ሳምንትም ቢቀረው ቀደም ብለን ሁላችሁንም እንኴን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን። የሚመጣው ሳምንት ደግሞ ሕማማት ነውና ስቅለትን በማሰብ መረዋ ለሳምንት እንደማትታተም ከወዲሁ የምንነግራችሁ የት ጠፋችሁ? እንዳትሉን ነው። ይህንን በቤተክርስቲያናችን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እስካሁን ደከመን ሳትሉ ከምእመናን ጎን በመሰለፍ የተነጠቀና የተረገጠ መብታችንን ለማስከበር በሚደረገው ትግል ተባባሪ በመሆን የምታደርጉት ተጋድሎ መጨረሻው እንደሚያምር መረዋ ጥርጥር የለውም። ከትላንትናው ዛሬ ጭላንጭልም እየታየ ያለ ይመስለናል። በስድብ አማንያንን ማናደድ እንጂ ማሰባሰብ እንደማይቻል ደግሞ በተጻራሪ ይጻፉ የነበሩት BOLGS እየተዘጉ መምጣታቸው ምስክር ይሆናል ብለን መናገር እንወዳለን። መሳደብ ለጊዜው ለሰዳቢው ያስደስት ይሆናል፡ እውነቱ ግን የሚሳደብ ሰው የሚሳደበው ይዞት የቀረበው ሃሳብ አዳማጭ አላገኘም ብሎ ሲያስብና የመጨረሻ ሽንፈት ላይ ደርሻለሁ ብሎ ድክመቱን መቀበል ሲያቅተው ብቻ ነው። ወንድሞችና እህቶች በስድብ ቢሆን ኖሮ እስካሁን በተለያየ ቦታ ብዙ ለውጥ በታየ ነበር።
ውድ አንባብያን። ባለፈው የመረዋ እትምታችን ማጠቃለያ ላይ በተጻራሪ እየተጻፉ ያሉትን የብሎጎ ጽሑፎች እንድታነቡ መጋበዛችን ይታወሳል። ምን አልባትም ክስ መመስረቱን በመፍራት ካልሆነም ብሎጉን ያስለጠፈው ድርጅት በደረሰው የሕግ ደብዳቤ መሰረት ብሎጎቹ መነሳታቸውን ለመታዘብ በቅተናል። እናንተም ለማንበብ ስትሞክሩ አጥታችሁት ከሆነ የተጻፈው በሙሉ ቅጅው ያለን በመሆኑ ለሚጠይቁን ሁሉ ለመላክ ዝግጁዎች ነን።
ብዙውን አማኝ ከምንም በላይ የሚገርመውና የሚያናድደው እንዴት ክርስቲያን እርስ በራሱ ይጨራረሳል? የሚለው ጥያቄ ነው። መረዋ ለእትምት ከበቃበት ቀን ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚለው ነገር ቢኖር "ክርስቲያን ይፋቀራል እንጂ አይፈነካከተም፡ እዚህ እኛ አካባቢ ያለው ችግር የኃይማኖት ሳይሆን የንዋይ ፍቅርና የፖለቲካ ሽኩቻ ነው"የሚል ነበር። የኃይማኖት ቢሆን ኖሮማ:
እንደዚህ መዘላለፍ
በተለያዩ ቦታዎች እየተሰበሰቡ ሌላውን ለማጥፋት እቅድ ማውጣት፡
በስብሰባ ላይ አይደግፉንም የሚሏቸውን ግለሰቦች እንዳይናገሩ ማፈን፡ የመናገር መብታቸውን መቀማት፡
በፖሊስ ማስፈራራት፡ ብሎም ከስብሰባ ማስወጣት ባላስፈለገ ነበር።
የኃይማኖት ጥያቄ ቢሆን ኖሮማ አባላትን ለማባረር ሕገ ደንቡን ምእመናን ሳይወያዩበት መቀየር ባላስፈለገ ነበር
የኃይማኖት ነገር ቢኖርበትማ ኖሮ እንደይሁዳ መረገሚያ $30 የክርስቲያንነት መመዘኛና መለኪያ ባልሆነ ነበር።
የኃይማኖት ነገር ቢኖርበትማ ኖሮ መካሰስ ባልመጣ ነበር።
የኃይማኖት ነገር ቢኖርበትማ ኖሮ የችግሩ መልስ ከመንፈሳዊ አባቶች እንጂ ከቦርድ አባላት ባልሆነ ነበር።
የኃይማኖት ነገር ቢኖርበትማ ኖሮ ወንጌልን ያስተማሩ መንፈሳዊ አባቶች ከመንበር ባልተባረሩ ነበር።
የኃይማኖት ነገር ቢኖርበትማ ኖሮ ለቤተክርስቲያኑ የለፉት እየተባረሩ በግርግር የገቡ ግለሰቦች ለእምነታችን ተጠሪዎች ክርስቲያን ለመሆናችን አጣሪዎች አባል ለመሆን ለሚቀርብ ማመልከቻ የግለሰብ ጀርባ ተመልካቾች ባልሆኑ ነበር።
የኃይማኖት ነገር ቢሆንማ ኖሮ የቦርድ አባላት የንስሐ አባቶችን ስልጣን ለመሻማት ባልተነሱ ነበር።
ይህንን ካየን ከታዘብን በኋላ ነው የኃይማኖት ሳይሆን የቡድን የስልጣን ፍላጎት፡ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው ብለን የደመደምነው። ወንድሞችና እህቶች ምንም የኃይማኖት ነገር በሌለበት ስለኃይማኖት መነጋገር ደግሞ እንዴት ይቻላል። እንዴው ለመናገር ያክል አንድ ቁም ነገር እናንሳ። እምነት ያለው ሰው "ወንድሞቼ እሕቶቼ ምን ሆናችሁ ብሎ ይጠይቃል እንጂ እንዴት ከቤተክርስቲያን ሕዝቡን ማባረር እንችላለን ብሎ እቅድ ያወጣል? በሚያምንና በማያምን መካከል ያለው መመሳሰል ምንድ ነው? ብሎ ለጠየቀ ሰው አንዱ ሲመልስ "ሁለቱም የቆሙለት ዓላማ መኖሩ ብቻ ይሆናል" ያለው ፈላስፋ ማን እንደሆነ ባናስታውስም እውነት ለመሆኑ ግን አባባሉ በቂ መልስ ይመስለናል።
ባለፈው እሁድ የሙዳዬ ምጽዋት ሳጥን ተሰብሮ ገንዘብ መሰረቁን የተናገሩት የቦርድ አባል ሳጥን መሰበሩንስ ይወቁ የገንዘብ መጥፋቱን እንዴት አወቁ? ብለን ተገርመናል። ሰው ያላስቀመጠውን ገንዘብ እንዴት ተሰረቀ ይላል? ከሳጥኑ የተገኘ ገንዘብ ደግሞ ለአዲስ ተመራጯ የቦርድ አባል ወይዘሮ ሰጥተናቸው ወደ ቦርዱ ጽ/ቤት ይዘው ሲወጡ አይተናል የሚሉ እህቶች መኖራቸውን ብንናገር ይክዱን ይሆን? ታዲያ ወይዘሮዋ የተረከቡት ገንዘብ ከስርቆት የተረፈ መሆኑ ነውን? የቤተክርስቲያኑስ የጥበቃ ካሜራ ያላነሳው የሰረቀው ግለሰብ ወይንም ግለሰቧ ግንዘቡን ሲቆጥር ወይንም ስትቆጥር አለማንሳቱ የቤት ሰው መሆኑን ካልሆነ መሆኗን አውቆ ይሆን? ይህንንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች የቦርድ አባላት መመለስ አለባቸው ብለን እናምናለን። እንዴው ለጫወታ ያክል ባለፈው ዓመት ያልተሰበረ የውስጥ በር ተሰበረ ተብሎ ፖሊስ አሻራ እንዲወስድ እንደተጠራ ሁሉ አሁንስ ገንዘብ ተሰረቀ ሲባል ፖሊስ ተጠርቶ ነበርን? እንዴው ለነገሩ ለማለት እንጂ መልሱ ጠፍቶን እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። አንባቢያንም ጥሩ ግንዛቤ ያገኛችሁ ይመስለናል። በዚሁ እለት እኚሁ የቦርድ አባል የተሰበረው ሳጥን ቁልፉ ስለተቀየረ የምትሰጡትን ገንዘብ በፖስታ በማድረግ ሳጥኑ ውስጥ ጨምሩት እንጂ ለግለሰብ ካሁን በኋላ እንዳትሰጡ ማለቱን ስንሰማ በጣም ገረመን። ገንዘቡ ከሳጥን ሲሰረቅ እኮ ቁልፍ ነበረው የቁልፉ መቀየር መሰበሩን አያስጥለውም እንዴዉም ለግለሰብ መስጠቱ እየተመዘገበ ስለሚቀበሉት የተሻለ ይሆናል ብለን አሰብን። ካባባላቸው በመነሳት ምን አልባት የጠረጠሩት ስለት የሚሰበስቡትን ግለሰብ ነው ማለት ይሆናል ብለን ጠረጠርን። ይንን ለመቀበል ደግሞ ግራ ተጋባን ስለት ሰብሳቢውን አዛውንት ስለምናውቃቸው በገንዘብ የሚጠረጠሩ አይደሉምና። ብቻ ዘንድሮ ሁኔታዎች እየተቀያየሩ ወደ መጥፎ ገደል እየተገፋን ነው። በቃ ማለት ከመወርወር በፊት እንላለን።
በሌላ ወገን SENBETE የተባለው የቦርዱ ደጋፊዎች BLOG ባለፈው እትምቱ ላይ በመሃበረ ቅዱሳን ላይ የተወሰነ የሲኖዶስ ውሳኔ ኮፒ በማውጣት መሃበረ ቅዱሳን አገር ቤት ሳይቀር ችግር ላይ እንደሆኑ ሊያሳዩን ሞክረዋል። ለነገሩ የተባለው ውሳኔ የቆየ ከመሆኑም በላይ እነሱ ዛሬ አይተውት አዲስ ሆኖባቸው ካልተደነቁ በስተቀር እንዳሉት ሳይሆን መሃበሩ በሰንበት ትምህርት ቤት ስር እንደሆነና የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ለመሃበሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በስልጣን ተዋረድ የሚሰራበትን ሁኔታ ያመቻቹበት ለመሆኑ ሙሉ ኮፒውን በማንበብ መረዳት ይቻላል እንላለን። የገረመን ሲኖዶስ አንቀበልም የሚሉት ቡድኖች ለነሱ የጠቀመ ሲመስላቸው ሊጠቅሱት ካልተስማማቸው ሊኮንኑት መሞከራቸው ነው። ወንድሞችና እህቶች የሰንበት ጸሃፊዎች። ወይ መጾም ወይ መግደፍ እንጂ እየጾምኩ እገድፋለሁ እየገደፍኩ እጾማለሁ የሚባል ነገር አለመኖሩን ማወቅ የግድ ነው ልንላችሁ እንወዳለን። የሲኖዶስ ውሳኔ ደግሞ ለሚያምን የእምነት መመሪያ ነውና ከመቀበል ባሻገር ሌላ ምርጫ ሊኖር አይችልም። አልቀበልም የሚል ቢኖር የኦርቶዶክስ ተከታይ ያልሆነ ብቻ ነው። እኛ እስከምናውቀው ድረስ ደግሞ መሃበረ ቅዱሳን ሲኖዶሱን ክደው አያውቁም። በፖለቲካ አመለካከት አመራርን መካድ ይቻላል፡ በእምነት ግን መንፈሳዊ አባቶችን መካድ የሃይማኖታችንን ምሰሶ መናድ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። መንፈሳዊ አባቶች እንደኛ ሰዎች ናቸው። በክርስቶስ የተመረጡ በመሆናቸው አባትነታቸውን ልንሳለቅበት ወይንም ልናላግጥበት አይቻለንም። ስልጣኑም ብቃቱም የለንምና። የተሳሳቱ አባቶች ቢኖሩ ሊገስጣቸው የሚችል አካል የመንፈሳዊ አባቶች ብሎም ክርስቶስ ብቻ ይሆናልና። አንዳንዴ በማናውቀው መዘባረቅ ቅስፈትን እንደሚያመጣም መጠርጠር ክርስቲያንነት ነውና ብንጠነቀቅ መልካም ነው። ካልሆነ እምነትን እንደፖለቲካ ማራመድ ካሁን የባሰ ችግር ውስጥ ይጥለንና በምድርም በሰማይም ኡኡታን ታቅፈን እንቀራለን።
በድጋሜ መልካም የትንሳኤ በዓል ለሁላችን።
በቸር ይግጠመን።