Wednesday, March 27, 2013

ማገርና ወራጅ የሌለው ቤት ጣራው መደርመሱ የግድ ነው።

እስከዛሬ የምናውቀው ለተሰደደ የሚጸልይ መንፈሳዊ አባት እንጂ የሚሰደድ አባት አልነበረምና ለተሰደዱት ጸልዩላቸው። የፈጣሪን ዘላለማዊ ግዛት ለማየት የሚጓጓ እንጂ ዙፋነ ሲመትን ካልያዝኩ ሃይማኖቱ ይፍረስ የሚል አባት ካያችሁ ይቅር በላቸው ብላችሁ ለምኑላቸው። "የመምጫዬ ቀን አይታወቅም ብሏልና  ንስሃ ግቡ" ብለው በሚያስተምሩበት ልሳናቸው፣ ካልገዛን ይዝጋን፣ የሚሉ ስታዩ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱላቸው። እኛ ፭ ኪሎ  እስክንደርስ ቤተክርስቲያኑ ይፍረስ፡ የሚሉ ከሰማችሁ ተዝካር በቁም አውጡላቸው።

ውድ የመረዋ እድምተኞች፣ የመብት መጣስን ተቃውማችሁ በሰለጠነው ዓለም ተቀምጠን መረገጥን፣ በሰላማዊ አገር እየኖርን መታፈንን፣ ገዴታ  እንጂ መብት የሌለበትን አባልነት ላለመቀበል አሻፈረን ብላችሁ እስካሁን የታገላችሁትን ሁሉ ዛሬ መረዋ እንኳን ደስ ያላችሁ ሊል ይወዳል። የዛሬ ፭ ዓመት ይህ ይሆናል ስትሉ፣ ስንል የሚሰማው ጥቂት ነበርና። ተጀምሮ  እስኪያልቅ ግን ያላችሁት፣ የተናገርነው፡ መሬት ላይ ጠብ አላለም። ዛሬ ይዋሹ የነበሩት የተጋለጡበት፡ ለመብት የቆሙት ደግሞ በኩራት የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሆኗል። ባለፈው ቅዳሜ የሚካኤል  ቤተክርስቲያ አባላት የስደት ሲኖዶስን መረጡ ሲባል ሰምተው የተናደዱ ቢኖሩ ትላንት ስንናገር አይሆንም፣ አይደረግም፣ ይሉ የነበሩ ግለሰቦች ብቻ ናቸው። ይህ ከሆነ "ቤቴን ወለድ አግድ አሲዤም ቢሆን ወደ  ሕግ እሄዳለሁ" ያሉት ግለሰብ ደላላ ሲያጠያይቁም አላየንም። ይልቅስ ያስተዋልንውን ሌላ ቁም ነገር እናጫውታችሁ። እነዳዊት አለማየሁን አናስገባም እያሉ ያኮረፉ ጓዶቻቸውን የስድስት ወር የአባልነት ጊዜ  እያራዘሙ ሲመልሱ ማየታችን ነው። ነገሩ የፖለቲካ ነው ካሉም ወሳኞቹ ባለስልጣናት እነዳዊትም እነሱ የማይደርሱበት የትግል ገድል እንደ ነበራቸው መናገር የግድ ይሏል። ሃይማኖተኛ የሆኑትን እየመረጥን ነው ካሉም መስፈርቱ ሌላ ካልሆነ ዳዊትን በዚህ የሚፈትኑት አልመሰለንም። ልንል የፈለግነው እምነትና ውሸት እየተጠላለፈ  መጣ ለማለት ነው። ሌሎች ስሞች መደርደር ቀላል ነው። የዛሬ ፬ ዓመት  የመሃበረ ቅዱሳን አባል ነህ ብለው የወነጀሉት ግለሰብ ምን ማለታቸው እንደሆነ ተጨንቆ እኔ ነኝ ቅዱሱ? ኧረ ባባቶች መሳለቅ ነው ማለቱን ሰምተን ነበር። በወቅቱ ውሸት መጥፎ  ነው በተለይ ውሸቱ ከቤተክርስቲያን ሲሆን እጅጉን ይዘገንናል ብለን መጻፋችንም ትዝ ይለናል።


እስቲ ዛሬ ልብ በሉ  ከ 4 ዓመት በፊት ስለባለስልጣኖቹ እቅድ ስንናገር ትንቢት ተናጋሪዎች ሆነን ሳይሆን አካሄዶችን በመመልከት የደረስንበት የግምጋሜ ውጤት ነበር። ያልነው ባይደርስ ለቤተክርስቲያን መልካም ነበር የፈራነው ግን ሆነ። እነሆኝ የስደት ሲኖዶስ ቤተክርስቲያኑን ለመረከብ ቻለ። እንዴው ለምስክርነት December 18 2009 መረዋ ቁጥር ፭ የጻፈውን ቀንጨብ አድርገን በድጋሜ ዛሬ እናስነብባችሁ። እንዲህ ይል ነበር...........

በግል እንደታዘብነውና ሂደቱን እንደተከታተልነው። ሕጉን ለምን በክስ መሃል ለመቀየር አስፈለገ ለሚለው? የራሳችን መልስ የሚከተለው ይሆናል።
1 የማይፈልጉትን አባላት ለማባረር።
2 አዲስ የሚገቡ አባላትን ለማጣራት ለማበጠር።
3 አባላት ተቀበሉትም አልተቀበሉት የራሳቸውን ውሳኔ በመሰላቸውና ከቦርዱ ጥቅም በመነሳት ለመወሰን።
4 የእምነትን ጉዳይ አስመልክቶ ቄሱ ምን መሰበክ እንዳለበትና እንደሌለበት ለመንገር።
5 አባላት ለመመዝገብ ሲመጡ እንደ አፓርትመንት የማመልከቻ ማስከፈል። አባልነታቸውን ተቀባይነት አገኘም አላገኘ የከፈሉት እንዳይመለስ ማድረግ።
6 ገለልተኛነትን በመስበክ የሲኖዶስን ቦታ መተካት። ነው ብሎ ለማለት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም።

አሁንም ያላችሁት አልተፈጸመም የሚሉ ካሉ የምንጨምረው ይኖረናል። ዛሬ አንጋፋ  የቤተክርስቲያን አባቶች ተባረዋል ከ 1150 አባላት በላይ የነበረው ቤተክርስቲያን ዛሬ 279 አባላት ብቻ እንዳለው የሚሰማ  ሰው ቤተክርስቲያኑ አይወድቁ አወዳደቅ እየወደቀ  እንዳለ  የሚስማማ  ይመስለናል። ቀሳውስት እውነትን ስለሰበኩ ሲባረሩ ስናይ እግዚኦ ብለን ነበር። አባቶች ካገር እንዲባረሩ ለኢምግሬሽን ደብዳቤ  ሲጻፍ ስናይ ኧረ  በክርስቶስ ብለን ነበር። ደብዳቤውን የሚጽፉት ደግሞ  የቤተክርስቲያን ባለስልጣናት ብሎም እራሳቸው በስደተኝነት መኖሪያ  ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን ስናስብ የበለጠ አዝነን ነበር፡፡ አባላት ለአባልነትም ከባላቸው ከሚስቶቻቸው እንዲለዩና እንዲመዘገቡ ሲደረግ እግዚኦ ብለናል። የከፈሉበት ሳይሆኑ የተሾሙበት ፈላጭ ቆራጭ ሲሆኑም አስተውለናል። ይህ የትላንት ሂደት ነበር። ዛሬ ጨዋታው መቀየሩን አይታችኋል።
የእምነቱን መንገድ ወደ  ፖለቲካ  የወሰዱት የመንግስት ተቃዋሚ ነን ባዮች ትልቅ ስህተት እየሰሩ ነው።
የቆሰለ  ዝንጀሮ ወደ መንጋው ሲጠጋ የሚድን ይመስለዋል ሲቀርብ ግን ቁስሉን ሁሉም እየላሱበት ይብስና  ይሞታል እንዲሉ ፣ የባሌ  መንገድ በጋርላንድ በኩል  የሚመሰላቸው ፖለቲከኞች  ካሉ ጊዜ  ይስጠን እንጂ  መንገድ መሪ አጥተው በጎዳና ሲንገላጀጁ ለማየት ጊዜ  እንደማይወስጅብን እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን። ትላንት እንዳልነው ጆሮ ቆራጭ መጣብህ እየተባለ ያደገ  ሕፃን አድጎ ቀልዳችሁን ተው እንደሚል ሁሉ አሁንም ቤተክርስቲያንህን ኢሕአደግ ሊወስድብህ ነው ያሉት ምእመን የወሰደበት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነኝ ባዩ እንጂ ኢህአደግ አለመሆኑን እያየው ነው። በሬ ያረደ ሰው በጎረቤት ሙዳ ስጋ  ሲጣላ  አላየንምና። ዱላ  ያለው ጠመንጃ ይመኛል ሲባል እንጂ ጠመንጃ  ያለው ዱላ  ይመኛል ሲባልም አልሰማንም ለማለት ነው።

ዛሬ ምእረፉ ተዘጋ  ለሚሉ የምስራች ወሬ አለን። ባለፉት ዓመታት የንብረት ጥያቄ  ክስ ይደረግ ሲባል ስንቃወም መቆየታችን እውነት ነው። ይህ ደግሞ መለያየትን እንዳያመጣ በመፍራት ነበር። የከሳሾችም ሆነ  የኛ  ፍላጎት መብትና እምነትን ከመለየቱ ላይ ነበርና። ዛሬ  ግን የእምነት ውሳኔ  መወሰን ተችሎ  ይሆናል፣ ንብረትን መንጠቅ ግን አይቻልም። አባላትን ማባረር ካህንን ማስጠንቀቂያ  መስጠት ከስራ  ማገድ ችለው ይሆናል በሌላው ገንዘብ መወሰን ግን አይቻልም። በእምነት አንግባ ያለው ዳኛም ከንብረት ጥያቄ  ሊሸሽ አይችልም። ከዳኛው ለመጥቀስ "በመጨረሻ ተከፋፍላችሁ እንደምትበተኑ ይታነኛል" ሲል የቤተክርስቲያኑ ጠበቃ  እሱን እኔም እላለሁ ብሎ  ነበር። ያ ቀን እንዲመጣ የጣሩት ባለስልጣናት ምኞታቸው ሊፈጸም መቃረቡን ታዲያ  ቀስ ብለን ሹክ እንበላቸው።
ክርስቶስ የቄሳርን ለቄሳር አለ እንጂ የቄሳርን ለመቅደስ አላለም። የተገፉትና  የተወረወሩት ምእመናን ወደ  ባህር ተወርውሮ ካሳነባሪ አፍ ገብቶ  እንደወጣው.................... ተመልሰው ነፍስ እንደሚዘሩ እርግጠኞች ነን።
የኛ ትግል ለምእመን መብት ነበር እንጂ ለግንብና  ለገንዘብ አልነበረም። አታመልኩም ካሉ: አትናገሩም ካሉ በጉልበት እንነጥቃለን ካሉ፣ እነሱ ያልከፈሉበት ገንዘብ ይዘው ቢከራከሩም ሕዝብ የለፋበትን፣ እናባርራለን ያሏቸውን፣ ያባረሯቸውን አባላት ድርሻ  የመስጠት ግን ግድ ይላል። እዚህ መድረሱ ያሳዝነናል። ይህ ደግሞ  በኛ ፍላጎት የተደረገ  እንዳልሆነ  ይታወቅ። ትንቢት መናገር ባትሉን ይህ እንደሚሆን ግን መተንበይ እንወዳለን። "ሲመሽ ስገዱልኝ ያለ  ሽፍታ ወጋጋን ሲቀድ  ይደበቃል።"

የሚካኤል ፈቃድ ይታከልበት

መልካሙን ለሁላችን።