የፈረንጁ ብቻ አይደለም የአበሻውም ገና ማለፉ እሙን ነው። ያላለፈውና ገና እያናወጠን ያለው የቤተክርስቲያናችን ችግር ግን እያገረሸበት ለመሆኑ ምስክሮቹ የቦርድ አባላት ይሆናሉ ብለን እናምናለን። እንደተለመደው ክሱ ቀጥሏል ብለው በፊታችን እሑድ እንደሚናገሩ መጠርጠራችን አልቀረም። እነሱ ከመናገራቸው በፊት መናገር ደግሞ ትንቢተኛነት ስለሚያስመስል ከመናገር እንቆጠባለን። ለመንደርደሪያ ግን ቦርዱ ከሳሾችን ከቤተክርስቲያን ላንዴም ለሁሌም ማባረር አለብን ብለው እየተወያዩ ለመሆኑ ግን ተጨባጭ መረጃ እየደረሰን መሆኑን ሳንነግራችሁ ብናልፍ በሌሎች የምንጠላውን ውሸት መለማመድ ይሆናል ብለን እንፈራለን። ሰዎችን በማቅረብ እንጂ በማባረር ሰላም ይመጣል ብለን እንደማናምን መናገር ደግሞ ክርስቲያናዊ ብሎም መብታዊ ግዴታ ነው ብለንም እንቀበላለን። ወንድሞችና እህቶች። ቦርዱ ሕጉን ለመቀየር የተነሳሳው " የተጀመረውን ክስ ለማክሸፍ በማሰብ ብቻ ነው" ብለው ድጋፍ ሰጥተናል የሚሉት ምእመናን ማወቅ ያለባቸው ጉዳይ ቢኖር ቤተክርስቲያን የእምነት እንጂ የፖለቲካ መድረክ አለመሆኑን ነው። ለእውነት ቆሞ መታገል እንጂ በውሸት ማመን እንዴት ክርስቲያናዊ ወይም ሃቅ ሊባል ይቻላል? መነሻው ምንም ይሁን ምን ወሸት ውሸት ነው። ፈረንጆች እንደ ዳክዬ ከጮኸ እንደ ዳክዬ ከተንቀሳቀሰ፡ እንደ ዳክዬ ላባውን ካራገፈ፡ አትጠራጠር ዳክዬ ነው ይላሉ። ለእውነት ያልቆመ ካህን ስለ እውነት ማስተማር እንደሚከብደው ሁሉ የማያምን ሰው ስለ እምነት መመስከር ቢከብደው መገረም የለብንም። መረዋ በመደጋገም በዚህ የቤተክርስቲያን ክርክር ሁላችንም ተሸናፊዎች እንጂ አሸናፊዎች አንሆንም ብለን በመደጋገም መናገራችን ይታወሳል። ይህንን አቌም የያዝነው በፍርሃት ሳይሆን የታየን እውነታ ስለሆነ ብቻ ነው። አሁንም ከዚህ ንቅንቅ አንልም። የአስመራጭ ኮሚቴው የሚጠቆሙ አባላት አጥቶ መቸገሩን እያየን በሁለት አባላት ምርጫ ብቻ አንድን ግለሰብ የቦርድ አባል እናደርጋለን ብሎ መነሳት ለዳላስ ምእመናን ስድብ ካልሆነ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ተቸግረናል። ስለሆነም መረዋ ከተላንቱ በተለየ መንገድ አቌም ለመውሰድ እየተገደደ ነው። ቦርዱና የቦርዱን ስራ አወዳሾች በሰከነ መንፈስ እንደገና እራሳቸውን መገምገም አለባቸው እንላለን። በቆየ የፖለቲካ ምስክርነት እንኴን የመኤሶን ከደርግ መሰለፍ በወቅቱ ጠቅሞ ሊሆን ይችላል፡ በመጨረሻ ሰለባ ከመሆን እንዳልዳነ ግን ያየነው ሃቅ ነው። የሕጉን አንቀጽ 11.2 ሳንቀይር የቦርዱን ወንበር አንለቅም ያሉት የቦርድ አባላት እኛ ከወረድን በኋላ ቦርዱ ሌላ ሕግ እንዳያወጣ ለመቆጣጠር እንዲያስችለን ነው ማለታቸውን ስንሰማ አልሳቅንም አዘንን እንጂ። ትክክል እንዳልነበሩ ልቦናቸው ያውቀው እንደነበረ እየመሰከሩ በመሆኑ። ለዚህም ነበር መረዋ ዛሬ የሚወጣው ሕግ ነገ ከስልጣን ሲወረድ እነሱኑ ሊያጠቃ እንደሚችል ቀደም ብለን የተናገርነው። እናቶችና አባቶች ለካ እውነት ትንቢተኛ ያደርጋል። "ዘረኛ ሆነው ሌላውን ዘረኛ የሚሉ ደካሞች ናቸው" ያለን አንድ ግለሰብ ለምን እንዲህ እንዳለ ስንጠይቀው "ዘረኝነት ከመሃይምነት የሚመጣ ብቻ ሳይሆን የደካማ ሃሳብና እምነት መጠለያ ዳስ ነው በሚል ነው" ብሎን አረፈ። ይህንን ቤተክርስቲያን ለማዳን ወደነበረበት ለመመለስ የሚታየን አማራጭ አንድ ብቻ ነው። ይኸውም ችግራችን ምንድነው? ብሎ ከማንኛውም ያገባኛል ከሚል ግለሰብ ጋር በመወያየት ብቻ ነው። በውይይት አይፈታም የሚሉ በኛ እምነት አንድም እውነት የሚያስፈራቸው፤ ካልሆነም በምእመናን እምነት የሌላቸው፤ ካልሆነም የሚደብቁት ያላቸውና፤ ለወደፊቱ የተንኮል ይፋ ያልሆነ እቅድ ያላቸው ብቻ ናቸው። ቤተክርስቲያኑን ለአባ ጳውሎስ አሳልፈው ሊሰጡ ነው የሚሉት ግለሰቦች በተዘዋዋሪ ምእመናን ምንም የማያውቁ የሚነዱ ግለሰቦች ናቸው ብለው እየተሳደቡ መሆኑን ይዘነጋሉ። ምእመን ካልፈቀደ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ካመንን የሚያስፈራ ምንም ነገር አይኖርም ማለት ነው። ወደ 1000 ተጠግቶ የነበረው የቤተክርስቲያን አባል ከመቶ በታች ሲወርድ ካላስፈራ ያላስፈራቸው ሰዎች እቅድ ምን ይሆን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል። ክፍያ ያቃታቸውን አባላት የሚያጠና ኮሚቴ ከማቌቌም ይልቅ አባላት እንደፈቃዳቸውና እንደችሎታቸው ይክፈሉ ማለት የተሻለ ለመሆኑ ተከራካሪው ማን ይሆን? የተቌቌመው ኮሚቴ መመዘኛው ምን ይሆን? የታክስ ወረቀት ወይንስ የግለሰቡ የመሃላ ቃል? የምችለውን ልክፈል ያለውን የለም ትዋሻለህ እያልነው አሁን እንዴት ሊታመን ይችላል? የመንግስት ድጎማ የሚያገኝ ከተበለ ደግሞ በተዘዋዋሪ ድጎማ የማያገኘው ቁጥር ስንት ይሆን? የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው ቤተክርስቲያን መጥቶ ችግረኛ ነኝ እርዱኝ የሚል? አባል ባይሆን ምን ሊቀርበት? ለመሆኑ የቦርድ አባላት ይከፍሉ የነበረው የወር መዋጮ ስንት ነበር? አዲስ የቦርድ ምልምሎችስ? መናገር ያለብን አልመሰለንም እንጂ መዘርዘሩ ቀላል ነው። 100 አባላት በ$30 ማሰባሰብ ይሻላል 1000 አባላት $10? ምነው የሂሳብም ችግር ያለ ይመስል?
ወንድሞች እህቶች፤ አባቶች እናቶች ከየትም ወገን ይምጡ ከየት አታውቁም የሚሏችሁን አትቀበሉ። አይገባችሁም ለሚሉ አትስገዱ። በይሉኝታ አትታሰሩ፤ ሌባውን ሌባ ከሃዲውን ከሃዲ ማለት ከጀመርን ምን አልባት አወቁብን ማለት ይጀመር ይሆናል። በመለማመጥ ለውጥ አይመጣም። እኛ ካልተመረጥን ካህናቶቹን ያባርሯቸዋል የሚሉን የቦርድ አባላት እዚህ እንድንደርስ ያደረሱን እነሱ ጭምር መሆናቸውን እንዴት አሌ ሊሉ ይችላሉ? ከተመረጡ ያፈርሱናል የሚሏቸውስ ግለሰቦች እንዲሰባሰቡ ያደረጔቸው በየግብዣው ሲያዞሯቸው የነበሩት እነሱ አልነበሩምን? እስቲ ሁላችሁም እራሳችሁን ጠይቁ። አሁንም መፍትሄ ብለን የምናምነው በችግሮቻቸን ዙሪያ መነጋገር ስንችል ብቻ ነው። አሁንም አሸናፊ አይኖርም:: አሸናፊዎች እኛን አለያይተው የቤተክርስቲያኑ አባላት እየቀነሰ ስለሆነ ቤተክርስቲያኑ ይሸጥና መለስተኛ ቤተክርስቲያን እንግዛ በማለት ገንዘቡን በደላላነት በውሸት ደረሰኝ እንወስዳለን ካልሆነም የስደት ሲኖዶስን በበላይነት አምጥተን ተሸፋፍነን እናመልጣለን የሚል እቅድ ያላቸው ብቻ ይሆናሉ።