Sunday, November 14, 2010

ጥርስ የሌለው ውሻ ጉልበቱ ከጩኸቱ ላይ ነው ቁጥር ፵፰

እንዴት ከረማችሁ

አዲስ የተከሰተ ነገር ባለመኖሩ ጊዜአችሁን ልናጠፋባችሁ አልፈለግንም፡፡ ለሥራ መሯሯጥ ደግሞ በዚህ አገር የግድ ነውና እንደምንራወጥ መሯሯጣችሁ ይገባናል ማለታችን ነው። ቢሉም ያራሩጣል ይሉ የለ። ሁሉም ነገር ትግል ሆነ። "ለምታበራቱን ድጋፋችሁ ላልተለየው ሁሉ ምስጋናችንን አድርሱልን። በረዳችሁን ቁጥር ሃላፊነት እየጣላችሁብን የጀመርነውን እንድንጨርስ እያደረጋችሁ ግፊት እየጣላችሁብን ነው ብላችሁ ንገሩልን"  ያሉት ለቤተክርስቲያናችን የመብት ትግል ግንባር ቀደምት ሚና  የሚጫወቱት ናቸው። እውነትም እኛም  ስናስተውለው ለጠበቃ የሚወጣውን ወጭ እናንተ  ምእመናን ባትጋሩት ኖሮ ለጥቂቶች ይከብድ ነበር ብለን አሰብን። የቦርዱ አባላት አሁንስ በቃ  እስክትሏቸው ድረስ እንደልብ የሚጽፉት ለጊዜው የማያልቅ የሚመስል ገደብ የሌለበት የባንክ ደብተር አላቸው። ገንዘብ ያላግባብ ማባከን አያስጠይቅም እንዴ? ብለው ሲጠይቁ ለነበሩ አባት በቦታው መልስ መመለስ አልቻልንም ነበር። አሁን እንመልስላቸው። አዎ  ያስጠይቃል ጠያቂው ግን  ምእመን መሆን አለበት። እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያለውን ጉዳይ ብትመለከቱት በዋናው ጉዳዩ ላይ ክርክር ሳይጀመር በስነስርዓት ነጥብ (PROCEDURAL ISSUE) ላይ መሆኑን እንደኛ ታዝባችኋልን? እኛ ካስተዋልነው ውሎ  አደረ።

ፖሊስ አታስመጡ፤ ምእመንን  ማባረር አትችሉም፤  ዶሴዎችንና ማናቸውንም የቤተክርስቲያኑን መረጃዎች አታጥፉ ተብለው ታዘዙ  ይግባኝ አሉ። ይህ ጉዳይ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ  እየጠበቀ  ያለ ነው።

ከከሳሾች ጠበቃ የቀረቡትን መጠይቆችን አንመልስም ብለው የቦርድ አባላት አሻፈረኝ አሉ። ይባስ ብለው የተከሳሾቹ  ጠበቃ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ አስቁሙልን ብለው ተማጸኑ።  ባለፈው እንደነገርናችሁ የሁለቱንም ጠበቆች ክርክር ሰምተው የተከበሩት ዳኛ ጥያቄዎችን የመመለስ ግዳጅ አለባችሁ ብለው ወሰኑባቸው። ይግባኝ ለማለትም 3 ቀን እንዳላቸው ነገሯቸው። አሁን የደረሰን ዜና እንደሚያስረዳን ይህንንም የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም የተከሳሾቹ ጠበቆች ይግባኝ ብለው ጉዳዩ  ለ DECEMBER 20  ተቀጥሮ ሁኔታውን የተከበሩት ዳኛ ስሚዝ በተባለው ቀን እንደሚያዩት ለመረዳት ችለናል።

በተጨማሪም በ DECEMBER 9 አሁንም የቦርዱ ጠበቆች ባጠቃላይ ክሱ ይሰረዝልን በማለት ለተከበሩ ዳኛ ስሚዝ የመከራከሪያ ዶሴ ( SUMMERY JUDGMENT) ማስገባታቸውና ይህም ለ DECEMBER 9, 2010 መቀጠሩን እንደነገርናችሁ የሚታወሰ ነው።

ባጠቃላይ ቀደም ሲል ሕጉን መቀየር ትችላላችሁ ተብሎ ከተወሰነላቸውና ይህም በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ካለው ጉዳይ ሌላ ይህንን አደረግን  የሚሉት የላቸውም። ይህንን ለማድረግ የከሰከሱት ገንዘብ ደግሞ ወደ $100,000 ደርሷል ወይንም አልፏል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህ ታዲያ ቤተክርስቲያኗ ከምእመናን ያጣችውን የገንዘብ ገቢ ሳያጠቃልል ነው። ይህንን ጉድ አናይም ብለው የተበተኑትን ምእመናን ደግሞ ወደ ገንዘብ መቀየር ስለማይቻል እንጂ ጉዳቱን የበለጠ የሚያስከፋ ያደርገዋል። በእኛ እምነት ከገንዘቡ የበለጠ የምእመናን ሽሽት ጎጅ ነው እንላለን። ታዲያ ሁኔታው የመብት ነውና የአማንያን መብት ሳናከበር ወደ ነበረበት መመለስ ይቻላል ብለው የሚሉትን ግለሰቦች መረዋ ሊጠይቅ የሚፈልገው ነገር ቢኖር የሚከተሉትን ነው፤

ማን ነው ሁለተኛ ደረጃ  ዜጋ ሆኖ የሚኖር?
ተመራጮች ነን ባዬች ፈላጭ ቆራጭ ያደረጋቸው ማን ነው?
የምእመን የበላይነት እንዴት ይከበራል?
ወጣቶችን አይደለም ሽማግሌን ከሚንቁ የቦርድ አባላት ጋር እንዴት መነጋገር ይቻላል?
አምባ ገነን ሆነው ቤተክርስቲያኑን  እየበተኑት ያሉትን መፍራት የሚቆመው መቼ ነው?
የሚቃወማቸውን ለማጥፋት ታጥቀው የተነሱ የቦርድ አባላት ሲያሰኛቸው ካህኑን፤ በረድ ሲሉ ጽዋ የሚጠጣውን፤ በፈቃደኝነት ሱቅ ውስጥ የሚያገለግሉትን፤ በፈቃደኝነት ወጣቶች የሚያስተምሩትን፤ በደጀሰላም የሚተባበሩትን ተባራችኋል እያሉ የሚበትኑን እስከመቼ  ነው?
ቤተክርስቲያኑን በጥቂት ተቆጣጥረው የሚበትኑበትን ቀን የሚጠብቁ መሪዎችን ከውጭ ስናወራ አይሰሙም እያልን እየተናገርን ስናያቸው ግን የምንሸማቀቀውና አንገት የምንደፋው እስከ መቼ  ነው?
የነሱ ጉልበት ሚካኤል ሳይሆን በድብቅ የሚጻፈው ጦማር (BLOGS) ሆኖ የሚቆየው እስከመቼ  ይሆን?
ፍቅር በመከባበር እንጂ በፍርሃትና በስድብ ይመጣልን?
በሕግ አምላክ ብሎ ወደ ሕግ መሄድ ነው የሚያስነውረው ወይንስ በተፈጠረ ጦማር መሳደብ?
የሚሰደቡት ናቸው ጥፋተኞች ተሳዳቢዎቹ? መመለስ ያለብን  እንደ ግለሰብ እያንዳንዳችን መሆን አለብን።

ለማንኛውም የሚነዛውን የውዥንብር ወሬ  ሳይሆን እውነቱን በራስ ተመራምሮ  ማግኘት ክርስቲያናዊ ግዴታም  ነው እንላለን።

ባለፈው እንደነገርናችሁ "እኛ እንዳየነው ጥፋቱ ሙሉ ለሙሉ የመልከኛው  ነው ካሳውን ግን ገበሬው ይካስ" አይነት ፍርድ የሚቀረው መቼ ነው?  አንድ እናት ባንድ ግብዣ ላይ "ልጆቼ ካወቃችኋቸው እነዚህን ከሳሾች ክሱን አቁሙ በሏቸው" ብለው ሲናገሩ አንዱ አዳማጭ እማማ የቦርዱን ተመራጮች ለምን ተው በሏቸው አላሉም?  ብሎ ለጠየቃቸው ሲመልሱ  "እያወቃችሁ እነሱ እንኴን ሰው ሚካኤልንም አያዳምጡም" አሉ ተብሎ  ነበር። ይህንን ያመጣነው ለቀልድ  ሳይሆን ያለውን ስሜት ለማሳየት ነው።

ለመብት የተነሱት ከሳሾች በእምነት አልከሰሱም በደረሰባቸው የመብት እረገጣ እንጂ። ክስ የመሰረቱት እናት የከሰሱት እንደሰማነው በሃይማኖት ጉዳይ አይደለም በደረሰባቸው በደል እንጂ። ታዲያ ይህንን ያደረገውን ዝም ብለን እናያለን የሚሉ ሁሉ ቤተክርስቲያኑን እያፈረሱ መሆኑንን  መረዳት ይኖርባቸዋል። 

ሁላችሁም ከቻላችሁ በሚመጣው DECEMBER  9 ከፍርድ ቤት በመገኘት የፍርድ ቤቱን ጉዳይ እራሳችሁ እንድትከታተሉ ጥሪ እናቀርባለን። ዜና ስትፈልጉ  ወደ መረዋ  ስድብ ለመስማት ደግሞ ወደሌላው ጦማር ጎራ  በሉ።

የሳምንት ሰው ይበለን።