Wednesday, December 2, 2009

መሳደብ የመሃይሞች፤ መነጋገር የብልሆች፤መደማመጥ የጠበብቶች ነው። ቁጥር ፪

ቆየት አለ መሰለኝ ዘመኑ። አንድ በጊዜው የትግሉ ሂደት ያልጣማቸው፤ ወጣቶቹ የሚጔዙበት መንገድ ያስፈራቸው፤ የኢድሕ አባል "በሂስና በግለሂስ" ድርጅታቸው ያምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ " በጭራሽ አናምንም፡ ሂስ ማለት እኮ የጨዋ ልጅን ማዋረድ ማለት ነው። ግለሂስ ደግሞ እራስን ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ነው። "ብለው ተናገሩ እየተባለ ሲወራ ሰምተን ስቀን ነበር። በወቅቱ የነበረውም መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ነን ባይ ድርጅቶችም "በሂስና ግለሂስ" እናምናለን ይሉ ስለነበር ነው የሳቅነው እንጂ አባባላቸው ሙሉ ለሙሉ ውሸት ሆኖ አልነበረም። ሂስ ለማረም ከሆነ ትምህርታዊ፤ ለዘለፋ ከሆነ ደግሞ ስድብ ይሆናል። ከግለሂስ መማር ከተቻለ ገንቢ ለፌዝ ከሆነ መሳለቂያ መሆኑ ነው። ዘንድሮ ደግሞ መሰዳደብ ጀግንነት ትእግስተኛ መሆን ደግሞ ፍርሃት ተደርጎ እየተወሰደ ነው።


አንድ ባካባቢያችን የሚጻፍ ብሎግ ለቤተክርስቲያናችን የቦርድ እጩዎች እንጠቁማችሁ በሚል የግለሰቦች ስም ሲጠቁም፡ ተወዳዳሪዎቹ ከታክሲ ነጂዎች ውጭ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀምጡ መሆን አለባቸው ማለቱን ስናነብ ደነገጥን። የዚህ ጽሑፍ ጸሃፊዎችም ሆኑ፡ ሰም ደርድረው ጻፉ ያልናቸው ግለሰቦች በአንድ ወቅት ታክሲ ሲያሽከረክሩ እንደነበር እውቅ ነበርና። ተሽከርካሪ ወንበር የጨመርነው እኛ ነን። ጠቌሚዎቹ ያሉት ግን መሁሮች ይመረጡ ነበር። ታክሲ የሚነዱ የተማሩ ግለሰቦች የሉም ማለታቸው ከሆነ፡ አባባላቸውን መሳብ ሊኖርባቸው ነው።
ክርስቲያን ነህ ወይ? የሚል ጥያቄ የሚጠይቁ፡ መልአክ ለመሆን ሳምንት የቀራቸው የሚመስላቸው፤ የራሳቸውን ስህተት ሳያስተውሉ የሌላውን የዐይን ጉድፍ ሊያጠሩ የሚነሱ፤ ወንድምና እህቶች ያሳዝኑናል። ባንፃሩ "አማኝ ነኝ በኦርቶዶክስ እምነት ይህ ትክክል ነው" ብለው ለማስተማር ስለተነሱ ብቻ እንደወንጀል ተቆጥሮባቸው "አክራሪዎች" አልፈው ተርፈው "ታሊባን" እያሉ የሚጠሯቸውና የሚዘልፏቸው ግለሰቦች እራሳቸውን ዞር ብለው ማየት ይኖርባቸዋል እንላለን። እኛ ለአባላት መብት ለሕግ የበላይነት መታገል አለብን የምንል ሁሉ ሃይማኖትና መብትን በየፊናው መረዳት ካልቻልን የጾምና የፍስክ ወጥ እንደተቀላቀለባት ጿሚ ሆነን እንቀራለን።
ትግላችን ለአስገዶም መብት፡ ወይንም ንግስትን ለቦርድ አባልነት ለማስመረጥ ብቻ ከሆነ ከጅምሩ ችግር አለብን ማለት ነው። ሁላችንም ለሕግ የበላይነት ከተነሳን፡ ደግሞ ዓለም ዘውድ ይመረጥ ዳግማዊ፡ በተናጠል ለውጥ አያማጣም ብለን ማመን አለብን። ዋናው የአባላትን መብት የሚጠብቅ፤ ሕግ እስከነደፍን ድረስና ይህንንም በሥራ እስካዋልነው ድረስ፡ ቀሪውን እንደድሮው እየተረዳዳን ማስተካከል ይቻላል ብለን ማመን ይኖርብናል። እስከዛሬ ቤተክርስቲያችን እዚህ የደረሰው ሊቃውንት የቦርድ አባላት ስለመሩት ነው የምንል ካለን ተሳስተናል። ይልቁንስ ሊቆች መረጥን ብለን እየተመነጠርን ነው። ፈላስፎቹ ዶክተሮችና ነርሶች ለበሽታችን መድሃኒት ሳይሆን መርዝ እያዘዙልን ነውና። ይህንን ጽሑፍ አንብቦ የግለሰብን ሚና ትክዳላችሁ የሚለን ቢኖር ካለሕግና ካለመመሪያ ግለሰብ ብቻውን ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ልንጠቁመው እንወዳለን። በነገራችን ላይ ጋንዲም ሞሶሎኒም ግለሰቦች እንደነበሩ አንዘንጋ።