Wednesday, April 28, 2010

የወንጌል ቃል የሚያስፈራው በእምነት ደካማ የሆነን ብቻ ነው። ቁጥር ፳፬

እውነትን ማጣመም ይቻል ይሆናል። መግደልና መቅበር ግን አስቸጋሪ ነው። የተለያየ ውሸትን በመወርወር አንዱ ይለጠፍና  ይቀር ይሆናል ብለው በሚያልሙ የቤተክርስቲያን መሰባሰብና  ሕዝቡ በሰላም ማምለኩ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣቱ እንቅልፍ በሚነሳቸው ግለሰቦች ዛሬም እንደትላንቱ የሸር ቱሻ እየገመዱ የሞቀ ቤት እያፈረሱ ይገኛሉ። አለቆቻቸው የቤተክርስቲያን ቦርድ ተመራጮች የበደል አለንጋቸውን እያወናጨፉ እነዚህን ግለሰቦች እንዲጮሁና እንዲናከሱ ትእዛዝም እንዳሰተላለፉላቸው ከድርጊታቸው መገንዘብ ይቻላል።

ውድ የቤተክርስቲያን አባላት። ባለፈው ቅዳሜ ከቤተክርስቲያን እንዲሰናበቱ የተደረጉትና  በቤተክርስቲያን አካባቢ እንኴን ዝር እንዳይሉ ቦርዱ ፖሊስ ጠርቶ ያስፈረማቸው ካህን ስለሁኔታው ሲናገሩ ያዳመጡ ግለሰቦች እንደነገሩን ከስራ  እንደተባረሩ ሲነገራቸው "መባረሬ መልካም ለእምነቴ የምከፍለው የጸጋ ዋጋ ነውና ቅር  አልሰኝም  ነገር ግን የቤተሰቤን የሕጋዊ ወረቀት ሂደት ( IMMIGRATION PROCESESSE) አስመልክቶ እያለቀ ያለ ነገር በመሆኑ ተባበሩኝ"  ብለው ቢማጸኑ እንኴን እንቢኝ እንደተባሉ  ስንሰማ እንደ ስደተኛነታችን ወላጅ እንደመሆናችን ከልብ አዝነናል። ውድ አንባብያን። እዚህ አገር ስደተኞችንም  ሆነ  የመኖሪያ ወረቀት የሌላቸውን ግለሰቦች  የሚረዱት የተለያዩ  ቤተክርስቲያናቶች መሆናቸው እየታወቀ፡ የኛ የቤተክርስቲያን መሪነን ባዮች ግን ፈቃድ ለማግኘት የተቃረቡትን አባት ከነልጆቻቸው ወደአገራቸው ለመመለስ ሽር ጉድ ማለታቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። ልጅ ያላችሁ ቤተሰብ የሆናችሁ የመኖሪያ  ወረቀት ችግር የነበረባችሁ ሁሉ ሊሰማችሁ ይገባል። ባገራችን ወንጀለኛ እንኴን ነፍሱን የሙጥኝ የሚለው ቤተክርስቲያን ተጠግቶ  እንደነበር እየተረሳን የመጣ ይመስላል::

አንድ ግለሰብ እዚህ አሜሪካን አገር ያሉ የስፓኒሽ ተወላጆችና  የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ ተጋዳዎች በአሜሪካ  ውስጥ ወደ 12 ሚሊዮን የሚደርስ የመኖሪያ  ወረቀት የሌለውን ግለሰብ የመኖሪያ  ወረቀት እንዲሰጠው መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ ሲያጨናንቁ እያየን እያለ፡ የኛ የቤተክርስቲያን መሪዎች ግን የካህኑን የመኖሪያ  ወረቀት ጉዳይ አስመልክቶ ለኢሚግሬሽን ደብዳቤ  በመጻፍ ለማጨናገፍ  ይጣደፋሉ። ይህ ደግሞ  "ፈጣሪ አንዱን ኢትዮጵያዊ አግኝቶ ምን ላድርግልህ?  ጠይቀኝና እፈጽምልሃለሁ  ያደረኩልህን እጥፍ ደግሞ  ለጔደኛህ አደርግለታለሁ ቢለው አንድ ዓይኔን  አውጣልኝ"  አለው የሚለውን ቀልድ ያስታውሷል አለን። አልሳቅንም ፈዘን ቀረን እንጂ።

ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች እያነሱ የመጡት ጥያቄ አባል እንሁንና  ከውስጥ መቀየር ይቻላል የሚል ነው። የረሱት ነገር ቢኖር

ትላንት አትናገሩም የተባሉት እኮ  አባላት ነበሩ።
ትላንት በፖሊስ የተባረሩት እኮ  አባላት ነበሩ።
ትላንት የስብሰባ  ወረቀት አስፈርመው ስብሰባ  የተከለከሉት አባላት ነበሩ።
ትላንት በስብሰባ ላይ የተሰደቡት አባላት ነበሩ።
በተጨማሪ ቀይረንዋል ባሉት ሕግ  2.1 መሰረት አንድ ክፍያ  ለ ስድስት ወር ያቆመ ግለሰብ አባል ለመሆን $50  ከፍሎ ማመልከቻ  ማስገባት እንዳለበት ጠቅሶ ማመልከቻው በቦርዱ ከጸደቀለት የመምረጥና  የመመረጥ መብት የሚኖረው ከአንድ ዓመት በኋላ መሆ ኑን ይጠቅሳል። ዓመት አይደለም ሁለት ወር ያልሞላው ቡድንም ያደረሰውን በደል እያየነው ነው።

እንደ ባንክ ብድር በፊርማቸው ብቻ  ስብሰባ  ያስጠሩ የነበረ  ዶክተር ሰሎሞን ለስብሰባ ሲመጡ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ያየ አባል በመሆን ካመት በኋላ  ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ እንዴት ሊያሳምነን ይችላል?

የተመረጡትን የቦርድ አባላት ያሰተዋወቁ የአማካሪ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ  ሰይፉ ካሳ ስብሰባውን ለመካፈል ሲመጡ አትገቡም ተብለው በመመለሳቸው እንዳዘኑ ይገባናል። የተባረሩት ግን የቀድሞውን ሊቀመንበር ይደግፋሉ በሚል እንጂ አባል ስላልሆኑ ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ?

ለመሆኑ አባል ቢኮንስ በፖሊስ አትድረሱ እያሉ ካላባረሩን በስተቀር የሚቀርብን ምን ይሆን? ጽድቅ ከበጎ ምግባርና  ከእምነት እንጂ አባል በመሆን የሚገኝ የሚመስላቸው ካሉ መመከር ያስፈልጋቸዋል።

ለናሙና አዲሱ መተዳደሪያ  ሕግ የሚለውን እናንሳላችሁ።

2.6 .................... ኮረም  ሁለት ጊዜ ካልሞላ ለውሳኔ  የቀረበው ጉዳይ ቦቦርዱ ውሳኔ ይወሰናል"
ትርጉም የራሳችን ።
በተገኘው ሰው ይወሰናል ቢል ይገባን ነበር በቦርዱ ይወሰናል ነው የሚለው። ታዲያ የአባላትን ሳይሆን የፈላጭ ቆራጭ ቦርድ ስልጣንን ለሚያጠናክር አካል ድጋፍ ለመስጠት ነው አባል የምንሆነው?
ለመሆኑ መተዳደሪያ ደንቡ እንዴት ተቀየረ? ማን ተወያየበት?
ሁላችንም በ40ቀን በ 80 ቀን ስንጠመቅ የቤተክርስቲያኑ አባል እንደሆንን እንዴት እንዘነጋለን።
በክርስቲያን መርህና እምነት ሳይሆን በፖሊስ ብዛት   እገዛለሁ የሚል የቤተክርስቲያን ቦርድ አካል ለመሆን ከሆነ  ጥረቱ ክርስቲያናዊ እሚሆነው እምኑ ላይ ነው?
በኛ እምነት ተሰባስበን መወያየት ተወያይተን መፍትሄ ላይ መድረስ አለብን እንላለን።
ነገ  በሺህ ግለሰቦች አስተዋጽኦ የተሰራው ቤተክርስቲያ 125 ባልሞሉ አባላት ተሸጠ ቢባል እንዳናዝን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዛውም ሁሉም ሳይስማሙበት።


SENBETE የሚለው ብሎግ እንደተለመደው  ቆንጆ  ስድብ አዝሎ  ወጥቷልና  እባካችሁ አንብቡላቸው። የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባየሁ ነው እንዲሉ።