Tuesday, June 29, 2010

የቅዳሜው ስብሰባ በስምምነት ተፈጸም ቁጥር ፴፭

ከስተሻል ጠቁረሻል ሆነ ጥያቄአቸው
ሽል አለ  በሆዴ  እንዴት ላሳያቸው።

ብላ  የዘፈነችው ማ ነበረች? ዘመኑ ገፋና  እኛም እየዘነጋን መጣን ማለታችን  ነው። ዘፋኟ ይህንን  ያለችው የወደደችው መኖሩን ለመጠቆም  ነበር። በቅዳሜው ስብሰባ  ላይ ግን ምን ብናደርግ ይሻላል? ለሚለው መልስ ሊፈልጉ የተላኩት 9 የከተማችን አዛውንቶች በቤተክርስቲያኑ የቦርድ ተመራጮች እንቢታ አዝነው መመለሳቸውን ለተሰበሰበው ምእመን ሲያቀርቡ ያላዘነ  አንድም ሰው አልነበረም። "ቤተክርስቲያንን መክሰስ አግባብ አይደለም  ብለን ስንቃወም ከርመናል አሁን ግን ለምን ከሳሾች ወደ ሕግ እንደሄዱ ሙሉ ለሙሉ ገብቶናል" ያሉት ሁለት ሰዎስት ግለሰቦች ሳይሆኑ  ስብሰባውን የተካፈለው በመላ  እንደ ነበር ስንነግራችሁ የሕዝቡ ቆራጥነት እኛንም  አስፈራርቶን   እንደነበር መናገር ደግሞ  እውነተኛ ምስክርነት ነው። "ይህ ክስ ባይመሰረት ኖር ከነቤተሰቦቼ  ከቤተክርስቲያን የምባረረው አንዱ ግለሰብ እኔ  ነበርኩ"  ያሉት አዛውንት "ድሮ  ቤተክርስቲያናችን የነፍሰ ገዳይ እንኴን ሳይቀር የአማልዱኝ ቦታ እንደነበረ ጠቁመው "እነሆኝ ዛሬ ቤተክርስቲያናችን አማንያንን ለማባረር ሲሯሯጥ ማየትን የመሰል የሚዘገንን ነገር ግን አለመኖሩን"  ተናግራዋል።

"ተወያይቶ በሃሳብ መለያየት አንድ ነገር ነው አንወያይም ማለት ግን ያውም በዚህ ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሃገር ኋላ ቀርነት ነው" ያሉት የኮሚቴው ተወካይ እሳቸውም እንደ ሌሎች ተናጋሪዎቹ ሁሉ ክሱን አስመልክቶ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበራቸው ጠቅሰው አሁን ግን ለቤተክርስቲያኑ ሰላም ያለው አማራጭ ሕግ ብቻ መሆኑን መቀበላቸውን አስምረውበታል። 

የኮሚቴው ወሳኔና አጠቃላይ ገለጻ ከመነበቡም ባሻገር የዘገባው ግልባጭ ለተሰብሳቢዎቹ ታድሏል። ክርስቲያኖች ነንና አሁንም እንዲሰሙን ከመጸለይ ማቆም የለብንም ያሉት መምህር ባህታውያን የሚይዙት የብረት ምርኩዝ ካናቱ መስቀል ከስሩ ደግሞ  አንካሴ  መሆኑን አትዘንጉ ብለው ምናልባት አንካሴው ለአውሬ  መከላከያ ሳይሆን አይቀርም ብለን ሲያስተምሩ ተሰብሳቢውን አስቀውታል።

በእለቱ የተደረገው ስብሰባ ስነስርአት የታየበት መከባበር የሰፈነበት እንደነበረ የተናገሩት የስብሰባው ሰብሳቢ እንደዚህ አይነት ስብሰባ  እኮ ነው የናፈቀን ብለዋል። ስብሰባውን የተካፈለው በሙሉ ከሕግ ውጭ ያለው አማራጭ የጠበበ  መሆኑን ተቀብሎ ያለው ኮሚቴ  እንዳለ  ሆኖ ከሳሾችን የሚደግፍ ኮሚቴ  አቌቁሞ ስራውን እንዲቀጥል ባንድ ቃል ከተስማማና ከወሰነ  በኋላ የስብሰባው ፍጻሜ  ሆኗል። በስብሰባው ላይ ለመጀመሪያ  ጊዜ የተገኙ አባቶች በምእመናኑ የስነስርዓት ስብሰባ የተገረሙ መሆኑንና ስለዚህ ስብስብ የተነገራቸውና ዛሬ  ያዩት ሰማይና  ምድር መሆኑን ሲናገሩም ተደምጠዋል። የሃሰት ወሬ  ማናፈስ የማይሰለቻቸው ግለሰቦች ነገ ሌላ  በሬ  ወለደ ወሬ ይዘው ቢመጡ መደናገጥ አይኖርብንም በማለት ያሳሰቡ ከመኖራቸውም በላይ ብዙ  ግለሰቦች ሕብረቱ ወደ አንድ አመለካከት መምጣቱ ለችግራችን መፍትሄ ለመስጠት ይረዳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። የስብሰባው ውሳኔ  ቅጂ ለተሰብሳቢዎቹ እንደሚታደል ተነግሮ  የነበሩው ኮሚቴ  አባላት እንዳሉ ሃላፊነቱን ወስደው እንዲቀጥሉ ተስማምቶ ስብሰባው በትምሕርትና  በጸሎት ተደምድሟል። 

መረዋም በስብሰባው አካሄድ የተደሰተ  መሆኑን እየገለጸ ስብሰባው ላይ ያልነበሩ ግለሰቦች በቀጣዩ የስራ  ክፍፍል በፈቃደኝነት እየተሳተፉ የቤተክርስቲያኑን ሰላም በፍጥነት የምናስከብርበትን መንገድ እንዲያጣድፉ ጥሪ ያደርል። በተጨማሪም ይህንን ስብሰባ እዚህ ውሳኔ  ላይ ያደረሱትን የኮሚቴ  አባላት መረዋ  ባንባቢዎቹ ስም ከፍ ያለ  ምስጋና ያቀርባል።

ከተባበርን ምንም አይነት ሃይል አያቆመንም። ክርስቲያን ፈጣሪውን እንጂ ሌላ  የሚፈራው ሃይል አይኖረውም።

መልካም ሳምንት።