Wednesday, April 7, 2010

ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከበረት ውጭ ታሳድራለች። ፳

ውድ አንባብያን እንኴን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ብለን ከሳምንት ዝምታ በኋላ በድጋሜ የመልካም  ምኞታችንን ስንገልጽላችሁ ዓመት በዓሉን በሰላም ከቤተሰቦቻችሁ ጋር እንዳሳለፋችሁ  በመተማመን ነው።  የትንሳኤ በዓል ለማክበር የተሰበሰበውን ሕዝብ ብዛት በማየት ያልተደነቀ ሰው ነበር ብሎ መናገር ይከብዳል። እውነትም የምእመናኑ ብዛት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ከመሰጠቱ ባሻገር ሁኔታውን የተመለከተ ያለሁት አገር ቤት ነው አሜሪካ? ብሎ ቢጠይቅ አይፈረድበትም። ማኅሌት የቆሙት ካህናት ሌሊቱን ሙሉ ደከመን ሳይሉ ሰርጓ እንዳማረላት ሙሽራ እየተውረገረጉ  ሲወርቡ ያየ ሰው ለመቀላቀል ቢነሽጠው  በተቀመጠበት ማሸበሽብ ቢጀምር ሁሉም አበጀህ ይለው እንደነበር መናገር ማጋነንም አይሆንም።

ታዲያ ሁኔታዎች እንደዚህ ባማሩበት የክርስቶስን ትንሳኤ በደሰታ በምናከብርበት ወቅት አስደንጋጭ ሁኔታ ተፈጠረ። መቅደሱ ውስጥ የነበሩት ካህን የድምጽ ማጉሊያውን በመጠቀም በሕግ አምላክ እያሉ ወደ ተሰበሰቡት ካህናት በመምጣት ታምረ ማርያሙ ሲነበብ መቅድሙ ታልፏልና መደረግ የለበትም በሕግ አምላክ በሕግ አምላክ ማለታቸውን ቀጠሉ። ለነገሩ ድጔው አልቦ መቅድም ወአልቦ መልክአ ስእል  ማለቱን ሰሞነኛው ቄስ የተረዱት አልነበረም። በትንሳኤ ቀን በሚደረግ ስርአት ላይ እንደ 33 የእመቤታችን በአላትና እንደተቀሩት እለተ ሰንበቶች   እንደማያስገድድ ደግሞ ለሳቸው እንግዳ ቢሆንባቸው አልተደነቅንም። በመቅደስ ውስጥ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አገልግሎት የሚሰጥ ካህን  አይደለም ማንም የመንፈሳዊ አባት በሕግ አምላክ ማለት ከጀመረ የእምነት ክስረት አለበት ብለን ብናስብ ትክክለኛ አመለካከት ይመስለናል። መገዘትን ያክል ስልጣን ያለው ካህን በሕግ አምላክ አለ ማለት ጠመንጃውን አስቀምጦ በቆመጥ ሊዋጋ  እንደሚነሳ  ወታደር ተምሳሊት አይነት መሆኑ ነውና።

ጥፋት አልተደረገም እንጂ ተደርጎ ቢሆን እንኴን ዲያቆናቱን በመላክ ወይንም ቀርቦ በሹክሹክታ እርስ በርሳቸው በመነጋገር መተራረም   ሲቻል ካልሆነም በሌላ  ጊዜ መወያየት ተገቢ ሆኖ ሳለ ምእመናን እስኪደናገጡ እናቶች በእንባ እስኪራጩ ድረስ ሕዝቡን ማስደንገጥ አሳፋሪ ነው ከማለት ሌላ ምን ማለት ይቻላል። የቄሳር ሕግ በቄሳር ስፍራ እንጂ በቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ለመጠቀም መሞከርስ ምን ማለት ነው?

ሁኔታውን የታዘበው ቀልደኛው ወንድማችን ማታ ላይ ምን አለን  መሰላችሁ። ጥፋቱ የጮሁት ካህን ሳይሆን እኝህ መንፈሳዊ አባት የማያውቁትን ማህሌት ያሳመሩት የድጔ የቅኔ የአቌቋም እውቀታቸውን በሚገባ  ያሳዩት የሌላው ካህን ጥፋት ነው። እሳቸው እውቀታቸውን ባያሳዩ  ኖሮ በሕግ አምላክን ባልሰማን ነበር። እኔም እንዳንተ አቌቋም ድጔ ባልማር ቅኔ ባልችል አዋቂ እኮ ነኝ ብለው ታምረ  ማርያም እንደሚያውቁ ለማሳየት በሕግ አምላክ ቢሉ ለምን ተገረማችሁ ብሎን አረፈ ። እንዴውም ከቅዳሴው በኋላ ወደ መጨረሻ እልል በይ ይል የነበረው ካህን እሱም የመዘመር እውቀት እንዳለው ለማሳየት ያደረገውን ጥረት አላስተዋላችሁምን? ብሎን አረፈ። ቀጠለና ይህ ያዘምር የነበረው ካህን የድምጽ ማጉያውን እኔ ስዘምር ትቀንሳላችሁ ብሎ  በመክሰሱ ለድምጽ ማጉያው የድምጽ መቀነሻና መጨመሪያው ቁልፍ ተሰርቶለት እንደተቆለፈ የነገረንም በዚሁ ወቅት ነበር። ወንድሞቼ ጽድቅ በጩኸት አይገኝም።

ስለ ቁልፍ መቀየር ካነሳን ዘንዳ የቤተክርስቲያኑ ቁልፍ $4000 በላይ ወጥቶበት በቁጥር የሚከፈት እንዲሆን መደረጉን እስካሁን ሰምታችኋል ብለን እናስባለን። ካሁን በኋላ ቤተክርስቲያኑን የሚከፍቱት ፈቃድ ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ይሆናሉ። የቤተክርስቲያኑን ኮምፒውተር ደግሞ እውቀት ያላቸው ዶክተር ከባለቤታቸው ጋር መረከባቸውን ስንሰማ አልተገረምንም።ነገ ደግሞ  ቤተክርስቲያን የሚያስቀድስ ሁሉ እንደስብሰባ አባልነቱ እየተጣራ  እንዲገባ  የሚደረግበት ሰዓት ይመጣል ብንል ትንቢት አይሆንም። የሁኔታዎችን አካሄድ ግንዛቤ  ውስጥ በማስገባት  ስለመጭው መናገራችን እንጂ።

ነገርን ነገር አነሳውና የድሮ  ቀልድ ታወሰን ሚስት የባሏን ኪስ ስትፈትሽ አንድ አይደለም 4 የራሷን ፎቶግራፍ አገኘች። ወደ ባሏ ሆደችና እንደምትወደኝ ገባኝ አንድ አይደለም 4 ፎቶዬን በኪስህ ይዘህ እንደምትጔዝ ደረስኩበት አለችው። እሱም አዎ "ችግር በገጠመኝ ቁጥር ፎቶሽን በማየት የገጠመኝ ችግር አነስተኛ ሆኖ እንዲታየኝ  ይረዳኛል" አለ  ይባላል።
በነገራችን ላይ እንዴው ሁኔታዎቹን ስናስብ የድሮ ግጥም ትዝ አለን

እናት አባት ቢሞት ባገር ይለቀሳል
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል። ይባል ነበር።

እኛም ሌላ ጥያቄ  እናንሳ። ምእመን ሲያጠፋ  በንስሐ አባት  በምእመን በሽማግሌ ይወቀሳል። ታዲያ  ባለው ሁኔታ ያጠፋ ካህን ሲያጋጥም በመጀመሪያ ማጥፋቱን የሚያየው አካል ማነው? የሚገስጠውስ ማን ይሆን?  ትክክል መሰራቱን የሚቆጣጠረው የትኛው አካል ይሆን? መልሱን ለናንተ  እንተዋለን።

ችግሩ እየሰፋ መጥቶ የት እንደደረስን ለመታዘብ እድል እንዲሰጣችሁ በሚል የሚከተለውን vidio እንድትመለከቱት መረዋ ይጋብዛል።

http://www.youtube.com/watch?v=xaYl8KZNKco&feature=related


በሌላ  በኩል በያዝነው ወር በ17 በሚደረገው አጠቃላይ ስብሰባ ቦርዱ አንድ አይነት አቌም ይዞ  እንዳልመጣ መስማታችንን ስንነግራችሁ ሁኔታው ያስፈራቸው የቦርድ አባላት በግል አባላትን እያነጋገሩ የተለመድ የፖለቲካ ቅስቀሳ እያኪያሄዱ መሆኑን ልንነግራቸሁ እንወዳለን። ለእውነት የቆመ ክርስቲያን ነገሮችን እንዳመጣጣቸው ይቀበላል እንጂ በቅድሚያ ተሰብስቦ ምን ብለን እንዋሽ አይልም።
በሚቀጥለው እትማችን  Senbete የተባለው ብሎግ ያወጣውን ጽሑፍ አስመልክቶ በመረጃ  የተደገፈ የራሳችንን ግንዛቤ በሰፊው እናቀርብላችኌለን። እስከዚያው ድረስ ሰላም ሁኑ።