ባለፈው እንደ ነገርናችሁ በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰላም መፍተሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በትላንትናው እለት ጠርቶት የነበረው ስብሰባ በመግባባትና በሙሉ ስምምነት መገባደዱን የደረሰን ዜና አስታውቋል። በወቅቱ በተደረገው ስብሰባ የተገኙት እንግዶች ከምሳ ግብዣው በኋላ ሰፊ ውይይት እንዳደረጉ ሲነገር፣ በወቅቱ የአራቱም የኮሚቴው ተወካዮች በየተራ ለተሰብሳቢው ስለተደረገው ያለፈ የኮሚቴ የስራ ክንውን መግለጫ መሰጠታቸውንም ለመረዳት ችለናል። በዜናችን መሰረት የመንፈሳዊ ኮሚቴ አባላት ከቤተክርስቲያናችን እየተገፉ የሚገኙትን አባላት መንፈሳዊ ጽናታቸን ለማጠናከር በዓርብ ምሽት የሚደረጉትን ትምህርቶች በየሰዎስት ወሩ የተዘጋጁትን የመንፈሳዊ ጉባኤዎች በሚያስደንቅ መልኩ ማካሄድ እንደቻሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል። ይህንንም ማድረግ የተቻለው ዓርብ ማታ በሚደረገው መንፈሳዊ ትምህርት ተካፋዮች ጉልበትና ከኪስ በተዋጣ ወጭ እንደ ሆነም የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ተናግረዋል። በወቅቱ ኮሚቴውን በማሰባሰብና በማስተማር በመምራት ያገለገሉት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በሌሊት በፖሊስ ተከበው የመሰናበቻ ወረቀቱን እንዲፈርሙ የተገደዱትና፡ ከቤተክርስቲያኑ ቦርድ ለኢሚግሬሽን በተጻፈ ደብዳቤ የኢምግሬሽናቸው ሁኔታ እንዲታገድና ከአገር ከነቤተሰባቸው እንዲባረሩ የተጠየቀባቸው መላከ ሳህል አወቀ ሲደልል እንደ ነበሩ ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት መላከ ሳህል አወቀ አትላንታ የሚገኝ ደብር ቀጥሯቸው ወደ አትላንታ መሄዳቸውም ለተሰብሳቢው ተገልጿል። ስለሆነም ቀደም ብለው ወደ አዲሱ ሥራቸው የተዛወሩት መላከ ሳህል አወቀ የዳላስን ምእመናንን ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት በፊታችን ዓርብ 1/28/2011ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ባሻገር በሚገኘው የኬንያውያን ቤተክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ እንደሚገኙ ሲነገር፡ ማንኛውም ምእመን ቤተሰባቸውንና እሳቸውን ለመሰናበት በዚሁ እለት እንዲገኝ ኮሚቴው ለሁሉም የዳላስ ምእመን ጥሪውን አቅርቧል። በዚህ አጋጣሚ መረዋ ለኝህ ቆራጥ ካህን ያለውን አድናቆትና ያላቸውን ቆራጥነት እያደነቀ፤ መጭው የሥራ ቦታቸው የተቃና እንዲሆን ምኞቱን ይገልጻል። መላከ ሳህል አወቀ እንደ አባት የሚርቁብን ቢሆንም ምሳሌነታቸው ግን ከልባችን ለዘላለም ይኖራል። የመንፈስ አባቶ ችን ስናነሳም እንደ ምሳሌ የምንጠቅሳቸው ይሆናሉ። ለቤተሰቦቻቸው ያለንንም አድናቆት ስንገልጽ በደስታ ነው። በተለይ ለውድ ባለቤታቸው መረዋ ያለውን አክብሮትና የመንፈሰ ጠንካራነት አርአያ መሆናቸውን መመልከቱን ሲጠቅስ በኩራት ነው።
የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ተዋካይ ደግሞ በተለያየ መንገድ ለአባላት የተላኩ መልእክቶች እንዲዳረሱ ማድረጉን በመናገር የኮሚቴው ልሳን የሆነው WWW.MELEKET4U.BLOGSPOT.COM ከመቼውም በበለጠ ከዚህ በፊት የተደረጉትንም ሆነ ወደፊት የሚደረጉትን ለአባላት ለማስነበብ በገጹ ላይ እንደሚለጥፍ ቃል ከመግባቱ ባሻገር ከብሎግ አልፎ WEB PAGE ወደፊት ለማውጣት እቅድ ላይ መሆኑን ተናግሯል።
የአባላት ኮሚቴ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የደጋፊዎቻችን ቁጥር ከ200በላይ እንደሆነ በመጠቆም አሁንም ከሌላው ወገን የሚሰነዘረውን የውሸት ወሬና ስድብ በተቋቋምን ቁጥር ካስተዋልኩት ደጋፊዎቻችን እየበዙ መሄዱን አውቃለሁ በማለት ጠቁመዋል። ለዚህም ዋናው መሳሪያችን ሲሳደቡ አለመሳደባችን፣ አለመዋሸታችን፣ ስንጀምር ያነሳነው የመብት ጥያቄ አሁንም በእንጥልጥል መሆኑና አለመዋዠቃችን እንደሆነ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።
የሕግ ኮሚቴ ተወካይ በበኩላቸው ቤተክርስቲያን እንዴት ይከሰሳል የሚሉት ግለሰቦች ለምን የአባላት መብት ይደፈራል? ሲሉ ያለመሰማታቸውን ተናግረው፡ ለመብት እንቆማለን ያለ ማንም ግለሰብ መብቱ ሲጣስ ያለው አማራጭ በጉልበት መጠቀም ሳይሆን በሕግ መከላከል ብቻ ነው፥ ብለው የሚገርመው ቤተክርስቲያንችን ተከሰሰ ያሉት የቦርድ አባላት ባዲስ መልክ እንደ መከላከያ ያመጡት ነጥብ ቢኖር በቦርድ አባልነታችን በግል መከሰስ የለብንም ቢፈልጉ ከሳሾች ቤተክርስቲያኑን ይክሰሱ ብለው ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል። ሆኖም ከትላንትናው በተሻለ ሁኔታ ጉዳዩ እየተፋጠነ መሆኑን አብራርተው ስለፍርድ ቤቱ ሁኔታ አጭር ገለጻ አድርገዋል፡፡
በገለጻቸው መሰረት ከዚህ በፊት ዳኛው ምእመንን ከቤተክርስቲያን አትከልከሉ። ፖሊስ ወደ መቅደስ አታስገቡ። ዶሴዎችና ማናቸውንም መረጃዎች አታጥፉ ብለው ያዘዙትን ትእዛዝ አንስማማም በማለትምእመንን የማባረር መብት አለን፣ ፖሊስ በመቅደስ ውስጥ ማስገባት አለብን፣ ዶሴዎችንና ማናቸውንም መረጃዎች እንድናጠፋ ይፈቀድልን፣ ብለው ይግባኝ ባሉት መሰረት በ 2/7/2011 3:00PM ላይ በ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት 3 ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የከሳሽና የተከሳሽ ጠበቆች 30 ፤ 30 ደቂቃ ተሰጥቷቸው ክርክር ስለሚያደርጉ ማንኛውም ሰው፥
600 COMMERCE DALLAS COUNTY COURT BUILDING 2nd FLOOR በመገኘት ማዳመጥ እንደሚችል ተናግረዋል።
በተጨማሪ በ 2/10/2011 192court በመገኘት ባለፈው እረዳት ዳኛ በቦርዱ ላይ የፈረዱባቸውን የከሳሾችን ጥያቄዎች እንዲመልሱ የታዘዙትን ቦርዱ አሻፈረኝ ብሎ ይግባኝ ባለው መሰረት ዳኛ ስሚዝ ፊት ቀርበው የሁለቱም ጠበቆች እንደሚከራከሩ ስንነግራችሁ አሁንም የምትችሉ ሁሉ ከላይ ባለው አድራሻ በ 9:00 AM በመገኘት እንድታዳምጡ ብለው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። አያይዘውም ዳኛው በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጡት ብይን ይግባኝ የሌለውና የመጨረሻ መሆኑንም ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።
በመደምደሚያው የስብሰባው ሰብሳቢ፣ ሁሉም ላደረጉት እርዳታ ከልብ መነካታቸውን ተናግረው ለመብት አለመቆም በራሱ ድክመት መሆኑን ተናግረዋል። በተለያየ መንገድ እርዳታ የሚያደርጉትን ግለሰቦች አመስግነው አሁንም እርዳታው እንዲቀጥል አሳስበዋል።
መረዋ ሁላችሁንም በተባሉት የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች እንድትገኙ ጥሪውን እያስተላለፈ ለዛሬው በዚሁ እንሰናበታችኋለን።
የሳምንት ሰው ይበለን።