Wednesday, September 8, 2010

ያያችሁት ሰው ሳይሆን ጥላ ነው ለሚል ሰው መድሃኒቱ የምን ጥላ? ብሎ መጠየቅ ብቻ ነው። ቁጥር ፵፪

በስደት ላይ 30 ዓመት እየሞላን ነው ብሎ  መናገር የሚያስደነግጠው አዳማጩን ሳይሆን ተናጋሪውን ለመሆኑ ቋሚ ምስክር ነን። ምን ስትሰሩ ከረማችሁ ለሚሉት አጥጋቢ መልስ መስጠት ያስቸግራልና። ስለ እውነት ለመናገር እንደ ቀልድ ያለፈው የስደት ዘመን የራሱ የሆነ  ውጣ ውረድ ነበረበት። ዛሬ እንደቀልድ የምናየው ነገር ትላንት የተራራ ያክል አስቸጋሪ እንደነበር ሲነገር ቀልድ ሊመስል ይችላል። ዛሬ የምንምነሸነሽበት ነፃነትና የግለሰብ መብት ትላንት በነበሩ የአሜሪካውያን ታጋዬች ደም የተገነባ መሆኑን መቀበል የሚከብደን ብዙዎች ብንኖር አይገርምም። በወቅቱ የነበረውን ዘረኝነት በምስክርነት የሚናገሩ ሰዎችን ስንሰማ እንኳን ድግግሞሽ ነው በማለት ማዳመጡ ሁሉ የሚያስጠላን  ልንኖርም እንችል ይሆናል።  የራሳችንን ጉብዝና እያጎላን የሌላውን ስንፍና መናገራችንም ያለ እውነታ  ነው። በዚህ በምንኖርበት አገር ዘረኝነት መኖሩን ለመቀበል ደግሞ  እራሳችን ችግር ውስጥ ገብተን መገኘትን አለብን። ካልሆነ የሌላው ስንፍና  እንጂ ለምን እኛ ከባሕር ማዶ  መጥተን ከነዋሪው መሰላችን የተሻለ  ኑሮ እንኖራለን ብለን የምንከራከር እንዳለን መካድ የሚያስገምተው እራሳችንን ብቻ ነው።

ዛሬ ይህንን ለማንሳት ያነሳሳን ሁሉም ነገር ጊዜውን እየጠበቀ ትላንት ሌላው እደረሰበት ዛሬ እኛም ለመድረሳችን ብልጭታ  እያየን በመምጣታችን ነው። የጽሑፋችን መነሻ  የሆነን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ  ተደርጎ  የነበረው ፱ኛው የኢትዮጵያ ቀን ላይ ያየነው ቅንነት የተሞላበት መሰባሰብ ነበር። በዓሉን ለማክበር የመጡት በሞላ አንድ ዓይነት አመለካከት አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋም ነበራቸው  ለማለት  ባንደፍርም መደረግ አለበት በሚባለው እቅድ ላይ ግን ምንም ልዩነት እንዳልነበረ በስፍራው ነበርንና ምስክርነት መስጠት እንችላለን።

ባለፈው በመረዋ እትምታችን ስለ ቅዳሜው የዘገብነው  እንዳለ ሆኖ እሑድ እለት የተገኘው ሕዝብ ቁጥር ከቅዳሜው የላቀ  ከመሆኑም በላይ በሁለቱ ቀን ጊዜ  ውስጥ $78,000  ለማዋጣት ቃል መገባቱን ግማሾቹም መክፈል መጀመራቸውን ስናይ የኢትዮጵያ መረዳጃ ማህበር አዳራሽ እውን እንደሚሆን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደብንም።

ከሁሉም በላይ የሚካኤል ቤተክርስቲያን ሲገዛ በግንባር ቀደምትነት ያስተባበሩትና እዳው በጥቂት ዓመታት ተከፍሎ እንዲያልቅ ያስደረጉት አቶ ሰይፉ ይገዙ በፈቃደኝነት የዚህም የመረዳጃ ማህበር የሕንፃ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን ስናይና በእለቱ ይህ ትላንት መደረግ የነበረበትን ሕልም ዛሬ እውነት ለማድረግ የተቻላቸውን ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን ቃል ሲገቡ ስንሰማ ይቻላል የሚለው መፈክር በጆሮአችን መደወል ጀምሮ ነበር። የኮሚቴው አባላት ስም ሲጠራም የጅምሩ እውነተኛነት የባሰውን እየጎላ  መጣ። እንዴው የመሃበሩን ሥራ  መጋፋት ነው ባትሉን ለአንባብያን ማንነታቸውን እናስተዋውቃችሁ።

1  አቶ  ሰሎሞን  ሐመልማል (የቦርዱ ተወካይ)
2  አቶ ሰይፉ ይገዙ
3  አቶ  በትሩ ገብረእግዚአብሔር
4  አቶ  ግርማቸው አድማሴ
5  ወይዘሮ ተዋበች
6  አቶ ሚደቅሳ በየነ
7  አቶ  መላኩ አቦዝን
8  አቶ ዳንኤል ግዛው   እንደሆኑ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።

በዚህም እለት በተደረገው የገንዘብ ማሰባሰብ ቃል የገቡትንና  የከፈሉትን ሥም ዝርዝር ከምናስታውሰው  ብንጠቅስ ስብስቡ የተለያየ  ክፍልን ያቀፈ  ለመሆኑ ግንዛቤ  የሚሰጥ መሰለን።

አቶ ብርሃን መኮንን እና ባላቤታቸው ወይዘሮ ተዋበች   $10,000
አቶ ኤልያስ                                                       $6,000
አቶ  ሃይሉ እጅጉ                                                $5,000
አቶ  ብዙአየሁ      (በ city shuttle )                     $5,000
አቶ ሙላው ወራሽ                                              $5,000
ዶክተር ስዩም                                                                               $1,000
አቶ ሃብቴ                    (በማሩ ግሮሰሪ ስም)               $1,000
አቶ መንግስቱ ሙሴ   (በአበባ  ግሮሰሪ ስም)              $1,000
አቶ  ሰይፉ ይገዙ                                                $1,000
አቶ ግርማቸው አድማሴ                                       $1,000
አቶ አበበ ጤፉ                                                   $1,000
አቶ መላኩ አቦዝን                                               $1,000 ለማዋጣት ቃል መግባታቸውን ስንነግራችሁ በርካታ ግለሰቦች በነፍስ ወከፍ $500 - 100  መለገሳቸውንና ቃል መግባታቸውን ለማየት ችለናል። በአጠቃላይ በበዓሉ ላይ በድምሩ $78,000   ቃል እንደተገባ ገሚሱም ገቢ እንደሆነ ከኮሚቴው በተሰጠው ገለጻ ለመረዳት ችለናል።
ታዲያ  እነዚህ ግለሰቦች በሙሉ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ስብስቡን  እንደሚቃወሙት  ግለሰቦች አባባል አገር ቤት ካለው መንግስት ድርጎ ፈላጊዎች ናቸው ብሎ መወንጀል ከተቻለ  ፍርዱን ለአንባብያን እንተዋለን::

በወቅቱ ለበዓሉ ድምቀት የሰጡት የጋርላንዱ ከንቲባ የመረዳጃ መሃበሩ ያዘጋጀውን ሽልማት ለተሸላሚዎች ከመስጠታቸውም በላይ በግላቸው መዋጮ ማድረጋቸውን ሳንናገር አናልፍም። አርክቴክ የሆኑትና  መሃበሩን በቦርድ ተመራጭነት የሚያገለግሉት  አቶ አብርሃም ተሰማም ለዚህ ሕንጻ መሳካት ይረዳ ዘንድ የሕንጻውን ንድፍ በነጻ እሰራለሁ በማለት በሺህ የሚቆጠረውን ወጪ ገምድለው ጥለውታል። ሁኔታውን የታዘቡት የእለቱ የኪነት አቀንቃኝ አቶ ይሁኔ በላይም ለሚመጣው የገንዘብ መዋጮ ስብስብ ቀን በነጻ እንደሚዘፍኑ ለተሰበሰበው ሕዝብ ቃል ገብተዋል።

በማጠቃለያ እንደቆየው የቻይኖች አባባል "የሺ ማይል ጉዞ  በእርምጃ  ይጀመራል" ነውና ባለፈው በታዘብነው ግን ከማይል በላይ መጓዝ እንደተቻለ  ለመመስከር ችለናል።

ሰው አልነበረም ለሚሉት ታዲያ እንደ አርእስቱ ሁሉ ይህ ታዲያ ከየት መጣ? ልንልላቸው እንወዳለን

በዚህ አጋጣሚ ለመላው የስልምና ተከታዬች መልካም የረመዳን በዓል በመረዋና  ባንባቢዎቻችን ስም እንመኝላቸዋለን::

የታሰበውን  ለማስፈጸም ይርዳን እያለ መረዋ ለዛሬ በዚህ ይሰናበታል።