Thursday, May 10, 2012

ማን አሸነፈ?

በቤተክርስቲያን አሸናፊ አይኖርም ብሎ  መረዋ የጻፈው ከ ፫ ዓመት በፊት ነበር። መረዋ ዛሬም ማንም አሸናፊ አይደለም ብሎ ያምናል። እንዴውም የገደለው ባሌ  የሞተው ወንድሜ የሚለውንም እንደ ምሳሌ መጠቀሙን ያስታውሳል። እንሆኝ የቤተክርስቲያናችን ውጣ ውረድ ከተጀመረ ከ ፬ ዓመት በላይ ሆኗል።
ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ይህ ሁሉ ክስ የመጣው ደግሞ ከሳሾች ገንዘብ ፈልገው አልነበረም።
ቢሆንማ  ኖሮ ካሳ በጠየቁ ነበር።
ለስልጣን ብለውም አልነበረም።
ቢሆንማ  ኖሮ ምእመን ሳይወያዩበት በቦርዱ "ጸደቀ"  የተባለው መተዳደሪያ ደንብ ለተመራጭ አስተዳዳሪዎች የፈላጭ ቆራጭ ስልጣን የሚሰጥ ነበር።
ለንብረትም አልነበረም።
ቢሆንማ  ኖሮ የንብረት ክስ ከተመሰረተ  ፍርድ ቤቱ ያገባዋልና ይወስንላችኋል ሲባል የንብረት ክስ አንመሰርትም ባላሉ ነበር።

ነገሩ የመብት ጉዳይ ሆነና ይኸው እስካሁን እያወዛገበ ይገኛል። ለስለሰብአዊ መብት እንከራከራለን የሚሉ ግለሰቦችና  ድርጅቶች መብት እንንፈግ ብለው ሲዶልቱ መክረማቸውን ያያችሁት ጉዳይ ነው ። በመብቴ  አልደራደርም ያለው አባል ከአባልነት እራሱን እያሸሸ ለመምጣቱ ደግሞ ምስክር መጥራት የሚያስፈልግ አልመሰለንም። ምስክሩ እናንተ ናችሁና።

፴ ብር ለይሁዳም አልበጀምና  ተው ሲባል ሰሚ አልነበረም። ይህ ግን ቤተክርስቲያኑን አደኸየ  እንጂ አልጠቀመም።
አቶ  ኃይሉ እጅጉ በመሰረቱት ቤተክርስቲያን አዳራሽ ለመብት ቆመሃልና  አትገባም ሲባሉ የዓይን ምስክር ነበርን። ነበራችሁ።
አቶ ሙላው ወራሽ እንደ ወረደባቸው አሉባልታና የስም ማጥፋት ዘመቻ  አገር ለቀው ይወጣሉ ብለው የጠበቁ ቢኖሩ የሚያስገርም አልነበረም።ያ ግን አልሆነም።

ደጋፊም ተቃዋሚም አሁንም አንድላይ ነን። አሁንም አንድ ላይ እያስቀደስን ነው ማለት እውነት ነው። ጸሎታችንን እኩል ይሰማል ማለት ግን አጠያያቂ ይሆናል። ትላንት ከአዳራሽ ያስወጡ የነበሩ እራሳቸው እንደወጡ ያያችሁት ነውና  መድገም አያስፈልግም።

ሰባት ጊዜ ሽማግሌ አናግረናል የሚሉት የመብት ተከራካሪዎች፡ ሰባቱንም ጊዜ ከሽማግሌዎች ጋር በአክብሮት ተወያይተን ተለያይተናል ብለው በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። በምስጋና የተለያዩት የመብት ተከራካሪዎች፣ የሚኮሩበት ጉዳይ ቢኖር ሽማግሌዎቹን ማሳመን መቻላቸው ብቻ  ሳይሆን ከመሃከላቸው ደጋፊና አብሯቸው የሚታገል ማትረፋቸው ነው። የዛሬ ሳምንት በቤተክርስቲያን የቦርድ መሰብሰቢያ  አዳራሽ በመገኘት ሁለቱም ወገኖች ታረቁ ተብሎ ሲነገር ሕዝቡ እልል ሲል ያየ ቢያለቅስ ምን ይፈረድበታል? ሁኔታው ግን ሰዓታትም ሳይቆይ  እርቅ ፈርሷል ተባለና ተቀየረ። ማን እንዳፈረሰው ደግሞ  ሽማግሌዎቹን መጠየቅ ይሻላል እንላለን።

የመብት ታጋዮቹን ደገፋችሁ በሚል የወሲብ አሉባልታ የተነዛባቸው ጠነከሩ እንጂ ሸብረክ ሲሉ አላየንም። ባልሰሩት የነፍስ ግዳይ የተወነጀሉት አሁንም እስር ቤት ገብተው አላየንም። ከመብት ተከራካሪዎቹ ቃለ አባባል እንውሰድ " እኛ የእምነትና የእውነት ድሃ  አይደለንም" የሚል ነው። ፍርድ ቤት ይለየን እንደተባለው እነሆ ፍርድ ቤት እየለየው ነው። ማሸነፍን ግን አላየንም።

 ውድ አንባብያን ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት የቦርድ አባላት ከሳሾችን ከዓመት በፊት ከቤተክርስቲያን እናባራችሁ ብለው በወሰኑባቸው ማግስት አታባርሩንም በሚል ስማቸው ተካቶ ከነበረው 28 ተባራሪዎች ውስጥ የሆኑ ምእመናን ክስ መመስረታቸው ይታወሳል። በመሆኑም የነበረውን በየጊዜው የፍርድ ቤት ውሎ መረዋ በወቅቱ የዘገበው ጉዳይ ነበርና ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሶ ሁኔታውን በመተንተን ጊዜአችሁን ከመሻማት ይቆጠባል። ነገር ግን የዛሬ ዓመት ክሱን እናቁም በማለት ከሳሾች ከደጋፊዎቻቻው ጋር በመስማማት ክሱን ቢያቆሙም ቦርዱ እስከዛሬዋ የፍርድ ሰዓት  ድረስ ለጠበቃ ያወጣንውን 89,000 ብር ይክፈሉን ሳይከፍሉን ክስ አናነሳም ብለው ሲከራረሩ ቆይ ተው ነበር። በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ዳኛው የዚህን ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ በመስጠት ገንዘብ መጠየቅ አትችሉም  ብለው ብይናቸውን ሰጥተዋል። ይልቅስ ይላሉ ዳኛው ይህንን የእምነት ጉዳይ በቤተክርስቲያን ደንብ በውስጥ ለመፍታት ብትሞክሩ መልካም ነው። በማለት ምክራዊ ብይንም ሰጥተዋል። ከሳሾች ለቦርድ አባላት ፩ ብር (አንድ ብር) እንዲከፍሉ እንደተወሰነባቸው ደግሞ የነገሩን የመብት ተከራካሪው ቡድን አባል ለዚህ ምእመናንን እርዳታ  አንጠይቅም በማለት እየሳቁ ነበር።

ይህ ቦርዶቹ የሚጠይቁት የጠበቃ  ገንዘብ  ባለፈው አወጣን የሚሉትን ከ140,00 ብር በላይ የሆነውን አያጠቃልልም። በቅርቡ መረዋ የደረሰውን የቦርድ አባላት ባለፈው ፩ ዓመት ተኩል ለጠበቃ ከፈልን ብለው ፍርድ ቤት ያቀረቡትን የ 89,000 የወጭ ሰንጠረዥና ከሳሾች በሁለት ዓመት ለጠበቃ  ከፈልን የሚሉትን 21,593 ብር  የወጭ ሰንጠረዥ  ያጠቃለለ  በገጹ ላይ እንደሚያትም ቃል ይገባል። ከየትም ይሁን  ከየት ማንም ከፈለው ማ ከፋዩ የቤተክርስቲያናችን አባላት ያዋጡት ገንዘብ ነውና።  ለአባላት ይጠቅም ዘንድ በእጃችን ያለውን ማናቸውንም መረጃ እንዳስፈላጊነቱ ለማሳወቅም እንደምንጥር ሰንናገር በእርግጠኝነት ነው።

ለመንፈሳዊ አባቶች ያለንን አድናቆትና አክብሮት እየገለጽን የኛን ወገን ዜና ማሰራጫ ሌላ መድረክ ስለሌለን ይህንን የመተንፈሻ ገጽ መጠቀማችንን እንዲረዱልን እንወዳለን።

ውድ ምእመናን ከኛ ወገን የሚተላለፍ መልእክት አለን 

ከጎናችን ሆናችሁ ለከረማችሁ፣  ለእውነት ስለቆማችሁ፣ ለተሰደባችሁ፣ ለተባረራችሁ፣ ሁሉ ሚካኤል ዋጋችሁን ይክፈላችሁ እንላለን። እኛና  እናንተ  እንቅልፍ ተኝተን እናድራለን እንቅልፍ ያጡ ሌሎች ናቸው።
እኛና እናንተ  በእሳት ተፈትነን የሕይወት ጓደኛ ሆነናል።
በየወንዙ የሚማማሉት ሌሎች ናቸው።
እኛ ትናንትናም ዛሬም ትክክል ነበርን፣ ለሰላምና ለአንድነት ታግለናል።
አቋማቸውን እንደጥላ  የማያምኑት ሌሎች ናቸው። 

ሚካኤል ፍርድ እየሰጠ ነው። ለክፋት በቆመው ላይ የዘላለም ፍርድ ይስጥ። 

እኛ ማንንም አንጠላም ለሚጠሉን እንጸልያለን።
በማንም ላይ አንፈርድም፣ በሚፈርዱ እናዝናለን።
ማንም ከስራ  እንዲወጣ አንፈልግም፣ ይህን ለሚያስቡ ሱባኤ  እንገባለን።
በማስፈራራት አንፈራም ከጥል ይልቅ ለፍቅር እንሰግዳለን።
ቤተክርስቲያናችን እንደሚኖር እኛ ግን እንደምናልፍ እናምናለን።
ቤተክርስቲያን የአባቶችና የክርስቲያን ስብስብ እንጂ ሕንጻና ገንዘቡ ነው ብለን ለደቂቃም አናምንም።  

ለሰላም እንጸልይ።

እንኳን ደስ አለን።