Thursday, July 4, 2013

ቀጥተኛ መስመር አቋራጭ የማይሆንበት ወቅት አለ

ለዚህ ያደረሰን አምላክ ክብር ይግባው እንደምንል ሁሉ መጭውንም ያሳምርልን ብሎ መለመን ደግሞ የተገባ  ነው። እንደኛ ሐጥያት ቢሆን ኖሮ ብዙ ቅጣት፣ ብዙ ግርፋት፣ ይገባን ነበር።  አምላክ ግን የምሕረትና የፍቅር አምላክ በመሆኑ ለሐጥያታችን ይቅርታን ብቻ  ሳይሆን ሕይወቱንም ከፍሎልናልና እነሆኝ አሁንም በምህረቱ እየዳሰሰን ነው። ለዚህም አምላክ ምስጋና ይድረሰው።

የቤተክርስቲያኑን ክስ አስመልክቶ ሰሞኑን የሰማንው ዜና አለ። ታዲያ “የዋሸን እለት ሞትን ማለት ነው፡ እውነቱን ነግረናችሁ እበረንዳ ማደሩን እንመርጣለን” ብለናችሁ ነበርና ዛሬም ቃላችንን አናጥፍም። ከናንተ የተደበቀ ምንም ነገር የለንም እስካሁን የሰነበትነው የናንተን አመኔታ በማካበታችን ለመሆኑ ሌላ ምስክር መጥርት አያስፈልግም። በመሆኑም በርእሱ እንደገለጽነው The shortest distance between two points is a  straight  line የሚለው የሂሳብ ሕግ አንዳንዴ  እንደማይሰራ መቀበል የግድ ይሏል። ስለሆነም ባለፈው ነግረናችሁ የነበረው የቤተክርስቲያን ክስ ክሱን መስርተውት የነበሩት ጠበቃ በነደፉት መልኩ መቀጠል ይሻላል አይሻልም በሚል ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ሁኔታውን እንደገና በመዳሰስ ክሱን የተረከቡት ጠበቆች (THE LAW FIRM)  ባቀረቡት ምክር ብሎም የሽምግልና ሂደትን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ብዙሃኑን ለማሳተፍ በሚልና ሌሎች አማራጮችንም በመዳሰስ የተጀመረ ሂደት ክስ እንዲሰረዝ ለዳኛው ማመልከቻ መግባቱን መስማታችንን ልንነግራችሁ እንወዳለን። ይህንን በአባላት ላይ የደረሰውን የቤተክርስቲያን አባላት ችግር ለመፍታት በዋናነት የመልአኩ ፈቃድ እንዲታከልበት ጸሎታችሁ አይለይ እያልን፣ ስለሁኔታው በሰፊው ዝርዝሩ እንደደረሰን እንደምናሳውቃችሁ ቃል እንገባለን።

በተሳፋሪነት የሚበሩ ሁሉ አብራሪው እኛ ነን ብለው ቢናገሩ ውሸት እንደሚሆን ሁሉ ጫፍ ይዘን ማሳረጊያ ልናወጋችሁ አንፈልግምና እስከዚያው ጆሯችሁን ሰጥታችሁ ጠብቁን።

የሳምንት ሰው ይበለን። 

Saturday, June 1, 2013

በትንሳኤ የሚያምን ሰው በሞት አይደናገጥም

ውድ ምእመናን


እንደኛ ክፋት፣ እንደኛ ተንኮል ቢሆን እስካሁን መሰንበት አልነበረብንም። ምህረት መደሰቻው የሆነ ፈጣሪ አምላክ ሁሉን ቻይ ነውና ከሐጥያታችን እንድንድን ተሰቃይቶ ሞትን እንደሞተልን ሁሉ ዛሬም በምህረቱ እየዳሰሰን ነው። እራስን ማታለል ይቻል ይሆናል ፈጣሪን ለመሸንገል መሞከር ግን ግብዝነት ነው። በሚያምኑ ላይ ማላገጥ ቀላል ነው ብሎ ማመን ይቻል ይሆናል። በእምነት ጸንቶ መቆየት ግን ብርታትን የእግዚአብሔርን እርዳታ ይጠይቃል። በዳላስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመብት ጥያቄ አኳያ በተነሱ አለመግባባቶች፣ አባላትን በማባረር ሰላም አይፈጠርም ብለን ስንናገር ሰንብተናል። የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናትን በመግደል የክርስቶስን ማደግ መግታት እንደማይቻል ሄሮዶቱስ ቢያውቅ ኖሮ ያንን ሁሉ በደል ባልፈጸመ  ነበር። ለእምነት የተሰበሰበ ክርስቲያን በእምነት አይጣላም ከሚል አመለካከት በመነሳት ሁሉን አደላዳይ አምላክ የተለያየነውን እንዲሰበስበን፣ የተቀያየምነውን እንዲያስታርቀን፣ ያራራቀንን እንዲያቀራርበን በማሰብ፣ ለሰደቧችሁ ይቅርታን፣ ላዋረዷችሁ ምሕረትን፣ ላባረሯችሁ እርሕራሔን እንዲሰጣቸው ፀልዩ ብለን መናገራችንን አሁንም አንዘነጋም። ይህንን ስንል ከፍርሃት በመነሳት አልነበረም።  በእምነታችሁ ተደራደሩ፣ ተረገጡ፣ መብታችሁን ተገፈፉ፣ ንብረታችሁን ተነጠቁ፣ ማለታችንም እንዳልነመረ ሁላችሁም የምታውቁት ይመስለናልና መደጋገም አንፈልግም። ቀደም ሲል ተነስተው የነበሩትን የመብት እረገጣን፣ የአባላትን ማባረርና የቦርድ አባላት የሆኑት መሪዎች የግለሰብን የአባልነት ማመልከቻ በፖለቲካ መነጽር እያዩ ደጋፊዎቻቸውን ሕጉን እየለጠጡ፣ ተቃዋሚዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ሕጉን እያጎበጡ ሲያስገቡና ሲያባርሩ ተመስርቶ የነበረውን ክስ ከጅምሩ ደግፈን በጽናት መቆየታችን ያደባባይ ሚስጥር ነው። ይህንን ስናደርግ እንዳወሩት ገንዘብ ተልኮልን፣ ድርጎ ተወስኖልን ሳይሆን ለራሱ መብት ያልቆመ ግለሰብ ለሌላው መብት መቆም አይችልም ከሚል መርህ በመነሳት ነበር። ባደረግነው አሁንም እንኮራለን። እንዳልነው ቤተክርስቲያኑ ያባላት ድሃ እስኪሆን ድረስ መንምኖ የተሰበሰበው ገንዘብ ሲቀንስ እንጂ ሲጨምር አለመታየቱ ለተናገርነው ማረጋገጫ መረጃ  ነው።

ባለፈው በመብት እረገጣ ክስ ላይ ተሰልፈው የነበሩ ግለሰቦች በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ብለው ላስቀየሟቸውና ለተቀየሙ ይቅርታን ባደባባይ ሲያሰሙ ሰምተን ብስለታቸውን አድንቀናል ከጥንካሪያቸው ተምረናል። በተደጋጋሚ እንዳልነው በዝሙት ዓለም እየታዩ ሌሎችን ዝሙተኛ፣ በየመጠጡ ቤት ሰክረው እየተወላገዱ ሌሎችን የአልኮል ሱሰኛ፣ በእጅ አመል እየተዳደሩ ሌላውን ዘራፊ ወንጀለኛ ለሚሉ አጸፋዊ መልስ መስጠት አቅቶ እንዳልነበረ ደግሞ መናገር እነሱ እንደሚሉት "መሃይምነት" እንዳልሆነ ዛሬም ቢነገራቸው አይከፋም። ለሚሳደብ መሳደብ ቀላል ነው መሳደብ ግን አለመብሰል ነው ብለን እናምናለን።

ውድ የቤተክርስቲያን ምእመናን አንድን ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቤት ከማባረር  የከፋ ነገር ያለ አይመስለንም። ይህ ደግሞ በምድር መቅሰፍትን በሰማይ አባታዊ ግሳጼንና  ፍርድን እንደሚያስከተል ዛሬም መናገር እንወዳለን። ሌላው ሲባረር የሚደሰቱ ካሉ ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። የተረከቡ የመሰላቸው ተሳስተዋል። "በእንግድነት የሚያድሩበት ቤት ማረፊያ  እንጂ መኖሪያ  አይሆንምና"

ታዲያ ትላንት የተጀመረው የአባላት ትግል ዛሬም ቀጥሎ በያዝነው ሳምንት በተለየ መንገድ አዲስ ክስ መመስረቱን ሰምተናል። የተጀመረው ክስ እንዳየነው የአስተዳደር ቦርድ አባላት "ቤተክርስቲያናችንን ከገለልተኛ አመለካከታችን አውጥተው፣ ከሃገራችን ሲኖዶስ ነጥለው፣ የፖለቲካ መስመር ለማራመድ ወደ ስደተኛ ሲኖዶስ ንብረታችንን አሳልፈው በመስጠታቸው የተናደዱ ግለሰቦች "ዛሬስ ያበጠው ይፈንዳ ሳንሞት አትቀብሩንም፣ ሳንታወር አትመሩንም፣ ያዋጣንውን ድርሻችንን እንካፈላን ብለው እንደሆነም ለማወቅ ችለናል። ትላንት የንብረት ጥያቄ  ይነሳ  ሲባል የቀድሞ ከሳሾችም ሆኑ መረዋዎች ተቃውመውት ነበር። ለምን ቢሉ የንብረት ክሱ መበታተንን ያመጣል ከሚልና  ችግራችንን በውይይት መፍታት ከተቻለ መሰነጣጠቁን ማቆም ይገባል ከሚል እምነት ነበር። ይህ በእውነትም አድማጭና ሰሚ ቢያገኝ ኖር መልካም አመለካከት ነበር። ሊሆን ግን አልቻለም። ለምን ቢሉ እየታረቁ የሚክዱ እየተወያዩ  የሚያሴሩ የቦርድ አባላት አሻፈረን በማለታቸው ነበር። አሁን ግን መረዋ ከሳሾች የጀመሩት የንብረት ክፍያ ጥያቄ ወቅታዊና አማራጭ የሌለው ነው ብሎ በመቀበል መጨረሻውን ያሳምረው ማለት ይወዳል። 

የአሁኑ ከሳሾች ለምነን ሰሚ አጣን፣ ተናግረን ተዘጋን፣ በእምነታችን ተቀጣን፣ በመውደዳችን ተገፋን፣ለዚህ ቤተክርስቲያን ደግሞ ላደረግነው አስተዋጽኦ መስካሪያችን አንድ አምላክ፣ ብሎም በመቀመጫውና  በግድግዳው ላይ ያለው አሻራችን በእጃችን የሚገኘው የቤተክርስቲያን ደረሰኝ መረጃችን ነው ይላሉ። ውሸትን መድገም ያሽቸግራልና ዛሬ ያስተዳደር ቦርድ መሪዎች ነን ባዮች የሚሉትን ለመስማት እንወዳለን። ምስክር ሆነው በመሃላ ሲመሰክሩ ማየትን እንናፍቃለን። አሁን ደግሞ  ምን ብለው እንደሚያወሩም መስማት እንጓጓለን። 

መረዋ በመደጋገም እንደ ጻፈው አሁንም ሰላም ማምጣት ካስፈለገ  ምርጫው አንድ ነው ብሎ ያምናል። ምላሹ የምእመናንን መብት ማክበር ብቻ  መሆን ይኖርበታል። የንብረት መካፈል ክስ የመሰረቱት ግለሰቦች ገንዘብ ወስደው ለመክበር አስበው እንዳልሆነ እናውቅላቸዋለን።  ትርፍ አትራፊ ካልሆነ ድርጅት የሚገኝ ገንዘብ በሕግ ትርፍ አትራፊ ላልሆነ ተግባር የሚውል ብቻ እንደሚሆን እናውቃለንና። ለስም እንዳልተነሱ እናውቃለን በፊትም ስማቸው ታዋቂ ነውና። በፖለቲካ እንዳልሆነ እናውቃለን አቋማቸውን ደብቀው አያውቁምና። ለመብት መሆኑን ግን አልደበቁም ትላንትም ካገር ያስወጣቸው እምነት ነውና።

መረዋ በሃይማኖት ጥያቄ መግባት አይይፈልግም ብሎ በተደጋጋሚ ለአንባብያን ቢናገርም የስደት ሲኖዶስ መኖሩን ግን አይቀበልም። የኢትዮጵያ ሲኖዶስ መንበሩ ቅድስት ማርያም እንጂ ሰሜን አሜሪካ አይደለም ብሎ ያምናልና። ከሃገራችን ተሰዶ  የነበረ ቢኖር የመድሃኒ ዓለም ጽላት በጣልያን ወረራ ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ወደ  ሎንዶን  እንደ ነበረ እናስታውሳለን። እሱም ንጉሱ ሲመለሱ ተመልሶ አገር ቤት ገብቷል። የኃይማኖት መሪዎችና እምነቱ ግን ከሃገራችን ተሰዶ  አያውቅም።

ስልጣን አለን ለሚሉ የተሰበሰበው ገንዘብ እስኪያልቅ እንፋለማለን ብለው ለሚፎክሩ የፖለቲካ ሰዎች መረዋ የሚለው ነገር ቢኖር "ደጀሰላም ያደገ፣ ምግብ ቤት ሁሉ ደጀሰላም ይመሰለዋል" እንዲሉ የተሰበሰበ  ስብስብ ሁሉ የፖለቲካ ደጋፊ አለመሆኑን እንዲረዱት ነው።

 ዛሬ የተጀመረው ክስ እንደ ትላንቱ ሳይሆን መፋታት ካለብን ድርሻችንን መካፈል መብታች ነው የሚል ስለሆነ መፍትሔው በሰላም መካፈል ብቻ  ይሆናል። አብረን መኖር አንችልም ብሎ ገንዘብንም ንብረትንም ነጥቆ መቅረት አለመቻሉን ደግሞ በፍርድ ቤት የቀረበ  ጉዳይ ነውና  መጨረሻውን በፍርድ ቤት የምናየው ይሆናል።

መሪ መሆን ጥሩ ነው ያሉበትን አለመገንዘብ ደግሞ "ግቻ ያሰረ እረኛ ዘውድ የጫነ  ይመስለዋል"  የሚለውን የድሮ  አባባል ያስታውሰናል። መረዋ በፊት እንዳለው አሁንም ማለት የሚወደው መፋታቱ ካልቀረ አሁንም ፍችው በበሰለ መንፈስ መመራት እንዳለበት ነው። ካልሆነ " የበሰለ ዳቦ መብሰሉ የሚታወቀው መሃከሉን በመንካት ነውና" ሊጥና  ብስሉን ለማየት እድሜ  ይስጠን።

በሰላም ዋሉ

Wednesday, March 27, 2013

ማገርና ወራጅ የሌለው ቤት ጣራው መደርመሱ የግድ ነው።

እስከዛሬ የምናውቀው ለተሰደደ የሚጸልይ መንፈሳዊ አባት እንጂ የሚሰደድ አባት አልነበረምና ለተሰደዱት ጸልዩላቸው። የፈጣሪን ዘላለማዊ ግዛት ለማየት የሚጓጓ እንጂ ዙፋነ ሲመትን ካልያዝኩ ሃይማኖቱ ይፍረስ የሚል አባት ካያችሁ ይቅር በላቸው ብላችሁ ለምኑላቸው። "የመምጫዬ ቀን አይታወቅም ብሏልና  ንስሃ ግቡ" ብለው በሚያስተምሩበት ልሳናቸው፣ ካልገዛን ይዝጋን፣ የሚሉ ስታዩ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱላቸው። እኛ ፭ ኪሎ  እስክንደርስ ቤተክርስቲያኑ ይፍረስ፡ የሚሉ ከሰማችሁ ተዝካር በቁም አውጡላቸው።

ውድ የመረዋ እድምተኞች፣ የመብት መጣስን ተቃውማችሁ በሰለጠነው ዓለም ተቀምጠን መረገጥን፣ በሰላማዊ አገር እየኖርን መታፈንን፣ ገዴታ  እንጂ መብት የሌለበትን አባልነት ላለመቀበል አሻፈረን ብላችሁ እስካሁን የታገላችሁትን ሁሉ ዛሬ መረዋ እንኳን ደስ ያላችሁ ሊል ይወዳል። የዛሬ ፭ ዓመት ይህ ይሆናል ስትሉ፣ ስንል የሚሰማው ጥቂት ነበርና። ተጀምሮ  እስኪያልቅ ግን ያላችሁት፣ የተናገርነው፡ መሬት ላይ ጠብ አላለም። ዛሬ ይዋሹ የነበሩት የተጋለጡበት፡ ለመብት የቆሙት ደግሞ በኩራት የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሆኗል። ባለፈው ቅዳሜ የሚካኤል  ቤተክርስቲያ አባላት የስደት ሲኖዶስን መረጡ ሲባል ሰምተው የተናደዱ ቢኖሩ ትላንት ስንናገር አይሆንም፣ አይደረግም፣ ይሉ የነበሩ ግለሰቦች ብቻ ናቸው። ይህ ከሆነ "ቤቴን ወለድ አግድ አሲዤም ቢሆን ወደ  ሕግ እሄዳለሁ" ያሉት ግለሰብ ደላላ ሲያጠያይቁም አላየንም። ይልቅስ ያስተዋልንውን ሌላ ቁም ነገር እናጫውታችሁ። እነዳዊት አለማየሁን አናስገባም እያሉ ያኮረፉ ጓዶቻቸውን የስድስት ወር የአባልነት ጊዜ  እያራዘሙ ሲመልሱ ማየታችን ነው። ነገሩ የፖለቲካ ነው ካሉም ወሳኞቹ ባለስልጣናት እነዳዊትም እነሱ የማይደርሱበት የትግል ገድል እንደ ነበራቸው መናገር የግድ ይሏል። ሃይማኖተኛ የሆኑትን እየመረጥን ነው ካሉም መስፈርቱ ሌላ ካልሆነ ዳዊትን በዚህ የሚፈትኑት አልመሰለንም። ልንል የፈለግነው እምነትና ውሸት እየተጠላለፈ  መጣ ለማለት ነው። ሌሎች ስሞች መደርደር ቀላል ነው። የዛሬ ፬ ዓመት  የመሃበረ ቅዱሳን አባል ነህ ብለው የወነጀሉት ግለሰብ ምን ማለታቸው እንደሆነ ተጨንቆ እኔ ነኝ ቅዱሱ? ኧረ ባባቶች መሳለቅ ነው ማለቱን ሰምተን ነበር። በወቅቱ ውሸት መጥፎ  ነው በተለይ ውሸቱ ከቤተክርስቲያን ሲሆን እጅጉን ይዘገንናል ብለን መጻፋችንም ትዝ ይለናል።


እስቲ ዛሬ ልብ በሉ  ከ 4 ዓመት በፊት ስለባለስልጣኖቹ እቅድ ስንናገር ትንቢት ተናጋሪዎች ሆነን ሳይሆን አካሄዶችን በመመልከት የደረስንበት የግምጋሜ ውጤት ነበር። ያልነው ባይደርስ ለቤተክርስቲያን መልካም ነበር የፈራነው ግን ሆነ። እነሆኝ የስደት ሲኖዶስ ቤተክርስቲያኑን ለመረከብ ቻለ። እንዴው ለምስክርነት December 18 2009 መረዋ ቁጥር ፭ የጻፈውን ቀንጨብ አድርገን በድጋሜ ዛሬ እናስነብባችሁ። እንዲህ ይል ነበር...........

በግል እንደታዘብነውና ሂደቱን እንደተከታተልነው። ሕጉን ለምን በክስ መሃል ለመቀየር አስፈለገ ለሚለው? የራሳችን መልስ የሚከተለው ይሆናል።
1 የማይፈልጉትን አባላት ለማባረር።
2 አዲስ የሚገቡ አባላትን ለማጣራት ለማበጠር።
3 አባላት ተቀበሉትም አልተቀበሉት የራሳቸውን ውሳኔ በመሰላቸውና ከቦርዱ ጥቅም በመነሳት ለመወሰን።
4 የእምነትን ጉዳይ አስመልክቶ ቄሱ ምን መሰበክ እንዳለበትና እንደሌለበት ለመንገር።
5 አባላት ለመመዝገብ ሲመጡ እንደ አፓርትመንት የማመልከቻ ማስከፈል። አባልነታቸውን ተቀባይነት አገኘም አላገኘ የከፈሉት እንዳይመለስ ማድረግ።
6 ገለልተኛነትን በመስበክ የሲኖዶስን ቦታ መተካት። ነው ብሎ ለማለት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም።

አሁንም ያላችሁት አልተፈጸመም የሚሉ ካሉ የምንጨምረው ይኖረናል። ዛሬ አንጋፋ  የቤተክርስቲያን አባቶች ተባረዋል ከ 1150 አባላት በላይ የነበረው ቤተክርስቲያን ዛሬ 279 አባላት ብቻ እንዳለው የሚሰማ  ሰው ቤተክርስቲያኑ አይወድቁ አወዳደቅ እየወደቀ  እንዳለ  የሚስማማ  ይመስለናል። ቀሳውስት እውነትን ስለሰበኩ ሲባረሩ ስናይ እግዚኦ ብለን ነበር። አባቶች ካገር እንዲባረሩ ለኢምግሬሽን ደብዳቤ  ሲጻፍ ስናይ ኧረ  በክርስቶስ ብለን ነበር። ደብዳቤውን የሚጽፉት ደግሞ  የቤተክርስቲያን ባለስልጣናት ብሎም እራሳቸው በስደተኝነት መኖሪያ  ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን ስናስብ የበለጠ አዝነን ነበር፡፡ አባላት ለአባልነትም ከባላቸው ከሚስቶቻቸው እንዲለዩና እንዲመዘገቡ ሲደረግ እግዚኦ ብለናል። የከፈሉበት ሳይሆኑ የተሾሙበት ፈላጭ ቆራጭ ሲሆኑም አስተውለናል። ይህ የትላንት ሂደት ነበር። ዛሬ ጨዋታው መቀየሩን አይታችኋል።
የእምነቱን መንገድ ወደ  ፖለቲካ  የወሰዱት የመንግስት ተቃዋሚ ነን ባዮች ትልቅ ስህተት እየሰሩ ነው።
የቆሰለ  ዝንጀሮ ወደ መንጋው ሲጠጋ የሚድን ይመስለዋል ሲቀርብ ግን ቁስሉን ሁሉም እየላሱበት ይብስና  ይሞታል እንዲሉ ፣ የባሌ  መንገድ በጋርላንድ በኩል  የሚመሰላቸው ፖለቲከኞች  ካሉ ጊዜ  ይስጠን እንጂ  መንገድ መሪ አጥተው በጎዳና ሲንገላጀጁ ለማየት ጊዜ  እንደማይወስጅብን እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን። ትላንት እንዳልነው ጆሮ ቆራጭ መጣብህ እየተባለ ያደገ  ሕፃን አድጎ ቀልዳችሁን ተው እንደሚል ሁሉ አሁንም ቤተክርስቲያንህን ኢሕአደግ ሊወስድብህ ነው ያሉት ምእመን የወሰደበት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነኝ ባዩ እንጂ ኢህአደግ አለመሆኑን እያየው ነው። በሬ ያረደ ሰው በጎረቤት ሙዳ ስጋ  ሲጣላ  አላየንምና። ዱላ  ያለው ጠመንጃ ይመኛል ሲባል እንጂ ጠመንጃ  ያለው ዱላ  ይመኛል ሲባልም አልሰማንም ለማለት ነው።

ዛሬ ምእረፉ ተዘጋ  ለሚሉ የምስራች ወሬ አለን። ባለፉት ዓመታት የንብረት ጥያቄ  ክስ ይደረግ ሲባል ስንቃወም መቆየታችን እውነት ነው። ይህ ደግሞ መለያየትን እንዳያመጣ በመፍራት ነበር። የከሳሾችም ሆነ  የኛ  ፍላጎት መብትና እምነትን ከመለየቱ ላይ ነበርና። ዛሬ  ግን የእምነት ውሳኔ  መወሰን ተችሎ  ይሆናል፣ ንብረትን መንጠቅ ግን አይቻልም። አባላትን ማባረር ካህንን ማስጠንቀቂያ  መስጠት ከስራ  ማገድ ችለው ይሆናል በሌላው ገንዘብ መወሰን ግን አይቻልም። በእምነት አንግባ ያለው ዳኛም ከንብረት ጥያቄ  ሊሸሽ አይችልም። ከዳኛው ለመጥቀስ "በመጨረሻ ተከፋፍላችሁ እንደምትበተኑ ይታነኛል" ሲል የቤተክርስቲያኑ ጠበቃ  እሱን እኔም እላለሁ ብሎ  ነበር። ያ ቀን እንዲመጣ የጣሩት ባለስልጣናት ምኞታቸው ሊፈጸም መቃረቡን ታዲያ  ቀስ ብለን ሹክ እንበላቸው።
ክርስቶስ የቄሳርን ለቄሳር አለ እንጂ የቄሳርን ለመቅደስ አላለም። የተገፉትና  የተወረወሩት ምእመናን ወደ  ባህር ተወርውሮ ካሳነባሪ አፍ ገብቶ  እንደወጣው.................... ተመልሰው ነፍስ እንደሚዘሩ እርግጠኞች ነን።
የኛ ትግል ለምእመን መብት ነበር እንጂ ለግንብና  ለገንዘብ አልነበረም። አታመልኩም ካሉ: አትናገሩም ካሉ በጉልበት እንነጥቃለን ካሉ፣ እነሱ ያልከፈሉበት ገንዘብ ይዘው ቢከራከሩም ሕዝብ የለፋበትን፣ እናባርራለን ያሏቸውን፣ ያባረሯቸውን አባላት ድርሻ  የመስጠት ግን ግድ ይላል። እዚህ መድረሱ ያሳዝነናል። ይህ ደግሞ  በኛ ፍላጎት የተደረገ  እንዳልሆነ  ይታወቅ። ትንቢት መናገር ባትሉን ይህ እንደሚሆን ግን መተንበይ እንወዳለን። "ሲመሽ ስገዱልኝ ያለ  ሽፍታ ወጋጋን ሲቀድ  ይደበቃል።"

የሚካኤል ፈቃድ ይታከልበት

መልካሙን ለሁላችን።
  























































Saturday, March 9, 2013

ጉቦ የተቀበለ ዳኛ የሚፈርደውን መረጃውን ሳያገናዝብ አስቀድሞ ያውቀዋል።

"ዝምታ  ወርቅ ነው" "ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም" ሲባል እንሰማና "ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል" "በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም" የሚለውን አባባል ስናዳምጥ ደግሞ ግራ እንጋባ ነበር። አሁን ግን ተረት አይደለም ምንም ነገር አያታልለንም። በመቆየት አረጀንና ከእድሜ ጋር ትእግስትም መጣ ቢባል እውነት መሆኑ እኮ ነው። አይገርምም? አገር ቤት ቢሆን ኖሮ አባባ፣ እማማ፣ ተብለን ወንበር የሚለቀቅልን፣ ስንገባ ነወር የሚባልልን፣ ሽማግሌዎች፣ ላስታራቂነት የምንፈለግ፣ የሰፈር ሕጻናት የሚፈሩን፣ የሚያከብሩን፣ አዛውንቶች እንሆን የነበርን ዛሬ እዚህ ባለንበት ሃገር፡ በስድብ ይወርዱብናል፣ የምናየው ደስ አይልም። ለምስክርነት የተቃወሟቸውን ግለሰቦች በሞት የተለዩ ወንድማቸውን እንኳን ባደባባይ እንዳይሰናበቱ፣ እንዳያለቅሱ ሲከለክሉ አስተውለናል። ሊደባደቡም ይቃጣቸዋል፣ ያስፈራራሉ። በደፈናው እዚህ ዳላስ ያልደረሰ ውርጅብኝ ምን አለ? ያም ሆኖ ግን ይህንን መላና  ዘይቤ  ብለው የተነሱ እየተጋለጡ መጡ እንጂ፣ የሚናገሩት እስኪጠፋቸው ድረስ ያልሆነ ያልተደረገ አወሩ እንጂ፣ በቤተክርስቲያን ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው በፖለቲካ የራቃቸውን በእምነት ሽፋን ገቡበት እንጂ፣ አባላቱን በተኑት እንጂ፣ ምንም ያተረፉት ነገር እንደሌለ ምስክሩ ምእመኑ ነው። የምናወራው ስለ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የችግር ጉዞ  ነው።

የቤተክርስቲያኑ ተመራጮች፣ ካህናትን አባረሩ፣ የሚሰበከውን እኛ አስቀድመን ማወቅ አለብን አሉ፣ ችግራቸው ግን  አልተፈታም።
እንዴት ቤተክርስቲያን ይከሰሳል እኛ እንደልባችን ፈልጠን ቆርጠን እንግዛችሁ አሉ። ሕዝቡ ግን መክሰስ የሚያውቅ ሰው እኮ የሕግን የበላይነት የተቀበለ ነው አላቸው። አትናገሩ ብላችሁ ስታፍኗቸው፣ በፖሊስ መቅደሱን ስታስደፍሩ፣ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ብሎም ጠየቃቸው። መልስ አልነበራቸውም። ያም ሆኖ  ሕዝቡ ግን ምን መአት ወረደብን ብሎ ወደ  ፈጣሪው እግዚኦ ማለቱን አላቆመም። በወንጀል ባደባባይ እየተከሰሱ እንኳን አበስ ገበርኩ ሳይሉ አሁንም የመንፈሳዊ ቤት መሪዎች  ነን ሲሉ ቅር አላላቸውም። ስለ ልጆቻቸው ሳይናገሩ ስለ ልጆቻችን ሊነግሩን ይፈልጋሉ። ስለ ባለቤቶቻቸው ሳያወሩ ባለቤቶቻችንን ሊወርፉ ይነሳሉ። የብዙውን ግለሰብ ሥም በየብሎጉ በውሸት እያብጠለጠሉ፣ ትዳር ሊያፋቱ፣ ጎጆ ሊያፈርሱ፣ ተነስተው ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ የተገላቢጦሽ ችግሩ በራሳቸው ላይ ሲመጣ እንደ ምልክት ቆጥረው አምላክን ሲማለዱ ግን አላስተዋልንም።

አንድ ነገር ግን እውነት እየሆነ  መጣ። በሕግ አምላክ ያሉት ግለሰቦች የተናገሩት አንዱም ከመሬት ጠብ አላለም። የዛሬ 4 ዓመት የጻፉት በቅደም ተከተል እየደረሰ  ነው። አሁንም እኛ ያስተዋልነውን እንንገራችሁ። የምናስበውን ካላደረግን ከሥልጣን አንወርድም የሚሉት ባለስልጣናት ይህን ማድረጋቸው መብታቸው ነው ለማለት ግን ጊዜ  አይወስድብንም። ሕጉን እንደፈለጋቸው መቀየር ይችላሉና። የዛሬ  ሳምንት ባዋጅ  ያራዘሙትን የምርጫ ጊዜ እስከ ማርች አይደለም እስከ ኦሜጋ ማድረግ ይቻላቸዋል። መንግሥት እነሱ ናቸውና። ማርች ያሉት ደግሞ ጾም ይገባልና  በጾም መሰብሰብ አይቻልም ብሎ ቀኑን ለማራዘም እንደሆነ  የሚጠፋው ሰው ይኖራል ብለው ያስቡ ይሆን? እንደዚህ ካሰቡ ተሳስተዋል። ትላንት ሲያደርጉት በማየታቸን ለኛ አዲስ አይደለምና?። የአባልነት ክፍያ ከስድስት ወር በላይ ያዘገዩትን በመሃል ተናደውባቸው የነበሩትን ጓዶቻቸውን ለመመለሰ የመክፈያውን ጊዜ አንድ ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ ሌላም የመቀልበሻ  አዋጅ ማወጅ ይችላሉ። ሕግ እነሱ ናቸውና። የሚነዳቸው ነገር ቢኖር የመንግስተሰማያት ቁልፍ በእጃቸው አለመኖሩ ብቻ  ይመስለናል። ያ ስልጣን  እነሱ ጋ ባለመኖሩ  ፈጣሪ ምስጋና ይግባው እንላለን።  ከዛሬ  ጀምሮ  የቦርድ አባል መሆን የሚችለው ከደብረታቦር  አውራጃ ከፋርጣ ወረዳ  የመጣ ብቻ  ነው ማለት ይችላሉ። ትግሬ  ከሆንክ የሸዋ ሰው የደቡብ ከሆንክ እኛ የምንለውን የምትቀበል ከሆነ  መልካም ካልሆነ ግቢያችንን ልቀቅ ማለት መብታቸው ነው። ሕግ በእጃቸው ነውና።  የምእመናን ግዴታ ደግሞ እነሱ ያሉትን መቀበል ብቻ ነው። እምቢ አሻፈረኝ የሚል ካለ ከቤተክርስቲያኑ ይባረራል፣ ተባሯልም። ይህ አልሆነም? አይደረግም? የሚል ካለ ለቤተክርስቲያኑ የለፉ እምነት ያላቸው ፈሪሃ  እግዚአብሔር ያደረባቸው ምእመናን ሰላም ባሉ ፍቅር በመናገራቸው የእምነትና የትግል የመደብ ጀርባቸው ተመርምሮ ከአባልነት የተከለከሉ የመስራች አባላት ስም መደርደር ይቻላል። የሚያሳፍረው ግን የሚያባርሩትንና የተባረሩትን ማመዛዘን  ሲጀመር ነው።

የቀድሞ  የቦርድ አባላት ሕጉን ከአባላት ፈቃድ ውጭ  መቀየር እንችላለን ሲሉ እግዚኦ  የመብት ያለህ የተባለው "ዛሬ ሕጉን የቀየሩ የቦርድ ባለስልጣናት ነገ  ሕጉ በነሱ ላይ እንደሚያነጣጥር ይወቁ ብለን የጮህነው፣ ይህ እንዳይከሰት ነበር።" "ገንዘብ በሰላሳ  እውቀት በስልሳ " ይሏል ይህ ነው።

አባቶችን እየተጋፋ ቀሳውስቶችን እያስፈራሩ እንግሊዝኛ የማይናገር ሁሉ መሃይም ነው ሲሉ ከረሙ። ባለፈው እሑድ በሰላም ያረፉትን መንፈሳዊ አባት አቡነ  ይስሐቅን ጭምር ሳይቀር ሲዘልፍ የነበረው የቤተክርስቲያናችን ዲያቆን ጸሎትና ምህላ  የሚያስፈልገው ሆኖ  ታይቶናል። በነገራችን ላይ ጳጳሳት ከግብጽ በሚመጡበት ሰዓት አረብኛ ተናጋሪ እንዳልነበሩ ሁሉ፣ በአገራችን ያሉ የመንፈሳዊ አባቶች በግእዝ የተካኑ እንጂ ብዙዎቹ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደማይናገሩ እየታወቀ ዛሬ እኔ እንግሊዘኛ በመናገሬ  ብቸኛ አዋቂ ነኝ ብሎ ሲዝናና ያየነው ዲያቆን ለድፍረቱ እግዚኦታ የሚያስፈልገው ነው። የስደት ሲኖዶስ እደግፋለሁ እያለ የአስታራቂ ለምድ ለብሶ የነበረው ይህ ዲያቆን ማንነቱን ለማወቅ ለብዙሃኑ ጊዜ  ፈጅቶ እንደሆን እንጂ እኛስ ቀደም ብለን አውቀነው ነበር። አገር ቤት ያሉ አባቶችም እያወቁ በምህረት ሲያልፉት ከርመው ሲበዛባቸው የወሰዱትን እርምጃ  ሁላችንም ያየነው ነው። ከእንግዲህ ለሰማይ ቤታችን እንጂ አላፊ ለሆነው ለአንድ ዓለም ባንጨነቅ መልካም ነው እንላለን።

ይህንን ካልን ዘንዳ በማጠቃለያው የምንናገረው አለን።

በስልጣን ላይ ያሉትን የቦርድ ባለስልጣናት የምንላቸው ነገር ቢኖር፣ ከወረዳችሁ ላትመለሱ ስለምትችሉ ሕጉን በመቀየር እራሳችሁን እድሜ ልክ ተመራጭ አድርጋችሁ እንድታስቀምጡ ነው።

ከውጭ ሲኖዶስ ጋር ከመቀላቀላችሁ በፊት የናንተን ዘላለማዊ ስልጣን እንዲቀበሉና  እንዲያጸድቁ በጽሁፍ ማረጋገጫ ብትጠይቁ መልካም ነው።

ከቤተክርስቲያኑ ስም ላይ የኢትዮጵያ የሚለውን ወደፊት ጭቅጭቅ እንዳይፈጥር አንስታችሁ በምትኩ ጁፒተር ወይም ጋርላንድ በሚል ብትቀይሩት የተሻለ  ነው። 

የእናንተን ስም  በመቅደስ የማያነሳ ካህን ካለ ማባረርን አትርሱ።

በስማችሁ ስለት የማያስገባ አባል ካጋጠመ አስወገዱ።

እናንተን የሚረዳ ከሆነ  በውስጥ ጠንካራ  ደጋፊ የሆነውን ጵጵስና አሰጡ።

የተረፈ  ገንዘብ ካለ የሚመጡት እንጋራ  እንዳይሉ በስማችሁ ሞግዚትነት ተከፋፍላችሁ አስቀምጡ።

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እምነት፣ መብት፣ ፍቅር፣ መከባበር የሚሉ አባባሎችን በድንጋጌ አዋጅ አግዱ።

ገንዘብ የሚከፍል ከጠፋ ከበር ላይ ደህና  ጎበዝ በማስቆም የመግቢያ ዋጋ ማሰባሰብ ጀምሩ።

የዛሬ  3  ዓመት እንደጠቆምነው ገቢው ካነሰ  ቅዳሴ  ጠበል በገንዘብ መሸጥን እንደ  ገንዘብ ማሰባሰቢያ  ተጠቀሙበት። 

የፖለቲካ አባላትን በማሰባሰብ እራሳችሁን አጠናክሩ።

ይህ ብዙውን "ችግራችሁን ይቀርፈዋል" ብለን እናምናለን።

ለሰማዩ ሳይሆን ለዚች አንድ ዓለም ምኞትም የሚያሟላ ይመስለናል። ይስመርላችሁ 11.2 ውሎ ይደር! አሜን።

ከዚህ በመቀጠል ካንባቢ የተጠቆምነውን ጽሑፍ ለእናንተ ለማዳረስ የድህረ ገጽ አድራሻውን ቀጥለን አስቀምጠንዋልና  በመጫን እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን።

የሲኖዶስ የፈተና ጉዞ
https://docs.google.com/file/d/0B5ikXekolDC4TWplNG1yZEVUZzg/edit?usp=sharing