Saturday, January 16, 2010

የሰሞኑ ውይይት? ቁጥር ፰

አቶ አያሌው፦ መምሬና ቀሲስ ልዩነቱ ምንድነው?
አቶ ከበደ፦ መምሬ ከቅስና በፊት የሚሰጥ ሹመት ነው።
ዲያቆን ብሩክ፦ ኧረ በወላዲቷ። መምሬም ቀሲስም አንድ ነው። አስተማሪና መምህር እንደማለት መሆኑ ነው ወንድሞቼ አንሳሳት።
አቶ ከበደ፦ታዲያ ቀሲስ መስፍንና መምሬ ዬሃንስ አንድ ናቸው ማለት ነው?
ዲያቆን ሲራክ፦አዎ አንድ ናቸው። ግን ቄስ ሁሉ እኩል እውቀት አለው ማለት አይደለም። ባገራችን "መምሬ እከሌ እኮ ሰሞነኛ ቄስ ነው" ከተባለ ከመቀደስ በስተቀር ምንም እውቀት የሌለው ነው፤ ወይንም መሪ ጌታ አይደለም ማለታቸው ነበር። ታዲያ መምሬው ሆኑ ልጃቸው የሰሞነኛ ቄሶች ናቸው ቢባል እውነት ነው። እንዴውም ወጣቱ ቄስ ቅስናውን ያገኘው ከተወገዘ ጳጳስ ነው በሚል ነፍሳቸውን ይማረውና በወቅቱ ሊቀ መንበር የነበሩት ሻለቃ ክፍሌ "እኔ እያለሁ አንተ በቅስና መቅደስ ውስጥ ገብተህ አትቀድስም" ይሉ እንደነበር ብዙዎች ዛሬም ይናገራሉ። ወደ ጥያቄው እንመለስና መቀደስ የሚችለው ሁሉም ቄስ ሆኖ ሳለ፤ አዲስና ብሉይን አውቆ ማስተማር የሚችለው ግን ጥቂት ይሆናል። ከዚህ አልፎ አቌቌምና ቅኔ፧ ድጔና ፆመ ድጔ ............... እያለ የእውቀቱ መመዘኛ እየሰፋ ይሄዳል። ምን አለፋህ ሁሉም ዶክተር ቀዶ መጠገን አይችልም እንደምንለው አይነት ነው።
አቶ አያሌው፦ታዲያ ለምን ቄስ መስፍን ይባረርልን? መላከ ሳህል ከቤተክርስቲያን ይወገዱልን? ብለው የሚጨቃጨቁት?
አባ መቻል፦ይህ የቀድሞ ፖለቲከኞች ነን ባዮች ጥያቄ ነው። እነዚህ ከኋላ ሆነው ነገር የሚገምዱ ፖለቲከኛ ነበርን ባዮች ሰላም ከተፈጠረ ታመው የሚያድሩ አይነት ናቸው። በቀድሞው የደርግ ትግል ዘመን በሰሜን አሜሪካ የተማሪዎች ማህበር ውስጥ ሆኜ በቦስተን ስታገል ነበር የሚሉትን ግለሰብ ያጠቃልላል። መዋሸት ደግሞ የከረመባቸው ናቸውና ተዋቸው እየተባሉ የሰነበቱ ናቸው። እሩቅ ሳትሄድ እዚሁ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉ የቀድሞ የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማህበር ESUNA አባላት የነበሩ ግለሰቦችን ብትጠይቃቸው ግለሰቡ በተማሪዎች ትግል ውስጥ እንዳላለፉ ይነግሩሃል። የቦስተኑ ታሪክ ሌላ ነው። ካስፈለገ በሰፊው መተረክ ይቻላል። ታዲያ በሕይወታቸው ጥሩ እንደመስራት እራሳቸው የቦርድ ተመራጭ ሆነው "እውቀት አለኝ የትግል ተመክሮ አለኝ" የሚሉትን በሥራ እንደመተግበር ቤተክርስቲያንን ለምን እንደሚያምሱ መመለስ ያለባቸው እራሳቸው ይሆናሉ። ችግሩ ደግሞ በተፈጥሮ የበታች ብቻ እንጂ የእውቀት የበላይ እንዲኖር የማይፈልጉ ግለሰብ በመሆናቸውም ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ ሊቀ መንበሩን እየወተወቱ የሰነበቱትን ቄስ እየጠመዘዙ፡ ለመጥፎ መሰለፍን እንደምርቃት የተቀበሉ በህይወታቸው ምንም ሳይሰሩ በመቆየታቸው ሌላው በሚሰራው በቅናት የሚቃጠሉ ግለሰብ ናቸው ብዬ አምናለሁ።
አቶ አያሌው፦ እውነት ቄሶቹን ያባርራሉ ብላችሁ ታምናላችሁ?
አባ መቻል፦ይህ እራሱን የቻለ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ነገሩን በመለወጥ ቀሲስ መስፍንን በጀት የለንም ብለው ለመቀነስ እንዳሰቡ የተረጋገጠ መረጃ አለ። መላከ ሳህልን ለጊዜው አባላትን ለማረጋጋት እናቆያቸው እያሉ መሆኑንንም ሰምተናል። ቀሪ ሁለት ቄሶችን አስመልክቶ ግን መግባባት አለ። በመጀመሪያ ከቴክሳስ የመንግስት ድጎማ ካህኑ አባት እንዲያገኙ ደሞዛቸው ለሁለት ተከፍሎ ለካህን ልጃቸው እንዲሰጥ ተደርጎ ያሉ በመሆኑ የመንግስት ድርጅቶችን ለማታለል በተደረገው መረብ ውስጥ ያለ ጉዳይ በመሆኑ ቤተክርሰቲያኑን ሊያስጠይቀው ስለሚችል ያልተቀጠረው ወጣት ካህን እንደተቀጠረ ተቆጥሮ መሰንበቱ የማይቀር ነው።
አቶ አያሌው፦ቄሱ መንግስትን እያታለሉ ነው ለዚህም ቤተክርስቲያናችን ለወንጀሉ ተባባሪ ነው የምትለን?
አባ መቻል፦ አዎ ይህንን የማያውቅ ሰው አለ ብለህ ነው? ሁሉም ያውቃል ግን ለመናገር ፍራቻ አለበት።
አቶ ከበደ፦ አዲሱን የቦርድ ምርጫ እንዴት ታየዋለህ?
አባ መቻል፦ ምን እሚታይ አለበት የፖለቲካ ስብስብ እየሆነ ነው። አቶ አበበ የአገራችን ድንበር ተወሰዶ ለሱዳን ተሰጥቷልና እናስቁም የሚለው ኮሚቴ አባል ነኝ ባይና በፖለቲካ ፓልቶኮች የኢኮኖሚ ጠበብት ተብለው ይናገሩ የነበሩ ግለሰብ ዛሬ የቤተክርስቲያን ተመራጭ እጩ ሆነው መቅረባቸውን ያሰተዋለ ግለሰብ ያለውን ላካፍልህ " እንጀራ ስለሸጠ የኢኮኖሚ ጠበብት ነኝ ብሎ ባደባባይ ፓልቶክ ላይ የቀረበ ፖለቲከኛ ግለሰብ ዛሬ ካህን ነኝ ቢልስ ምን ይገርማል" ብሎ ነበር የደመደመው። ሌሎቹ የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። ልጃቸውን ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እየላኩ የኛን ልጆች እገስጣለሁ የሚሉት ወይዘሮ ሰሎሜ ጭምር ጥረታቸው እየተሳካ እየመጣ መሆኑን ታያለህ። ስልጣናቸውን በቅርቡ የሚነጠቁት ሊቀመንበር ኮሎኔል አጥናፉን ይመስሉኛል። የመንግስቱ ኃይለማርያምን የአሰራር ጥበብ የተካኑት ደግሞ የቦርዱ ዶክተር ናቸው።
አቶ አያሌው፦ አሁን ገባኝ አቶ አበራ ሃምሳ አለቃ ለገሰ መሆኑ ነው። ሌላ ያልተነሳ ነገር አለ? ሲኖዶስና የስደት ሲኖዶስ ምንድነው? ለግንዛቤ ያክል ባውቀውም እንደገና አስረዳኝ።
ዲያቆን ሲራክ፦ጥያቄው ለኔ ይመስላል? ሲኖዶስ የኦርቶዶክስ እምነታችን የበላይ አካል ማለት ነው። ሲኖዶስ እንደ ፖለቲከኞች የፓርቲ አወቃቀር ብንወስደው የማእከላዊ ኮሚቴ አይነት ማለት ነው። በውስጡ ጳጳሳት ያሉበት የሃይማኖታችን የበላይ ኮሚቴ ይሆንና ኮሚቴው ከመሃከሉ ሊቀመንበር ይመርጣል ተመራጩ ፓትርያርክ ሆኖ ይሰየማል ማለት ነው። ታዲያ የቀድሞው ፓትርያርክ "ታምሜያለሁና በቃኝ" ብለው ካገር ስለወጡ አባ ጳውሎስ በምርጫ ፓትርያርክ ሆነው ተሰየሙ። በነገራችን ላይ የቀድሞው ፓትርያርክ አሜሪካ በስደት ከመጡ በኋላ በስደት ቤታቸው የድሮውን ስምና ስልጣን በመፈለግ የስደት ሲኖዶስ ይቌቌም ብለው በሰሜን አሜሪካ ሌላ ሲኖዶስ እንዲቌቌም አደረጉ ማለት ነው።
ወይዘሮ ሰላማዊት፦አባ ጳውሎስ ዘረኛ ናቸው እየተባለ ትግሬነታቸው እየጎላ ከኢህአደግ ጋር ያላቸው እስስርና መመሳጠር እየተነገረ መንግስት እንደሾማቸው ለምን ይወራል ታዲያ?
ዲያቆን ሲራክ፦ ካቅሜ በላይ የከበደ ጥያቄ እየጠየቃችሁ እኔንም ኃጥያት ልታናግሩኝ ነው። የሆነ ሆኖ፤ በአገራችን ታሪክ ጳጳስ መሰየም የተጀመረው (ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ለማለት ነው) በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነበር። ከዚያ በፊት ጳጳሳት የሚላክልን ከግብጽ ከአለክሳንድርያ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ጃንሆይ ያቌቌሙት ሲኖዶስ የእሳቸውን ስልጣን እሚቃረን ጳጳስ ስልጣን ላይ አላወጣም። ደርግ ስልጣን ላይ ሲወጣም ጭቁን መነኩሴ ፈልጉልኝ ብሎ ሕዝባዊ ለማድረግ፡ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ መነኩሴ አስፈልጎ ማስመረጡ እሙን ነው። ደርግ ይህንን ሲያደግ ለኦርቶዶክስ አስቦ ወይንም ሃይማኖት ኖሮት አልነበረም። በመካከሉም የጎንደር የኢሰፓ አንደኛ ፀሐፊ በነበረው በገዛኸኝ ወርቄ አቅራቢነት አቡነ መርቆሪዎስ የጎንደር ክፍለሃገር ጳጳስ ስለነበሩና "ሞቴም ሽረቴም ከዚህ መንግሥት ጋር ነው" በማለታቸው ከመንግስቱ ኃይለማርያም ፊት ቀርበው ቃል ገብተው ለመመረጣቸው የዐይንና የጆሮ ምስክሮች እዚህም ዳላስ ይገኛሉ። ከዚህ በመነሳት መንግሥት የሚደግፊውን ጳጳስ አያስመርጥም የሚል ይገኛል ብዬ አላምንም። ለነገሩማ በነፍስ ግድያ የተካነው ሻለቃ መላኩ ተፈራ የደብረታቦር ልጅ መሆኑን አትዘንጋ ያውም የፋርጣ ተወላጅ። ታዲያ የስደት ሲኖዶስ የሚሉት ጳጳሳትም ሆኑ እዚህ የሚያምሱን አሁን ለቦርድ እጩነት የቀረቡትም አቶ ሙሉአለም ጭምር እንዲሁ የፋርጣ ተወላጅ መሆናቸውን ታውቅ ነበር? የመላኩ ዘመድም እንደሆኑ ይነገራል። ሻለቃው ጅቡቲ ሸሽተው ወጥተው በነበረበት ሰዓት ወደ አሜሪካ ለማሰወጣት እዚህ የተደረገውን ጥረትም ሰዎች እስካሁን ያወጉታል። ደግነቱ ኢህአደግ ጠልፎ በወህኒ ከተታቸው። ዛሬ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው የቀይ ሽብር ወንጀለኞች አንዱ እኝሁ ሻለቃ ናቸው። ይህን የማነሳልህ በአገር ልጅነት ሁሉንም ለመወንጀል ሳይሆን ግንኝነቱን ተከታትለህ እንድታውቅ ለማድረግ ነው። የስደት ሲኖዶሱ የፋርጤ ስብስብ ለመሆኑ ስለማይካድም ነው። አንተ በዘር እየተደራጀህና እየተሰባሰብክ እንዴት ሌላውን ትወነጅላለህ ብሎ ለማለትም ያክል ነው።
አቶ ከበደ፦ዲያቆን የሚለው እውነት ነው። ነገር ግን ፍትሓነገሥቱ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም ይላልና ነው የስደቱ ሲኖዶስ አሁንም ስልጣኑ የእኔ ነው የሚለው። ይህንን እነዲያቆን አይነግሩህም። ለምን መሃበረ ቅዱሳንን በመደገፉ። መሃበረ ቅዱሳን ደግሞ በአባ ጳውሎስ የተቌቌመ የጠረባ ቡድን ነው።
ዲያቆን ሲራክ፦ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ። የተናገርከው የእውነትም የሃሰት ድብልቅ ነው። እርግጥ ነው ፍትሐነገስቱ ጳጳስ በሕይወት እያለ ሌላ ጳጳስ አይሾምም ይላል።ንጉሥ እያለ ሌላ ንጉሥ አይነግስም እንደሚለው ሁሉ። ደርግ ስልጣን የያዘው ንጉሱ ሞተው አይደለም። ደርግ የመጀመሪያውን ጳጳስ ሲሾም በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አቡነ ቴዎፍሎስ በእስር ቤት እነደነበሩ አትዘንጋ። ፍትሐ ነገሥቱ አንድም ቦታ ሞት የፈራ መነኩሴ ይሰደድ አይልም። መነኮሰ ማለት እኮ ሞተ ማለት ነው። ታዲያ የሞተ መነኩሴ እንዴት ይሰደዳል። አመመኝ አልቻልኩም ካለ ግን መብቱ ይመስለኛል። ያላመመውን ታምሜአለሁ ካለ ደግሞ ዋሸ ማለት ነው። ታዲያ መነኩሴ ይዋሻል? ለውይይትም አይመች ነገር። መሃበረ ቅዱሳንን አስምልክቶ የተናገርከው ግን ይቅርታ አድርግልኝ ውሸት ነው። መሃበረ ቅዱሳንን ያቌቌሙት አባ ጳውሎስ ሳይሆኑ ብጹእ አባታችን አቡነ ጎርጎሪዎስ የሸዋ ክፍለ ሃገር ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ስሙን የሰጡአቸው ደግሞ አቡነ ገብርኤል እንደነበሩ ይነገራል። መሃበሩ የጠረባ ቡድን ሳይሆን ለሃይማኖት መስፋፋት ለኦርቶዶክስ እምነት መጠናከር የተቌቌመ ድርጅት መሆኑን ብትናገር የሚሰራውን ስራዎች አመስግነህ ድክመቱን ብትጠቁም ልቀብልህ እንችል ነበር። የሚሰራ ይሳሳታልና። ያልሆነ ስም መስጠቱ ግን አንተንም ትዝብት ላይ ይጥልሃል። መሃበሩ አባቶችን እንደአባትነት ተቀብሎ ስህተቶች መታረም አለባቸው በማለት በውስጥም የሚታገል ድርጅት ነው።
ወይዘሮ ሰላማዊት፦ዲያቆን ከጀመርን እንጨርሰው የቤተክርስቲያናችን እጣ ምን ይመስልሃል?
ዲያቆን፦ እሱን ለፖለቲከኞቹ ልተውላቸው። የእምነት ሳይሆን ችግሩ የፖለቲካ ነውና።