"አንድ አክስቴ የነገረችኝ ትዝ አለኝ" አለን ከመሃከላችን ተቀምጦ የነበረ ጔደኛችን። "ሌባ ገንዘብ ሰረቀና ተያዘ አሉ። እንደተያዘ ወዲያውኑ መስረቁን አመነና የስጋ መቀጫውን ሊቀበል በእስር ቤት እየተዘጋጀ ለነፍሱ ደግሞ ንስሐ አባቱን አስጠርቶ ተናዘዘ። የንስሐ አባቱ ተግሳጽና ምክር ሰጥተው፤ የሚገባውን ቅጣት ከቀጡት በኋላ ልጄ ሁለተኛ እንዳይለመድ፤ ቃል ግባልኝ ብለው ቃል ካስገቡት በኌላ ምክራቸውን ሲለግሱትና ነገሮችን አስፍቶ ማየት እንዲችል ሲያስተምሩት ምን አሉ መሰለህ? ካንተ በላይ እኮ ንስሐ መግባት ያለበት የዘረፍከው ሰውዬ እንደሆነ ታውቃለህ? ምክንያቱም ገንዘቡ እንደጠፋ አላፊ አግዳሚውን፤ ዘመድ ጔደኛውን ተጠራጥሮ ነበርና ብለው አስረዱት" ብላ አጫውታኝ ነበር ብሎ አወጋን። ነገሩ የበደለው ሳይሆን የተበደለም እንዲሁ ሳያውቀው ሃጥያት መስራት ይችላል ለማለት የቀረበ ነው።
በዚህ በከተማችን የተጀመረው የቤተክርስቲያን ሽኩቻ አሁንም እየተፋፋመ፤ እየተጋጋለ ነው። ከሁለቱም ወገን የሚሰነዘሩት አስተያየቶች የሚያስፈሩም የሚያስደነግጡም ናቸው። ከቤተክርስቲያን ይህንን ሰማሁ ካለ አንድ ሰው ማን ነገረህ ብሎ "የወሬ አባቱን" መጠየቅ የተለመደ ሆኗል። ሰብሳቢው ነው ከተባለ አይ ተወው እሱ እኮ በውሸት የተካነ ነው የሱን ወሬ ወሬ ብለህ አደባባይ ይዘህ ትወጣለህ የሚሉ ብዙሃን ናቸው። የሽምግሌዎች (የአማካሪ) ኮሚቴ ለምን ፈረሰ ሲባል ቦርዱን መደገፍ የማይችሉበት ላይ ስለደረሱ ነው ያለን ግለሰብ ለአባባሉ የተለያየ መረጃዎች ሊሰጠን ተነስቶ ነበር። እንዳልሰማን አለፍነው እንጂ።
ሌላው የማስፈራሪያ መሳሪያ ሆኖ የቀረበው ደግሞ የመሃበረ ቅዱሳን ነገር ነው። ለእውነት እንነጋገር ከተባለ ከቤተክርስቲያን አባላት ውስጥ መሀበረ ቅዱሳንን የሚያውቅ ማን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ በአዎንታ መላሹ ጥቂት ይሆናል። መሃበረ ቅድሳን የሚለውን ቃል ያስተዋወቀን የቤተክርስቲያኑ ቦርድ እንደነበረ አሌ ማለት የሚቻል አይመስለንም። ጥሩነታቸውን መመስከር ብቻ አይደለም የገንዘብ ድጎ ማ ያደርግላቸው የነበረውም ቦርዱ ነበር። በበጎ አድራጎት ስራዎችም ባገር ቤት አስፈጻሚ እንዲሆኑ የመረጣቸው ቦርዱ ነበር። ዛሬ ተቀልብሶ መሃበረቅዱሳን ማለት በቦርዱ እይታ "ሰይጣን" እንደማለት ሆኗል። ይህ ሁሉ ሲሆን መሃበረቅዱሳን ሲሳደቡም፤ ሲከሱም፤ አላየንም። ትእግስት ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ያስመሰከሩ ለመሆናቸው የምንስማማ ይመስለናል።
ባገራችን እንኴን
የምግል ዋሻው ቀሲስ መሸሻ፤
ሲሻው በመስቀል ሲሻው በጋሻ።
ይባል እንደነበር እናስታወሳለንና። ቄስም ሲነደው መቌሚያ ያነሳል ይባል የነበረውን አስታውሰን እነሱ ለፈጣሪ መተዋቸው ይሆን? ብለን በማሰብ በጥንካሪያቸው እንቀናለን። ባንሳሳት ሁለት ዓመት ሞላው መሰለን፤ እዚህ በዳላስ ከተማ መሃበረቅዱሳን አውደ ትርእይት አሳይተውን ነበር። በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሃበረ ቅዱሳንን እንደ ድርጅት ለማየትም እድል አገኘን። ጥሩ ሥራ ለመስራት በቁጥር መብዛት አያስፈልግ ያልነውም ያኔ ነበር። መሃበረቅዱሳን እምነት፡ ነው፤ መሃበረቅሱሳን ሃይማኖት ነው፤ ለሚሉትና መሃበረቅዱሳን የአባ ጳውሎስ ሰላዮች ናቸው ብለው ስማቸውን የሚያጎድፉትን አይተን፤ ከሀገር ቤት ከቤተክህነት የሚቃጣባቸውን አለንጋ ስናይ ደግሞ ግራ እንጋባለን። አንድ የምናውቀው ግለሰብ መሃበርቅዱሳን ዓርብና እሮብ አትብሉ ይላሉ፤ አለቁርባን ማግባትን አይቀበሉም፤ ከሕግ በላይ ካህንን ያከብራሉ። አገር ቤት የተጎዱ ገዳማትን ሰለረዱ ብቻ የፀደቁ ይመስላቸዋል። በቤተክህነት እውቀታቸው በመመካት የቅዳሴ አይደለም የማህሌት ስህተት አያሳልፉም ብሎ ሲናገር፡ ሌላው ታዲያ ባጭሩ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ናቸው አትለንም ብሎ መመለሱ ትዝ ይለናል።
እኛ ውስጣቸውን ስለማናውቅ እንዲህ ናቸው ማለት ይከብደናል። "አክራሪነት መጥፎ ነው" ብለን ሙሉ ለሙሉ ስንቀበል፡ የከረረውን ሳያሳዩን አባባሉን ብቻ የሚነግሩን ከሆነ ማስፈራራት ይሆናል። ቁጭ ብለን ብናወራ እኛም የማንስማማበት ነገር ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን። ነገር ግን በጥቅሉ መኮነንን በጅምላ መፈረጁን ነው የምንቃወመው። ባላየነው ወሬ ለመፍራት ደግሞ አረጀን። ለነገሩማ መሃበረ ቅዱሳንን ቦርዱ አስተዋወቀን፤ ዛሬ ደግሞ በመኮነን አይናችሁ ላፈር በሏቸው አለን የሚለውን ለመጠቆም ያክል ነው።
ባለፈው በዚህ ብሎግ ላይ በቤተክርስቲያናችን ክርክር አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም ብለን ለጻፍነው አስተያየት ቀጥተኛ ትርጉም በመስጠት "አዎ ተሸናፊና አሸናፊ ይኖራል" የሚል መልስ በሌላ ብሎግ ማንበባቸን ገርሞናል። ይህ ይጠፋቸዋል የሚሉ ካሉ ተሳሰተዋል። መልስ ላለመስጠት ወሰንንና ብዙዎች አብራሩልን ስላሉ መመለስ የግድ ሆነብን። አሁንም ለማንም ይፈረድ ለማንም ሁላችንም ተሸናፎዎች ነን ብለን እናምናለን። ፍርድ ቤት ይፈርዳል ግን ለማንም ይፍረድ ለማን አንድ እንሆናለን ወይ? ነው ጥያቄው። የተፈረደለት ይፈነጥዝ ይሆናል፤ ሰላም ፍቅር መጣ ማለት ግን አይደለም። ሰላም የሚፈጠረው፤ አንድነት የሚመጣው መነጋገር ሲቻልና ልዩ ነቶችን በጋራ ተወያይተን መፍትሄ ስናገኝላቸው ብቻ ነው።
ሴትዬዋ እርጉዝ ነች እሚለው ላይ ከተስማማን፤ መውለዷ የግድ ነው እዛ ላይ መከራከር አያስፈልግም የሚያዋልዳት ዶክተር የሚረዳት ሆስፒታል እስካለች ጊዜ ብቻ ይሆናል። ወልዳ እንዴት ማሳደግ ትችላለች እሚለው ላይ ግን የዶክተሩ ሚና አይኖርም ለማለት ነው። በዛ ላይ ሚና መጫወት የሚችሉት ቤተሰብና ዘመድ ጔደኛና የሰፈር አዛውንቶች መሆናቸውን መካድ እንዴት ይቻላል? ካልተግባባን ሌላ ችግር አለ ማለት ነው። ስለሆነም በቤተክርስቲያናችን ሰላም መውረድ የሚችለው ሁላችንም ከልህና ከቁጭት ወጥተን በመነጋገርና በመመካከር ብቻ ነው። ወንድሞችና እህቶች ይህ የእምነት ስብስብ መሆኑንም አንዘንጋ።
በመደምደሚያው ባለፈው እሁድ የከርስትና ክፍያ ለአባላት ተነስቷል ተብሎ ሲነገር፤ ለቦርዱ አቤት ብዬ በማሳሰብ ያስፈጸምኩት እኔ ነኝ ያሉን ካህን ከአውደ ምሕረት ቆመው ሲዋሹ አለማፈራቸው እንዳሳፈረን ለመናገር እንወዳለን።
ምሕረቱን ያውርድላቸው።
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን