ዛሬ የምንጽፈው ባለፈው ቃል እንደገባንላችሁ የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ ለናንተ የሰማነውን ለማካፈል ነው። እንደ ሌሎቹ "ምሑራዊ" ትንተና ልንሰጣችሁ አይደለም። አንባቢዎቻችን ክፉና ደጉን ማበጠር እንደምትችሉ፤ እውነትና ውሸትን እንደምትለዩ፤ የነገሮችን አካሄድ ጠንቅቃችሁ እንደምትገነዘቡ እናውቃለንና። ዛሬ በዛኛው ጎራ እንዳነበባችሁት ሥም እየጠራን ልንሰድባችሁ አይደለም። ይህ የነሱ እንጂ የኛ ባሕርይ አይደለምና። ለዚህ አይነቱ ስድብ አስተዳደጋችንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ስለሚገታን። ሌላውን ስንሳደብና ስናንቋሽሽ የሚታዩን ያሳደጉን ቤተሰቦቻችን በመሆኑ፡ አሳዳጊ የበደለው ተሰኝተን መሰደብ አንወድምና። ሃላፊነታችን የነበረውን እንዳለ ማቅረብ ብቻ ይሆናል። ፖለቲካ ከቤተክርስቲያናችን መውጣት አለበት ስንል ካየነውና ከታዘብነው ብሎም ከሚጽፉት በመነሳት ነው። ከዋሸን እነሱ ጋ ጎራ በማለት በማንበብ ማመዛዘን ይቻላል። እኛ ደግሞ ቃላችንን ከወለድነው ልጅ የበለጠ እናከብረዋለን። እኛ አፕልና ብርቱካን እንደማናደባልቅ ደግሞ ምስክሮቻችን እናንተ ናችሁ። ስለብርቱካን እያወራን ስለ አፕል መዘባረቅ አለመደብንም። ይህንን የሚያደርግ በግንዛቤ ሰንካላ ወይንም ድኩም የሆነ ብቻ ነው ብለን ስለምናምን።
ለመግቢያ ይክል ይህንን ካልን በኌላ በዛሬው እለት ስለዋለው ችሎት እናውሳችሁ።
በቦርዱ ጠበቆች ማመልከቻ መሰረት ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረውን ጉዳይ የተመለከቱት ዳኛ የተከበሩ ሸርሊን ማክፈርላንድ ነበሩ። ዳኛዋ የካውንቲው እረዳት ዳኛ (ASSOCIAT JUDGE) ናቸው። ጉዳዩን ስላላነበብኩት አስረዱኝ ያሉት ዳኛ ከቦርዱ ጠበቆች የቀረበ ገለጻና የከሳሾችን ጠበቃ መልስ አዳምጠዋል። በመሰረቱ ክሱ የከሳሽ ጠበቃ ይሰጡኝ ብሎ የጠየቀውን ከ50 በላይ የሆኑ ጥያቄዎች አንሰጥም በማለት የቀረበ ክርክር ነበር። በጥቅሉ የቦርዱ ጠበቆች ክርክር የነበረው ከሳሾች የሌላ እምነት ተከታዬች በመሆናቸው፡ ከዚህ በፊት በሌላ ክስ የከሰሱ በመሆኑ፡ አባላት ባለመሆናቸው፡ ይህ የእምነት ጉዳይ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የማየት ስልጣን ስሌለለው ጥያቄውን ያስቁምልን የሚል ነበር። የከሳሾች ጠበቃ በበኩሉ የጠየቃቸው ጥያቄዎች አንድም የእምነት ነገርን እንዳልያዘ በመጥቀስ ለናሙና ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
1 የአባላት ዝርዝር
2 የቦርድ አመራረጥን የሚያሳይ ሰነድ
3 የገንዘብ ወጪና ገቢ ሰነድ
4 ቃለጉባኤ
5 የደብዳቤ ልውውጦች ወዘተረፈ መሆናቸውን አስረድቷል።
የተከበሩ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ሁኔታውን ካዳመጡ በኋላ የቦርዱ ጠበቆች የተጠየቁትን ሰነድ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲሰጡ ወስነዋል። ተከሳሾቹ በውሳኒያቸው ካልተስማሙ ለዋናው ዳኛ 3 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይግባኝ ብለው በተከበሩ ዳኛ ስሚዝ ፊት በመቅረብ መከራከር እንደሚችሉ ነግረዋቸዋል። የተከሳሾች ጠበቃ በውሳኔው ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የጠየቁትንም ሆነ ዶሴዎቹን ከእኔ ቢሮ መጥተው እንዲያዩ ይታዘዝልኝ ብለው ያሳሰቡትን ዳኛዋ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ይህ የዛሬው የከሳሾች ድል ጉዳዩ የሃይማኖት ሳይሆን የመብት ጉዳይ ለመሆኑ ሌላ ማረጋገጫ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሚመጣው ወር ማለትም በ12-09-2010 የቦርዱ ጠበቆች ክሱ ይሰረዝልን በማለት ሌላ የፍርድ ሃሳብ ያስገቡ መሆናቸውን እየነገርናችሁ በዚያም ቀን በተከበሩት ዳኛ ስሚዝ ችሎት የሚደረገውን ክርክር ውሳኔ እንደምናቀርብላችሁ ካሁኑ ቃል እንገባለን።
እውነት ሁልግዜም እውነት ነው።
እውነት እንደሚያሸንፍ የሚጠራጠር ደግሞ እምነተቢስ ነው።