Thursday, July 14, 2011

የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ

ውድ ምእመናን እንደምን ከረማችሁ እኛ በፈጣሪ ቸርነት እስካሁን አለን። ምነው ጠፋችሁ?  ብላችሁ ለጠየቃችሁን መልእክት ለጻፋችሁልን ሁሉ አለን ክብሩ ይስፋ ለመድኅኒዓለም  እንላለን። ከ ሁለት ቀን በፊት የ5ኛው districte ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በወይዘሮ  ጥሩአየርና  በአቶ ዳግም በተመሰረተው የቦርድ አባላት ያለአግባብ የስልጣን አጠቃቀም ክስ ላይ ብይን መስጠቱን ለአንባብያን መናገር እንወዳለን። መረዋ  ብይኑን ሙሉ ለሙሉ አንባብያን እንድታነቡት ሲያቀርብላችሁ እራሳችሁ አንብባችሁ ግንዛቤ  እንድትወስዱ በማሰብ ነው። በተከበሩት ዳኛ ኤልዛቤት ሜየር የተጻፈው የብያኔ  ትችት እንደሚያስረዳው፣ ይግባኝ ባዮቹ ከሳሾች የቤተክርስቲያኑ የቦርድ አባላት አላግባብ ስልጣናቸውን ተጠቅመው መተዳዳሪያ  ደንቡን መቀየራቸው አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው መክሰሳቸውን ተነተርሶ የቀረበ  ክስ መሆኑን አስታውሶ ክሱ በመብት መደፈር አኳያና የቤተ ክርስቲያኑ ንብረት ይገባኛል ጥያቄ አንስቶ ቢሆን ኖሮ ፍርድ ቤቱ መግባትና መወሰን ይችል እንደነበር አውስቶ ነገር ግን በመተዳደሪያ  ደንቡ ላይ ብቻ ያተኮረ ስለሆነ ይህ ደግሞ በውስጥ መፈታት ያለበት እንጂ ፍርድ ቤት በእምነት ውስጥ ጣልቃ  መግባት የለበትም የሚል ብዙ ተመሳሳይ የቆዩ ውሳኔዎችን በመጥቀስ የበታች ፍርድ ቤት ቦርዱ የመተዳደሪያ  ደንቡን መቀየር ይችላል ብሎ  የበየነውን ውሳኔ አጽንቶ ወስኗል። የቤተክርስቲያን ቦርድ አባላት ክሱ በውሸት የተመሰረተ  የቦርድ አባላትን ስራ ለማስፈታት የተመሰረተ  መሆኑን የይግባኝ ፍርድ ቤቱ እንዲወስንላቸውና  ካሳ  እንዲጥልላቸው ያቀረቡትን ሳይቀበለው ቀርቷል።

ለምን ታዲያ የንብረት ይገባኛል ጥያቄውን ከመጀመሪያው አላነሳችሁም ብለን ያነጋገርናቸው ለጉዳዩ  ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች የነገሩን ቢኖር ከመጀመሪያው ይህ  ሃሳብ ቀርቦ የከሳሾች ፍላጎት የቤተክርስቲያኑን አባላት መብት ለማስጠበቅ እንጂ ለመበታተን ስላልነበር ሃሳቡ ተነስቶ  ውድቅ እንደተደረገ ለመገንዘብ ችለናል።

ባሁኑ ሰዓት ግን የንብረት ይገባኛል ክስ ቢመሰረት ማንም ምእመን ሊቀበለው የሚችል ለመሆኑ በሂደት በቤተክርስቲያኑ አባላት ላይ የደረሰው በደልና  አሁን ቤተክርስቲያኑ ያለበትን  በማሰብ መናገር ይቻላል ብለው እንደሚያምኑም ለመረዳት ችለናል።

መረዋ  በእትምት ጅምሩ ላይ የጠቆማቸው ሁሉ ተራ  በተራ ተፈጻሚ ሆነዋል።

ካህናት ተባረዋል
አባላት ተበትነዋል
የስደት ሲኖዶስ ከበራፍ ቆሞ እየጠበቅ ነው
እምነት ሳይሆን ስልጣን፣ አባላት ሳይሆኑ ተመራጮች ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል።
የነበረው ገንዘብ መንምኗል፥
ፖለቲከኞች መሰባሰቢያ  ሲያገኙ አማንያን ከስብሰባ  ታግደዋል
በእምነት ሳይሆን በፖሊስ ለማስፈራራት ተሞክሯል
የቦርድ አባላት ወንጀል በይቅርታ  ሲታለፍ ግለሰቦች ወደፍርድ ቤት በመሄዳቸው ወይም ቦርዱ የሚደረገውን በመቃወማቸው ነፍሰገዳይ ዝሙተኛ ሌባ ሴሰኛ እየተባሉ ከእግዜር በተላከ ቁጣ የሞት ፍርድ ሳይቅር እንደተፈረደ  ሁሉ ተጽፏል።
በአባላት ላይ የክፍያ  ጫና  ተጥሏል።
በዘር እንዲከፋፈል ተደርጓል
የስደት ሲኖዶስ አባላት ሰፈር ተወለጆች እንዲጠናከሩ ሲደረግ ሌሎች በዘራቸው ተወንጅለዋል።
ሲፈርዱ የነበሩ ፈራጆች ዛሬ ተፈርዶባቸዋል።
የቤተክርስቲያን መስራቾች በመመስረታቸው ተነቅፈዋል ወዘተ

ልንል የፈለግነው ያላሰብነው አዲስ ክስተት አልተፈጠረም ለማለት ነው
ባጋጣሚ ትላንትና የደረሰን ዜና  ደግሞ  ወጣት የቤተክርስቲያን ልጆች ጥያቄ  አቀረባችሁ ተብለው መባረራቸውን መስማታችን ነው። ጥያቄው ምን ነበር ስንል
ለምን የረባ  ምሳ አትሰጡንም?
ገንዘብ የለንም ካላችሁ ለምን መብራትና ቴሌቪዥን ግዢ ሄዳችሁ?
በእኛ ስም ከበጎ አድራጊዎች የተገኘ ገንዘብ የት ገባ?
ሳንማር የምንመረቀው እንዴት ነው? የሚሉ እንደ ነበሩ ለመረዳት ችለናል።

እነዚህ  እዚህ የተወለዱና  ያደጉ ሕጻናት ደግሞ ፖለቲካውም አይገባቸው ውሸትም አይዋጥላቸው፥

መረዋ ላለፉት 5 ዓመት ከልባቸው ለእውነት ለፍትህ ለመብት ለታገሉ ምእመናን በሙሉ ያለውን አክብሮትና አድናቆት እየገለጸ ወደፊትም በዚህ መልክ ለሚነሱና ካሁን በኋላ  የንብረት ጥያቄ  ለሚያነሱ  ሁሉ ድጋፉን ለመለገስ ወደ ኋላ  እንደማይል ካሁኑ ቃል ይገባል።

የማንም መብት ሲጣሰ የግል መብት እንደተጣሰ  መቁጠር ትክክለኛ  ውሳኔ  ነው።

የሚሸነፍ ሰው ለመብቱ የማይነሳ ብቻ  ነው።

ሰላምና ፍቅር ለሁላችሁ ይሁን፥

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዳለ  ለማንበብ የምትፈልጉ ከዚህ በታች ያለውን በመጫን ያንብቡ

http://www.5thcoa.courts.state.tx.us/cgi-bin/as_web.exe?c05topin.ask+D+510527