Sunday, August 1, 2010

እስረኛም መብት አለው። ቁጥር ፴፰

እንዴት ከረማችሁ ምእመናን።
እስካሁን ያሰነበተን አምላክ እንዲያከርመን ስንጸልይ፤ ለመልካም ተነስተናልና  ያሰብነውን ከግቡ እንደሚያደርስልንም ባለመጠራጠር ጭምር ነው። ብዙ የስድብ ውርጅብኝ ሰማን ችግራችን ግን አልተፈታም። ግለሰቦች የግል ሕይወታቸው አንሶላ ውስጥ አደረጉት የተባለው ሳይቀር ለአደባባይ ተነገረ  ችግራችን ግን አልተፈታም። መንፈሳዊ አባቶችን ከክርስቲያን በማይጠበቅ ቃላት ሲዘለፉና ሲወነጀሉ ሰማን ችግራችን ግን አልተፈታም። ቤት ትዳር ያላቸውን ካህን አንዴ  መምሬ  ወረድ ብሎ ደግሞ መነኩሴ  እያሉ ሲዘልፏቸው ሰማን ችግራችን ግን አልተፋታም።  ታዲያ  ስድቡ ለውጥ ካላመጣ መፍትሄ የሚገኘው እንዴት  ነው?  ብሎ  መጠየቅ ያዋቂ ብልሃት ነው እንላለን። አንድ በቅርብ የምናውቀው  ጔደኛችን  ስለሚጻፈው ስድብ ስንወያይ ያለውን እናካፍላችሁ። "በመጀመሪያ የተሰደቡት ግለሰቦቹ ሳይሆኑ ሕብረተሰቡ መሆኑን እንቀበል። የሰዎችን ጥፋትና  ድክመት መጠቆም፡  በሃሳብ ላይ መለያየትና  መከራከር  የተገባ ሆኖ ሳለ ግለሰቦችን ለማስፈራራት ያልተደረገ ፈጥሮ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲጧጧፍ ግን ባንድ ላይ ተነስተን ማውገዝ ሲገባን በዝምታ  መመልከታችን ለችግሩ ተባባሪ ያደርገናል። እስቲ የማውቀውን ላካፍላችሁ"  ያለን ይህ ግለሰብ "የማውቀውን ስላልተናገርኩ እኔንም ጥፋቱ ይመለከተኛል"  በማለት የሚከተለውን አጫወተን።

"በዚህ የስድብ ብሎግ ላይ ተፈራወርቅን እየተሳደቡ ቆይተው የሆሎታ  ምሩቅ  እንደሆነ ከሆሎታም የስንተኛ ኮርስ እንደሆነ  ጭምር  ሁሉ ጠቅሰው ዋሽተው ጽፈዋል። የሚገርመው ዘጋቢዎቹ ይህንን ያሉት አውቀው ሳይሆን የተደጋገመው ውሸት እውነት መስሏቸው ሊሆንም ይችላል። እውነቱ ግን ተፋራወርቅ በ 1965 ዓ ም  እንደ ኢትዮጵ አቆጣጠር ከሐረር መድሃኒዓለም 2ኛ ደረጃ  ት/ቤት ተመልምለው ከገቡት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ  የሐረር  ጦር አካዳሚ 19ኛ ኮርስ  አባል መሆኑን ላሳያችሁ ብሎ በ1999 መስከረም ላይ የታተመውን የጦር  አካዳሚውን መጽሃፍ አሳየን። መጽሐፉ ከ1950-1969ዓ ም ያለውን ያካተተ በፎቶግራፍ የተደገፈ ሆኖ  አገኘነው። የሚገርመው በመጽሐፉ ላይ የያንዳንዱን  መኮንን የትምሕርት ደረጃና አሁን  የት እንዳለ  ጭምር  የሚዘግብ ሆኖ  አነበብን። ለናሙና   ያክል ተፈራወርቅ አሰፋ  ሻለቃ እንደነበረና በማኔጅመንት የመጀመሪ ዲግሪውን ከአ አ ዩንቨርሲቲ  ማግኘቱን ብሎም በሶቬት ህብረት የማስተር ዲግሪ በፖለቲካ  ሳይንስ መመረቁን ይናገራል። ይህ እውነት እያለ  ለምን ይዋሻሉ ለሚለው አሁንም መልሱን ለናንተ እንተዋለን። ሻለቃ ተፈራወርቅ ያደረጉት ጥፋት ካለ መናገር መንቀፍ ሲቻል ካልነበሩበት ነበሩ ማለት ግን ወንጀል መሆኑን ማወቅ የተገባ ይመስለናል። ጥፋትን መጠቆምና  ሂስ ማቅረብ ሌላ ስም ማጥፋት ደግሞ  ሌላ።  የየካ ሚካኤል አስተዳዳሪ የነበሩትን አባት አልወደድንዎትም ማለት ሌላ ነገር ሆኖ  እያለ  ያላደረጉትን እያነሱ ያልሆኑትን እየፈጠሩ መሳደብ  ክርስቲያናዊ የሚሆነው የቱ ላይ እንደሆነ ሊገባን ግን አልቻለም ?  በውሸት ተሞልተው በቂም በበቀል ተጠቅልለው "ንስሃ  ግቡ"  የሚሉት ጸሃፊዎች ንስሃ  ምን እንደሆነስ  ያውቃሉን?  ብሎ ቢጠይቅ ጠያቂው እውነት አለው።

ችግራችን የሃይማኖት ሳይሆን የመብት ነው የምንለውም ከዚህ በመንደርደር ነው። እነዚህ በስድብ የተካኑ የብሎግ ጸሃፊዎች ከአስተዳደር ቦርዱ ጋር ያላቸውን ቅርበት ለማወቅ ደግሞ  እሩቅ መሄድ የሚያሻ  አይመስለንም። ባለፈው ተደርጎ  በነበረው ስብሰባ  ለይ ምን አጀንዳ  እንደነበረ ያነበብነው ስብሰባው ከመደረጉ በፊት በዚሁ ብሎግ ላይ እንደነበረ  መጥቀሱ ተገቢ ይመስለናል። ለቦርዱ በጽሑፍ ጥያቄ  ያቀረቡ ግለሰቦች መልሳቸው ሳይነገራቸው መከልከላቸውን የሚሰሙት በዚሁ በብሎግ ላይ ካነበቡ በኋላ  መሆኑን ይናገራሉ። ከቦርዱ ጀርባ የወደፊት እጣችንን  የሚወስኑልን የከተማችን ፈላጭና  ቆራጮች እንዳሉ ደግሞ ከሂደቱ ማየት ይቻላል። የቤተክርስቲያኑ ሊቀመንበር በመሃላ ባለፈው በፍርድ  ቤት ባስገቡት  ቃላቸው ላይ እዚህ ያሉትን መሃበረ ቅዱሳንን "የኮሚኒስት የናዚ የወጣት ሊግ አይነት ናቸው"  ሲሉ የተናገሩትን አውቀውት ነው ለማለት እንቸገራለን።

ስለ መብት በተነሳ  ቁጥር"አባል አይደላችሁምና አባል ሁኑና  እናወራለን " የሚሉት ቡድኖች የማይነግሩን ነገር ቢኖር።

1 አባል ለመሆን ፈቃጁ ቦርዱ መሆኑን "Amended Bylaw Article 2.1"

2 አባልነት ቢፈቀድ እንኴን አንድ ዓመት  ስብሰባ  የመካፈልና  የመምረጥ መብት እንደሌው "Amended Bylaw Article 2.1"

3 በአባላት የተመረጠው  ቦርድ ከአባላት በላይ መብት እንዳለው:: 2/3 አባላት ሳይስማሙበት (ምልአተ  ጉባኤ ሞልቶ በስብሰባ ላይ ከተገኘው   ውስጥ 2/3 ሳይሆን ከጠቅላላ አባላት ማለት ነው) ሕጉን ማሻሻል አይቻልም እያሉ በ2/3 ድምጽ ያልተመረጠው ቦርድ ግን ሕግ መቀየር ይችላል ማለታቸውን

5 አስመራጭ  ኮሚቴውን የሚመመረጠው ከኮሚቴ አባላት መሆኑን ሲናገሩ ኮሚቴውን የሚፈጥረው ግን ቦርዱ መሆኑን "ARTICLE 2.10"

6 ለቦርድ እጩ የሚሆን / የምትሆን ግለሰብ 2 ዓመት በኮሚቴ  አባልነት ያገለገሉ ወይንም 10 ዓመት በአባልነት የቆየ መሆን እንዳለባቸው ሲናገሩ ኮሚቴ  ውስጥ የሚገቡትን መራጮቹ የቦርዱ አባላት በመሆናቸው ለተመራጭነት የሕዝብ ድጋፍ ሳይሆን የቦርድ ፈቃደኝነት እንደሚያስፈልግ "ARTICLE 2.1"

7 ስብሰባ  ተጠርቶ  ሁለት ጊዜ ምልአተ  ጉባኤው ካልሞላ  አሁንም  በመጨረሻ  የተሰበሰበው ሕዝብ በድምጽ ብልጫ ይወስናል ሳይሆን ቦርዱ የተስማማበት ተፈጻሚ ይሆናል እንደሚል "ARTICLE 2.6"

8 ቦርዱ በማናቸውም ጉዳይ የቤተክርስቲያኑ ሃላፊ ነው በማለት ከአስተዳደር ባሻገር የሃይማኖትን ስልጣን  መጠቅለሉን "ARTICLE 1.1,  4.3, 7.3....." 

9 መተዳደሪያ  ደንቡ ላይ ያለው መብት ለሚደግፉት የሚሰራ ለተቃወመ የሚሰረዝ መሆኑን " ARTICLE 7.3, 7.1, 2.9, 9.1"

እነዚህንና የመሳሰሉትን ሸፋፍነው ማለፋቸው ነው። ታዲያ  በርእሱ ላይ እንደጠቀስነው የመብት  ነገር ሲነሳ እኛ መብት ስንል በኩልነት ላይ ያለ  መብት እንጂ   "ሁሉም  ሰው እኩል ነው ጥቂቶች ግን የበለጠ እኩሎች ናቸው" የሚለውን የሰነበተ  THE ANIMAL  FARM መጽሐፍ አይነት ማለታችን   አይደለም።  ስለመብት ካነሳን የታሰረም እስረኛ በእስር ቤቱ የተወሰነ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን የሚዘነጋው የለምና።

ስለመብት እንታገላለን የሚሉ ቡድኖች መብት እንዲደፈር ሲታገሉ ስናይ እናዝናለን። ስለሃይማኖት የሚሰብኩ ደግሞ  የስድብ አለንጋ  ሲያወርዱ ስናይ ደግሞ ምን እርግማን ነው ብለን እንተክዛለን። ባለፈው በነበረ የምእመናን ስብሰባ  ላይ ተነስተው የተናገሩት ግለሰብ "እኔ  መሰደቤ  መልካም ባገራችን እሬሳ  እናከብራለንና የሞተ ወንደሜን ስሙን ማንሳታቸው ግን ተሰማኝ" ሲሉ ከልብ ያላዘነ አልነበረም። "ከቤተክርስቲያኑ ፎቅ ላይ ሕጻናትን ሊወረውሩ ማቀዳቸውን ሰምቻለሁ" የሚሉትን ካመንን ምንም ነገር ማውራት ይቻላል። "ነገ በሬ ምጥ ያዘው እርዱን" ሲሉ ብንሰማ አይገርመንም ማለት ነው። ድሮ  አንድን ተናጋሪ "የወሬ አባትህ ማነው?" የሚሉ ግለሰቦች ዛሬ ለምን ይህንን ይሉ እንደነበር እየገባን እየመጣ ነው።

ታድያ መፍትሄው ምንድነው ለሚለው? መፍትሔው የአማንያንን መብት መጠበቅ ብቻ ነው። እምነትንና አስተዳደርን መለየት ካልተቻለ አሁንም ችግር ይኖራል። የብዙሃኑን መብት መርገጥ ለጊዜው ተችሎ  ይሆናል መረገጥህን ተቀበል ማለት ግን  የሚቻለው ማንም አይኖርም።
በእኛ እምነት የግለሰብን መብት እስካከበርን ድረስ የብዙሃኑን መብት ማስከበራችን ነው ብለን እናምናለን።

የእግዚአብሔር እርዳታ  ይታከልበት

ሰላም ሁኑ