Friday, December 18, 2009

ማንም ሳያሸንፍ ቀረ ቁጥር ፭

በትላንትናው እለት ይጠበቅ የነበረውን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለማየትና ለመስማት ተገኝተን ነበር። ከሳምንት በፊት ዳኛው ለማንም ፈረደ ለማን ተሸናፊና አሸናፊ አይኖርም ብለን መናገራችን ይታወሳል። ትላንት አስችሎ የዋለውን ችሎትም ካየን በኋላ አባባላችን ትክክል መሆኑን ያረጋገጥን ይመስለናል። የከሳሾቹ ጠበቃ " እነዚህ ሰዎች ያላግባብ ዘልፈውናል ቴሬሪስት ናቸው ብለውም ወንጅለውናል" ብሎ መናገር ሲጀምር ዳኛው እሱን መስማት አልፈልግም ብሎ ጠበቃቸውን ሲያስቆመው ስናይ ከተቀመጥንበት ተነስተን እግዚአብሄር ይስጥህ ልንል ምንም አልቀረን ነበር። የቦረዱ ጠበቃ የሃይማኖት ጉዳይ መሆኑን ሊያስረዳ ሲነሳ እሱንም እንዲሁ እሱን ማዳመጥ አልፈልግም ብሎ ሲያስቆመው ስናይና ሁለቱም ወደ ጭብጥ ጉዳዩ እንዲገቡ ሲነግራቸው ሚዛናዊ አመለካከት እንደሚኖር ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነበርን። የቦርዱን ጠበቃ ለምን ሕጉን ቀየራቸሁ? የቀየራችሁት የማትፈልጉትን አባላት በማባረር፡የምትፈልጉትን ብቻ ይዛችሁ በጥቂት ሰዎች ቤተክርስቱያኑን ለመቆጣጠር መሆኑ ግልጽ ነው። ዛሬ 10 ዓመት ብላችኌል ነገ ደግሞ 28 ዓመት ትሉ ያሆናል ብሎ በንዴት የተናገረው ዳኛ፡ ለመሆኑ ግለሰቦችን ስታባርሩ ወይንም አላስፈላጊ ውሳኔ ስትወስኑ አባላት ምን መከላከያ መንገድ አላቸው? ብሎ የቦርዱን ጠበቃም ጠይቆት ነበር። የቦርዱ ጠበቃ መልሱ የነበረው ያልፈለጉትን የቦርድ አባል በምርጫ ማውረድ ይችላሉ። በተጨማሪም የተወሰነባቸው ውሳኔ አግባብ አለመሆኑን በመጠቆም አቤቱታ ቦርዱ ለሚያቌቁመው የእንባ ጠባቂ ኮሚቴ ማቅረብ ይችላሉ የሚል ነበር። የከሰሰ ከአባልነት ይባረራል አባላትን የሚመርጠው ቦርዱ ነው። ቦርዱ ያወጣውን ከፍያ የማይከፍል ወዲያውኑ መባረር አይደለም እየከፈለም ቦርዱ ካልወደደው አይቀበለውም ያለው የከሳሾች ጠበቃ የተናገረው ዳኛው ለመሆኑ ባዲሱ መተዳደሪያ ደንብ ምን የተቀየረ ሌላ ነገር አለ ብሎ? ለጠየቀው መልሰ ሲሰጥ ነበር። ሕጉን ለመቀየር የቤተክርስቲያኑ መተዳደሪያ ሕግ አንቀጽ 11.1 እና 11.2 ለቦርዱ መብት ይሰጣል አይሰጥም የሚለውን የጠበቆቹን ገለጻ አዳምጦ ውሳኔ እነደሚሰጥ ተናግሮ መልካም ገና ለሁሉም ተመኝቶ ዳኛው ችሎቱን ዘግቶታል።
በግል እንደታዘብነውና ሂደቱን እንደተከታተልነው። ሕጉን ለምን በክስ መሃል ለመቀየር አስፈለገ ለሚለው? የራሳችን መልስ የሚከተለው ይሆናል።
1 የማይፈልጉትን አባላት ለማባረር።
2 አዲስ የሚገቡ አባላትን ለማጣራት ለማበጠር።
3 አባላት ተቀበሉትም አልተቀበሉት የራሳሸውን ውሳኔ በመሰላቸውና ከቦርዱ ጥቅም በመነሳት ለመወሰን።
4 የእምነትን ጉዳይ አስመልክቶ ቄሱ ምን መሰበክ እንዳለበትና እንደሌለበት ለመንገር።
5 አባላት ለመመዝገብ ሲመጡ እንደ አፓርትመንት የማመልከቻ ማስከፈል። አባልነታቸውን ተቀባይነት አገኘም አላገኘ የከፈሉት እንዳይመለስ ማድረግ።
6 ገለልተኛነትን በመስበክ የሲኖዶስን ቦታ መተካት። ነው ብሎ ለማለት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም።
ታዲያ ከላይ ያልነው ተፈጻሚ ከሆነ የተጎዳው ማን ነው? መልሱን ሁላችንም በግል መመለስ ያለብን ይመስለናል። መልሱን ከዳኛ መጠበቅ የለብንም ለማለት ነው። አባላት የሚፈልጉት ይህንን ከሆነ ከሳሾች ቢያሸንፉም መጨረሻው ይኸው ይሆናልና።
ዛሬ ስልጣን ላይ ሆነው ያወጡት ሕግ ነገ ከስልጣን ሲወርዱ መልሶ እነሱንም እንደሚያጠቃ ማወቅ ደግሞ ብልህነትን አይጠይቅም።
ለመብትና ለእምነት ብሎም ለእኩልነት መታገል እንጂ ለማሸነፍና የሌላውን መብት ለመዳመጥ መነሳት መንፈሳዊም፤ ሕጋዊም ፖለቲካዊም መሆን አይችልም።
የዳኛውን ውሳኔ አልሰማንም ምንም ይሁን ግን መፋቀርን አያመጣም። ቤተክርስቲያን የመንፈስ እረፍት ያለበት ቦታ እንጂ የጭቅጭቅ ስፍራ መሆን የለበትምና።
ከፍርድ ቤት ውሳኔ እንሰማለን በውሳኔው ግን አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም።
መልካሙን ለሁላችን እንመኝ።