ቆየት ብሏል ዘመኑ ታሪኩን ያጫወቱኝ ዘመዴ ዛሬ በሕይወት የሉም። መሬቱን ገለባ ያድርግላቸው። ብዙ ታሪክ ይነግሩኝ ነበር። ታዲያ ቀደም ባለው ዘመን ወሎ ተፈጸመ የተባላውን ሲያወጉኝ እንዲህ አሉ። "በወቅቱ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በግንባሩ ላይ በእጁ ላይ መስቀል ተነቅሶ ወይንም ማተብ አስሮ መስቀል ባንገቱ አንጠልጥሎ በመንቀሳቀስ ማንነቱን ሲያስመሰክር፤ እስላሙ ደግሞ ጉፍታ በመከናነብ የስላም ኮፍያ በማጥለቅ ማንነቱን ያሳውቅ የነበረበት ወቅት" እንደነበር ነገሩኝ፡፡ "በጊዜው የሃይማኖቱ ልዩነት እየገፋ መጣና እርስ በእርስ መገዳደል ተጀመረ። ታዲያ ሁሉም እየተፈራራ ባለበት ሰዓት በመንገድ ላይ ሁለት ሰዎች ተገናኙ። ሁለቱም የመስቀል ምልክት አልነበራቸውም ወይንም የእስላም ኮፍያ አላጠለቁም ነበር። ከሁለቱ አንደኛው ጎራዴ ካፎቱ አወጣና ሌላውን እስላም ክርስቲያን? ብሎ ጠየቀው የግለሰቡ መልስ ምን ነበር መሰላችሁ "ሃይማኖት የለኝም"የሚል ነበር"። ግለሰቡ ይህንን ያለው ጎራዴ ያወጣበት ሰው ሃይማኖቱ ምን እንደነበረ መናገር ስላልቻለ እንደነበረ ለመረዳት እንችላለን። ይህንን ያጫወተን እንደ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ የፍቅር እስከ መቃብር ጉዱ ካሳ ከመሃከላችን ሁኖ እየተናገረ የሚያስቀን በቀልድ ቁምነገር የሚያስተላልፈው አባላችን ነው።
ዘንድሮም በከተማችን የእየተከሰተ ያለው እንዲሁ እየሆነ እየመጣ ነው። የሚካኤል ቤተክርስቲያን አባል ነህ አይደለህም? ሲባል በኦርቶዶክስ እምነት የተጠመቅሁ ቤተክርስቲያኑ ሲሰራ ካለኝ ቆንጥሬ አነሰ ሲሉ በወር ከፋፍዬ የምችለውን የሰጠሁ፡ በየጊዜው ከቅዳሴ በኋላ ሙዳዬ ምጽዋት ሲዞር የለገስኩትን ማወቅ ያለበት ሚካኤል ብቻ ነውና ጠቅልዬ እሰጥ የነበረ መሆኔን የሚያውቅ ያውቀዋልና ምስክር መጥራት የለብኝም የሚሉ ብዙ ናቸው። አባል ነኝ ብዬ አምናለሁ እነደትላንትናው በአቶ ሙሉዓለም ከቅዳሴ በኋላ በታወጀው አዋጅ አይደለህም ቢሉኝ ደግሞ አልገረምም የሚሉ ደግሞ እንዳጋጠሟችሁ እርግጠኛ ነን። አቶ ሙሉዓለም ያወቁ መስሏቸው ከመቅደሱ ፊት ቆመው "እኛ ሕዝብን ለማስደሰት በሕዝብ ግፊት አንሰራም በሕጋችን መሰረት ለ 6 ወር የአባልነት ክፍያ ያልከፈለ ሁሉ $50 የመመዝገቢያ ከፍሎ ማመልከቻውን ቦርዱ ካየውና ካጠናው በኋላ አባልነቱን እንፈቅድለታለን ወይንም እንከለክለዋለን" ብለው ያወጁትን አዋጅ ከሰሙ በኋላ የተባለውን ነው የምናጫውታችሁ። አዋጁን ስንሰማ እኛንም የቀድሞውን አሰፋ ይርጉን አስታወስን። የሳቸው ከዛኛው የሚለየው ድምጻቸውና ያነባበብ ችሎታቸው ብቻ ነበር። ቤተክርስቲያን የቤት ክፍያ እንዳቃታቸው ግለሰቦች አባላትን በገንዘብ ተመን ስታስወጣ ማየትን የመሰለ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ። የሚገርመው አዋጁ የተነበበው ሊያስቀድስ ለመጣው ሕዝብ መሆኑ ነው። ከርስቲያን ሆነህ የምንልህን ካልከፈልክ አባል አይደለህም ይሉና የሚናገሩት አባል ለሚሉት ሳይሆን በእንግድነት ለመጣው ሕዝበ ክርስቲያን መሆኑ ነው። አቶ ሙሉዓለም ወይ የኦርቶዶክስ አማኝ ሁሉ ወንድምና እህታችን ነው ይበሉ ካልሆነ ለጥቂት ደጋፊዎቻቸውና አባላትለሚሏቸው በፖሰታቤት ልከው አዋጁን ተፈጻሚ ያድርጉት። ሁለት መርጦ አይሆንም። ገንዘብ የለንም ነገር ግን ትምህርት ቤት እናሰራለን። ገንዘብ የለንም ነገር ግን አስተማሪ እንቀጥራለን። ገንዘብ የለንም ነገር ግን የመኪና ማቆሚያ እንጠግናለን። ገንዘብ የለንም ጣራውን እናሰራለን ቀለሙን እንቀባለን። ገንዘብ የለንም ዶክተሩን ለቤተክርስቲያን አስተዳዳሪነት እነቀጥራለን ይህንንም በቆዩ የሽማግሌ አባላት በኩል ተፈጻሚ እናደርጋለን ካላደረጉ በተካንንበት ዘዴያችን ስማቸውን እንበክላለን ወይም እንደልማዳችን በደጀሰላም ቀርበን እናስፈራራቻዋለን። ሲሉ ይቆዩና የምንችለውን እንክፈል የሚሉትን ምእመናን ደግሞ እኛ ያልነውን ካልከፈላችሁ ገደል ግቡ ሲሉ እንሰማለን።
ይህ እንደሚመጣ ደግሞ ቀደም ብለው የነገሩን ግለሰቦች ነበሩ። መቼም ትንቢተኛ ባገሩ አይከበርም ሆነና ያዳመጥናቸው ግን ጥቂቶች ነበርን። ዛሬ ደስተኛ የሆንነው ትላንት ቤተክርስቲያናችንን ሊያፈርሱ ተነስተዋል ይሏቸው የነበሩትን ግለሰቦች ይቅርታ አድርጉልን ቤተክርስቲያናችንን የምታፈርሱት እናንተ ሳትሆኑ እነዚህ በቡድን ቦድነው የተመረጡት አንባ ገነኖች መሆናቸውን ደርሰንበታል ሲሉ ስንሰማ ነው። ሰው አይሳሳትም አይባልም ትልቅነቱ የሚለካው ነገሩ ሲገባው ይቅርታ እውነቱ አሁን ተገልጾልኛል ሲል ነው።
የዚህ ቤተክርስቲያን ችግር $30 በመክፈልና ባለመክፈል ነው የሚል ሰው ካለ እንደገና እራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። የ $30 ብር ክፍያ ሳይመጣ በፊት ይህ ቤተክርስቲያን ብዙ ገቢ ነበረውና። ገንዘባቸውን ለቤተክርስቲያኑ ያፈሰሱት ደግሞ የዛሬዎቹ ተመራጮች በፈጠሩት ደባ የተናደዱና መክፈላቸውን ያቆሙ አባላት እንጂ ከተመረጡት ውስጥ ምናልባት ካንዱ ግለስብ በስተቀር በልገሳ አይጠረጠሩም አይታሙም። ለዚያውስ ቤተክርስቲያኑ ተገዝቶ ተከፍሎ ያለቀው ዓምና እነዚህ ዛሬ የሚያምሱን ተመራጮች የተቀላቀሉን ትላንትና።
መንገድ ዳር ተቀምጦ የሚያለቅስ ልጅን አይቶ ምንሆንክና ታለቅሳለህ ቢለው?ነገር ከሆዴ ገብቶ እየተናደድኩ ነው። እንጀራ እናቴ ከመምጣቷ በፊት እረሃብ ምን እንደነበር አላውቅም ነበር አሁን ግን መራብ አይደለም እራበኝ ሲሉ እየቀለድሁ ያለፍኴቸውን ሰዎች እያሰብኩ ጭምር ነው የማለቅሰው አለ ይሉ ነበር። 20 ዓመት በሰላም የተቀመጠ ህብረተሰብ በጥቂቶች በቅርብ ጊዜ ታምሶ እዚህ መድረሱ የሚያሳዝን ነው። የነዚህ ግለሰቦች ሕልም እውነት የሚሆነው፡ "የኦርቶዶክስ እምነትን ከተቻለ ማጥፋት ካልሆነ መከፋፈልና መሸርሸር "የሚለውን ዓላማቸውን ማኮላሸት የሚቻለው አሁንስ በቃ ማለት ስንችል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ መካሪ አነሳሽ አያስፈልገንም። የምእመኑን ጉልበት የምእመናኑን ታጋሽነት እንዳለማወቅ የወሰዱት የቡድን ተወካዮች ትምህርት ሊያገኙ የሚችሉት ውሸት በቃን የተነጠቅነውን ሕብረት መመለስ መቻል አለብን ቤተክርስቲያኑ ንብረታችን ነው ማለት ስንችል ብቻ ነው።
ከሁሉ የሚገርመው አዲስ የያዙት ፈሊጥ የራሳቸውን ልጆች ከቤተክርስቲያንችን እያሸሹ በልጆቻችን ስም የአዞ እንባ እያለቀሱ መነሳታቸው ነው። አባቶቹንና እናቶቹን እያባረሩ ልጆቹን እንፈልጋለን ማለት ከስጋው ጦመኛ ነኝ ከመረቁ አውጡልኝ ያለውን አይነት ይመስላል። ትምህርት ቤት የሚሰራው ወጣቶች የሚሰባሰቡት ወላጆች ፍቅር ሲኖራቸው እንጂ በጥል መሃል ሊሆን አይችልም።
ስለሆነም እነዚህን በአድማ የተመረጡ የቦርድ አባላትን በመለማመጥ ሰላም ይፈጠራል ብለን የምናምን ካለን ለነሱ የነገር መግመጃ ጊዜ ከመጨመር በስተቀር መፍተሄ እንደማያመጣ መረዋ ዛሬ ሊያረጋግጥ ይወዳል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን። ሊገል ቆርጦ የመጣን ጠላት ማርኮ አሰሮ ይተወኛል ማለት ሞኝነት ካልሆነም የዋህነት ነው። አንድ ሰው መደራደር የሚችለው እኮ ችግርህ ምንድነው?ብሎ ከሚያዳምጥ ሰው ጋር እንጂ ተባረሃልና የምታመጣውን አያላሁ ከሚል ቡድን ጋር ሊሆን አይችልም።
የደቡብ አፍሪካው ታጋይና የሃይማኖት መሪ ዲዝሞን ቱቱ ሲናገሩ "ነጮች መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው መጡ ዓይናችሁን ጨፍኑና ጸልዩ አሉን ጨፍነን መጸለይ ጀመርን ዓይናችንን ስንገልጽ እነሱ መሬቱን ወስደውት እኛ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘን ቀረን" ብለው ነበር። እኛም እንዲሁ አይነት እድል ገጠመን ብንል ማጋነን አይሆንም። አቶ አበራ ፊጣ ከመመረጣቸው በፊት "ቤተክርስቲያናችን ገንዘቡ ተዘረፈ የቦርድ አባላት ያለገደብ መብት ተሰጣቸው"ሲሉ እንዳልነበር ዛሬ ታግለው ያላገኙትን ስልጣን ባቌራጭ አገኙና "ሲሾም ያልበላ ........ "ይሉን ጀመር። የቤተክርስቲያንችን ዶክተር ወደ ዳላስ ያስመጧቸውን ሰዎች ውለታ ለመመለስ አድርግ የተባሉትን ሥራ ላይ ለማዋል ጥረው ግረው ምኞታቸው በሥራ ሲተገበር ለማየት እድል ገጠማቸው። የመጨረሻ መደምደሚያቸው ለራሳቸው ሥራ ለምፍጠር ነውና ባረቀቁት ሕጋቸው መሰረት "አንድ የቦርድ ተመራጭ ተቀጣሪ ሆኖ ማገልገል ይችላል የሚለውን" አንቀጽ ተጠቅመው ለመቀጠር ቁጭ ብድግ እያሉ መሆኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን። ሌላው የስደት ሲኖዶስ ጉዳይ ነው እሱንም "በአባላት ስብሰባ"ለማስመረጥ እየተሯሯጡ ለመሆኑ ብትጠይቌቸው የሚክዱ አይመስለንም። ያመጧቸውን ሰዎች ውለታ ለመክፈል መብቃት ይኽ ነው።
ትላንትና አቅፈው ደግፈው ዶክተር ለቤተክርስቲያናችን ያሉ ቡድኖች ዛሬ ኧረ በሚካኤል ቢሉ የሚሰማቸው ከቦርዱ ሊያገኙ አልቻሉም። ስለተናደዱባቸው ንዴታቸውን የሚገልጹላቸው ይጠሩበት የነበረበትን የመሃበር ድግስ በመከልከል ሆኖ አይተነዋል። ነገሩ የማር ጋንን አስረክቦ ሰጥቶ ሰፈፍ መከልከል አይነት መሆኑ ነው።
ትላንትና ሲነገራቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት የተፈነቀሉት ሊቀመንበር ዛሬ አንገታቸውን ደፍተው በአቶ አበበ ጤፉ ግልምጫ በአቶ ሙሉ ዓለም እርግጫ እየተናደዱ ለኔም ቀን ይመጣል እያሉ እየጠበቁ ነው።
ዛሬ ያልሆነ ተስፋ በመስጠት ነገሮች ይስተካከላሉ ቁጭ ብላችሁ ጠብቁ ማለትን መስማት የሚፈልግ ሰው ካለ በጣም የዋህ ነው። ማንም ያናግራቸው ማን የቦርዱ አባላት ለምን ምእመን እንዳለ ተገልብጦ አይወጣም እኛ የምንፈልገውን እንጂ የናንተን ፍላጎት አናሟላም ብለው ነግረውናል። ለነገሩማ ባወጡት ሕጋቸው ላይ ቤቱ የወሰነውን ቦርዱ መሻር ይችላል ብለው አውጥተው የለ። ሕጋቸውን እንጂ የአባላትን ሕግማ አሽቀንጥረው ጥለውታል። ትላንት ተው ሲባሉ ይኽ ነገር አደገኛ ነው ሲባሉ ያልሰሙ የትላንትና የቦርድ አባላት ዛሬ ሕጋችን ብለው ተደሰተውበት የነበረው ይኽው ለነሱም ማነቆ ሆኖባቸ ተቸግረዋል። በመሆኑም ትልንት እንዳልነው ዛሬም መፍትሄ ነው ብለን የምናምነው ፦
1 ቦርዱ ከስልጣን እንዲወርድ ሲደረግ
2 መተዳደሪያ ደንባቸን ወደቀድሞው ሲመለስ
3 የሽግግር ኮሚቴ የሚሆኑ የተከበሩ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሽማሎች ተመልምለው ለመረከብ ሲበቁ
4 በፈቃዳቸው ካልለቀቁ ባስቸኴይ ተጨማሪ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ሲቻል
5 የፖለቲካ ድርጅቶች ከቤተክርስቲያናችን ለቀው እንዲወጡ ግልጽና የማያሻማ ጥያቄ ሲቀርብ ይህም ተግባርዊ ሲሆን ብቻ ነው ብለን እናምናለን።
ካልሆነ አሁንም የተቀደደ ከበሮ እየደበደብን ነው ማለት ነው።
ሚካኤል እራሱን ይጠብቃል። ለሚንቁ ብሰለትን:ለሚተበትቡ ምህረትን፡ ለሚጠሉ ፍቅርን፡ ለሚሳደቡ ቅን አንደበትን፡ ለሚዋሹ ምህረትን ያውርድልን።
ክርስቶስ በፍቅር ያሰባስበን።