Tuesday, December 11, 2012

ሰላም የሚፈጠረው ሰላም ብሎ በመነሳት ብቻ ነው።


                    ሁሉንም ቻይ አምላክ እንደየሥራችን የእጃችንን ይከፍለናል ማለት እውነት መሆኑ ባይካድም ምሕረቱ  የማያልቅበት እየሱስ ክርስቶስ አብሮት የተሰቀለውን ነፍሰ ገዳይ እንደማረ ሁሉ እኛንም በምሕረቱ ይዳስሰናል ብለን እናምናለን። ደካሞች ነንና ጥንካሬን፣ ፈሪዎች ነንና ድፍረትን፣ ንፉግ ነንና ቸርነትን፣ ቂመኞች ነንና ይቅርታን፣ ከሀዲዎች ነንና እምነትን፣ እንደሚቸረን ደግሞ ደጋግሞ የተነገር በመሆኑ የቃሉ ፍጻሜ ላይ መጠራጠር ከሌለ በስተቀር ይሆናል ያለው እንደሚሆን  በሙሉ እምነት መናገር ይቻላል። 
            አዞ አፉን ከፍቶ በመተኛቱ የሞተ እየመሰላቸው የሚጠጉትን  እንደሚያድን ሁሉ የፈጣሪን አምላክነት የሚፈታተኑትን በመንግሥቱ ቀናዊ ነውና እንደሚገስጻቸው ደግሞ ለዘመናት ያየነው ያስተዋልነው በመጽሐፍ ያነበብነው ነው። 
             ይህንን ካልን በኋላ ሰሞኑን በዚህ በዳላስ የተደረገውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን የሰላም ጉባኤ  በጉጉት ከጠበቁትና በመጨረሻም በውጤቱ ከተበሳጩት መሃል እራሳቻንን እንደምራለን። ሰላም ወረደ ማለት የሁሉም ጊዜ እምነትን በማስፋፋትና በማጠናከር ላይ እንጂ በማፍረስ ላይ አይሆንም ከሚል አመለካከት። የመንፈሳዊ አባቶች ሱባኤና ጸሎት፣ የምእመናን ለቅሶና እግዚኦታ ምላሽ ያገኝ ይሆናል ከሚልም መንደርደሪያ  በመነሳት ነበር።   
       ለምን አልሆነም ለሚለው የበኩላችንን መናገር እንችላለን። ዋንኛውና  የማንጣላበት ግን እሱ ስላልፈቀደ ብቻ  ነው። ከሃገር ቤት የመጡ አባቶች ግዝትን አንስተው እዚህ ያሉትን መንፈሳዊ አባቶች ስልጣን ተቀብለው ከነክብራቸውና ከነማእረጋቸው እንዲገቡ መስማማታቸውን ሲቀበሉ፣ በስደት ያሉ መንፈሳዊ አባቶች  ግን ለ 20 ዓመት ሲያነሱት የኖሩትን የመንበረ  ስልጣን ጥያቄ አሁንም የሙጥኝ  ማለታቸው ግን ሁላችንንም አሳዝኖናል።
                    ክርስቶስ እንደሚገደል እያወቀ  ወደ  መሰቀያው የሄደው እኮ መሰወር አቅቶት አልነበረም። የሰቀሉትን ግፈኞች የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ያለው መቅጣት ተስኖት አልነበረም። የተሰቀለው በደሙ ከሃጥያታችን ሊያነጻን ይቅር ያለው ምህረትን ሊያስተምረን ነው እንጂ። ለሐዋርያት ስልጣን የሰጠውም እንደኔ ሆናችሁ አስተምሩ በስሜ  ወንጌልን ስበኩ ህሙማንን ፈውሱ አርአያም ሁኑ በማለት ነው። ታዲያ አባቶች ለዚህ መንፈሳዊ ስልጣን ያበቃቸውን አምላክ በተሰበጣጠረው ምእመን ችግር መፍትሄ  እንጂ መለያያ ባይሆኑ እንዴት መልካም ነበር። መቼም እድሜ የማይደበቅ ስጦታ ነውና ለመጠራት የቀረን ስንት ጊዜ  ይሆን  ብሎ መጠየቅም መልካም ነው። ሰላምን ለሚፈልግ ምእመን ሰላም ለክሙ ማለት እንጂ መለያየትን እንዴት ለማሳለፍ ይፈለጋል። ተአምር የሚገለጽባቸው ገዳማት ደግሞ ያሉት ሃገር ቤት ነው ብለን እንቀበላለን። ያ የሆነው በየጥሻው በየዋሻው፣ በየሰቀላው፣ በየዱር ገደሉ ተጠልለው በሚጸልዩ መነኮሳትና አበው እንደሆነ እናምናለን።
              ስለሆነም ዛላለማዊ ስፍራን እንጂ ጊዚያዊ ወንበርን በመተው ለሰላም እንዲነሱ እንለምናለን። ፈጣሪያችን የኢትዮጵያን ለቅሶ ሰምቶ ምህረቱን ይላክ።