ላለፉት ወራቶች በቤተክርስቲያናችን የተፈጠረው ችግር አሳስቦአቸው መፍትሄ ማግኘት አለብን ብለው የተነሱት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አባላት በቤተክርስቲያኑ አዳራሽ ለመሰብሰብ መከልከላቸው ሳያናድዳቸው የሆቴል አዳራሽ ተከራይተው "የተባበሩት የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የመፍትሄ ኮሚቴ" ማቌቋማቸው የሚታወስ ነው። ይህ በጅምሩ የ200 አባላትን የሥም ዝርዝር ይዞ የተዋቀረው ኮሚቴ የደጋፊዎቹ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሄዱን በመግለጽ በሃላፊነት የተቀበለውን ሥራ ለማቀላጠፍ ይረዳ ዘንድ በትላንትናው ስብሰባው የተለያየ ኮሜቴ ማዋቀር አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው 9 ኙ የኮሚቴ አባላት በተዋረድ የሚሳተፉበት 4 ኮሚቴዎች ማቌቌማቸውን ከስፍራው የተገኙ ምእመናን ገልጸውልናል።
በእለቱ በተደረገው የኮሚቴ ማዋቀር ስብሰባ ላይ እንደተነገረው አባላት ምነው ዘገያችሁ? ማለታቸው የተገባ ጥያቄ መሆኑን የዘገቡት የኮሚቴው ሰብሳቢ "ጥልን ለማፋፋም እንጂ ሰላምን ለመፍጠር ጊዜ እንደሚፈጅ መታወቅ እንዳለበት ጠቅሰው በተለያየ መልኩ ግን ብዙ በይፋ ያልወጡ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንና በተለይም ባለፈው ወር በግለሰብ ተጠርቶ በነበረ ውይይት ላይ በመገኘት ከተላያዩ ጉዳዩ ይመለከተናል ከሚሉ የቤተክርስቲያን አባላት ጋር ውይይት ኮሚቴው ማድረጉን " ለተሰብሳቢዎቹ ገለጻ አድርገዋል"። ይህ ዛሬ የተቋቋመው ኮሚቴ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢ በኮሚቴው ውስጥ ገብቼ ለማገልገል እፈልጋለሁ ለሚል ለማንም ኢትዮጵያዊ በሩ ክፍት መሆኑን ጠቅሰው፡ አሁንም መፍትሄ የምናመጣው ተሰብሰቦ በመነጋገርና በመወያየት መሆን አለበት ብሎ ስብስቡ እንደሚያምንና በዚህም መርህ እንደሚመራ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የሰላም መንገዱ የተዘጋ በመሆኑ ደግሞ የሕግን የበላይነት በሕግ ማስከበረ አማራጭ የሌለው መንገድ ሆኖ መገኘቱን ለተሰብሳቢው አስረድተዋል።
በእለቱ የተሰበሰቡት የኮሚቴ ተመራጮች ስራቸውን ለማከናወን እንዲራዳቸው በጸሎት የከፈቱት የመንፈሳዊ አባቶች የራሳቸው ችግር ሳይሆን የምእመናን መበታተን እያስፈራቸው እንደሆነ ጠቅሰው ክርስቲያን ሽንፈትን የሚቀበል ሳይሆን ጥንካሬን የሚያስተምር መሆን አለበት ብለው ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል። በነሱ ላይ ያለው የፈቃድና የኢኮኖሚ ችግር የሚቀረፍበትን መንገድ ተሰብሳቢዎቹ እንዲያስቡበትም ለተሰብሳቢዎቹ ማሳሰቢያ አቅርበዋል። ከሁሉም በላይ ግን የክርስቲያኖቹ መበታተን አሁንም እያሳሰባቸው በመሆኑ ከቤተክርስቲያን በኩርፊያ መቅረት እንደማይገባ አስተምረው ከጸለይን ከተማጸንን የማይሆን ነገር እንደማይኖር መቀበል ደግሞ ክርስቲያናዊ እምነታችን ነው ብለዋል።
በእለቱ
፩ የሕግ ክፍል
፪ የአባላት ጉዳይ ክፍል
፫ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል
፬ የመንፈሳዊ ክፍል
ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንና የሥራ መመሪያ መንደርደሪያ ለያንዳንዱ ኮሚቴ መሰጠቱን ዘጋቢዎቻችን ጠቅሰውልናል። በቅርቡም ኮሚቴው የራሱ የሆኑ መጽሔት እንደሚያዘጋጅ የሕዝብ ግንኙነቱ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተናገሩ ሲሆን በስድብ ሳይሆን እውነትን በመዘገብ ደጋፊን ማበርከት እንደሚቻል በግብር እየታየ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል። የእለቱ ስብሰባ በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት መገባደዱን ምእመናኑ ጨምረው እንዳወሱን ልንነግራችሁ እንወዳለን።
ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንና የሥራ መመሪያ መንደርደሪያ ለያንዳንዱ ኮሚቴ መሰጠቱን ዘጋቢዎቻችን ጠቅሰውልናል። በቅርቡም ኮሚቴው የራሱ የሆኑ መጽሔት እንደሚያዘጋጅ የሕዝብ ግንኙነቱ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተናገሩ ሲሆን በስድብ ሳይሆን እውነትን በመዘገብ ደጋፊን ማበርከት እንደሚቻል በግብር እየታየ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል። የእለቱ ስብሰባ በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት መገባደዱን ምእመናኑ ጨምረው እንዳወሱን ልንነግራችሁ እንወዳለን።
መረዋ በዚህ አጋጣሚ ይህንን ስብስብ እዚህ እንዲደርስ ለማድረግ ለጣሩ ሁሉ በተገፉትና በተሰደቡት ምእመና ሥም ምስጋና እያቀረበ። መሳደብን እንደበትር፤ አሉባልታን እንደ እምነት፤ ትልቅ ሰውን ማዋረድን እንደ ጀግንነት፤ የሚወስዱትን ልቦ ናቸውን ያራራው ዓይናቸውን ይክፈትላቸው እያለ፡ ትዳር ለማፍረስ፤ ግለሰብ ለማዋረድ ፤ የተነሱትን ከመናቅ በስተቀር፡ የነሱን መንገድ መከተል ግን የድክመትም ድክመት እንደሚሆን ያምናል። አዛውንቶችን በመሳደባቸው አሸነፍን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ካሉ እየከሰሩ መሄዳቸውን እንጂ ማሸነፋቸውን እንደማያሳይ ማረጋገጥም ይወዳል ። ሳይሰደቡ ትዳራቸው የፈረሰው የተሳዳቢዎቹ እንጂ የተሰዳቢዎቹ አለመሆኑንም መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለናል። ለልጆቻችን ምን እያስተማርን ነው? ብለን መጠየቅ ያለብን ደግሞ ሁላችንም ነን። እከሌ ዘሩ እንደዚህ ነው ብሎ በዘር ግለሰብን መፈረጅ ደግሞ አዋቂነት ከመሰላቸው መቀጠል ይችላሉ። እስከዛሬ የተሰደቡትን ግለሰቦች በማየት ሰዳቢዎቹ እነማን እንደሆኑ ለመገመት በመቻሉ የከተማው ነዋሪ ጥሩ ግንዛቤ እንያገኘ መሆኑንም መናገር የተገባ ይመስለናል። ይህ ስድብ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ባህላችን አለመሆኑን የሚቀበል ማናቸውም የክርስቲያን አባል ይህንን የተቌቌመውን ኮሚቴ እንዲቀላቀል መረዋ ጥሪውን ያቀርባል።
ከቁልቌል ዛፍ እንጆሪ ይበቅላል፤ ከዶሮ ጅማት ማሲንቆ ይሰራል፤ ማለት ደናክል በረሃ ጤፍ ለማምረት እንደመጣር ያክል ነውና፡ ተሳዳቢዎቹም ይቀየራሉ ብሎ ማለም እንዲሁ ውሃ እየናጡ ቅቤ እንደ መጠበቅ ነው እንላለን።
ለኮሚቴው መልካሙን እየተመኘን የኮሚቴው ልሳን የሆነው መጽሔት ሥራውን ሲጀምር መረዋ የአባላትን የበላይነት በመቀበል የብሎግ እትምቱን እንደሚያበቃ ለአንባብያን በቅድሚያ ልናሳውቅ እንወዳለን።
እስከዚያው በሰላም ያድርሰን።