Sunday, September 5, 2010

ከማያዳምጥ ጋር መወያየት ትርፉ የእራስን ቃል መልሶ ማዳመጥ ብቻ ነው። ቁጥር ፵፩

ደህና  አደራችሁ ሳይሆን "ደህና ያደራችሁ አላችሁ?" ብለው ይጠይቁ የነበሩ ግለሰብ እንደነበሩ ያወጉኝ አዛውንት በገበያ መሃል ቀን በቀን ፋኖስ ይዞ ሲጓዝ የነበረን የድሮ ፈላስፋ ምን እየሰራህ ነው? ተብሎ ሲጠየቅ  ሰው እየፈለግሁ ነው ማለቱንም እያስታወሱ ነበር። እንዴው ለልማዱ እንዴት ከረማችሁ?እንበል እንጂ ያለፉት ሳምንታት እንዲሁ ሕብረተሰባችን እየታመሰ ተሳዳቢዎቹ ስድባቸው አልቆ እባካችሁ የምንዘልፈው አልቆብናልና ያላችሁን ላኩልን እያሉ ሲማጸኑ የሰማንበት ወቅት እንደነበረ ሁላችሁም የታዘባችሁት ጉዳይ ነው።

በሌላ ወገን ደግሞ ይሳደቡ የነበሩት ስድቡ ማንንም እንዳልሳበላቸው ሲረዱ አሁንም ከመንበሩ ሆነው ከደሙ ንጹሕ ነን ማለታቸውን ስንሰማ፡ አልተደነቅንም። ይህ እንደሚሆን እናውቅ ነበርና። ሰዳቢዎቹን ይደግፉ የነበሩት ሁኔታው መስመር ማለፉን ሲገነዘቡ ይህ መቆም አለበት በማለታቸው እነሱም የስድቡ ጅራፍ እየደረሳቸው ለመሆኑ በአካል ቀርበው ያነጋገሩን እንዳሉ ስንነግራችሁ እሰየው ብለን አልነበረም። ስንሰደብ የተሰማንን እያስታወስን ድጋፍ ሰጠናቸው እንጂ። እኛ ደስተኛ የምንሆነው አሁንም የስድብ ሙዚቃ የሚማርካቸው ዘላፊዎች በተራቸው አሁንስ በቃን ሰውም አልወደደልን ፈጣሪንም አስቀየምን የሚሉበት ቀን ሲመጣ ብቻ  ነው። ያ ደግሞ እሩቅ እንዳልሆነ  ብዙ ፍንጭ እያየን ይመስለናል።

ሁላችሁንም ልንጠይቅ የምንወደው ለስድባቸው ጆሮ በመንፈግ የሚሉትን ባለማራባት አዳማጭ እንዲያጡ ለማድረግ እንድትተባበሩን ሲሆን፤ አድማጭ ሲያጡ እርስ በርሳቸው እየተሰዳደቡ እንደሚለያየዩ እርግጠኛ በመሆን ነው። ገበያተኛ የሌለበት ጠጅ ቤት ሰካራሙ ሰራተኛው ብቻ ይሆናል ይባላልና። 

በቤተክርስቲያናችን የስደት ሲኖዶስን ለማስገባት የሚደረገው ጥድፊያ እየታየ  ሲሆን፤ ባለፈው እንደነገርናችሁ ድቁና ለማግኘት ወደ ሂውስተን ተልከው የነበሩትን ሕጻናት ለድቁና መብቃታቸውን በደብዳቤና በስልክ ያረጋገጡት የሚካኤል ካህን ይህንን ሲያደርጉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ለናንተ  መንገር አይኖርብንም። መልሱ ለሁላችሁም ግልጽ ነውና። በደብዳቤ  እውቅና  ሰጥቶ እከሌን ሹምልኝ እያሉ እኔ ገለልተኛ ነኝ ማለት ደግሞ  "አጨስኩ እንጂ አልዋጥኩትም"  የሚለውን  ያለፈ የአሜሪካ ባለስልጣን አባባል ያስታውሰናል። ይህ ቤተክርስቲያን በሬሳችን ላይ እንጂ በሕይወት እያለን ለስደት ሲኖዶስ አይሰጥም ይሉ የነበሩትን አዛውንቶች በሉ መሞቻችሁ ይኸው ተቃረበ ለማለት አንወድም፡ መሞታቸውን አንፈልግምና። ይልቁንስ ድቁና የሚሰጡት የስደቱ ሲኖዶሶች ከሆኑ ልጆቻችንን አንልክም ብለው አቋም የወሰዱትን ቤተሰቦች መረዋ በዚህ አጋጣሚ  ስም ሳይጠራ አድናቆቱን ሊገልጽ ይወዳል።    

በሌላ መንገድ ተሳዳቢዎቹ የመሳደብ መብት እንዳላቸው የአሜሪካን አገርን ሕገ መንግስትን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ሲናገሩ አድምጠናል። እንዴው አተካሬ  ላለማብዛት ልንተወው ፈለግንና አላስችል አለን። አንድ ሰው በሕግ እራስን ለመከላከል መግደል እንደሚችል ተደንግጓል ያ ማለት ግን ሰው መግደል ይቻላል ማለት አለመሆኑን ቢገነዘቡ መልካም ነው። 

ስለፍቅር የሚሰብኩ ቤተክርስቲያን ለምን ይከሰሳል የሚሉ የስደት ሲኖዶስም ደጋፊ አለውና ስለነሱ ባትናገሩ ጥሩ ነው ብለው የድርጅታቸውን ኦፊሻላዊ የአቋም መግለጫ የሚያስተጋቡ አሁንም ነገሮች በውይይት መፈታት አለባቸው የሚሉ መጣጥፎችንም ተመልክተናል። "በፍርድ ቤት ሰላም አይመጣም ማንም ቢያሸንፍ ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን"  ብለን በመረዋ ተከታታይ እትምቶቻችን የምንናገረው ስለነበረ  እንኳን ለዚህ አበቃችሁ  እንኳን እውነታው ተገለጸላችሁ ከማለት በስተቀር አባላችንን ኮረጁት  ብለን አልተናደድንም።

ለናሙና ያክል ካለፈ መረዋ  እናካፍላቸው።

........አሁንም ለማንም ይፈረድ ለማንም ሁላችንም ተሸናፎዎች ነን ብለን እናምናለን። ፍርድ ቤት ይፈርዳል ግን ለማንም ይፍረድ ለማን አንድ እንሆናለን ወይ?ነው ጥያቄው። የተፈረደለት ይፈነጥዝ ይሆናል፤ ሰላም ፍቅር መጣ ማለት ግን አይደለም። ሰላም የሚፈጠረው፤ አንድነት የሚመጣው መነጋገር ሲቻልና ልዩነቶችን በጋራ ተወያይተን መፍትሄ ስናገኝላቸው ብቻ ነው።

ሴትዬዋ እርጉዝ ነች እሚለው ላይ ከተስማማን፤ መውለዷ የግድ ነው እዛ ላይ መከራከር አያስፈልግም የሚያዋልዳት ዶክተር የሚረዳት፤ ሆስፒታል እስካለች ጊዜ ብቻ ይሆናል። ወልዳ እንዴት ማሳደግ ትችላለች እሚለው ላይ ግን የዶክተሩ ሚና አይኖርም ለማለት ነው። በዛ ላይ ሚና መጫወት የሚችሉት ቤተሰብና ዘመድ ጔደኛና የሰፈር አዛውንቶች መሆናቸውን መካድ እንዴት ይቻላል? ካልተግባባን ሌላ ችግር አለ ማለት ነው። ስለሆነም በቤተክርስቲያናችን ሰላም መውረድ የሚችለው ሁላችንም ከልህና ከቁጭት ወጥተን በመነጋገርና በመመካከር ብቻ ነው። ወንድሞችና እህቶች ይህ የእምነት ስብስብ መሆኑንም አንዘንጋ።

በሌላ እትምታችን ደግሞ በመረዋ ቁጥር  ፲፫ ።

1 ሕጉ ወደ ነበረበት መመለስ አለበት
2 አባላት ያለምንም ጥያቄ መክፈል የሚችሉትን እየከፈሉ መመዝገብ አለባቸው።
3 የቦርድ አባላት ነን ባይ አንባገነኖች ሕዝቡ ለመረጣቸው ጊዜአዊ ኮሚቴ አስርክበው መውረድ አለባቸው።
4 የሚደረገው ስብሰባ በገለልተኛ ምእመናን መመራት ይኖ ርበታል ብለን እናምናለን።

በተጨማሪም በመረዋ ቁጥር ፲ " ዝምታ በራሱ ተቃውሞ ነው" የሚለውን በከፊል እንጥቀስ።

ቤተክርስቲያናችን ወደ መፍረሱ እየተቃረበ ለመሆኑ ሁሉም የተስማማበት ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት። ይህንን መጥፎ ሂደት ለመግታተ የሚቻለው የሚከተሉት ማረሚያውች ባፋጣኝ ሲደረጉ ብቻ ነው ብሎ ያምናል።
1 ቦርዱ በጊዚያዊ ኮሚቴ ሲተካ
2 የቀድሞ አባላት ወደ አባልነታቸው እንዲመለሱ ሲፈቀድ
3 ተቀየረ የተባለው የአንባገነን ሕግ ተሽሮ ወደ ድሮው ሕግ ስንመለስ
4 ቤተክርስቲያኑ የአምልኮ እንጂ የፖለቲካ ስፍራ መሆኑ ሲቆም
5 የእምነትን ጉዳይ ካህናቱ ብቻ መምራት ሲችሉ
6 የቤተክርስቲያን ገንዘብ የሰረቁ ምህረት ሲደረግላቸው ብቻ ነው ብለን እናምናለን።
ይህ ካልሆነ ቀጣዩ ትግል በዝምታ መሆን አይችልምና ዝምታ በራሱ ተቃውሞ መሆኑ ቢገባንም ተሰብስበን በመነጋገር መፍትሄ መፍጠር አለብን በማለት ጥሪ ማድረግ እንወዳለን። "  የጥቅሱ መጨረሻ 

ይህ ታዲያ የመረዋ የቆየ  አቋም ብቻ  ሳይሆን አሁንም የምንታገልበት መርህ መሆኑን በ ድጋሜ ማስረገጥ  እንወዳለን።

ከቤተክርስቲያን ባሻገር በትላንትናው እለት 9ኛውን የኢትዮጵያ ቀን ለማክበር ሄደን ጥሩ ምሽት ማሳለፋችንን ስንመሰክር፤ የዳላስ ፎትዎርዝ አካባቢ ፍልሰታቸው ከኢትዮጵያ  የሆነ ሁሉ የሚገናኙበት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት የተጀመረው ሥራ ግቡን እንደሚመታ ከኮሚቴው አባላቱ ገለጻና  በወቅቱ ከነበረው የሕዝብ የገንዘብ ችሮታ እሽቅድምድሚያ በመነሳት ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። መረዋም የኮሚቴው ጥረት ግቡን  ይመታ  ዘንድ ሁላችንም መተባበር እንዳለብን ሊያሳስብ ይወዳል። ባንሳሳት በውቅቱ ቃል የተገባው ከ $50000 በላይ ገንዘብ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የእጥፍ እጥፍ እንደሚሆን  ጥርጥር የለንም።

እንዲሁ ካካባቢው ሳንወጣ በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በምእመናን የተቋቋመው የተባበሩት የቅዱስ ሚካኤል መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ልሳን የሆነ  ብሎግ መፈጠሩንና  ብሎጉም በጅምር ላይ መሆኑን የደረሰን ዜና ያረጋግጣል። ለብሎጉ እድገት ኮሚቴው ትብብራችሁን እንደሚጠብቅም ተነግሯል። 
 http://www.meleket4u.blogspot.com/

 እውነትን የያዘ ማሸነፉ የግድ ነው
መልካም ሳምንት።