Tuesday, December 8, 2009

ስህተትን ማሰተካከል ሽንፈት አይደለም ቁጥር ፫

ሰላም ለናንተ ይሁን

ባለፈው እሁድ የአስተዳደር ቦርዱ ለከርስትና ይከፈል የነበረውን ክፍያ ማንሳቱን ማስታወቁ ይታወሳል። አጀማመሩ የሚደገፍ ቢሆንም ክፍያው የተነሳው ለቤተክርስቲያኑ አባላት ብቻ መሆኑን ስንሰማ ግማሹ ሊጥ ሆኖ አገኘነው። አባላት ያልሆኑ ክርስትና ለማስነሳት $150 መክፈል አለባቸው የሚለው አሁንም መነሳት ይኖርበታ እንላለን። ወንደሞችና እህቶች፤ ክርስትና በእምነት እንጂ በገንዘብ መገዛት የለበትም። ባለፈው ለምን ማስከፈል አስፈለግ ሲባል "ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሁሉ እየመጡ በነጻ ስለሚያስነሱ ነው" መባሉ አስገርሞን ነበርና። ከርስቲያን ድንበር የለውም ወንድሞች። ለማንኛውም ይህ እንዲሆን ለታገሉና የተጠየቁትን በስራ ለማዋል ለተነሱ ምስጋናችን የላቀ ነው። በመጭው እሑድ ደግሞ ለማንም ሰው የክርስትና ክፍያ ተነስቷል ብለው እንደሚያውጁ ተስፋ አለን። የአስተዳደር ቦርዱ ቅዳሜ አድርጎት በነበረው ስብሰባ $30 መክፈል የማይችሉ የቤተክርስቲያን አባላት በነፃ አባል የሚሆኑበትን መንገድ ለመወሰን መወያየቱን ስንሰማ ምን አስፈራቸው እንደድሮው ተመልሰናል ቢሉ እኮ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆንላቸው ነበር አልን። በተጨማሪም ከ $30 በላይ ይከፍሉ የነበሩ ነገር ግን በአውጅ ክፍያ ጨምረናል ሲባል ተናደው ክፍያቸውን ያቆሙ አንጋፋ የቤተክርስቲያናችን አባላት ወደ ደብራቸው እንዲመለሱ ይረዳል ብለንም እናምናለን።
በሰንበተ እሁድም እንደተለመደው በቤተክርስቲያናችን ያሉ የፖለቲካ ካድሬዎች ከቦርዱ ጋር እንደተነጋገሩ ስነሰማ ምን መአት ሊያመጡ ይሆን ብለን መስጋታችን አልቀረም። እነዚህ ከባሌ ሳይሆን ከጋርላንድ አዝማች ሆነው ጦር ሊመሩ የተነሱ ግለሰቦች በየሳምንቱ የቤተክርስቲያኑን የቢሮ ደረጃ ካልተመላለሱበት እንቅልፍ የሚነሳቸው፤ ከላይ ሆነው ደጀ ሰላሙ ውስጥ ማ ከማ ጋር ተቀምጦ አወራ የሚለው የሚያረካቸው፤ የማይማሩ ወይ የማያስተምሩ ሆነው ስናያቸው ማዘናችንን መናገርም አስፈላጊ ይሆናል። ቦርዱ እነዚህን ግለሰቦች እንደሚያዳምጥ ሌሎችንም ለማዳመጥ ቢችል ኖሮ ምናልባትም እዚህ አለንበት ሁኔታ ላይ አንደርስም ነበር። "በቤተክርስቲያናችን ግለሰቦች እየተሰለሉ ነው" ብለው ሊያሳምኑን የተነሱት እነዚህ ምእመናን ሰላዩ ማን ነው? ሲባሉ "አገርቤት ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት"እንደሆነ ይነግሩናል። ወንድሞችና እህቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚበጠብጡንን ግለሰቦች ዞራችሁ ተመልከቱና ማንነታቸውን አስተውላችሁ እነሱን ፈርቶ የሚሰልል መንግስት አይደለም ግለስብ ካለ ለጔደኝነት ቀርቶ ለጎረቤትነት አትመኙት። ለመሰለልም እኮ የሚሰለል ሰው መኖር አለበት:: "የሚገርመው የተናጋሪው ሳይሆን ያዳማጩ ነው" ይሉ ነበር በፊት።
በዘር መጡ አልሆነም፤ በፖለቲካ መጡ አልተሳካም፤ ስም በማጥፋት ተሰማሩ አልሰመረም፤ ወረቀት በተኑ አልሰራም፤ ብሎግ ከፈቱ አልተዋጣም፤ የጀመሩት ሁሉ ከሸፈ የሸረቡት ቱሻ ሆነ የተበተቡት ተበጣጠሰ። ካሁን በኋላ ወደ ነበረበት ለመመለስ መንገዱ አንድ ብቻ ነው። ስሕተትን አምኖ ንስሃ መግባት ብቻ። እሱም እምነቱ ካለ።
በነዚህ ግለሰቦች ውሸት የተጭበረበሩት ደግሞ አሁን ነገሩ እየገባቸው እየመጣ ነው። ፈረንጆች "አንዴ አታለኝ ቅሌታም ነህ ሁለት ጊዜ አታለኝ ቅሌታሙ እኔ ነኝ"ይላሉ።
ለቦርድ አባላት ልናሳስብ የምንወደው አሁንም ወደነበረበት ለመመለስ አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል።
1. መተዳደሪያ ደንቡን ወደነበረበት መመለስ።
2. የአባልነት ክፍያ ገደብ ማንሳት። የታገዱ አባላትን መመለስ።
3. ቤተክርስቲያኑን የፖለቲካ ሳይሆን የእምነት ቤት ማድረግ።
4. በፖሊስ ሳይሆን በእምነት መመካት::
5. መንፈሳዊ ውሳኔዎችን ለመንፈሳዊ አባቶች መተው።
6. መስራቾችን አባረን ገንዘብ እነዘርፋለን ብለው የተነሱትን በቄስ ማስመስከር መጽሐፈ ቄደር ማስጠመቅ።
አንጋፋ አዛውንቶችን ሰብሰቦ አባላት እንዲወያዩ ማድረግ መፍትሄ ይሆናል ብለን እናምናለን። በተጨማሪ ደግሞ፤ የቤተክርስቲያን ምእመናን በሞላ እውነቱን ለይተን ለእውነት ከቆምን ለመፍተሄው ትልቁን ስራ ሰራን ማለት ይሆናል። የምናምንበትንና እውነቱን እነጂ አዳማጩን እያየን መናገር ካቆምን ወደ ሰላም መመለስ የሚቻል ይመስለናል። ክስ የመሰረቱትም ግለሰቦች ከዚህ የተለየ ፍላጎት ካላቸው ሊነግሩን ይገባል። ብዙ ሰው እንዳለው በዚህ ቤተክርስቲያን ተሸናፊና አሸናፊ መኖር የለበትምና።
ሰላም ዋሉ