Friday, December 25, 2009

ዳኛው ውሳኔ ሰጠ ቁጥር ፮

ከሁሉም በማስቀደም እንኴን ለፈረንጆች ገና አደረሳችሁ እያለ መረዋ ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል።

በቤተክርስቲያናችን እየተፈጠረ ያለውን መከፋፈል በመመልከት በመረዋ መጽሔት በተደጋጋሚ አሸናፊ አይኖርም ብለን መናገራችን ይታወሳል። ዛሬም ዳኛው ሕጉን የመቀየር መብት ቦርዱ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 11.2 መሰረት አለው ብሎ ከተከሳሽ ጠበቆች ጋር መስማማቱን ይፋ ያደረገው ማክሰኞ እለት መሆኑን ለመስማት ችለናል። ባለፈው እንደነገርናችሁ ዳኛው የቦርድ አባላትን ሲናገር "ይህንን የምታደርጉት አባላትን ከቤተክርስቲያኑ ለማባረር፤ በስልጣናችሁ በመጠቀም አባላትን አስገብራችሁ ለመሰንበት፤ ቤተክርስቲያኑን በጥቂት ግለሰቦች እጅ አስገብቶ ፈላጭና ቆራጭ ሆኖ ለመቀጠል ነው።" ያለውን እንደ ምክር ቦርዱ የወሰደው አልመሰለንም። "ተስማምቶ ልጅ መውለድ እያለ በጉልበት ደፍሮ ማስረገዝ " የተለያዩ መሆናቸውን እንዳለማወቅ አይነት መሆኑ ነው። በሚመጣው እሁድ የአስተዳደሩ ቦርድ ወንድሞቼ አሸነፍን እንደሚልና ደሰተኛ መሆኑን በደጋፊዎች እልልታና ጭብጨባ ለማሳጀብ እንደተነሳ እወቁ ብለን ያናገርናቸው ከሳሾች ያሉን ነገር ቢኖር ከሳምንት በኋላ ደግሞ እንደለመዱት ተከሰናል እንደሚሉ በእርግጠኝነት ልንነግራችሁ እንወዳለን የሚል ነበር። ከአባባሉ እንደተረዳነው ክሱ ከትላንትናው በከፋ መልክ እየቀጠለ መሆኑን ነው። ወንድሞችና እህቶች ቀደም ብለን አሸናፊ አይኖርም ያልናችሁ ለዚሁ ነበር። የተናገርነው እውነታው እየታየ ነው። በመሃከሉ የሰማንው ጥሩ ወሬ ቢኖር ተጣልተው የነበሩት የቦርድ አባላት በሽማግሌ የመታረቃቸው ዜና ነው። የነሱ መታረቅ ጥሩ ሆኖ እያለ "ከከሰሱን ጋር አናወራም" ማለታቸው ግን እየገረመን እየመጣ ነው። ለጠበቃ ያወጣንውን እናስከፍላለን ብለው ቢነሱም ዳኛው አታስከፍሉም ስላለና ስለወሰነ መናደዳቸውን በየቦታው እየዞሩ የሚናገሩት የቦርድ አባላት በሁለቱም ወገን የሚጠፋው ገንዘብ የዚሁ የቤተክርስቲያን አባላት ንብረት መሆኑንን ሊገነዘቡ አለመቻላቸው ይደንቀናል። በነሱ ወገን አላግባብ ገንዘብ ማባከንም ተመልሶ በግለሰብ ሊያስጠይቅ እንደሚችል ማወቅም ይኖርባቸዋል። ማንም ይሁን ማን በቤተክርስቲያን ጉዳይ ቂም ይዞ ባይሄድ ጥሩ ነው። የቦርድ አባላት ከሳሾቹ የሂትለሩ የናዚ ፋሺስት ፓርቲ የወጣት ማህበር አባላት አይነት ናቸው ብለው በመሃላ ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሲሰጡ ማፈር ነበረባቸው። ወንድሞችና እህቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የጨረሰውን ናዚን ከወንድሞችና ከእህቶት ክርስቲያኖች ጋር ማመሳሰል ወንጀል ነው። ብልግና ነው። ቦርዱ አዲስ ኮሚቴ አቌቁሞ ሕጉን እንደገና ለማሻሻል እያስጠና መሆኑን እንደኛ ሰምታችሁ ይሆናል። ባለፈው የተቀየረው እንዳስፈራን የዛሬው ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ብለን መፍራታችን አልቀረም። ፍራቻቸን ለሌላ ክስ መነሻ መንደርደሪያ ወይም ማጠናከሪያ ይሆናል እንጂ በተያዘው መልክ መቀጠሉ ጥቅም የለውም ብለን ስላመንን ነው።


የቦርድ አባላትም ሆኑ ካሳሾች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ቢኖር። ይህ የቤተክርስቲያን ጉዳይ መሆኑንና በቤተክርስቲያን ጉዳይ ደግሞ ስልጣን የሚኖረው የመንፈሳዊ አባቶች መሆኑናቸውን ነው። ለነገሩ ይህንን ቦርዱ የያዘው መንገድ መሆኑንና መከራከሪያውም እሱ እንደሆነ የተቀበል ለመሆኑ "ይህ ጉዳይ በሲኖዶስ በኦርቶዶክስ እምነት መፈታት ያለበት እንጂ በፍርድ ቤት መሆን የለበትም" ብሎ በመከራከሩ ሌላ አዲስ የማስታረቂያ መንገድም እንደከፈተ መታወቅ አለበት እንላለን። ሁላችንም ቦርዱ እንዳለው ሁሉ በሲኖዶሱ ማመንና የሲኖዶሱን ሕግ መቀበል ይኖርብናልና።


በነገራችን ላይ ልብ ብላችሁ መተዳደሪ ደንቡን ብታነቡት ይኸው የሚያጣላው የሕግ አንቀጽ 11.1 ላይ " ......... የኢትዮጵ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ሕግና ስርዓት ተከትሎ" ደንቡ መሻሻል እንደሚችል ያሳስባል። ምን ማለት ነው? ለአንባብያን እንተወው። በየወሩ ሕግ ከማሻሻል ይልቅ ተሰብሰቦ በመወያየት የችግሮችን መንሰኤ አውቆ የማያዳግም መልስ መስጠት ይበጃል ብለን አሁንም ስለምናምን ልባችንን ሰፊ ብናደርግና ለሰላም ብንነሳ መልካም ነው። ክሱን አሸነፍን ብለው የተደሰቱ ካሉ የተከፉትን አለማጤን ይሆናል። ክርስቲያን ደግሞ ወንድሙ ሲበሳጭ የሚደሰት አይደለምና። ከሳሾች ክስ የመሰረቱት "እምነት ብለው ሳይሆን የመብት እረገጣ ሲበዛ፤ ቦርዱ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ አንጋፋዎቹን እየገፋ የማናውቃቸውን አዲስ መጤዎች በማስገባት ስለበጠበጠን። ቦርዱ አስተዳደርን አልፎ የመንፈሳዊ አባት ሊሆን ሲሞክር፡ ክርስትና የሚያነሱትን ማስከፈል ሲጀምር፡ የሌለ ክፍያ በጉልበቱ ሲተምን። አይደግፉኝም ብሎ የጠረጠራቸውን አባላት ከኮሚቴ ሲያባርር። በፖሊስ ለማፈን ሲሞክር። ስብሰባ ይጠራና እንወያይ ያሉትን እንደወንጀል በመቁጠር በሃሰት " የከሳሽ ደጋፊ ወይንም ከሳሾች ናችሁ ብሎ የመናገር መብታቸውን በመግፈፉ"............. ነው ብለው ይናገራሉ። ይህንን ደግሞ አልሆነም የሚል እስካሁን አላጋጠመንም። አልሆነም ሲሉ የሰማነው የቦርድ አባላት በፍርድ ቤት በመሀላ ብቻ መሆኑን ታዝበናል። "አባላት አይደሉም ከሚለው ጀምሮ የፈረመ ሁሉ ከሶናል" እስከሚለው ድረስ። ለዚህም ነው ፍርድ ቤት እየተዋሸ ቤተክርስቲያን ተመልሶ ንስሃ ከመግባት ይልቅ ምን ሆንክ? ምን ሆንሽ? ብሎ በመወያየት ዘላቂ መፍትሄ ማግኘቱ ይሻላል የምንለው። ከሳሾች በመክሰሳቸው ሊወገዙ አያስፈልግም መወገዝ ካለብን ተወጋዦቹ እኛ ነን። ችግሩ እየገጠጠ ሲመጣ ስነስርዓት ብለን ቢሆን ኖሮ ዛሬ እዚህ ባልደረሰ ነበርና። ግለሰቦችን አናስቀይምም ብለን አማንያንን እየበታተንን ነው። ባገራችን ሽማግሌ ሽማግሌ የሚባለው በሽበቱ ሳይሆን በበሰለ ተመክሮና አመለካከቱ እንደነበር ማስታወሱ ይጠቅማል። የቤተክርስቲያናችን ችግር ታዲያ የሕግ ብቻ ሳይሆን የሽማግሌዎች መጥፋት ጭምር ነው። የቤተክርስቲያኑን ጉዳይ ከግል የኤኮኖሚ ጥቅም ጋር ካያያዝነው የእምነት መሆኑ ይቀርና የዓለማዊ ድክመት ይሆናል። "ከጎረቤት የነበረው ቤተክርስቲያን ለምን አይገዛም" ብለው የተናደዱት ምእመናን ሳይሆኑ ኮሚሽን የቀረባቸው ደላላዎች እንደነበሩ ትዝ ይለናልና።


አሁንም እንደግማለን ያሸነፈ ሰው የለም የተሸነፍነው ሁላችንም ነን። አንድም ሰው ማጣት ሊያሳስበን ይገባል። ቤተክርስቲያናችን የገንዘብ ችግር አለበት የሚሉን ወደ $48 ሺ ወጪ ሲያደርጉ ግን ቅር አላላቸውም። ከሳሾች ምን ያክል እንዳወጡ በይፋ ባይነግሩንም እንደዚሁ ብዙ ገንዘብ እንደሆነ መገመት ግን ይቻላል።


ለሰላም ጸልዩ