Wednesday, May 19, 2010

ለመብታችሁ የቆማችሁ እንኴን ደስ ያላችሁ ቁጥር ፳፰

ፍርድ ቤት እንዴት ዋለ? ይላል የአገራችን ሰው። አዲስ እሱን የሚመለከት ነገር እንዳለ  ለመጠየቅ ሲያስብ ነው ይህንን  የሚለው። እናንተም በፊናችሁ የትላንቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ  እንዴት ነበር?  ብላችሁ ብትጠይቁ ያገኛችሁት መልስ የተለያየ  ሊሆን ይችላል። የስኴር በሽታ ይዞት አንድ እገሩ ስለተቆረጠ ሰው ሁኔታ የተለያየ  ሰዎች ሲያወሩ የተለያየ  ነገር ቢናገሩ አይገርምምና። "አንደኛው የሚያሳዝን ነው አንድ እገሩን ቆረጡት" ሲል ሌላው ደግሞ  በፊናው " እግዜር ይመስገን ሁለት እግሩ ሳይቆረጥ ቀረ" ብሎ እንደሚናገረው አይነት መሆኑን ለመጠቆም ያክል ነው። መረዋ በበኩሉ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር፤ ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችልና የግለሰቦች የማምለክ መብት በጥቂት ጉልበተኞች ሊነጠቅ አለመቻሉን ነው።

በትላንትናው እለት ሁለት ነገር የተከናወነ  ሲሆን አንደኛው በይግባኙ ቀጠሮ አስፈላጊው የመልስና የመከራከሪያ ነጥቦች ለፍርድ ቤቱ በጠበቃው ተቀነባብሮ መግባቱን ስንነግራችሁ ውጤቱን ወደፊት በሚደርስ ሰዓት የምንሰማው  ነውና መረዋም ጉዳዩን ተከታትሎ   የሚዘግብ   መሆኑን  ቃል ይገባል። በተረፈ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይደርሱ ተወስኖባቸው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል ሁለት ግለሰቦች መስርተውት የነበረው ክስ የፍትሕ ቀኑ ደርሶ  የተፈጠረውን ለመመስከር የደረሰባቸውን በደል ለዳኛው ለማሳየት እድል በማግኘታቸው ማንም ለመብት እቆማለሁ የሚል ግለሰብ ሊደሰትበት የሚገባ ጉዳይ እንደነበረ ልናወሳችሁ እንወዳለን። 

ምንም ነገር ሳያደርጉ ለመጸለይ ከመጡበት ቤተክርስቲያን በፖሊስ ታስረው የወጡት እናት ከምስክር ወንበር ላይ ሆነው የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ  ሁኔታው እየታወሳቸው ያለቅሱ የነበሩት እሳቸው ብቻ  ሳይሆኑ ያዳምጣቸው  የነበረው  ሁሉ እንደነበር መናገርም እውነት ነው። በቀኑ የነበረውን ሁኔታ  እነደገና በቴሌቪዥን እንዳየነው በድጋሜ ፍርድ ቤት ሲታይ በእውነት ይህ የተደረገው እኛ  ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው? የሚያሰኝም  ነበር።  ወንድሞቼ  ሽማግሌዎቻችን የት ደረሱ? የሚል ቢያጋጥማችሁ አትገረሙ።
የተለያዩ ምስክሮችን ያቀረቡት የከሳሽ ጠበቃ  ከተጠበቀው በላይ ጉዳዩን እንዳጠኑት በግልጽ ያሳይ ነበር።
በእለቱ የቦርዱን ውሳኔ ትክክለኝነት ለመናገር በምስክርነት ቀርበው የነበሩት ዶክተሩና አቶ አበራ  ምን ብለው እንደመሰከሩ ወደፊት የፍርድቤቱን የቃል በቃል ግልባጭ  (TRANSCRIPT)  ስናገኝ ቃል በቃል እንደምናቀርብ ቃል እየገባን በሁኔታው እራሳቸው እንኴን ደስተኛ እንዳልነበሩ ግን  መናገር ሃቅ ይሆናል።

ይህ ክስ ከተጀመረ  በኋላ  ለጠበቃ ገንዘብ ከቤተክርስቲያኑ ካዝናም ሆነ ባንክ አላወጣንም ያሉት እነዚህ ግለሰቦች የተናገሩት እውነት መሆን አለመሆኑን በሂደት ወደፊት የምናየው ሲሆን ለጊዜው ገንዘብ ለማውጣታቸው የቀረበ  ማስረጃ  ባለመኖሩ የገንዘቡ እገዳ  ሲነሳላቸው የቀረው እገዳ  ግን ጉዳዩ ወደፊት በሰፊው እስኪታይ ድረስ እንዲቆይ መወሰኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን።

በውሳኔው መሰረትም

1  ማንም አማኝ ከቤተክርስቲያን ሊወገድ እንደማይችል የእምነት መብቱ የተጠበቀ  መሆኑን የቦርድ አባላትም ይህንን መብት   መጋፋት እንደማይችሉ የተወሰነ  መሆኑን።

2   ምንም አይነት የቤተክርስቲያኑ ዶሲዎች እንዳይነኩ እንዳይጠፉ

3  ፖሊሶች በምንም አይነት ወደ መቅደሱ እንዳይደርሱ መወሰኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን።

ለራስ መብት መቆም ማለት የሌላውንም መብት ማስከበር ነውና  በቦርድ አባላት ውሳኔ  ተገፎ  የነበረው (THE FIRST AMENDMENT RIGHT ) የመጀመሪያው የአሜሪካን ሕገ መንግስት ማሻሻያ መብት ማንም ሊጋፋው የማይችል መሆኑን የቦርድ ባለስልጣኖችም እንዲገነዘቡት መደረጉ ለሁላችንም የወደፊት ተስፋ  ነው።

ትግላችን የመብት ጉዳይ ነው

ፍትሕ ባለበት አንባገነኖች አይነግሱም