Saturday, June 1, 2013

በትንሳኤ የሚያምን ሰው በሞት አይደናገጥም

ውድ ምእመናን


እንደኛ ክፋት፣ እንደኛ ተንኮል ቢሆን እስካሁን መሰንበት አልነበረብንም። ምህረት መደሰቻው የሆነ ፈጣሪ አምላክ ሁሉን ቻይ ነውና ከሐጥያታችን እንድንድን ተሰቃይቶ ሞትን እንደሞተልን ሁሉ ዛሬም በምህረቱ እየዳሰሰን ነው። እራስን ማታለል ይቻል ይሆናል ፈጣሪን ለመሸንገል መሞከር ግን ግብዝነት ነው። በሚያምኑ ላይ ማላገጥ ቀላል ነው ብሎ ማመን ይቻል ይሆናል። በእምነት ጸንቶ መቆየት ግን ብርታትን የእግዚአብሔርን እርዳታ ይጠይቃል። በዳላስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመብት ጥያቄ አኳያ በተነሱ አለመግባባቶች፣ አባላትን በማባረር ሰላም አይፈጠርም ብለን ስንናገር ሰንብተናል። የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናትን በመግደል የክርስቶስን ማደግ መግታት እንደማይቻል ሄሮዶቱስ ቢያውቅ ኖሮ ያንን ሁሉ በደል ባልፈጸመ  ነበር። ለእምነት የተሰበሰበ ክርስቲያን በእምነት አይጣላም ከሚል አመለካከት በመነሳት ሁሉን አደላዳይ አምላክ የተለያየነውን እንዲሰበስበን፣ የተቀያየምነውን እንዲያስታርቀን፣ ያራራቀንን እንዲያቀራርበን በማሰብ፣ ለሰደቧችሁ ይቅርታን፣ ላዋረዷችሁ ምሕረትን፣ ላባረሯችሁ እርሕራሔን እንዲሰጣቸው ፀልዩ ብለን መናገራችንን አሁንም አንዘነጋም። ይህንን ስንል ከፍርሃት በመነሳት አልነበረም።  በእምነታችሁ ተደራደሩ፣ ተረገጡ፣ መብታችሁን ተገፈፉ፣ ንብረታችሁን ተነጠቁ፣ ማለታችንም እንዳልነመረ ሁላችሁም የምታውቁት ይመስለናልና መደጋገም አንፈልግም። ቀደም ሲል ተነስተው የነበሩትን የመብት እረገጣን፣ የአባላትን ማባረርና የቦርድ አባላት የሆኑት መሪዎች የግለሰብን የአባልነት ማመልከቻ በፖለቲካ መነጽር እያዩ ደጋፊዎቻቸውን ሕጉን እየለጠጡ፣ ተቃዋሚዎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ሕጉን እያጎበጡ ሲያስገቡና ሲያባርሩ ተመስርቶ የነበረውን ክስ ከጅምሩ ደግፈን በጽናት መቆየታችን ያደባባይ ሚስጥር ነው። ይህንን ስናደርግ እንዳወሩት ገንዘብ ተልኮልን፣ ድርጎ ተወስኖልን ሳይሆን ለራሱ መብት ያልቆመ ግለሰብ ለሌላው መብት መቆም አይችልም ከሚል መርህ በመነሳት ነበር። ባደረግነው አሁንም እንኮራለን። እንዳልነው ቤተክርስቲያኑ ያባላት ድሃ እስኪሆን ድረስ መንምኖ የተሰበሰበው ገንዘብ ሲቀንስ እንጂ ሲጨምር አለመታየቱ ለተናገርነው ማረጋገጫ መረጃ  ነው።

ባለፈው በመብት እረገጣ ክስ ላይ ተሰልፈው የነበሩ ግለሰቦች በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ብለው ላስቀየሟቸውና ለተቀየሙ ይቅርታን ባደባባይ ሲያሰሙ ሰምተን ብስለታቸውን አድንቀናል ከጥንካሪያቸው ተምረናል። በተደጋጋሚ እንዳልነው በዝሙት ዓለም እየታዩ ሌሎችን ዝሙተኛ፣ በየመጠጡ ቤት ሰክረው እየተወላገዱ ሌሎችን የአልኮል ሱሰኛ፣ በእጅ አመል እየተዳደሩ ሌላውን ዘራፊ ወንጀለኛ ለሚሉ አጸፋዊ መልስ መስጠት አቅቶ እንዳልነበረ ደግሞ መናገር እነሱ እንደሚሉት "መሃይምነት" እንዳልሆነ ዛሬም ቢነገራቸው አይከፋም። ለሚሳደብ መሳደብ ቀላል ነው መሳደብ ግን አለመብሰል ነው ብለን እናምናለን።

ውድ የቤተክርስቲያን ምእመናን አንድን ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቤት ከማባረር  የከፋ ነገር ያለ አይመስለንም። ይህ ደግሞ በምድር መቅሰፍትን በሰማይ አባታዊ ግሳጼንና  ፍርድን እንደሚያስከተል ዛሬም መናገር እንወዳለን። ሌላው ሲባረር የሚደሰቱ ካሉ ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። የተረከቡ የመሰላቸው ተሳስተዋል። "በእንግድነት የሚያድሩበት ቤት ማረፊያ  እንጂ መኖሪያ  አይሆንምና"

ታዲያ ትላንት የተጀመረው የአባላት ትግል ዛሬም ቀጥሎ በያዝነው ሳምንት በተለየ መንገድ አዲስ ክስ መመስረቱን ሰምተናል። የተጀመረው ክስ እንዳየነው የአስተዳደር ቦርድ አባላት "ቤተክርስቲያናችንን ከገለልተኛ አመለካከታችን አውጥተው፣ ከሃገራችን ሲኖዶስ ነጥለው፣ የፖለቲካ መስመር ለማራመድ ወደ ስደተኛ ሲኖዶስ ንብረታችንን አሳልፈው በመስጠታቸው የተናደዱ ግለሰቦች "ዛሬስ ያበጠው ይፈንዳ ሳንሞት አትቀብሩንም፣ ሳንታወር አትመሩንም፣ ያዋጣንውን ድርሻችንን እንካፈላን ብለው እንደሆነም ለማወቅ ችለናል። ትላንት የንብረት ጥያቄ  ይነሳ  ሲባል የቀድሞ ከሳሾችም ሆኑ መረዋዎች ተቃውመውት ነበር። ለምን ቢሉ የንብረት ክሱ መበታተንን ያመጣል ከሚልና  ችግራችንን በውይይት መፍታት ከተቻለ መሰነጣጠቁን ማቆም ይገባል ከሚል እምነት ነበር። ይህ በእውነትም አድማጭና ሰሚ ቢያገኝ ኖር መልካም አመለካከት ነበር። ሊሆን ግን አልቻለም። ለምን ቢሉ እየታረቁ የሚክዱ እየተወያዩ  የሚያሴሩ የቦርድ አባላት አሻፈረን በማለታቸው ነበር። አሁን ግን መረዋ ከሳሾች የጀመሩት የንብረት ክፍያ ጥያቄ ወቅታዊና አማራጭ የሌለው ነው ብሎ በመቀበል መጨረሻውን ያሳምረው ማለት ይወዳል። 

የአሁኑ ከሳሾች ለምነን ሰሚ አጣን፣ ተናግረን ተዘጋን፣ በእምነታችን ተቀጣን፣ በመውደዳችን ተገፋን፣ለዚህ ቤተክርስቲያን ደግሞ ላደረግነው አስተዋጽኦ መስካሪያችን አንድ አምላክ፣ ብሎም በመቀመጫውና  በግድግዳው ላይ ያለው አሻራችን በእጃችን የሚገኘው የቤተክርስቲያን ደረሰኝ መረጃችን ነው ይላሉ። ውሸትን መድገም ያሽቸግራልና ዛሬ ያስተዳደር ቦርድ መሪዎች ነን ባዮች የሚሉትን ለመስማት እንወዳለን። ምስክር ሆነው በመሃላ ሲመሰክሩ ማየትን እንናፍቃለን። አሁን ደግሞ  ምን ብለው እንደሚያወሩም መስማት እንጓጓለን። 

መረዋ በመደጋገም እንደ ጻፈው አሁንም ሰላም ማምጣት ካስፈለገ  ምርጫው አንድ ነው ብሎ ያምናል። ምላሹ የምእመናንን መብት ማክበር ብቻ  መሆን ይኖርበታል። የንብረት መካፈል ክስ የመሰረቱት ግለሰቦች ገንዘብ ወስደው ለመክበር አስበው እንዳልሆነ እናውቅላቸዋለን።  ትርፍ አትራፊ ካልሆነ ድርጅት የሚገኝ ገንዘብ በሕግ ትርፍ አትራፊ ላልሆነ ተግባር የሚውል ብቻ እንደሚሆን እናውቃለንና። ለስም እንዳልተነሱ እናውቃለን በፊትም ስማቸው ታዋቂ ነውና። በፖለቲካ እንዳልሆነ እናውቃለን አቋማቸውን ደብቀው አያውቁምና። ለመብት መሆኑን ግን አልደበቁም ትላንትም ካገር ያስወጣቸው እምነት ነውና።

መረዋ በሃይማኖት ጥያቄ መግባት አይይፈልግም ብሎ በተደጋጋሚ ለአንባብያን ቢናገርም የስደት ሲኖዶስ መኖሩን ግን አይቀበልም። የኢትዮጵያ ሲኖዶስ መንበሩ ቅድስት ማርያም እንጂ ሰሜን አሜሪካ አይደለም ብሎ ያምናልና። ከሃገራችን ተሰዶ  የነበረ ቢኖር የመድሃኒ ዓለም ጽላት በጣልያን ወረራ ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ወደ  ሎንዶን  እንደ ነበረ እናስታውሳለን። እሱም ንጉሱ ሲመለሱ ተመልሶ አገር ቤት ገብቷል። የኃይማኖት መሪዎችና እምነቱ ግን ከሃገራችን ተሰዶ  አያውቅም።

ስልጣን አለን ለሚሉ የተሰበሰበው ገንዘብ እስኪያልቅ እንፋለማለን ብለው ለሚፎክሩ የፖለቲካ ሰዎች መረዋ የሚለው ነገር ቢኖር "ደጀሰላም ያደገ፣ ምግብ ቤት ሁሉ ደጀሰላም ይመሰለዋል" እንዲሉ የተሰበሰበ  ስብስብ ሁሉ የፖለቲካ ደጋፊ አለመሆኑን እንዲረዱት ነው።

 ዛሬ የተጀመረው ክስ እንደ ትላንቱ ሳይሆን መፋታት ካለብን ድርሻችንን መካፈል መብታች ነው የሚል ስለሆነ መፍትሔው በሰላም መካፈል ብቻ  ይሆናል። አብረን መኖር አንችልም ብሎ ገንዘብንም ንብረትንም ነጥቆ መቅረት አለመቻሉን ደግሞ በፍርድ ቤት የቀረበ  ጉዳይ ነውና  መጨረሻውን በፍርድ ቤት የምናየው ይሆናል።

መሪ መሆን ጥሩ ነው ያሉበትን አለመገንዘብ ደግሞ "ግቻ ያሰረ እረኛ ዘውድ የጫነ  ይመስለዋል"  የሚለውን የድሮ  አባባል ያስታውሰናል። መረዋ በፊት እንዳለው አሁንም ማለት የሚወደው መፋታቱ ካልቀረ አሁንም ፍችው በበሰለ መንፈስ መመራት እንዳለበት ነው። ካልሆነ " የበሰለ ዳቦ መብሰሉ የሚታወቀው መሃከሉን በመንካት ነውና" ሊጥና  ብስሉን ለማየት እድሜ  ይስጠን።

በሰላም ዋሉ