Thursday, May 19, 2011

አትደግ ያለው ልጅ በእሳት ይጫወታል።

ወንድሞችና እህቶች እንደምን ከረማችሁ። ካነበባችሁን ውሎ አደረ። በየሳምንቱ በሬ  ወለደ ብለን መጻፍ አልለመደብንምና ወይንም እኛ ስንፈልግ እንጂ ከሌሎች ፉክክር በመግባት እንካ ስላንቲያ ማለት ባለመፍቀዳችን   ለናንተ የሚሆን ዜና አግኝተን እስክናዘጋጅ ድረስ ቆየን። ከወዲያኛው ጎራ የሴት ዘጋቢ የፍርድ ቤት ውሎ እንድትዘግብ ተለምና ከምትጓዝበት እንደቀረችና ፍርድ ቤት እንደዋለች ስናነብ ከምር ከልባችን ሳቅን። መሳቅ ብቻ አይደለም የቆየ የአለቃ ገብረሃናን ቀልድ አስታወሰን። ቀልዱ እንዲህ ነው። አለቃ ገብረሃና ከሸንጎ ላይ እንዳሉ አሽከራቸውን ይጠሩና በጆሮው ያችን ሴት ሂድና ማታ  አለቃ ይፈልጉሻል በልና  ጠይቀህ መልሱን ሰው እንዳይጠረጥር በወንድ ጾታ ቀይርና ንገረኝ ብለው ይልኩታል ሲመለስ ምን አለ? ብለው አሽከራቸውን ሲጠይቁት አሽከራቸው አልችልም ነፍሰ ጡር ነኝ ብሏል አለ ይባል ነበር። አባባሉ ፍርድ ቤት የነበረ ሴት አለማየታችንን ለመናገር ያክል ነው። የነበሩትን በመመልከት ደግሞ ጸሃፊዎቹን ማወቅ ብዙም የተወሳሰበ አልነበረም።

በእለቱ የከሳሽና  የተከሳሽ ጠበቆች ከዳኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ  መልስ የሰጡ ሲሆን የከሳሽ ጠበቃ ክርክር አጭርና የማያሻማ ነበር። ይኽውም ክሱ የመብት እንጂ የኃይማኖት እንዳልሆነና ቦርዱ ካለ አባላት ፈቃድ በክርክር መሃከል ሕግ መቀየሩ አግባብ አይደለም የሚል ነው።

የቦርዱ ጠበቆች ክርክሩ የኃይማኖት መሆኑን በተለይም መሃበረ ቅዱሳን የተባለ  እምነት በመላው አሜሪካ እየረበሸን ነው ይህም የዳላስ ክስ የዛ ተቀጥላ ነው የሚል እረጅም ገለጻ ማድረጋቸውን ለመረዳት ችለናል። ጠበቆቹ ደግሞ ነገሮች በተራዘሙ ቁጥር ተጠቃሚዎች ናቸውና ለምን የቃል ክርክሩን መረጡ ማለት የዋህነት ነው። የከሳሾች ጠበቃ የቃል ክርክሩን ጊዜ ለመቆጠብና የጠበቃን ወጪ ለመቀነስ እንደማይፈልግ በይግባኝ ወረቀቱ ላይ መጥቀሱ ይታወሳል። የቦርዱ ጠበቆች ግን ገቢያችንን አትቀንስብንም እኛ እንፈልጋለን ብለው ቀጠሮው ተያዘ ክርክሩም ተደረገ። አሁን ዳኞቹ ምንም ይፍረዱ ምን ክርክሩ ይቀጥላል። ምን አልባትም የፌድራል ፍርድ ቤት ሊያየው የሚገባ  አቤቱታም እንደሚኖር ከምንጫችን የደረሰን ዜና ይጠቁማል። 

የሰው ስም ሲያጠፉ ግለሰብን ሲዘልፉ ቤተስብን ሲወነጅሉ የነበሩት የማዶ ጸሃፊዎች መከሰሳቸውን የሰማነው ከነሱ ብሎግ ላይ አልነበረም። በስድባቸው እንደሚቀጥሉና እንደማይፈሩ ያነበብነው ግን በብሎጋቸው ላይ ነው። እንደማይፈሩ እኛም እናውቃለን የሚፈራ ሰው ክፉና ደጉን የሚለይ ብሎም የሚመጣበትን ነገር አመዛዝኖ  የሚለይ ብቻ ነውና።  በፈንጂ የሚጫወት የማያውቅ ሰው ብቻ ነው ይባል የለ። 

ከሳምንት በፊት ቀደም ሲል በድንገት ከመከላችን በሞት የተለየች እህታችንን አርባ ለመደገስ የቤተክርስቲያኑን አዳራሽ $500 ከፍለው ሃዘንተኞቻቸውን የጋበዙት ቤተሰቦች በእለቱ ሊያሳዩት የነበረውን የሟችቷን የሕይወት ታሪክ ያዘለ የ 7 ደቂቃ ፊልም ለማሳየት የማሳያ ፕሮጀክተሩን በመልከላቸው ሲያዝኑ በአካል ታዝበናል። ቦርዱ አይቻልም ብሎ ሲነግራቸው ያዳመጡት ከሐዘንተኞቹ አንዱ ግለሰብ እኛ እኮ ቤተክርስቲያን አጥተን አይደለም እዚህ የመጣነው አልገባቸውም አሁን ግን እስከመጨረሻው አጡን ሲሉ አዳምጠናል። በመንፈሳዊ ጉዳይ ዘር ቦታ ሲኖረው ከማየት ይሰውረን ወንድሞችና እህቶች።  ይህንን የወሰኑት የቦርድ  አባላት የገደለ ጥይት ድምጹ ከሩቅ አይሰማም ብለው ከሆነ ተሳስተዋል። የግፍ  እንባ መጥፎ  መሆኑን ከመጽሐፍ እንረዳለንና። እዚህ ደግሞ ዜና ማሰራጫው ዘዴ ብዙ ነው። ካልሰማው ይልቅ የሰማው ብዙ ነው። ሰምቶ ምን አደረገ? ማለት ግን ትክክለኛ ጥያቄ  ነው።
ሌላው ዜና የቤተክርስቲያኑ የቦርድ አባላት ባለፈው ቅዳሜ አጠቃላይ የአባላት ስብሰባ ጠርተው እንደ ነበረ የሰማችሁት ጉዳይ ነው። በእለቱ ዙፋነ ወንበር የጨበጡ የመሰላቸው አዲስ ተመራጭ አቶ ሰሎሞን ከጎናቸው ከነበሩት ከአቶ ከተማ ጋር በመሆን።

አቶ  ሃይሉ እጅጉን   
ወይዘሮ ገነት ከበደን
ዲያቆን አርአያ  ኃይለመስቀልን ከስብሰባ  እንዳይገቡ መከልከላቸውን ስንሰማ  አዘንን። ለምን ቢሉ ቤተክርስቲያናችን መልሶ ከመሰባሰብ ወደ መፈራረስ መሄዱ ስለታየን ነው።አቶ ሰሎሞን አባራሪ አቶ ሃይሉ እጅጉ ተባራሪ ------- ወገኖቼ የሆነ ነገር የጎደለ  አይመስላችሁም።
አቶ ከተማ  ቤተኛ ዲያቆን አርአያ ባይተዋር -------- እግዚኦ ማለት አሁን መሰለን።
ወይዘሮ ገነት ተባራሪ ቀሪው አባራሪና አጋፋሪ------- ነገ  በኔ ማለት ይገባል።
የንብረት ጥያቄ  ቢመጣ እኮ ድርሻህን አሳየኝ ማለት እንደሚጀመር አንርሳ። የአቶ ኃይሉ እጅጉ በሺህ የሚቆጠር ችሮታ ቤተክርስቲያኑን እንደ ገነባው የምንጣላ  አይመስለንም። የአቶ  ከተማና የአቶ  ሰሎሞን ፉከራ  ግን  ቤተክርስቲያኑን  እያፈረሰው እንደሆነ አከራከሪያ ሆኗል። 
የዲያቆን አርአያ ለዚህ ቤተክርስቲያን ያበረከቱት አስተዋጽ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። የአሁኑ የቦርድ አባላት ውሳኔ  ግን የቤተክርስቲያኑን ውድቀት እንደሚያጣድፈው እድሜ  ሰጥቶን የምንመለከተው ይሆናል።
የወይዘሮ ገነት ከበደ ለዚህ ቤተክርስቲያን ያደረጉትን እርዳታ ለማወቅ ምስክር ፍለጋ መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለንም ። ምስክር የሚያስፈልገውስ የዛሬዎቹ ፍርድ ሰጪዎች አስተዋጽኦ ጉዳይ ነው። 

ግለሰቦቹ መዋጮ ሲከፍሉ እንቢ አልተባሉም። እምቢ የተባሉት ገብተው የሚያቀርቡት ጥያቄ ስላስፈራ ብቻ ነው።  የሕግ ሰዎች ይህንን
taxtion without reperesentation  ይሉታል።

ዛሬ የተባረሩትን አይተናል ነገ ደግሞ ሽማግሌ ነን ብለው የተቀመጡት አዛውንቶች ተራቸው ይደርሳል። ያኔ እነሱ ዛሬ ተነሰተው እንዳልቆሙ ሁሉ ለነሱም የሚቆም ይጠፋል። ትላንት ሕጉን ያጸደቁ ዛሬ ያሳለፉት ሕግ እነሱን እየጎዳቸው እያስተዋልን ነውና።

የድሮ ታሪክ ታስታውሳላችሁ ሁለት ሴቶች አንድ ሕጻን የእኔ ነው በማለት ተካሰው ቀርበው ዳኛው የማንኛችሁ እንደሆነ ማወቅ ስለማይቻል ሕጻኑ በቢለዋ ለሁለት ተሰንጥቆ ተካፈሉት ብለው ሲፈርዱ እናት ያልሆነችው በፍርዱ ስትስማማ እውነተኛዋ  እናት ግን እኔ ይቅርብኝ ሕጻኑን እሷ ትውሰደውና ታሳድገው  ያለችው። እኛም ያለውን ሁኔታ ስናስተውለው ከሳሾች ቤተክርስቲያኑን ለማዳን ቦርድ ነን ባዮች ደግሞ ፍርስርሱን ለማውጣት እየተጣደፉ ያለ ይመስለናል።

የቅዳሜው ስብሰባ  ምልዓተ ጉባኤው  አልሞላም ተብሎ  መበተኑን ስንታዘብ ሊቀመንበሩ አቶ  ሙሉጌታ  እንዳሉት ሁለተኛ ስብሰባ  በ 4  ይጠራና አሁንም በቂ ሰው ካልተገኘ በሕጉ መሰረት የቦርዱ ውሳኔ  ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ብለዋል ይህ ደግሞ መጀመሪያ ሕጉን ቀየርን ሲሉ የተነሳውን  ተቃውሞ ያጠናክረዋል። ቦርዱ መተዳደሪያ ደንብ እንደ ፈለገው ከቀየረ፡ኮረም አልሞላም ብሎ  የ$10000 የእደሳ ባጀት ካጸደቀ፣ የማይፈልጋቸውን ማባረር ከቻለ አባል የሚኮነው ለምን ይሆን?

አንድ የገረመን ነገር ቢኖር የተባረሩትን ግለሰቦችና ያባራሪዎቹን የክርስትና እምነት ጥንካሬ ስናሰላስል የተሰማን ሃዘን ነው። እስቲ እያንዳንዳችሁ በግላችሁ ታዘቡ ፍርዱን እናንተው ለናንተው ስጡ።
 
ማን ነበር ተከራይና አከራይ እኩል ለቤቱ ጣራ አይጨነቁም ያለው? እየቆየ አባባሉ እየታወሰን  ተናጋሪው እየጠፋን ነው።
 
ይልቅስ አንድ የታወቀ ባንክ ዘራፊ ተይዞ ለምን ባንክ ዘረፍክ?ተብሎ ሲጠየቅ የመለሰውን እናስታውሳችሁና  እንሰናበታችሁ "ገንዘቡ ያለው እዛ ስለሆነ  ነው" ብሎ  ነበር። ቦርዱ የላከው 2009 የሂሳብ ሰንጠረዥ $ 75000 ለጠበቃ እንደዋጣ ያሳያል 2010 ስንት እንደሆነ አልነገሩንም ምናልባትም አይነግሩንም ይህ ገንዘብ የወጣው  እነ አቶ ሃይሉ እጅጉን ለማባረር፣ እናቶ ከተማን ለመሾም መሆኑ ነው። የፖለቲካ  ፍልሚያ  ነው ስንል ያልሰሙን ሰዎች ዛሬ እውነት አላችሁ ይሉናል ብለን እናምናለን።
 
በጉልበትና በፍርድ ቤት ፍቅር አይመሰረትም እውነትን የያዘ  ያለጥርጥር ያሸንፋል።

በእሳት የሚጫወት ግን አትደግ የተባለ ብቻ  ነው።