Tuesday, May 11, 2010

የተጠራው ስብሰባ በጥሩ መንገድ ተጠናቀቀ ቁጥር ፳፯

ምእመናን እንዴት ከረማችሁ።

ባለፈው ቅዳሜ የቤተክርስቲያናችን ችግር ያሳሰባቸው ግለሰቦች ጠርተውት የነበረው ስብሰባ  ከ 300 ያላነሰ  የኦርቶዶክስ አማንያን የተሳተፉበትና ለመጀመሪያ ጊዜ ሥነ ስርዓት የታየበት: መደማመጥና መግባባት የሰፈነበት እንደነበረ ከስፍራው በመገኘት ለመመስከር እድል ማግኘታችንን ልናወሳችሁ እንወዳለን። ተሰብሳቢው ምእመናን በቤተክርስቲያናችን አካባቢ የተደረገው ድርጊት ያስቆጣቸው መሆኑን ባንድ ቃል ከመስማማታቸውም በላይ፤ ወደፊት ለሚደረገው ሁሉ በሙሉ ልብ ተሳታፊ ለመሆን ቆርጠው መነሳታቸውንና ቤተክርስቲያኑን ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ መግባባት እንዲሰፍን፤ መከባበር ጎልቶ እንዲታይ ሙሉ ጥረት ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ልንነግራችሁም እንወዳለን። በስብሰባው ላይ በቀረበ ጥያቄና  መልስ ደግሞ 22 የቤተክርስቲያን አባላት ከቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ቦርዱ በመወሰኑ፤ በሁኔታው የተበሳጩ የመብታቸው መረገጥ ያንገበገባቸው ግለሰቦች በትናንትናው እሁድ ቦርዱ በፖሊስ ሊያባርራቸው መወሰኑን ለማስቆም ወደ ፍርድ ቤት ሄደው አርብ እለት ከፍርድ ቤት የማገጃ ወረቀት ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ማገጃ  መሰረት

ማናቸውም ለጸሎት የሚመጡ ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን መግባት እንዳይከላከሉ  ወስኗል። ይህንን ውሳኔም ፖሊስ እንዲያውቀው መደረጉም ለተሰብሰቢው ተነግሯል፡


2   የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ለቤተክርስቲያኑ አስፈላጊ የቀን ተቀን ወጭዎች ሌላ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ  እንደተደረገበትም  ለተሰብሳቢው ተነግሯል ፤


3  የቤተክርስቲያኑ ዶሲዎችና በኮምፒውተር ያሉ ሰነዶች በተለያየ መንገድ የተያዙ  ማናቸውም መረጃዎች እንዳይጠፉ  እንዳይቀደዱ እንዳወረወሩ ፍርድ ቤቱ ማዘዙን ግለሰቦቹ  ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቱ ጊዜዊ እገዳ ውሳኔ ሲነበብ ተሰብሳቢው ዳር እስከዳር በጭብጨባ ድጋፉን እንደሰጠም መናገር እንወዳለን።

ውድ የኦርቶዶክስ ቤተሰቦች  

አሁንም መረዋ ትናንት ይል እንደነበረው በክስ የቤተክርስቲያን ፍቅርና  ሰላም ይመለሳል የሚል እምነት እንደሌለው እየገለጸ፤ አማራጭ አጥተው ወደ ሕግ የሄዱትን  ግን ሙሉ ለሙሉ አክሄዳቸውን የሚቀበልና ለምን እንዳደረጉት እንደሚገባው መናገር ይወዳል። በልመና እስካሁን መቆየቱ የባሰ  ችግር እንጂ ሰላም አላመጣምና።

ቤተክርስቲያን እንዴት ይከሰሳል?
ብለው ለሚጠይቁ ግለሰቦች እናንተም በበኩላችሁ
ፖሊስ እንዴት መቅደስ እንዲገባ ተደረገ?
ብላችሁ ልትጠይቌቸው ይገባል። ሁላችንም እንደምናምነው   ቤተክርስቲያን ይቅርና ትምሕርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንኴን ፖሊስ የመግባት መብት የለውም ብለን እንከራከር የነበርን ግለሰቦች እንዴት ዛሬ  መቅደሱን በ k9 የፖሊስ  አድምበታኞች  እናስደፍራለን?  

ስለመብት እንሞታለን የሚል ግለሰብስ እንዴት የሌላውን የመጸለይ መብት ሊጋፋ  ይነሳል?

ስለ ሃይማኖት አላውቅም ማለት ሌላ ነገር ሆኖ  እያለ በእምነት ፖለቲካ  ማካሄድ ደግሞ ሌላ ስህተት አይደለምን?
ባለፈው እሁድ ቦርዱ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የበተነውን ወረቀት ያየ  ደግሞ ቦርዱ እምነትን ወደ ጎን ትቶ ፖለቲካ  እያካሄደ  ለመሆኑ ግልጽ መረጃ እየሰጠ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት  አጸዳኋቸው  ያለንን የመሃበረ ቅዱሳንን አባላት  ዛሬም       "ጆሮ ቆራጭ " መጣብህ  አይነት  እያነሳ  ሊያስፈራራን መሞከሩን ስናይ አዘንን እንጂ አልተገረምንም። ይልቅስ ቦርዶቹ የምእመናንን ግፊት ተቀብለው  የስደት ሲኖዶስ አንቀበልም ማለታቸውን ስናነብ  ሃሌ ሉያ ማለታችን ልንነግራቸው እንወዳለን።

በማያያዝ ሃይማኖትን የዘር መለያያ ለማድረግ፤ አማራ ትግሬ በማለት መንግስትንና  እምነትን ለማጠላለፍ መሞከራቸው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል። ነገሩ የውሸት ውንጀላ ነው እንጂ ቢሆን እንኴን እነሱ የተለያየ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ሆነው ለማምለክ እንደሚመጡ ሁሉ ሌላውም የመንግስት ደጋፊ የመደገፍ መብት እንዳለውና ለአምልኮ  መምጣትም እንደሚችል መቀበል ነበረባቸው። አማራ የሆነ መብት ካለው ደግሞ ኦሮሞም ትግሬም ኤርትራዊም ሆኖ  ባንድ የማምለክ መብቱ ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ነው እንላለን።  ስለሚካኤል በፖለቲካ  ሳይሳካልን  ሲቀር ሕዝቡን በእምነት አንከፋፍለው።

በመጨረሻም በዚሁ በቅዳሜው ስብሰባ  የነበረው ሕዝብ ባንድ ቃል ቤተክርስቲያናችን ወደነበረበት ለመመለስ ተስማምቶ ለዚህም ሕጉ ወደነበረበት እንዲመለስ። አባላት ካለምንም ገደብ ይከፍሉ የነበረውን እየከፈሉ መመዝገብ እንዲችሉ እንዲደረግ ይህንን በስራ ሊተረጉሙ የሚችሉ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው የስልጣን ሱስ ያላናወዛቸው ግለሰቦችን ማሳተፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንዲሆን፤ ይህንንም በስራ  ለመተግበር ከቦርዱ ጋር እሚያቀናጁ 9 ምእመናን ያለበት ኮሚቴ አቌቁመው የስብሰባው ፍጻሜ  ሆኗል።

ተሰብሳቢዎቹ ያላግባብ የተሰናበቱት ካህናት ወደ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ጥረት እንዲደረግ አሳስበው፤ ለዚህም ቦርዱ የመቻቻል መርህ ቢከተል የተሻለ  እንደሚሆን አሳስቧል። ክርስቲያን የሆነውን የኦርቶዶክስ አማኝ አይደለህም የማለት ችሎታውም ብቃቱም የሌለው ቦርድ እራሱን እንዲያስተውልና  ወደሰላም እንዲመለስ ጥረት ቢያደረግ ይሻላል  በማለትም ስምምነት ላይ ደርሷል።

ቦርዱ ያባረራቸውን ካህን እርዳታ አስመልክቶ ቀደም ሲል  ለዚሁ ጉዳይ ተሰብስቦ  የነበረው ቡድን ያቌቌመው ሌላ ኮሚቴ ስራውን እየሰራ  መሆኑ ተነግሮ  በተለይም የካህኑን የመኖሪያ  ፈቃድ ለማደናቀፍ ቦርዱ የሚያደርገውን አሳፋሪ ተግባር እንዲያቆም ጥያቄ  ለማቅረብ መታሰቡን ከስፍራው የነበሩ ግለሰቦች ገለጻ ሰጥተዋል። ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ ትብብራችንና  እርዳታችንን እንድናሳይ መረዋም በበኩሉ ጥሪ ያደርጋል። ቤተክርስቲያን ስደተኛን ትደግፋለች እንጂ ስደተኛ ለመፍጠር አትተባበርምና።

የጅምሩን ፍጻሜ  ያሳምርልን

አሜን