ቤተክርስቲያን እንዴት ይከሰሳል? የሚል ጥያቄ ለሁለት ዓመት ሲጠየቅ መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም።በተለያየ ወቅት ይህንን ጥያቄ አስመልክቶ ባጥጋቢ መልስ የተሰጠበት በመሆኑ ዛሬ በዚያ ላይ ጊዜ ማጥፋት አንፈልግም። እንዳዲስ ተነስተው "ቤተክርስቲያን እናት ነችና እናት እንዴት ትከሰሳለች?" እያሉ ለሚጠይቁ ግን ያገሩን ሕግ ካለማወቅ የመጣ ጥያቄ በመሆኑ እናት መከሰስ አይደለም የእናትነት ግዳጇን ካልተወጣች የእናትነት መብቷ ተገፎ ልጆቿን እንደምትነጠቅ መጠቆም እንወዳለን።ቤተክርስቲያንን እናስተዳድራለን ብለው በደል የሚፈጽሙትን ደግሞ ከመክሰስ ሌላ አማራጭ አይኖርም። አማራጭ ቢኖር በጉልበት መፋለም ይሆናል። ያንን ደግሞ እኛ አጥብቀን እንቃወማለን። በተራችን ለጠያቂዎቹ የምንጠይቃቸው ጥያቄ ግን አለን። እምነት የማይገዛውን የአመራር ቡድን፤ ሽማግሌ የማያከብረውን የአመራር ቡድን ፤ አዛውንቶችን ለማናገር እንኳን ፈቃደኛ የማይሆንን የቦርድ ተመራጮች፤ የምእመናንን ፊርማ ያዘለ የስብሰባ ጥሪ አሽቀንጥሮ የሚጥልን አንባ ገነን፤ ሕገ ወጥ አሰራሩን ማስቆም የሚቻለው እንዴት ነው ብለው ያስባሉ?
አባትና እናት እየበተኑ፡፡ ወላጆችን ከቤተክርስቲያን እያባረሩ። ልጆቹን እያስተማርን ነው ብለው ሲናገሩ አይቀፋቸውምን?የልጆች ነገር አይሆንልኝም የሚሉት አዛውንትስ የወላጆችን መበተን በጸጋ መቀበላቸው ለምን ይሆን? የሚፈሩት ነገርስ ምንድነው? ይህ ባደባባይ የሚነገር ጥያቄ ሆኖ እየሰማነው ነው።
ባለፈው ሳምንት ካህኑ "ልጆቼንና ባለቤቴን ሸጠህ ትምህርት ቤት አሰራ" ብለውኛል ተብሎ ከመቅደስ ሲነገር ተገርመን ነበር። ቤተክርስቲያናችን የሰውን ልጅ መሸጥና መለወጥ የማትደግፍ መሆኗን አለማወቅም አስመስሏል።ነገሩ ለአባባል ተብሏል ሊባል ይችል ይሆናል። ነገር ግን የሚነገሩ ቀልዶች የሚያመጡት መዘዝ እንዳላቸው ማሳሰብ ፈልገን ነው። ያንን ማየት መረዳት ደግሞ የማመዛዘን እውቀትን ይጠይቃል።
ባለፈው እንደነገርናችሁ በአቶ ሰይፉ ይገዙ የሚመራ የሽማግሌዎች ቡድን የአማራጭ አፈላላጊ ኮሚቴንና የቦርዱ ደጋፊዎች ነን የሚሉ ግለሰቦችን ማነጋገራቸው የሚታወስ ነው። የሽማግሌዎቹ ቡድን ይህንን ካደረገ በኋላ ከቦርዱ ጋር ቀጠሮ ይዘው በብዙ ውጣ ውረድ በቀጠሮው ቀን ሲሄዱ ለማነጋገር የጠበቃቸው ቦርዱ ብቻ ሳይሆን የቦርዱ አጃቢዎች ጭምር ነበሩ። ሽማግሌዎቹ እኛ ልናነጋግር የመጣነው ቦርዱን ነውና አጃቢዎቹን አስወጡልን አላሉም። አብረው መወያየታቸውን ቀጠሉ እንጂ። የቦርዱም አባላት ከአጃቢዎቻቸው ውጭ ለመነጋገር ፈቃደኞች አልነበሩም።ታዲያ ሽማግሌዎቹ ለመናገር ለምን ፈሩ? ለሚለው አሁንም መልስ ያላገኘ በግልጽ መቅረብ ያለበት ጥያቄ ይመስለናል። አቶ ሰይፉን የተሳደቡት የቦርድ ተመራጭ ባለቤት በአቶ ሰይፉ አንደበት ሲወደሱ የሰማ ግለሰብ ጆሮውን አላምን ብሎ እጎኑ ያነበረውን ግለሰብ ምን እየተናገሩ ነው? ብሎ እንደጠየቀ ሰምተን ተገርመን ነበር።
ለመሆኑ የቦርዱ አጃቢዎች እነማን ነበሩ
የኢንጅነሩ ተጠሪ አቶ አበበ
የቅንጅቱ አቶ ደጀኔ
የኢሕአፓው አቶ ከተማ
ቶውትራኩ አቶ መሰለ እንደሚገኙበት ለማረጋገጥ ችለናል።
ሽማግሌዎችን ወክለው የተሰበሰቡት ደግሞ
አቶ ሰይፉ ይገዙ
አቶ በትሩ ወልደ አማኑኤል
አቶ ጌታቸው ትርፌ እንደ ነበሩም አረጋግጠን ነበር።
ስብሰባው እንደተጀመረ "የምን ብጥብጥ ነው ቤተክርስቲያናችን ሰላም ሰፍኗል" ያሉት የቦርድ ተመራጭ የግንዛቤ እንጂ የአካል እይታ ችግር እንደሌለባቸው ብናውቅም አባባላቸው አንድ ነገር አስታወሰን።
ለጥየቃ ኢትዮጵያ ሄዶ የመጣ ግለሰብ ዘመዶቼ ደህና ናቸው ቢሆንም እናቴ አርፋለች። አባቴ እኔ እዛ ሄጄ በሚስቱ ሞት ደንግጦ ወደቀና ሞተ። እህቴ በቤተሰብ ሐዘን ተጎድታ አርባቸውን ሳታወጣ እንኳን አለፈች። የቀረ ዘመድ የለኝም ያለውን ማለታችን ነው።
በስካር መንፈስ በየመጠጥ ቤቱ እደባደባለሁ እገላለሁ እያሉ የሚጋበዙት የቅንጅቱ አቶ አበበ ዛሬ የትጥቅ ትግል ያሉበትን ያልያዙትን ጠመንጃቸውን ጥለው መስቀል ይዘው ማየታችን ቢገርመንም ይህ ደግሞ ለመልካም ሆኖላቸው ከስካር ቢያድናቸው መልካም በሆነ ነበር። እንደ ቅንጅቱ ማሕተም የቤተክርስቲያኑን ማሕተም ለንግድ ማዋል ይቻላል ብለው በማሰብ ገብተው ከሆነ እንደማይሳካላቸው ካሁኑ ሊነገራቸው ይገባል።ለማንኛውም በዛሬው እለት በመለከት ጦማር ላይ የወጣው የሽማግሌዎችና የአማራጭ አፈላላጊ ኮሚቴ የመጨረሻ ስብሰባ ያረጋገጠልን ነገር ቢኖር ተመራጮቹ ሰላምን እንደማይፈልጉ ቀደም ብለን የተናገርነውን ማረጋገጡ ብቻ ነው። ሽማግሌዎቹ ካሁን በኋላ ያላቸው ምርጫ ቢኖር ብዙሃን ምእመንን ተቀላቅለው በሕግ መፋለሙን መቀጠል ብቻ ይሆናል። ካልሆነ ዝምታን እንመርጣለን ማለት ሳይመለስ ተንጠልጥሎ ያለውን ጥያቄ ይኸውም የሚያስፈራቸው ምንድነው? የሚለውን የሚቀሰቅስ ይሆናል። ዛሬ ያለው ምርጫ አንድ ነው። የተደፈረውን የምእመናን መብት በሕግ ማስከበር ብቻ ነው። እራሳቸው አውጥተነዋል የሚሉትን ሕግ እንኳን የማያከብሩ የቦርድ ተመራጮች ከዛሬ ነገ ልባቸው ይራራል ብሎ የሚጠብቅ ካለ፡ የዝሆን ጆሮ አሁን ካሁን ይወድቅ ይሆናል ብሎ እንደሚከተለው ጅብ አይነት መሆን ይመስለናል።
አቶ አበበ ጤፉ
አቶ አበራ ፊጣ
አቶ መሰለና
የቦርዱ ዶክተር ዘማሪ ሆነው መመረቃቸውን ስናይ መመረቅ የማይሰለቻቸው ዶክተር አላልንም ዳላስ በመሪነትና በዘማሪነት የሚያቀርበው እነዚህን ብቻ ከሆነ እውነትም ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለነው አልን እንጂ።
ይህንን ቤተክርስቲያን ወደነበረበት ለመመለስ ብዙ የበኩላችንን ጥረናል። ታግሰናል። ሲሰድቡን አልተሳደብንም። ሲያስፈራሩን ፍርድ ቤት አልሄድንም። ሕይወታችን አደጋ ላይ እንደሆነ ሲነገረን ፈርተን አላፈገፈግንም። አሁንም የተረገጠ መብታችንን ሳናስከብር ወደኋላ አንልም። ለሽማግሌዎች ልንናገር የምንወደው ስለህጻናት ብዙ ተብሏልና የእኛም ልጆች ሕጻናት መሆናቸውን ነው። የእኛም ልጆች የኦርቶዶክስ ልጆች መሆናቸውን ነው። ወላጆችን አባሮ ልጆቹን እንፈልጋለን ማለት ደግሞ ሕዝብን ገድሎ አገርን ማስቀረት አይነት መሆኑን እንዲገነዘቡትም እንወዳለን። ከስጋው ጦመኛ የሆነ ሰው ከመረቁ አይከጅልምና።
በልጆች ስም መነገድ መቆም ይኖርበታል። የሁሉም ልጅ እኩል ነው ብለን እንቀበል።
አቋም ከሌለው ወዳጅ ይልቅ አቋሙ የሚታወቅ ጠላት ይከበራል።
በ DECEMBER 9 በፍርድ ቤት
በ DECEMBER 19 በተጠራው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተዘጋጁ።
በቸር ይግጠመን።