Thursday, November 25, 2010

መረዋ ዛሬ ዓመት ሞላው ቁጥር ፵፱

እነሆ መረዋ ከተመሰረት ዛሬ አንድ ዓመት ሞላው። ባለፈው እንዳልነው አሁንም እንኳን አደረሳችሁ እንላለን። ዓመት ማለፉን ከማስላት በስተቀር የተቀየረ ነገር ግን የለም። የሚገርመው የዛሬ ዓመት መረዋ የጻፈውን ስናነብ ዛሬ የተጻፈ መሰለን። አንባብያን እንድታነቡና እንድትፈርዱ የዛሬ ዓመቱን እትምት እንዳለ ከዚህ ጽሑፍ ግርጌ እናቀርብላችኋለን።
ዛሬ ዓመት ሞላን ብለን ሻማ አናበራም ሰላሙን ስጠን ብለን እንጂ።
የማንወዳቸውን አጥፋልን ብለን አንጠይቀውም ልቦናቸውን ክፈትላቸው  ብለን እንጂ። በሞቱ አንደሰትም፥ በታሰሩ ጮቤ አንረግጥም ከክፉ ሁሉ አድነን እንላለን እንጂ።
ትዝ ቢላችሁ የዛሬ ዓመት መረዋ ከሌላ ጎን የሚረጨውን የውሸት ወሬ ለመቋቋም ብሎም እውነተኛውን ዜና ለምእመናን ለማዳረስ ይህንን ጦማር ከፈተ። ጦማሩ በመከፈቱ  የተናደዱ ቢኖሩ እውነት መስማት የሚያስፈራቸው በስድብ የተካኑ ስም በማጥፋት የነገሱ ምእመናንን  በትነው ቤተክርስቲያኑን ሳይሆን ንብረቱን እንካፈላለን ብለው የሚያልሙ ደካሞች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ  ቅዠት ሆኖ ይቀራል እንጂ ሕልም እንኳን እንደማይሆን አሁንም ቃል እንገባላችኋለን። የኛ ጥንካሬና ጉልበት የሚካኤልና የምእመናን ድጋፍ ነውና። በድጋፋችሁ እዚህ ደርሰናል የምስራቹን አብረን እንደምንሰማ አሁንም አንጠራጠርም።

ለእምነት መሰደብ አይደለም መገደልም ያለ ነው። በዛኛው ብሎግ በወሲብ የተሰደባችሁ፤ ትዳራችሁ እንዲፈርስ የውሸት ወሬ የተነዛባችሁ። ሰላም ይፈጠር በማለታችሁ ከካህን ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት አላችሁ ተብሎ የተጻፈባችሁ። የከሰሱት እውነት አላችው በማለታችሁ የውሸት አሉባልታ የተነዛባችሁ። ቤታችሁ በድንጋይ የተደበደበ። መኪናችሁ የተሰበረ። ማስጠንቀቂያ በግለሰብ የደረሳችሁ። አገርቤት ያለው መንግሥት ሰላዬች ተብላችሁ የተወነጀላችሁ። የመንግሥት ግብር አልከፈላችሁም ተብላችሁ ማስፈራሪያ የደረሳችሁ። ሁሉ ዛሬ ከተሳዳቢዮቹ በላይ መሆናችሁን እንዳትጠራጠሩ። እዚህ አካባቢ የግለሰብ ሕይወት  ቢጠፋ ተጠያቂዎቹ ደግሞ የስድቡን ጦማር የሚያቀነባብሩት ግለሰቦች ለመሆናቸው ካሁኑ ማሳሰብ እንወዳለን። እኛ ግን እየተሰደብንም ማስፈራሪያ  እየደረሰንም ለመብታችን መታገላችንን  አናቆምም። እውነትን በመያዛችን ትላንት ከማዶ  የነበሩ ዛሬ ከብዙሃኑ እየተቀላቀሉ ነውና። በድጋሜ እንኳን አደረሳችሁ!!!!! 
DECEMBER 9, 2010
ባለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሁላችሁም እንድትገኙ  ጥሪያችንን እያቀረብን።
የዛሬ  ዓመት የተጻፈውን መረዋ እንደገና እንድታነቡት እንጋብዛችሁ።

ይቅርታ የክርስቲያን ባህርይ ነው ቁጥር ፩


                                                                                                 Thursday, November 26, 2009

በዛሬው (THANKSGIVING) የፈጠረን አምላካችንን ተሰባስበን በምናመሰግንበት እለት፡የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ፡ የፍቅር ዝናብ እንዲያካፋ፡ የይቅርታ ጥላ እን ዲያጠላብን መፀለይ የተገባ ከመሆንም አልፎ ክርስቲያናዊ ግዳጅችን መሆኑን መቀበል የግድ ይሏል። በቂም በቀል የሚመራ ክርስቲያን ከመሃከላችን ካየን በጸሎት በምክር መርዳትም እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ግዳጃችን መሆን ይኖርበታል። እንዳንስማማ የተስማማን ይመስል በሁሉ ነገር ተጣልተን እስከመቼ እንዘልቃለን? ብለንም እራሳችንን ብንጠይቅ ምን አልባት ካንቀላፋንበት እንባንን ይሆናል። ውድ የቤተክርስቲያን አባላት በዛሬው የፈረንጆቹ በዓል እንድታደርጉ የምነጠይቃችሁ ነገር ቢኖር ሁላችሁም በቤተክርስቲያናችን የተከሰተውን መለያየትና መናቆር እንዲቆም በጸሎት እንድታስቡት ብቻ ነው። ከደጋፊና ከተቃዋሚ እየተባለ የሚጻፈውን የስድብ ውርጅብኝ፡ የቃላት ሽኩቻ አንብበናል። "መሳሪያ የታጠቀ ሁሉ ነፃ አውጭ ነው" ማለት ስህተት እንደሆነ ሁሉ፡ የተነገረው በሙሉ እውነት ነው ብሎ መቀበል የዋህነት ይሆናል። እያንዳንዳችን ምን እያደረግን ነው? ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ ምንአልባትም የችግሩ መልስ በቀላሉ የሚገኝ ይመስለናል። "ሽማግሌዎች ቢኖሩ ኖሮ እዚህ አንደርስም ነበር" ለሚሉት እውነት አላችሁ እያልን፡ አባባላቸውን ስንጋራ፡ "አሁን ለምን ሽማግሌዎች ሊያስታርቁ ተነሱ" ብሎ መተቸትና መሰናክል ለመፍጠር መነሳት ግን ሌላ ስህተት ነው ብለን ደግሞ እናምናለን። በፍርድ ቤት ትእዛዝ ችግራችን ይፈታል ብሎ የሚያምን ካለ የዋህ ነው ብሎ መናገር ማስፈራት የለበትም። ፍርድ ቤት በሚሰጠው ብያኔ ፍቅር አይመጣም አንድነት አይፈጠርም። ይህ ሊሆን የሚችለው የተለያየ ሃሳብ ይዞ የሚከራከረው ቡድን ተቀምጦ መነጋገር ሲችል ብቻ ነው። ክስ የመሰረቱትን ለምን ክስ መሰረቱ ብሎ መኮነን ደግሞ ሲደረግ የነበረውን መካድ ይህንን ባያደርጉ ኖሮ ዛሬ እንደዚህ ለመናገር የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንሆን እንደነበር አለመቀበል ይሆናል። የቤተክርስቲያን ገንዘብ ስላለ ከሳሾቹን ገንዘባቸውን አስጨርሰን እንዲሸነፉ እናደርጋለን የሚሉት የቤተክርስቲያኑ ተመራጮች ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር የተመኩበት ገንዘብ ከምእመናን የተዋጣ መሆኑን ነው። ምእመኑ ካልደገፈ የገንዘቡ ቌት እንደሚሟጠጥ ከሳሾችንም ከአሁኑ በበለጠ እየደጎሙ እየደገፉ እንዲቀጥሉ ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ማሰብም የተገባ ነው። ከሳሶችም ሆኑ የቤተክርስቲያኑ ተመራጮች ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር ያለ ምእመን ድጋፍ የትም ሊሄዱ እንደማይሄችሉ ነው። በተናጠል ቤተክርስቲያን አይገነባምና። ተሰዳደብን፡ ተካሰስን፡ ተወነጃጅለን አሁን ደግሞ ወደ አንድነት ለመምጣት ምን አስተዋጽኦ እናድርግ ብሎ መነሳት ክርስቲያናዊ ነውና ሁላችንም በተናጠል እራሳችንን ጠይቀን ለሰላም እንነሳ። እከሌን ብናገረው እንጣላለን ከመሃበር ያባርሩኛል ያልሆንኩትን ስም ይሰጡኛል፡ ዝምድናችን ይፈርሳል ጔደኝነታችን ይቀራል በቡድን ያጠቁኛል ብሎ በመፍራት ለእውነትና ለመብት አለመነሳት ደግሞ በሕሊና ማስጠየቅ ይኖርበታል እንላለን። ስለሆነም ለሁላችሁም ዛሬ ጥያቄዎች ማቅረብ እንወዳለን። በግል ምን እያደረግን ነው? ሰለኛ ሌሎች እስከመቼ ይወስናሉ? መብትና እምነት፡ ሕግና አምልኮን መለየት የምንችለው መቼ ነው? ከራሳችን ጋር እንዴት እንታረቃለን? መንፈሳዊ አባት እየዘለፍን እንዴት መንፈሳዊ ነን ማለት እንችላለን? መንፈሳዊ አባቶቸስ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ሲያልፉ እንዴት እናስቆማቸዋለን? የነዚህን ጥያቄዎች ከመለስን የችግሩን ብዙውን ጎን ቀረፍነው ማለት ነው ብለን እንስማማ።
አሁን ምንእላለሁ ከምንስ ላይ ቆሜ፡
የገደለው ባሌ የሞተው ወንድሜ።ይሉ አልነበር።






Sunday, November 14, 2010

ጥርስ የሌለው ውሻ ጉልበቱ ከጩኸቱ ላይ ነው ቁጥር ፵፰

እንዴት ከረማችሁ

አዲስ የተከሰተ ነገር ባለመኖሩ ጊዜአችሁን ልናጠፋባችሁ አልፈለግንም፡፡ ለሥራ መሯሯጥ ደግሞ በዚህ አገር የግድ ነውና እንደምንራወጥ መሯሯጣችሁ ይገባናል ማለታችን ነው። ቢሉም ያራሩጣል ይሉ የለ። ሁሉም ነገር ትግል ሆነ። "ለምታበራቱን ድጋፋችሁ ላልተለየው ሁሉ ምስጋናችንን አድርሱልን። በረዳችሁን ቁጥር ሃላፊነት እየጣላችሁብን የጀመርነውን እንድንጨርስ እያደረጋችሁ ግፊት እየጣላችሁብን ነው ብላችሁ ንገሩልን"  ያሉት ለቤተክርስቲያናችን የመብት ትግል ግንባር ቀደምት ሚና  የሚጫወቱት ናቸው። እውነትም እኛም  ስናስተውለው ለጠበቃ የሚወጣውን ወጭ እናንተ  ምእመናን ባትጋሩት ኖሮ ለጥቂቶች ይከብድ ነበር ብለን አሰብን። የቦርዱ አባላት አሁንስ በቃ  እስክትሏቸው ድረስ እንደልብ የሚጽፉት ለጊዜው የማያልቅ የሚመስል ገደብ የሌለበት የባንክ ደብተር አላቸው። ገንዘብ ያላግባብ ማባከን አያስጠይቅም እንዴ? ብለው ሲጠይቁ ለነበሩ አባት በቦታው መልስ መመለስ አልቻልንም ነበር። አሁን እንመልስላቸው። አዎ  ያስጠይቃል ጠያቂው ግን  ምእመን መሆን አለበት። እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያለውን ጉዳይ ብትመለከቱት በዋናው ጉዳዩ ላይ ክርክር ሳይጀመር በስነስርዓት ነጥብ (PROCEDURAL ISSUE) ላይ መሆኑን እንደኛ ታዝባችኋልን? እኛ ካስተዋልነው ውሎ  አደረ።

ፖሊስ አታስመጡ፤ ምእመንን  ማባረር አትችሉም፤  ዶሴዎችንና ማናቸውንም የቤተክርስቲያኑን መረጃዎች አታጥፉ ተብለው ታዘዙ  ይግባኝ አሉ። ይህ ጉዳይ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ  እየጠበቀ  ያለ ነው።

ከከሳሾች ጠበቃ የቀረቡትን መጠይቆችን አንመልስም ብለው የቦርድ አባላት አሻፈረኝ አሉ። ይባስ ብለው የተከሳሾቹ  ጠበቃ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ አስቁሙልን ብለው ተማጸኑ።  ባለፈው እንደነገርናችሁ የሁለቱንም ጠበቆች ክርክር ሰምተው የተከበሩት ዳኛ ጥያቄዎችን የመመለስ ግዳጅ አለባችሁ ብለው ወሰኑባቸው። ይግባኝ ለማለትም 3 ቀን እንዳላቸው ነገሯቸው። አሁን የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳን ይህንንም የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም የተከሳሾቹ ጠበቆች ይግባኝ ብለው ጉዳዩ  ለ DECEMBER 20  ተቀጥሮ ሁኔታውን የተከበሩት ዳኛ ስሚዝ በተባለው ቀን እንደሚያዩት ለመረዳት ችለናል።

በተጨማሪም በ DECEMBER 9 አሁንም የቦርዱ ጠበቆች ባጠቃላይ ክሱ ይሰረዝልን በማለት ለተከበሩ ዳኛ ስሚዝ የመከራከሪያ ዶሴ ( SUMMERY JUDGMENT) ማስገባታቸውና ይህም ለ DECEMBER 9, 2010 መቀጠሩን እንደነገርናችሁ የሚታወሰ ነው።

ባጠቃላይ ቀደም ሲል ሕጉን መቀየር ትችላላችሁ ተብሎ ከተወሰነላቸውና ይህም በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ካለው ጉዳይ ሌላ ይህንን አደረግን  የሚሉት የላቸውም። ይህንን ለማድረግ የከሰከሱት ገንዘብ ደግሞ ወደ $100,000 ደርሷል ወይንም አልፏል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህ ታዲያ ቤተክርስቲያኗ ከምእመናን ያጣችውን የገንዘብ ገቢ ሳያጠቃልል ነው። ይህንን ጉድ አናይም ብለው የተበተኑትን ምእመናን ደግሞ ወደ ገንዘብ መቀየር ስለማይቻል እንጂ ጉዳቱን የበለጠ የሚያስከፋ ያደርገዋል። በእኛ እምነት ከገንዘቡ የበለጠ የምእመናን ሽሽት ጎጅ ነው እንላለን። ታዲያ ሁኔታው የመብት ነውና የአማንያን መብት ሳናከበር ወደ ነበረበት መመለስ ይቻላል ብለው የሚሉትን ግለሰቦች መረዋ ሊጠይቅ የሚፈልገው ነገር ቢኖር የሚከተሉትን ነው፤

ማን ነው ሁለተኛ ደረጃ  ዜጋ ሆኖ የሚኖር?
ተመራጮች ነን ባዬች ፈላጭ ቆራጭ ያደረጋቸው ማን ነው?
የምእመን የበላይነት እንዴት ይከበራል?
ወጣቶችን አይደለም ሽማግሌን ከሚንቁ የቦርድ አባላት ጋር እንዴት መነጋገር ይቻላል?
አምባ ገነን ሆነው ቤተክርስቲያኑን  እየበተኑት ያሉትን መፍራት የሚቆመው መቼ ነው?
የሚቃወማቸውን ለማጥፋት ታጥቀው የተነሱ የቦርድ አባላት ሲያሰኛቸው ካህኑን፤ በረድ ሲሉ ጽዋ የሚጠጣውን፤ በፈቃደኝነት ሱቅ ውስጥ የሚያገለግሉትን፤ በፈቃደኝነት ወጣቶች የሚያስተምሩትን፤ በደጀሰላም የሚተባበሩትን ተባራችኋል እያሉ የሚበትኑን እስከመቼ  ነው?
ቤተክርስቲያኑን በጥቂት ተቆጣጥረው የሚበትኑበትን ቀን የሚጠብቁ መሪዎችን ከውጭ ስናወራ አይሰሙም እያልን እየተናገርን ስናያቸው ግን የምንሸማቀቀውና አንገት የምንደፋው እስከ መቼ  ነው?
የነሱ ጉልበት ሚካኤል ሳይሆን በድብቅ የሚጻፈው ጦማር (BLOGS) ሆኖ የሚቆየው እስከመቼ  ይሆን?
ፍቅር በመከባበር እንጂ በፍርሃትና በስድብ ይመጣልን?
በሕግ አምላክ ብሎ ወደ ሕግ መሄድ ነው የሚያስነውረው ወይንስ በተፈጠረ ጦማር መሳደብ?
የሚሰደቡት ናቸው ጥፋተኞች ተሳዳቢዎቹ? መመለስ ያለብን  እንደ ግለሰብ እያንዳንዳችን መሆን አለብን።

ለማንኛውም የሚነዛውን የውዥንብር ወሬ  ሳይሆን እውነቱን በራስ ተመራምሮ  ማግኘት ክርስቲያናዊ ግዴታም  ነው እንላለን።

ባለፈው እንደነገርናችሁ "እኛ እንዳየነው ጥፋቱ ሙሉ ለሙሉ የመልከኛው  ነው ካሳውን ግን ገበሬው ይካስ" አይነት ፍርድ የሚቀረው መቼ ነው?  አንድ እናት ባንድ ግብዣ ላይ "ልጆቼ ካወቃችኋቸው እነዚህን ከሳሾች ክሱን አቁሙ በሏቸው" ብለው ሲናገሩ አንዱ አዳማጭ እማማ የቦርዱን ተመራጮች ለምን ተው በሏቸው አላሉም?  ብሎ ለጠየቃቸው ሲመልሱ  "እያወቃችሁ እነሱ እንኴን ሰው ሚካኤልንም አያዳምጡም" አሉ ተብሎ  ነበር። ይህንን ያመጣነው ለቀልድ  ሳይሆን ያለውን ስሜት ለማሳየት ነው።

ለመብት የተነሱት ከሳሾች በእምነት አልከሰሱም በደረሰባቸው የመብት እረገጣ እንጂ። ክስ የመሰረቱት እናት የከሰሱት እንደሰማነው በሃይማኖት ጉዳይ አይደለም በደረሰባቸው በደል እንጂ። ታዲያ ይህንን ያደረገውን ዝም ብለን እናያለን የሚሉ ሁሉ ቤተክርስቲያኑን እያፈረሱ መሆኑንን  መረዳት ይኖርባቸዋል። 

ሁላችሁም ከቻላችሁ በሚመጣው DECEMBER  9 ከፍርድ ቤት በመገኘት የፍርድ ቤቱን ጉዳይ እራሳችሁ እንድትከታተሉ ጥሪ እናቀርባለን። ዜና ስትፈልጉ  ወደ መረዋ  ስድብ ለመስማት ደግሞ ወደሌላው ጦማር ጎራ  በሉ።

የሳምንት ሰው ይበለን።


Monday, November 8, 2010

በእንጎቻ ያመሸ እረኛ እራቱ እንጀራ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ፵፯

እንደምን ከረማችሁ ምእመናን

ዛሬ የምንጽፈው ባለፈው ቃል እንደገባንላችሁ የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ ለናንተ የሰማነውን ለማካፈል ነው። እንደ ሌሎቹ "ምሑራዊ" ትንተና ልንሰጣችሁ አይደለም። አንባቢዎቻችን ክፉና  ደጉን ማበጠር  እንደምትችሉ፤ እውነትና ውሸትን እንደምትለዩ፤ የነገሮችን አካሄድ ጠንቅቃችሁ እንደምትገነዘቡ እናውቃለንና። ዛሬ በዛኛው ጎራ እንዳነበባችሁት ሥም እየጠራን ልንሰድባችሁ አይደለም። ይህ የነሱ እንጂ የኛ ባሕርይ አይደለምና። ለዚህ አይነቱ ስድብ አስተዳደጋችንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ስለሚገታን። ሌላውን ስንሳደብና ስናንቋሽሽ የሚታዩን ያሳደጉን ቤተሰቦቻችን በመሆኑ፡ አሳዳጊ የበደለው ተሰኝተን መሰደብ አንወድምና። ሃላፊነታችን የነበረውን እንዳለ  ማቅረብ ብቻ  ይሆናል። ፖለቲካ ከቤተክርስቲያናችን መውጣት አለበት ስንል ካየነውና  ከታዘብነው ብሎም ከሚጽፉት በመነሳት ነው። ከዋሸን እነሱ ጋ  ጎራ  በማለት በማንበብ ማመዛዘን ይቻላል። እኛ ደግሞ  ቃላችንን  ከወለድነው ልጅ የበለጠ እናከብረዋለን። እኛ አፕልና  ብርቱካን እንደማናደባልቅ ደግሞ ምስክሮቻችን እናንተ  ናችሁ። ስለብርቱካን  እያወራን ስለ አፕል መዘባረቅ አለመደብንም። ይህንን የሚያደርግ በግንዛቤ ሰንካላ ወይንም ድኩም የሆነ  ብቻ ነው ብለን ስለምናምን።

ለመግቢያ  ይክል ይህንን ካልን በኌላ  በዛሬው እለት ስለዋለው ችሎት እናውሳችሁ።

በቦርዱ ጠበቆች ማመልከቻ  መሰረት ለዛሬ ተቀጥሮ  የነበረውን  ጉዳይ የተመለከቱት ዳኛ የተከበሩ ሸርሊን ማክፈርላንድ ነበሩ። ዳኛዋ የካውንቲው እረዳት ዳኛ (ASSOCIAT JUDGE) ናቸው። ጉዳዩን ስላላነበብኩት አስረዱኝ ያሉት ዳኛ ከቦርዱ ጠበቆች የቀረበ ገለጻና የከሳሾችን ጠበቃ መልስ አዳምጠዋል። በመሰረቱ ክሱ የከሳሽ ጠበቃ ይሰጡኝ ብሎ  የጠየቀውን ከ50 በላይ የሆኑ ጥያቄዎች አንሰጥም በማለት የቀረበ  ክርክር ነበር። በጥቅሉ የቦርዱ ጠበቆች ክርክር የነበረው ከሳሾች  የሌላ  እምነት ተከታዬች በመሆናቸው፡ ከዚህ በፊት በሌላ  ክስ የከሰሱ በመሆኑ፡ አባላት ባለመሆናቸው፡ ይህ የእምነት ጉዳይ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የማየት ስልጣን ስሌለለው ጥያቄውን ያስቁምልን የሚል ነበር።  የከሳሾች ጠበቃ በበኩሉ የጠየቃቸው ጥያቄዎች አንድም የእምነት ነገርን እንዳልያዘ በመጥቀስ ለናሙና ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

1 የአባላት ዝርዝር 
2 የቦርድ አመራረጥን የሚያሳይ ሰነድ
3 የገንዘብ ወጪና  ገቢ ሰነድ
4 ቃለጉባኤ   
5 የደብዳቤ ልውውጦች ወዘተረፈ መሆናቸውን አስረድቷል።

የተከበሩ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ሁኔታውን  ካዳመጡ በኋላ  የቦርዱ ጠበቆች የተጠየቁትን  ሰነድ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲሰጡ ወስነዋል። ተከሳሾቹ በውሳኒያቸው ካልተስማሙ ለዋናው ዳኛ  3 ቀን ባልበለጠ ጊዜ  ውስጥ ይግባኝ ብለው በተከበሩ ዳኛ ስሚዝ ፊት በመቅረብ መከራከር እንደሚችሉ ነግረዋቸዋል። የተከሳሾች ጠበቃ በውሳኔው ላይ ማሻሻያ  ለማድረግ የጠየቁትንም ሆነ ዶሴዎቹን ከእኔ  ቢሮ  መጥተው እንዲያዩ ይታዘዝልኝ ብለው ያሳሰቡትን ዳኛዋ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ይህ የዛሬው የከሳሾች ድል ጉዳዩ የሃይማኖት ሳይሆን የመብት ጉዳይ ለመሆኑ ሌላ  ማረጋገጫ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሚመጣው ወር ማለትም በ12-09-2010 የቦርዱ ጠበቆች ክሱ ይሰረዝልን በማለት ሌላ የፍርድ ሃሳብ ያስገቡ መሆናቸውን እየነገርናችሁ በዚያም ቀን በተከበሩት ዳኛ ስሚዝ ችሎት የሚደረገውን ክርክር ውሳኔ እንደምናቀርብላችሁ ካሁኑ ቃል እንገባለን።

እውነት ሁልግዜም እውነት ነው።

እውነት እንደሚያሸንፍ የሚጠራጠር ደግሞ እምነተቢስ ነው።