ዘንድሮ እንዴው ነገር እያስፈራን መጣላት እያስጠላን ሌላው አርግዞ እኔ በወልድኩ እያልን መጣንና ዝምታ አጠቃን እንጂ፤ የሚደረገው ነገር ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ሁላችንም በተናጠል የምናወራው ጉዳይ ነው። መረዋ በተደጋጋሚ ይህ ሊሆን እንደሚችል መናገሩም የሚታወስ ነው። አንድ እብድ "ነገ ቤት ይቃጠላል" ስትል አመሸችና የሚያዳምጣት አጣች። ታዲያ በነጋታው የሰውን ቤት ለኩሳ ሲቀጣጠል ሰው ሁሉ ኡ ኡ ማለቱን ሰምታ ምን አለች መሰላችሁ "ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል"። እንዴው ወዴት ከፍ ከፍ አትበሉን እንጂ ሌላው ቢቀር በሃይማኖታችን ክርስቶስን ስለገደሉት ክርስትና ተስፋፋ እንጂ አልሞተም ብለን የምናምን ሰዎች እኮ ነን። እስከመባረር የሚያደርስ ቅጣት ሊቀበሉ የደረሱ ምእመናን በመሃከላችን መኖራቸው ደግሞ የሚያኮራን እንጂ የሚያሳዝነን ሊሆን አይገባም።
ባለፈው የቦርድ ስብሰባ ላይ ለጊዜው በሊቀመንበርነት የሚያገለግሉት ግለሰብ ሰባኪ ከውጭ እናስመጣ በሚል ባቀረቡት ሃሳብ የነገው እጩ ሊቀመንበር ለመሆን የቸኮሉት ዶክተር አባ ወልደተንሳይን እናስመጣ በማለት መከራከራቸውን ወይዘሮ ፈትለወርቅም በሃሳቡ መደሰታቸውን እንደገለጹ ስንሰማና ለጉዳዩ ተጋብዘው የነበሩት ካህን መምሬ ሞገስ እንኳን ሳይጠበቅ ግብዣውን ተቃውመው መነሳታቸውን ስንሰማ ወይ ጉድ አላልንም። ለምን ቢባል የዶክተሩ እቅድ ዛሬ ተመረጡ የተባሉትም ተመራጮች እቅድና ትግል የስደቱን ሲኖዶስ ለማስመጣት ነው ብለን ስንናገር ከርመናልና። ሰሚ ያገኘነው ግን አሁን ነው። እንዴውም ከሰሙን አንዱ መምሬ ሞገስ መሆናቸውን ስንረዳ ሃሌ ሉያ የክርስቶስ ተአምር አያልቅም ብለናል።
ውድ የክርስቲያን ቤተሰቦች። ካህናቶቹን ካላባረርን የሚሉት ዶክተሩና አቶ አበራ ዛሬ የተመረጡትን ግለሰቦች ይዘን በድምጽ ብልጫ ምኞታችንን ሥራ ላይ እናውላለን እንደሚሉ ይገባናል። እንደወንድምነታችን ምክር እንለግስ ይህንን ከማድረጋቸው በፊት ቢያስቡበት መልካም ነው።
ለስደት ሲኖዶስ እንሰግዳለን ብለው መነሳታቸውንም ሰምተናል። ስለራሳቸው አያገባንም እኛን ግን ወክለው ይህንን ማድረግ እንደማይችሉ ካሁኑ በግልጽ ልናስቀምጥላቸው እንወዳለን። ተማክረው................... አይሸትም ይላሉና።
አቶ አበበ ጤፉ
ወየዘሮ ሰሎሜም ሆኑ
አቶ ሙሉአለም እንኴን ደስ ያላችሁ የተመኛችሁትን አገኛችሁ እኛ እስከምናውቀው ድረስ ለቤተክርስቲያን አገልገሎት የሚመረጥ ሰው ተጠይቆ እንጂ ተፈነካክቶ መመረጥን ሰምተን አናውቅም። በዚህ መልክ በመመረጣችሁም ተለያይቶ የነበረውን አካል እንዲነጋገር መንገድ በመክፈታችሁ ምስጋና ለናንተ ይሁን። ለመሰንዘር ላሰባችሁት ቡጢም ሆነ እርግጫ ከሚካኤል እርዳታ ጋር ተዘጋጅተን እየጠበቅናችሁ መሆኑንም መንገር ማስፈራራት አይደለም።
ይህንን ቤተክርስቲያን እናፍርስ ብለው የተነሱት ግለሰቦች ህልም እውነት እንዳይሆን የሁሉም ምእመን ግዴታ ነውና ከዝምታ ወጥተን አሁንስ ይብቃ ማለት መቻል አለብን። የተራበ ጅብ ፍየል እያየ በሙዳ ሥጋ አይመለስምና።
ከስልጣን የወረዳችሁት ወንድሞችና እህቶች፡ ሆይ የትላንትናውን ለትላንትና እንተውና ቤተክርስቲያናችንን ወደ ነበረበት ለመመለስ አብረን እንሰለፍ። ግዴላችሁም ስላልተነጋገርን እንጂ ሁላችንም የምንለው " ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ " ሳይሆን የቀረ አልመሰለንም::
ይህ የብሎግ አምድ ባካባቢያችን የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችን መወያያ ይሆን ዘንድ ተከፈተ። ከተወያየን እንስማማለን ከተነጋገርን ችግሮቸን እንፈታለን። አርፋችሁ ተቀመጡ ብለው የሚሰብኩን ደግሞ የሚያስተምሩን ጥንካሬን ሳይሆን ፍርሃትን ነው።
Monday, January 25, 2010
ሥልጣን ተዘዋወረ እንጂ ለውጥ አልመጣም። ቁጥር ፱
በትላንትናው ምርጫ የተደሰቱና የተከፉ እንዳሉ እውነት ቢሆንም፤ እኛን ግን አላስደነገጠንም፤ አላስገረመንም። ማንም ይመረጥ ማን በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በእምነት ፍቅር ስንቆራኝ በክርስቲያን ወንድምነትና እህትነት ስንጎዳኝ ልዩነታችንን በውይይት መፍታት ስንችል ብቻ ነው ብለን ከማመን ንቅንቅ አላልንም። አሁን እንደሚታየው የተደራጀ የፖለቲካ ቡድን የበላይነቱን ወስዶ ምእመንን አማኝ ሳይሆን ያልተመለመለ ተጋዳይ ስሙን ያልሰጠ የፖለቲካ አባል ማድረግ ይቻላል ከሚል አባባል በመንደርደር ግለሰቦች ቤተክርስቲያኑን ወደ ፖለቲካ መስመር እንወስዳለን ብለው መነሳታቸው የሚያሳዝን ነው። ይህ ደግሞ መሐመድ በግብዣ ላይ አብሮ ስለበላ ብቻ ሳይጠመቅ ክርስቲያን ሆነ እኮ ብሎ እንደማውራት። ገብረየሱስ እነፋጡማ ሰርግ ላይ በመታየቱ ሰለመ ብሎ እንደመመስከር ይሆናል። ይህ ቤተክርስቲያን የአማንያን ሳይሆን የጥቂቶች የተደራጁ ቡድኖች ንብረት ይሆናል የሚል አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች እስካሉ ድረስ ሰላም በምንም አይነት ይፈጠራል ብላችሁ እንዳታስቡ። በፊታችን ቅዳሜ ስብሰባ ከሳሽ የተባሉ ግለሰቦችን ከቤተክርስቲያን ለአንዴም ለሁሌም ለማባረር ስብሰባ እንደተጠራ ሰምተናል። ስብሰባ መጠራቱ ሳይሆን ይህ መሆን አለበት ብለው የወሰኑት ዛሬ የመሰናበት እጣ የደረሳቸው የቦርድ አባላት ጭምር መሆናቸውን ሁላችሁም የምታውቁት ይመስለናል። ይህም የሆነው ዛሬ ተመረጡ በተባሉት የቦርድ እጩዎች ግፊት እንደነበረ ሁላችንም የምንስማማበት ጉዳይም ነው። ታዲያ የታለሉት ይህንን ብናደርግ ደግመን እንመረጥ ይሆናል ያሉት እንጂ ይባረሩ የሚባሉት ግለሰቦች አይደሉም። ነገ ከሳሽ ናችሁ ተብለው ሊባረሩ የተወሰነባቸው ግለሰቦችማ ከሁላችንም በፊት ነገሩ ገብቷቸው ልክ ያልሆነን ነገር በመቃወም የመብት መደፈርን ለማስቆም በተቻላቸው ሁሉ ጥረው መፍትሄ ሲያጡ ወደ ሕግ አምርተዋል። ወደ ሕግ ማምራታቸውን ባንቃወምም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ደግሞ ፍትህ እንጂ ፍቅር ይመጣል ብለን ስለማናምን አሁንም መፍትሄው መወያየት ነው ብለን ለሁለቱም ወገን መናገር እንወዳለን።