም የሚለውን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ  የመንፈሳዊ አባት በጭለማ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ ተጠርተው በፖሊስ ታጅበው መባረራቸው ኦርቶዶክሳዊ አለመሆኑን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ አንዱ ካህን ያልወደዱት ካህን መቅደስ አይገባም ማለት ኦርቶዶክሲያዊ እምነታችንም ሆነ  መንፈሳዊ መመሪያችን አለመሆኑን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ ምእመናን በፖሊስ መባረራቸው አግባብ አለመሆኑን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ ሰባኪዎች የሚያስተምሩት ወንጌል እኛ ላይ ያነጣጠረ  በመሆኑ ያስተማረው ካህን ከመቅደስ እንዳይደርስ ወስነናል  የሚለውን የቦርዱን ውሳኔ ትክክል አለመሆን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ አባላትን እንዴት ማባረር እንችላለን ብሎ ነገር መሸረብ ክርስቲያናዊ አለመሆኑን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ውግዘቱ ባልከፋ  ቦርዱ የሃይማኖት የበላይ ሊሆን እንደማይችል ቢነገርና ጳጳስን ሊተኩ መነሳታቸው አግባብ አለመሆኑን ቢያጠቃልል ኖሮ።

ስለሆነም አህያውን ፈርተው ዳውላውን  እንዳይሆን እያሰብን መረዋ ግን በስድቡ ውስጥ የሌለ  በመሆኑ የተባለው እንደማይመለከተን ምስክሮቻችን እናንተ በመሆናችሁ መደጋገም አንፈልግም።

ለማንኛውም ሰላም ለመፍጠር መደማመጥ መወያየት እንጂ እልህና የኔ ብቻ እንደማያዋጣ የተገነዘብን ይመስለናል።  በሌላ  መልኩ በማስፈራራት ፍቅር፡ በውሸት ሰላም፡ በማባረር ሕብረት፡ በንቀት ክብረት፡ በስድብ አንገት ማስደፋት ይቻላል ብሎ  ማሰብ የዋህነት መሆኑን መቀበል አዋቂነት ነው እንላለን።

መረዋ እንደትላንቱ እውነተኛውን መንገድ እየመረጠ መጔዙን ይቀጥላል።


የሰላም ሳምንት ያድርግልን