Sunday, May 2, 2010

ቤተክርስቲያናችን የፖለቲካ መፋለሚያ ሜዳ እየሆነ ነው ቁጥር ፳፭

ውድ የቅዱስ ሚካኤል አማንያን። እስካሁን ትእግስቱን ያደላችሁ ፈጣሪ አምላክ አሁንም ትእግስቱን ይስጣችሁ። በአማንያንና እምነት በማያስፈራቸው መካከል ፤ አንገታቸውን በደፉና የልብ ልብ በተሰማቸው መካከል ያለውን ልዩነት እያየን ያለን   ይመስለናል። ፈሪሃ  እግዚአብሔር ያደረበት በክርስቶስ አምላክነት የሚያምን ሰው የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪዎች ምእመናትን በፖሊስ አስከብበው አምልኮ ለማድረግ እየሞከሩ ነው ብላችሁ ስትነግሩት ለማመን የሚቸገር የኦርቶዶክስ አማኝ ቢያጋጥማችሁ የእምነት ጥንካሬውን ያሳይ እንደሁ እንጂ ጥርጣሬ እንዳይመስላችሁ።

በዛሬው እለት አቶ አበበ የቦርዱ ጸሐፊ በመላከ ሳህል አወቀ  ላይ የተደረገውን ወሳኔ አስመልክቶ ለመባረር ያደረሳቸውን ጥፋት ለመተንተን በቤተክርስቲያኑ መንበር ላይ ወጥተው ሊናገሩ ሲሞክሩ ነገሩ ያንገሸገሻቸው እናቶች ጥያቄ አለን እያሉ ሲናገሩ አቶ ሙሏለምና አቶ አበራ ፊጣ ከውጭ ሆነው ትእዛዝ ይጠባበቁ የነበሩትን ፖሊሶች ከነጫማቸው እየመሩ ወደቤተክርስቲያን በማስገባት እናቶች እግዚኦታቸውን በጉልበት እንዲያቆሙ አድርገዋል። እግዚኦታ አናቆምም ያሉት እናት ታስረው ወደ ፖሊስ መኪና ሲወሰዱም ያዓይን ምስክር ነበርን። በሌላ ወገን እኝሁ አቶ  ሙሉዓለም የቦርዱ  ም/ ሊቀመንበር ፖሊሶችን እየመሩ ወደ ትምህርት ቤቱ በመሄድ አቶ ቴዎድሮስንና አቶ  መንግስቱን ከቤተክርስቲያኑ እንዲያባረሩላቸው ከመጠየቃቸውም በላይ ሁለተኛ ወደ ቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ ፖሊሶች እንዲያስፈርሟቸው ማድረጋቸውን ለመረዳት ችለናል።

ትላንት ለኛ አልተገዙም ያሉትን ካህናት ያባረሩ የቦርድ አባላት፤ ዛሬ እናቶችን በልጆቻችን ፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ ማጎሳቆልና ማሳሰር፤ የማይፈልጉትን እየመረጡ እንዳትመጣ እያሉ ማስፈራራትንና ማስፈረምን ተያይዘዋል። ሕግ አክባሪ የሆነው ምእመን በሁኔታው እያዘነ በተለይ እናቶች ነጠላቸውን እያነጠፉ እናት እንደሞተበት እንባቸውን ሲያነቡ ያየ  ያለሁት በእውነት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው ወይ? ብሎ  ቢጠይቅ እውነት አለው።

የሁሉንም እንባ የሚቀበል ፈጣሪያችን የናቶችንና ያባቶችን በተለይም የወጣቶቹን እንባ  እንደሚሰማ  ምንም ጥርጥር የለንም።
ስለሆነም በተደረገው ሳንደናገጥ ባንድ ላይ መቆም ያለብን አሁን ነው። ድል የመቱ የመሰላቸው ፖለቲከኞች እንደ ልማዳቸው እየተሳሳቱ መሆኑን ለማሳየት ባንድ ላይ ሆነን በሕግ ከመታገል ሌላ  ምንም አማራጭ እንደሌለ መገንዘብ የግድ ይሏል። የሽማግሌዎችን የስራ ውጤት እስካሁን ጠበቅን ካሁን በኋላ አማራጩ ሕጋዊ ብቻ መሆን አለበት። አባል መሆን ብቻ ነው የሚያዋጣው ለሚሉት መልሰ: ቤተክርስቲያን አትድረሱ እያለ  በፖሊስ የሚያባርር የቤተክርስቲያን አመራር አባል የማይፈልገውን አባል $50 ከፍሎ  ማመልከቻ  ቢያስገባ ይፈቅዱለታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለናል።  ያውም ከዓመት በኋላ ለሚሰጥ የመምረጥና  የመመረጥ መብት። በ ፩ ዓመት ውስጥ በዚህ ቤተክርስቲያን ላይ ምን ያክል በደል ሊያደርሱ እንደሚችሉም መመልከት የማይችል ወይም የነሱን ሥራ የሚያጸድቅ ብቻ  ነው ዓመት መጠበቅ አለብን የሚለን።

አባት ሽምግሌዎችን አይተናል አልተንቀሳቀሱም። የቦርዱ አመራሮች አሁን በፖሊስ እስከተመኩ ድረስ እኛ ደግሞ በሕግ መብታችንን ለማስገበር መነሳት አማራጭ የሌለው ነው እንላለን።

ቀጣዩን  እርምጃ  ሰሞኑን እናሳውቃችኋለን። በፖሊስ ታስረው ለነበሩ እናት ከልብ ሐዘናችንን እየገለጽን ክርስቶስ ለቅሶአቸውን እንደሚሰማ እንዳይጠራጠሩ አብረን በጸሎት እናበረታታለን።

ክርስቶስ ልባቸው የደነደነውን ያስብ። መንፈስ ቅዱስን ያውርድላቸው።

አሜን