Thursday, November 25, 2010

መረዋ ዛሬ ዓመት ሞላው ቁጥር ፵፱

እነሆ መረዋ ከተመሰረት ዛሬ አንድ ዓመት ሞላው። ባለፈው እንዳልነው አሁንም እንኳን አደረሳችሁ እንላለን። ዓመት ማለፉን ከማስላት በስተቀር የተቀየረ ነገር ግን የለም። የሚገርመው የዛሬ ዓመት መረዋ የጻፈውን ስናነብ ዛሬ የተጻፈ መሰለን። አንባብያን እንድታነቡና እንድትፈርዱ የዛሬ ዓመቱን እትምት እንዳለ ከዚህ ጽሑፍ ግርጌ እናቀርብላችኋለን።
ዛሬ ዓመት ሞላን ብለን ሻማ አናበራም ሰላሙን ስጠን ብለን እንጂ።
የማንወዳቸውን አጥፋልን ብለን አንጠይቀውም ልቦናቸውን ክፈትላቸው  ብለን እንጂ። በሞቱ አንደሰትም፥ በታሰሩ ጮቤ አንረግጥም ከክፉ ሁሉ አድነን እንላለን እንጂ።
ትዝ ቢላችሁ የዛሬ ዓመት መረዋ ከሌላ ጎን የሚረጨውን የውሸት ወሬ ለመቋቋም ብሎም እውነተኛውን ዜና ለምእመናን ለማዳረስ ይህንን ጦማር ከፈተ። ጦማሩ በመከፈቱ  የተናደዱ ቢኖሩ እውነት መስማት የሚያስፈራቸው በስድብ የተካኑ ስም በማጥፋት የነገሱ ምእመናንን  በትነው ቤተክርስቲያኑን ሳይሆን ንብረቱን እንካፈላለን ብለው የሚያልሙ ደካሞች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ  ቅዠት ሆኖ ይቀራል እንጂ ሕልም እንኳን እንደማይሆን አሁንም ቃል እንገባላችኋለን። የኛ ጥንካሬና ጉልበት የሚካኤልና የምእመናን ድጋፍ ነውና። በድጋፋችሁ እዚህ ደርሰናል የምስራቹን አብረን እንደምንሰማ አሁንም አንጠራጠርም።

ለእምነት መሰደብ አይደለም መገደልም ያለ ነው። በዛኛው ብሎግ በወሲብ የተሰደባችሁ፤ ትዳራችሁ እንዲፈርስ የውሸት ወሬ የተነዛባችሁ። ሰላም ይፈጠር በማለታችሁ ከካህን ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት አላችሁ ተብሎ የተጻፈባችሁ። የከሰሱት እውነት አላችው በማለታችሁ የውሸት አሉባልታ የተነዛባችሁ። ቤታችሁ በድንጋይ የተደበደበ። መኪናችሁ የተሰበረ። ማስጠንቀቂያ በግለሰብ የደረሳችሁ። አገርቤት ያለው መንግሥት ሰላዬች ተብላችሁ የተወነጀላችሁ። የመንግሥት ግብር አልከፈላችሁም ተብላችሁ ማስፈራሪያ የደረሳችሁ። ሁሉ ዛሬ ከተሳዳቢዮቹ በላይ መሆናችሁን እንዳትጠራጠሩ። እዚህ አካባቢ የግለሰብ ሕይወት  ቢጠፋ ተጠያቂዎቹ ደግሞ የስድቡን ጦማር የሚያቀነባብሩት ግለሰቦች ለመሆናቸው ካሁኑ ማሳሰብ እንወዳለን። እኛ ግን እየተሰደብንም ማስፈራሪያ  እየደረሰንም ለመብታችን መታገላችንን  አናቆምም። እውነትን በመያዛችን ትላንት ከማዶ  የነበሩ ዛሬ ከብዙሃኑ እየተቀላቀሉ ነውና። በድጋሜ እንኳን አደረሳችሁ!!!!! 
DECEMBER 9, 2010
ባለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሁላችሁም እንድትገኙ  ጥሪያችንን እያቀረብን።
የዛሬ  ዓመት የተጻፈውን መረዋ እንደገና እንድታነቡት እንጋብዛችሁ።

ይቅርታ የክርስቲያን ባህርይ ነው ቁጥር ፩


                                                                                                 Thursday, November 26, 2009

በዛሬው (THANKSGIVING) የፈጠረን አምላካችንን ተሰባስበን በምናመሰግንበት እለት፡የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ፡ የፍቅር ዝናብ እንዲያካፋ፡ የይቅርታ ጥላ እን ዲያጠላብን መፀለይ የተገባ ከመሆንም አልፎ ክርስቲያናዊ ግዳጅችን መሆኑን መቀበል የግድ ይሏል። በቂም በቀል የሚመራ ክርስቲያን ከመሃከላችን ካየን በጸሎት በምክር መርዳትም እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ግዳጃችን መሆን ይኖርበታል። እንዳንስማማ የተስማማን ይመስል በሁሉ ነገር ተጣልተን እስከመቼ እንዘልቃለን? ብለንም እራሳችንን ብንጠይቅ ምን አልባት ካንቀላፋንበት እንባንን ይሆናል። ውድ የቤተክርስቲያን አባላት በዛሬው የፈረንጆቹ በዓል እንድታደርጉ የምነጠይቃችሁ ነገር ቢኖር ሁላችሁም በቤተክርስቲያናችን የተከሰተውን መለያየትና መናቆር እንዲቆም በጸሎት እንድታስቡት ብቻ ነው። ከደጋፊና ከተቃዋሚ እየተባለ የሚጻፈውን የስድብ ውርጅብኝ፡ የቃላት ሽኩቻ አንብበናል። "መሳሪያ የታጠቀ ሁሉ ነፃ አውጭ ነው" ማለት ስህተት እንደሆነ ሁሉ፡ የተነገረው በሙሉ እውነት ነው ብሎ መቀበል የዋህነት ይሆናል። እያንዳንዳችን ምን እያደረግን ነው? ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ ምንአልባትም የችግሩ መልስ በቀላሉ የሚገኝ ይመስለናል። "ሽማግሌዎች ቢኖሩ ኖሮ እዚህ አንደርስም ነበር" ለሚሉት እውነት አላችሁ እያልን፡ አባባላቸውን ስንጋራ፡ "አሁን ለምን ሽማግሌዎች ሊያስታርቁ ተነሱ" ብሎ መተቸትና መሰናክል ለመፍጠር መነሳት ግን ሌላ ስህተት ነው ብለን ደግሞ እናምናለን። በፍርድ ቤት ትእዛዝ ችግራችን ይፈታል ብሎ የሚያምን ካለ የዋህ ነው ብሎ መናገር ማስፈራት የለበትም። ፍርድ ቤት በሚሰጠው ብያኔ ፍቅር አይመጣም አንድነት አይፈጠርም። ይህ ሊሆን የሚችለው የተለያየ ሃሳብ ይዞ የሚከራከረው ቡድን ተቀምጦ መነጋገር ሲችል ብቻ ነው። ክስ የመሰረቱትን ለምን ክስ መሰረቱ ብሎ መኮነን ደግሞ ሲደረግ የነበረውን መካድ ይህንን ባያደርጉ ኖሮ ዛሬ እንደዚህ ለመናገር የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንሆን እንደነበር አለመቀበል ይሆናል። የቤተክርስቲያን ገንዘብ ስላለ ከሳሾቹን ገንዘባቸውን አስጨርሰን እንዲሸነፉ እናደርጋለን የሚሉት የቤተክርስቲያኑ ተመራጮች ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር የተመኩበት ገንዘብ ከምእመናን የተዋጣ መሆኑን ነው። ምእመኑ ካልደገፈ የገንዘቡ ቌት እንደሚሟጠጥ ከሳሾችንም ከአሁኑ በበለጠ እየደጎሙ እየደገፉ እንዲቀጥሉ ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ማሰብም የተገባ ነው። ከሳሶችም ሆኑ የቤተክርስቲያኑ ተመራጮች ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር ያለ ምእመን ድጋፍ የትም ሊሄዱ እንደማይሄችሉ ነው። በተናጠል ቤተክርስቲያን አይገነባምና። ተሰዳደብን፡ ተካሰስን፡ ተወነጃጅለን አሁን ደግሞ ወደ አንድነት ለመምጣት ምን አስተዋጽኦ እናድርግ ብሎ መነሳት ክርስቲያናዊ ነውና ሁላችንም በተናጠል እራሳችንን ጠይቀን ለሰላም እንነሳ። እከሌን ብናገረው እንጣላለን ከመሃበር ያባርሩኛል ያልሆንኩትን ስም ይሰጡኛል፡ ዝምድናችን ይፈርሳል ጔደኝነታችን ይቀራል በቡድን ያጠቁኛል ብሎ በመፍራት ለእውነትና ለመብት አለመነሳት ደግሞ በሕሊና ማስጠየቅ ይኖርበታል እንላለን። ስለሆነም ለሁላችሁም ዛሬ ጥያቄዎች ማቅረብ እንወዳለን። በግል ምን እያደረግን ነው? ሰለኛ ሌሎች እስከመቼ ይወስናሉ? መብትና እምነት፡ ሕግና አምልኮን መለየት የምንችለው መቼ ነው? ከራሳችን ጋር እንዴት እንታረቃለን? መንፈሳዊ አባት እየዘለፍን እንዴት መንፈሳዊ ነን ማለት እንችላለን? መንፈሳዊ አባቶቸስ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ሲያልፉ እንዴት እናስቆማቸዋለን? የነዚህን ጥያቄዎች ከመለስን የችግሩን ብዙውን ጎን ቀረፍነው ማለት ነው ብለን እንስማማ።
አሁን ምንእላለሁ ከምንስ ላይ ቆሜ፡
የገደለው ባሌ የሞተው ወንድሜ።ይሉ አልነበር።