እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ። ለመጭው ዓመት በሰላም አቅፎ ደግፎ እንዲያደርስን እየጸለይን ሰላምና ፍቅሩን እንዲያድለን አጥብቀን እንለምነዋለን።
መረዋ ከብዙ ዓመታት ጋብቻ በኋላ ልጆቻቸውን አስተምረው አስመርቀው የልፋታቸውን ውጤት እያስተዋሉ አሁንስ ለራሳችን እናስብ ብለው ባለፈው ቅዳሜ ሥጋወደሙ የተቀበሉትን የቤተክርስቲያናችን አንጋፋ ሽማግሌ የነበሩትንና የሚካኤል ቤተክርስቲያን የቦርድ አባል፡ የሽማግሌ ኮሚቴ አባል ሆነው ለዘመናት ያገለገሉን አቶ ዳኜንና ባለቤታቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ሊል ይወዳል። በሚካኤል ቤተክርስቲያን የፋሲካ ዋዜማ ቅዳሜ በመሃከላችን ባለመኖራቸው ያዘነው ብዙ እንደ ነበርን ለማወቅም ችለናል። ሐዘኑ የተፈጠረው ለምን ወደ ሌላ ቤተክርስቲያን ሄደው ሥጋወደሙ ተቀበሉ በማለት ሳይሆን ይህ እንዲሆን ምን ሚና ተጫወተን ይሆን? የሚለውን ወደኋላ መለስ በማለት የችግሮቹን ሂደት በመቃኘት ጭምር እንደሆነም ለማወቅ ችለናል። ስለሆነም የትም ቤተክርስቲያን ይሁን የት ዋናው የነሱ ምኞት መፈጸሙ ነውና መረዋ በድጋሜ እንኳን ደስ ያላችሁ እያለ ለአቶ ዳኘ ቤተሰብ በመላ ስሜቱን ሲገልጽ ለደረሱበት መንፈሳዊ ድል ደግሞ መንፈሳዊ ቅናት እያደረበት ነው።
ከዚህ በፊት በነበረው እትምታችን ጠቅሰንላችሁ እንደነበረው ባለፈው ሳምንት በነበረው ቀጠሮ የከሳሽና የተከሳሽ ጠበቆች የመከራረሪያ ነጥባቸውንና የፍርድ ሃሳባቸውን አጠናቅረው ማቅረባቸውን ልንነግራችሁ እንወዳለን። የከሳሾች ጠበቃ ፋይሉን ያስገባው የስቅለት እለት ዓርብ እንደ ነበረ ስንረዳ ይህ ባጋጣሚ የሆነ እንጂ ሆን ተብሎ የተደረገ እንዳልነበረም ለማረጋገጥ ችለናል። ካሁን በኋላ ዳኛው ስሚዝ ጉዳዩን እልባት ለመስጠት የግድ መወሰን ስላለባቸው በሳምንት ውስጥ ብይን ይሰጣሉ ብለን እንጠብቃለን። መረዋዎችም ውሳኔአቸው እንደደረሰን ለአንባብያን ለማቅረብ አሁንም ቃል እንገባለን።
በሚካኤል ቤተክርስቲያን በአቶ ጸሐይ ጽድቅ ተገዝቶ ከ 5 ዓመት በላይ ሲያበራ የነበረው የቤተክርስቲያን መብራት እሳቸውን ለመጉዳት በሚል እንዲወርድ መደረጉን ስንሰማ እጅጉን አዘንን። መብራቱን ለግሰው የነበሩት አቶ ጸሐይ ጽድቅ ቡራኬውን በወቅቱ የተቀበሉ ስለሆነ ብሎም ለሚካኤል ካበረከቱ በኋላ የሳቸው ንብረት ሊሆን እንደማይችል እየታወቀ ይህ መደረጉ ደግሞ የሚደንቅ ነው። የአቶ ሙላው ወራሽ ስጦታ የነበረው ቴሌቪዥንም እንደዚሁ ከደጀሰላም መነሳቱን ሰምተናል። የመብራቱን መነሳት ለመመስከር ስንችል የቴሌቪዥኑን መነሳት ግን ከመስማት ባሻገር መደረጉን ለማረጋገጥ ገና እድል እንዳላገኘን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ያም ሆነ ይህ በቂም ላይ የተመረኮዘ ማናቸውም ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ ከመናገር ግን ወደ ኋላ አንልም። በዚህ መንገድ ከተቀጠለ ደግሞ ቦርዱ የማይወዳቸውን ግለሰቦች የመዋጮ ስጦታና የስለት ገንዘብ ከባንክ እያወጣ እንዳይበትነው እንሰጋለን ቢባል ትክክለኛ ጥርጣሬ ይመስለናል። የስደት ሲኖዶስ ለጊዜው ይቆይ የተባለው የምእመናንን ተቃውሞ በመፍራት እንደሆነም መስማታችንን ስንነግራችሁ የመብት ትግል መቼም ይሁን በማ እየቀጠለ እንደሚሄድ አሁንም ቃል እንገባላችኋለን። በሚመጣው ሳምንት ቀደም ባለው ጊዜ በወይዘሮ ጥሩዓየርና በአቶ ዳግም ተመስርቶ የነበረው ክስ ይግባኝ የቃላት ክርክር እንደሚኖር ባለፈው የጠቀስን በመሆኑ መደጋገም አስፈላጊ አልመሰለንም። ይህ የቤተክርስቲያን የመብት ጥያቄ ክርክር ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ እየሆነ ነው። ሳምንት ይቆያሉ ብለው ያላሰቡን የቦርድ ዓባላት በጥንካሬአችን መገረማቸውን እራሳቸው እየመሰከሩ ነው። ዛሬ መስራች አባላት በቦርዱ ውስጥ የሉም ዛሬ ትላንት የቦርድ አባላት ሆነው ሲወሰኑ የነበሩት እንደባይተዋር እየተባረሩ ነው ። እንዳልወሰኑ እየተወሰነባቸው ወዳጅ እንዳልተባሉ ጠላትነታቸው እየተነገራቸው፡ ሕግ አስፈጻሚ እንዳልነበሩ ሕግ እየተፈጸመባቸው። ደንብ እንዳልጠቀሱ ደንብ እየተጠቀሰባቸው ነው።
ብዙዎች ከቤታቸው ገሚሶች ወደሌላ ቤተክርስቲያን መበተናቸውን በደስታ የሚመለከተው ቦርድ ጥቂት ሆነን ፈላጭ ቆራጭ ሆነን እንከርማለን ብለው አስበው ከሆነ አሁንም ተሳስተዋል እንላለን። ያላካበቱትን፡ ያልለፉበትን ገንዘብ መበተን፣ ያልሰበሰቡትን ምእመን አበሳጭቶ ማስኮረፍና ከቤተክርስቲያን ማስቀረት ቀለላል ሊሆን ይችላል መገንባት ግን የዘመናት የሥራ ውጤት መሆኑን መረዳት ቢችሉ ግን ትልቅነት ይመስለናል። ኩርፊያ ያለበት ቤተመቅደስ ደግሞ ቁጣን እንጂ ሰላምን ያመጣል ማለት አይቻልም። ምእመናንን ብቻ ሳይሆን ካህናትንም የሚከለክል ደግሞ ትልቅ ድክመት ያለው ነው እንላለን።
እሱ ከመቃብር እንደተነሳ እኛስ ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው።
ቸር ወሬ ያሰማን