Monday, March 8, 2010

ጣር የያዘው ሲንፈራገጥ ላላወቀ የሚራገጥ ይመስላል። ቁጥር ፲፯

እንዴት ከረማችሁ? ባልን ቁጥር የግላችንን ካልሆነ በስተቀር በቤተክርስቲያናችን የሚደረገውን ሽኩቻ ከሆነ የምትጠይቁን መልሱን ፈጣሪ አምላክ ይፍታው እያልን ነው ያለነው ትሉን ይሆናል። እኛም ከናንተ የተለየ መልስ የለንም። ባለፉት ሁለት ሳምንታት፤ በየብሎጉ የተጻፉትን የሐሰት ውንጀላዎች፤ ስም ማጥፋቶች፤ ስድቦችና ማስፈራሪያዎች ያነበበ ሁሉ አገር ለመልቀቅ ከተማ ለመቀየር ቢያስብ አይፈረድበትም። ከውሸትም እኮ እውነት የሚመስል ውሸት አለ። የነዚህ ግን ዓይን ያወጣ ሃሰት ሆነብን። በቅሎ ትወልድ ይሆናል ብሎ መጠራጠርና በቅሎ ስትወልድ አየሁ ማለት የተለያዩ ናቸውና። ለነገሩ ስማቸው በሃሰት የጠፋው ግለሰቦች በሕግ በደላቸውን ለመበቀል በመነሳት አስፈላጊውን ሕጋዊ መንገድ እያጣደፉት በመሆኑ በቅርቡ ይፋ የሚሆን ለሁላችንም ትምህርት ሊሆን የሚችል የሕግ መፍትሄ እንደሚኖር ተጠግተው ያዳመጡ ሁኔታውን የተከታተሉ አስተማማኝ ምንጮች ሹክ ብለውናል። ይህንን ስንሰማ አልተደሰትንም ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መሄዱን ተገነዘብን እንጂ። ቀልደኛው ጔደኛችን ምን ትቆዝማላችሁ "ምከረው ምከረው ካልሰማ መከራ ይምከረው"ይባላል እኮ። እንዴውም ሰሞኑን የደረሰኝን ቀልድ ልንገራችሁ አለና የሚከተለውን አጫወተን። "አንድ አስተማሪ ስለ አሳነባሪ ሲያስተምር አሳ ነባሪ ሰውን መዋጥ አይችልም ምክንያቱም አፉ ሰፊ ቢሆንም ጉሮሮው ጠባብ ነው ብሎ ሲያስተምር አንድ ወጣት ተነሳችና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርታችን ላይ በአሳ ነባሪ የተዋጠውን ዮናስን መንግስተሰማያት ሳገኘው እጠይቀዋለሁ። ብላ ላስተማሪዋ ነገረችው። አስተማሪውም በሹፈት መልክ ዩናስ ገሃነመ እሳት ገብቶስ ከሆነ?ብሎ ሲጠይቃት ሲኦል ከገባም ችግር የለውም አንተ ትጠይቀዋለህ ብላ መለሰችለት።" ብሎ አሳቀን። የታሪኩ መልእክት እምነትን የሚመለከት ነው። ማብራሪያ የሚያሻው አልመሰለንም።

እድገትን መቀበል መልካም ነው። እድገት ደግሞ በተለያየ መልክ ይገለጣል። ባካባቢያችን ያሉ ወጣቶች የሚናገሩትን በመስማት የተቀየረውን አማርኛ ማጣጣምና ምን ማለት ነው? ብሎ መረዳት የግድ ሆኗል። "ይመችህ" የሚለው አባባል ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ወጣት መጠየቅ መሃይም መሆን አይደለም። እኛ የምናውቀው አማርኛ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ነው። እንደትላንትናው "እኔ አላምንም" የሚለው የአነጋገር ዘይቤ ተቀየሮ ዘንድሮ "እንዲህማ አትለኝም" "እንደሱማ አታረገኝም" ሲሉ መስማት ለኛ እንግዳ ይሆን ካልሆነ በስተቀር ለወጣቶቹ ትክክለኛ ቌንቌ ነው። ለነገሩ ይህንን ያነሳነው ቌንቌና የቌንቌ ግንዛቤ የባህል ክፍል ነውና ከአዲስ መጤው ቌንቌ ጋር እየተካለስ የተለየ የራሱን እድገት እንደሚመራ ለመጠቆም ያክል ነው። ሃይማኖትም ይህ እንዳይደርስበት ቀንና ሌሊት መታገል ሊኖርብን ነው። በተለይ የኛ የኦርቶዶክስ እምነት እስካሁን ጠብቆ የቆየውን መለያ እንዲያጣ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ነው። ይህ ትግል ደግሞ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ለመጧጧፉ እሩቅ መሄድ አያስፈልግም። "ማርያም አታማልድም " የሚሉ ድሮ ተወግረው ተገድለዋል። ዛሬ ታማልዳለች ብለን የምናምነውን ሊወግሩን ተነስተዋል። "ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ በተገኛችሁበት ሁሉ እገኛለሁ" ያለውን ቃል ዘንግተው። እጅ ለእጅ ተያያዘው እየጸለዩ: በጋራ እየለመኑ፡ እኔ ጸልዬ አድንሃለሁ እያሉ ይቆዩና የማሪያም ምልጃ ሲነሳ ግን ያንገፈግፋቸዋል። "አንቺ ሴት ቀኔ አልደረሰምና አታስቸግሪኝ"ሲል ቆይቶ "ያላችሁን አድርጉ"በማለቷ ውሃውን ወደ ወይን የመቀየሩን የቃነ ዘገሊላውን ተአምር ሲያነሱባቸው ፊታቸውን ያዞራሉ።

ወንድሞችና እህቶች ጾም በአዋጅ ቢነሳ ደስ የሚለን ብዙዎች ነን። ግን አይሆንም። ቅዳሴ በመኪናችን ወስጥ ባለ ካሴት አዳምጠን ቤተክርስቲያን ከመሄድ ብንቀር የምንፈልግም እንኖራለን። ከነጫማችን የቤታችንን ወለል ለመርገጥ ተጠይፈን ለምን ቤተክርስቲያን ጫማ እናወልቃለን የምንል ብዙዎች ነን። በፈቃድ የምናደርገውን እንደ ትእዛዝ የምንወስድም ብዙዎች ነን። ያገር ልብስ መልበስ አላዋቂነት ከረባት ማሰር የምሁርነት መለኪያ የሚመስለን ብዙዎች ነን። ይህ ካለማወቅ የመጣ በመሆኑ ማንም ማንንም መንቀፍ የለበትም። የኦርቶዶክስ እምነት ኋላ ቀር ነው የሚሉ ሰባክያን ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ለመሆናቸው የሚከተለውን በመጫን የተቀረጸውን ተመልክተው የራስዎን ግንዛቤ ይውሰዱ።


ይኸንን ልናነሳ የወደድነው እናንተን ለመስበክ ሳይሆን አንዳንዴ ምን እየተደረገ ነው የሚለውን ማዳመጥ ጥሩ ነው ብለን ስለምናምን ነው። አዲሶች የቦርድ ተመራጮችና በጣት የማይቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ከኛ የተለዩትና ጠንካራ የሆኑት እኛ ፈጣሪን ስለምንፈራ አባቶችን ስለምናከብር ወጣቶችን ስለምናዳምጥ ሲሆን እነሱ ግን ከራሳቸው በስተቀር የሚያከብሩትም ሆነ የሚፈሩት ምንም ነገር ስለሌለ ነው። ከሁሉ በላይ የሚያስፈራ ጠላት ደግሞ ምንም አይነት እምነት የሌለው ነው ይላሉ። ባይሆንማ ኖሮ ሽማግሌዎች ሲያናግሯቸው፡ ምእመናን ሲለምኗቸው፡ ከመሳደብ ይልቅ ማዳመጥን በወደዱ ነበር። በግል አነሳሽነት የቤተክርስቲያኑ ጉዳይ ያሳሰባቸው ግለሰቦች የከሳሽን ቡድን ክሁለት ጊዜ በላይ የቦርድ አባላትንም እንዲሁ ማነጋገራቸውን ሰምተን ነበር። አሁን የደረሰን ዜና ደግሞ አማራጭ ነው የሚሉትን ሃሳብ ለከሳሽም ለቦርድ አባላትም ማቅረባቸውን ነው። ያቀረቡት ሃሳብ ቅጂ ሲደርሰን ለናንተ ለማቅረብ ቃል እየገባን ባላየነው ሃሳብ ላይ ለዛሬ አስተያየት ከመስጠት እንቆጠባለን።

እንዴው ለፈገግታ እንዲሆንላችሁ በቤተክርስቲያን አካባቢ የተባለውን እንንገራችሁ። የቀድሞው ሊቀመንበር ካንድ የቦርድ አባል ጋር ስለ አጀንዳ ሲወያዩ የቦርዱ አባል የቀድሞውን ሊቀ መንበር "መቼ ነው ይህንን ደግሞ የወሰንነው?" ብሎ ቢጠይቀው "ወንድሜ ዘንድሮ እኮ እኔና ተዋበች ማለት የቀድሞው ብዙአየሁና ሰሎሞን ማለት ነን አለ ብለው ነገሩን" በሰፈሩት ቁና መሰፈር ይሏል ይኸ ነው።

የቀድሞው የቦርድ ተመራጭ የነበሩትና ከስልጣን በምርጫ የተሸነፉት ዓመቱን ሲጨቃጨቁ የከረሙበትን አይምሯቸውን ለማዝናናት በሚቀጥለው ወር ከባለቤታቸው ጋር ለአንድ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ ስንሰማ አይ ጉዳቸው ጉዞአቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያገናኙና መከራቸውን ያሳዩአቸዋል ብለን ለነሱ እኛ አዘንን። እነሱ ትላንት ሌላውን እንዲያ ማለታቸውን ዘንግተን አይደለም፡ ግን ዘንድሮ እኮ አገርቤት ገብቶ መምጣት ወንጀል ነው ብለው የሚሰብኩን ደግሞ እየተመላለሱ ያሉት የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። ስም እንጥቀስ እንዴ? የለም እኛ ከነሱ በላይ ሆነን መገኘት እንፈልጋለን። እነሱ ይሳደቡ፡ ያላደረግነውን አደረጉ ብለው ይወንጅሉን፡ እኛ ይቅር በላቸው ብለን እንጸልይላቸዋለን።

አንድ ልጅ እናቷን "እማማ ለምን ጸጉርሽ ሽበተ ጀመረው? ብላ ትጠይቃለች አሉ እናትየዋም "ልጄ አንቺ ያመጣሽብኝ ጣጣ ነው ባናደድሽኝ ቁጥር በዋሸሽኝ ቁጥር ሽበቴ ይጨምራል" አለቻት ልጅቷም አሰበችና ታዲያ ያያቴ ፀጉር ለምን ሁሉም ነጭ ሆነ? ብላ ደግማ እናቷን ጠየቀች ይላሉ።

በሚቀጥለው እትማችን የአማርጭ ፈላጊ ቡድንንና የሰላም ፈላጊን ተመራጮች የደረሱበትን ጠይቀን ልንነግራችሁ ቃል በመግባት እነሰናበታችሁ። ቤተክርስቲያኑ እንዳይፈስ የምንታገለው እኛና እናንተ መፍረሱን ለማጣደፍ የሚራወጡት ደግሞ የቦርዱ ተመራጮችና በጣት የማይቆጠሩ አፈ ጮሌ ደጋፊዎቻቸው መሆናቸውን አትዘንጉ። ሁላችንም ላመንበት ከቆምን ለውጥ እናመጣለን ብለን እናምናለን።
ደህና ሁኑ።
















የሰላም ኮሚቴ የደረሰበትንና የአማራጭ ሰጪ ኮሚቴ