Saturday, April 10, 2010

{ሰበር ዜና } የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል !! ቁጥር ፳፩

"ያረገዘ  መውለዱ አይቀርም ይሉ ነበር አንድ የአብማ  ወይዘሮ "


እኛ እንኴን ቀጠሯችን በሌላ እርእስ  ነበር።  የሆነ ሆኖ "በእለተ ቀኑ በአለእግዚአብሔር ቸር ወሬ እንድንሰማ አደረገን" የሚሉ አባላት አነጋግረን ስላጋጠማቸው  ደስታቸው ደስ ለሚላቸው አማንያን መናገሩን እኛም አመንንበት። በእለተ ቀኑ የተሰማው ቸር ወሬ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?  ለቤተክርስቲያኑ አባላት መብት መታገል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው  የሚሉት አባላት ክስ መስርተው ባለፈው ዳኛው "ቦርዱ ሕግ የመቀየር መብት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አለው የሚል የሚያሻማ ሐረግ በመኖሩ የቀየሩት በግልጽ አባላትን ለማባረር የቤተክርስቲያኑን ንብረት ለመቆጣጠር እንደሆነ ቢገባኝም ድርጊቱ በመብታቸው ዙሪያ ነው በማለት"የወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ከሳሾች ይግባኝ በማለታቸው ነው።  

የይግባኙን ዶሴዎች የተመለከተው THE  TEXAS 5TH DISTRICT APPEALE COURT OF DALLAS በ 04-07-10 ፋይሎችንና የተቀረጹ የክርክሩን የድምጽ ካሴቶች በማዳመጥ "እውነት ነው ይግባኙ መታየት አለበት ብሎ"  በመስማማቱ የመጀመሪያው የጠበቆች ክርክር በ 05-18-10 እንዲሰማ መቀጠሩንም እኛም ተከታትለን እንደደረስንበት ልንነግራችሁ እንወዳለን። 


ውድ የቤተክርስቲያን አባላት። ክርክር መጥፎ እንደሆነ በተለይም ክርክሩ በቤተክርስቲያን አካባቢ ሲሆን ይበልጥ እንደሚጎዳ መረዋ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል። ማንም አሸነፈ እንደማይሆን  የምንጎዳው ደግሞ ሁላችንም ነን ብለንም ነበር። .............የገደለው ባሌ የሞተው ወንድሜ.............አይነት። ግና ከቦርድ ተመራጮች ወገን የምናየውና የምንሰማው ትንሽ እያስከፋን እየመጣ መሆኑን ሳንናገር ብናልፍ በራሳችን ላይ መዋሸት ይሆናል። በተለያየ ወቅት ሊያናግሯቸው የመጡትን ሁሉ ገንዘብ ተበድሮ መመለስ እንዳቃተው ተበዳሪ ምክንያት እያበዙ ከውይይት ሲሸሹ መመልከታችንንም መደበቅ አንወድም። አንድን መንፈሳዊ አባትን "ካድሬ ቄስ" ብሎ የሚጠራ የቦርድ አባል ዞር ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት እንላለን። ሰሞኑን ደግሞ ባለፈው እንደነገርናችሁ በቤተክርስቲያኑ ተከስቶ የነበረውን የካሕናት ችግር ላይ ቦርዱ በወገነኝነት ያጠፋውን ሳይሆን ያላጠፋውን ለመገሰጽ እንዳሰቡ ስንሰማ ጊዜው ሲደርስ የምንለው ብዙ ነገር መኖሩንና የተደገሰው ድግስ እንደሰማነው እውነት ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የአባላትን ተሳትፎ በሰፊው የሚጠይቅ እርምጃ ለመውሰድ መረዋ መነሳቱን በቅድሚያ ማሳሰብ እንወዳለን።

ውድ አንባብያን ኒቆዲመሶች በብዛት እንዳሉ እናውቃለን የጴጥሮሶች እጦት እንዳለ ግን የተገነዘብን አልመሰለንም። ቼ ጉቤራን መፍጠር ቀላል ይሆን ይሆናል ትልቁ ችግር ማርቲን ሉተርን መፍጠር ላይ ነው።  ይሁዳ መሆን ያጔጔ ይሆናል የሚከብደው እነደ አቡነ  ጴጥሮስ እራስን መሰዋት ነው። ሃገር ወዳዶች ነን ማለት ይቀል ይሆናል፤ የሚከብደው ከዘር ማነቆ አስተሳሰብ መውጣቱ ነው። ፖለቲከኛ መሆን ፈቃድ የማይጠየቅበት ክፍት ስራ ነው፡ የሚከብደውና እውቀት የሚጠይቀው የመነፈሳዊ አባት መሆንና መንፈሳዊ ተግባር ማሳየት ነው።

በዳግም ትንሳኤ ቦርዱ ምን እንደሚል መተንበይ ተቸግረናል በትንሳኤው እለት ሊቀመንበሩ ያነበቡት እስካሁን ምን እንደሆነ አልገባንምና።

እንዴው ለፈገግታ ያክል አንዱ አንባቢያችን የላኩልንን ቀልድ እናካፍላችሁ። ከአረብ አገር ወደ አሜሪካ የመጡ ቤተሰቦች የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነውን ልጃቸውን አብዱል ከሪምን ትምህርት ቤት አስገቡት። በመጀመሪያው ቀን አስተማሪው የልጁን ስም ጠየቀው ልጁም ስሙን ተናገረ መምህሩም ስምህ ስለረዘመ ብሎም ለአሜሪካዊ ጔደኞችህ መጥራት እንዳይከብዳቸው ከዛሬ ጀምሮ ዊልያም እያልን እንጠራሃለን አለው። ቀኑን ሙሉ ሁሉም ዊልያም እያለ ሲጠራው ዋለ። የትምህርቱ ቀን አለቀና እቤት ሲደርስ እናቱ አብዱል ከሪም ብላ  ስትጠራው እማየ የለም ዊልያም ብለሽ ጥሪኝ አላት በሁኔታው የተናደደችው እናት ትላንትና  አሜሪካ  መጣህና የኛ ስም አስጠላህ ብላ ገረፈችው። አባቱም እንዲሁ ሁኔታውን ሰምቶና ተናዶ ልጁን እንደ እናትየው ደበደበው። በማግስቱ ወጣቱ ትምህርት ቤት ሲሄድ ስሙን ያወጣለት አስተማሪ በልጁ አካል ላይ ያለውን ሰንበር ተመልክቶ ምን ሆንክ? ብሎ ሲጠይቀው  ወጣቱ ምን አለ  መሰላችሁ ሁለት አረቦች አሜሪካዊ መሆኔን በስሜ ሲያረጋግጡ  ተባብረው ደበደቡኝ አለ አሉ። ፈገግታ መልካም ነው እህቶቼና ወንድሞቼ። ሁላችንንም ከሃዘን ይሰውረን።

ቸር አሰምቶ በቸር ይግጠመን