እንደምን ከረማቸሁ? እንኴን ለዓመቱ ለሰኔ ሚካኤል ክብረ በዓል አደረሳችሁ እያልን መጭውን ዓመት የፍቅርና የደስታ እንዲያደርግልን መረዋ ከልብ ይመኛል። ባለፈው ዓመት ምን አጣላን ብለን ማሰብ ብቻ ሳይሆን መጭውን ዓመት እንዴት የሰላም ዓመት ማድረግ ይቻላል ብለንም ከማሰብና ከመጨነቅም አንቆጠብም። ምን ግዜም ጥረታችን ሰላም መፍጠር ነውና።
እስካሁን ድረስ ሰው ስንዘልፍ አላያችሁንም። በመረዋ ምክንያት ግን ግለሰቦች ተዘልፈዋል። እስካሁን ድረስ የማንንም መብት ስንጋፋ አላያችሁንም። በመረዋ ምክንያት ግን ግለሰቦች ዘራቸው ተቆጥሮ፤ የሞቱት ዘመዶቻቸው ተወስተው፤ የፍቅር ግንኙነታቸው ሳይቀር ተነስቶ፤ የመንፈስ ጥንካሬአቸው ተተችቶ፤ ምስጢረ ቁርባን መሳለቂያ ሆኖ የፖለቲካ ጀርባቸው ታይቶ፤ ባልዋሉበት እንደወንጀለኛ ተፈርጀዋል። ይህ ሁሉ መሸካከርን ከማምጣቱ ሌላ መቀራረብን ይፈጥራል ብሎ ግን መረዋ አያምንም። መረዋ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰላምና ፍቅር አይመሰረትም ያለው ቀደም ባለው ሰዓት እንደ ነበር ለአንባብያን በድጋሜ ማስታወስ ይወዳል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ባለፈው ተመስርቶ በነበረው ክስ ማለትም ከቤተክርስቲያኑ ሰው ማባረር አትችሉም፡ ያልረበሸን ግለሰብ በፖሊስ አታባርሩም፡ መረጃዎችን አታጠፉም: የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ ያላግባብ ማጥፋት አትችሉም ተብሎ ተመስርቶ በነበረው ክስ ዳኛው የሰጠውን ብያኔ ለምእመናን በቤተክርስቲያኑ መንበር ቆመው "እንኴን ደስ ያላችሁ አሸነፍን" ብለው ተናግረው የነበሩት የቦርድ አባላት አሁን ለምን ይግባኝ ጠየቁ?
ያሸነፈ እንዴት ይግባኝ ይጠይቃል?
ካልሆነ የተሰጠው ውሳኔ ያስፈራቸው ከምኑ ላይ ነው?
ይግባኙ ምእመንን ማባረር አለብን፡
ዶሴዎችን መረጃዎችን ማጥፋት ይፈቀድልን፡
በፖሊስ ታጅበን ቅዳሴ እንድናደርግ ይፈቀድልን ማለት ይሆን?
ይህንን ያነሳነው ገንዘብን አስመልክቶ የተነሳው ጥያቄ ለጊዜው ዳኛው አልተቀበለውምና እንደፈለጋቸው ቼክ እየጻፉ መክረምን ለምን ጠሉት? በማለት ነው።
መረዋ የራሱ መልስ አድርጎ የወሰደው መሸነፋቸውን ተቀብለዋል ባይሆንማ ኖሮ ይግባኝ መጠየቅን ምን አመጣው? የሚል ይሆናል።
በተጨማሪ ቀደም ብሎ ተመስርቶ የነበረውና ቦርዱ አሸንፎ ከሳሾች ይግባኝ ያሉበት ሌላው ክስ የቦርድ አባላት በያዝነው ወር JUNE 17, 2010 መልስ እንዲሰጡ ተወስኖ የነበረውን ቀነ ቀጠሮ በጠበቃቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበው ተጨማሪ አንድ ወር እንደተሰጣቸው ማወቃችንን ለአንባብያን መግለጽ እንወዳለን። በሚመጣው እትማችን ሰፋ ያለ ዘገባ የምናቀርብበት ሌላ ጉዳይ እንዳለ እየነገርናችሁ ለዛሬ በዚሁ እንሰናበታለን። እንዴ ው ለማሳሰቢያ ያክል፦
ማንም ሰው ከየትም ይወለድ ትወለድ ክርስቲያን ከሆነ ወንድም ነው ከሆነች እህት ነች።
ማንም ሰው ምንም የፖለቲካ አመለካከት ይኑረው ይኑራት በኦርቶዶስ እምነታችን አምኖ ከተጠመቀ አምና ከተጠመቀች ቤተክርስቲያናችንን ከተቀላቀለ ከተቀላቀለች ወንድም ነው ወይም እህት ነች።
በሰላም ይግጠመን።