Saturday, October 30, 2010

ከሰገነት ያለ ሰው እይታው ሁል ጊዜ ቁልቁል ነው ቁጥር ፵፮

እንዴት ከረማችሁ ላላችሁን ሁሉ ሰላሙን ያድላችሁ እያልን ከልብ ለሚያበረታታው የ E MAIL መልክታችሁ  አሁንም  በምእመናን ስም ምስጋና እንድናቀርብ ፍቀዱልን። የፈጣሪና የእናንተ እርዳታ ባይታከልበት ኖሮ እዚህ እንደማንደርስ መናገር ደግሞ እውነት ነው። በመሃከሉ የራስም የሕይወት ትግል ያዘንና ስንሯሯጥ ከረምን።ያም ሆኖ አዲስ የተከሰተ ነገር ባለመኖሩ "ከቤተክርስቲያኑ ሱቅ ሰራተኞች መባበር"  ሌላ እሱንም ባለፈው የተናገርነው መሰለን፡ ብዙ ያጋጠመን የለም ለማለት ነው። መረዋ የናንተ ነውና የሰጣችሁንን ምክር በመቀበል አሁንም በከፍታው ላይ ለመራመድ ቃል እንገባለን።

በምንም ዓይነት እረግረግ ውስጥ ገብተን በቆሻሻ ዋልካ ተጨማልቀን፡ በስድብ ተበሻቅጠን አታዩንም።
በምንም ዓይነት በመብታችን ተደራድረን በፍራቻ አጎብድደን አታስተውሉንም።
በምንም ዓይነት ከመልአኩ እግር ሥር እንጂ ከግለሰብ እግር ሥር ወድቀን አታዩንም።
በምንም ዓይነት ለፈጣሪ ካልሆነ  በስተቀር ለግለሰብ አናጎበድድም።
በምንም ዓይነት ለፍቅር እንረታለን እንጂ ለጥላቻ አንበረግግም።
በምንም ዓይነት የሚያከብሩንን እናከብራለን እንጂ አንፈራም። ስለሆነም እናንተው እንዳላችሁት " ለሚሳደቡ ጸልዩላቸው" ለሚታገሉ እንዱሁ ለብርታታቸው ሁሌ በጸሎት አትርሷቸው።

አንድ መንፈሳዊ አባትን አንዱ ምእመን አባቴ ዋና የሚያጸድቅ ነገር ምንድነው? ብሎ  ለጠየቃቸው ሲመልሱ "የሚያጸድቀው ለማድረግ የሚከብደው ነገር ነው። የሚያስኮንነው ግን በየቀኑ የምታደርገው ቀላሉ ነገር ነው" አሉት። እንዲያ ካሉ እግዚአብሔር የለም ማለት እኮ ቀላል ነው አላቸው። እሳቸውም "አሁን የሲኦልን ቁልፍ አገኘኸው"  አሉት።   ሰውን መግደል እኮ  እንደዚሁ ቀላል ነው ሲላቸው "አሁን ደግሞ  የሲኦልንም የዘብጥያውንም ቁልፍ ተረከብከው ማለት ነው" አሉት ይባል ነበር።

ባጋጣሚ ሰሞኑን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የቢል ክሊንተንን MY LIFE  "ሕይወቴ"  የሚለውን  መጽሐፍ ስናነብ ያየነውን እናካፍላችሁ። ፕሬዚዳንት ክሊንተን ሁለተኛ ደረጃ  እንደገቡ የጻፉትን ድርሰት አስታውሰው ሲያስነብቡ (PAGE 58) ......."I, ME, MY, MINE........ THE ONLY THINGS THAT ENABLE WORTHWHILE USES OF THESE WORDS ARE THE UNIVERSAL GOOD QUALITIES WHICH WE ARE NOT TOO OFTEN ABLE TO PLACE WITH THEM - FAITH, TRUST,LOVE, RESPONSIBILITY, REGRET, KNOWLEDGE." ብዙ ጊዜ አናደርገውም እንጂ እኔ በግሌ  የኔ የግሌ ........የሚሉትን ቃላቶች ከአምልኮ ከእምነት ከፍቅር ከሃላፊነትመቀበል ከቁጭትና ከእውቀት ጋር ብናጣምራቸው አለማቀፋዊ ስምምነት ያለው መልካም ምግባር ይሆን ነበር። ትርጉም የራሳችን።

ይህንን ያነሳነው እያንዳንዳችን ያደረግነውን መጠየቅ ብንጀምር ስህተትን ለማረም ይረዳ ነበር ለማለት ያክል ነው።

ሚስቴ ለምን ፈታችኝ ከማለት ይልቅ? ምን ብበድላት ነው የተጣላችኝ? ማለት የተለያየ ትርጉም እንዳለው ሁሉ የተለያየ መፍትሄ  ላይም ይጥላል።

ይህንን ካልን ዘንዳ ወደ ጉዳያችን ስንመለስ ባለፈው በ DECEMBER ወር ተቀጥሮ  የነበረው ቀጠሮ አሁን ወደ 192 ፍርድ ቤት በመዛወሩ ዳኛው ካላቸው የቀጠሮ ቅደም ተዋረድ ጋር በማዛመድ ለJANUARY 10 2011 ለክርክር  መቀጠሩን ስንነግራችሁ፡ ሌሎች እንዳስፈራሩን መንፈቅ ሳይሆን አንድ ወር ብቻ በመራዘሙ ደስተኞች መሆናችንን በመግለጽ ጭምር ነው። ፍርድ ቤት ለችግራችን ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ይሰጣል ብለን አስበን እንደማናውቅ ሁሉ መብታችንን እንደሚያስከብርልን ግን ለሴኮንድም ተጠራጥረን አናውቅም።

ለእምነቱም እኮ  መብት መኖር አለበት
ለማስቀደሱም መቆሚያ
ለማስጠመቁም ማጥመቂያ
ለማስፈታቱም መጠጊያ  ሲኖር ነው።


እናት ሃገር ቢሞት ባገር ይለቀሳል
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል ያለውን ያስታውሷል።

አንዴ በደርግ ዘመን መሆኑ ነው ባለቤቷ ፊቱን እያዞረ ያስቸገራት ሚስት ወደቀበሌ ሄዳ ችግሯን ለቀበሌ ትናገራለች። ቀበሌም ሁኔታውን አዳምጦ ባልየው ፊቱን ሁልግዜ  እያዞረ  መተኛት እንደሌለበት ይነገረውና ትእዛዙን ተቀብሎ ማታ ሚስቱን አቅፎ ያድራል። በነጋታው ካሁን በኋላ  አላደርገውም ብሎ ለሚስቱ ሲነግራት ባለቤቱ "ወደህ በቀበሌ ተገደህ" ብላ አለች ይባል ነበርና እኛም ለጊዜው በቤተክርስቲያን ማስቀደስ መቻላችን በሕግ ግዳጅ እንጂ ተወርውረን ተጥለን እንደነበር ለመጥቀስ ያክል ነው። ማንም ለማስቀደስ የቦርዱን ቡራኬ  ማግኘት ይኖርበታል ብለን አናምንምና። እዚህ ቤተክርስቲያን ደግሞ  ከዚህ በፊት እንደተናገርነው አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ሆኖ መቀጠል አይቻልም። ሁሉም እኩል ነው ማለት እስካልተቻለ  ድረስ ደግሞ ትግሉ ይቀጥላል። ለአምልኮ ቡድን የሚያስፈልግበት ምክንያት አይታየንም። እንዴውም ቤተክርስቲያን ዘመድ ለሌለው ብቸኛ ለሆነ አልነበረም እንዴ?
በቅዳሴ ሰዓት ከሰገነት ተቀምጠው ቁልቁል በማየት ንቀት የለበሱ ካሉ ማንጋጠጥ መልመድ አለባቸው እንላለን። ካልሆነ መጨረሻው አያምርምና። አቶ ሃይሉ እጅጉን ጠርተው እንከስሃለን ብለው የተሳደቡ የቦርድ አባላት። ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ለሚያደርጉት ሥራ  ሁሉ በግል ተጠያቂ እንደሚሆኑ የዘነጉ ይመስላል። ባለፈው በደጋፊዎቻቸው ብሎግ ላይ እንዳሉት እኛ ምን እንሆናለን የመድሕን ድርጅቱ ይጨነቅበት ማለት አይቻልም። እዚህ አገር ደግሞ  እንኳን የዚህ የቤተክርስቲያን የቦርድ አባላት ቀርቶ የአሜሪካዊውም ፕሬዚዳንቱም ካጠፉ ፕሬዚዳንት ነኝ አልጠየቅም ማለት አይቻላቸውም። የኒክሰንን የዋተር ጌት ቅሌት ያስታውሷል። ማንም በድርጅት ሽፋን ተነስቶ  ምእመናንን መተናኮል አይችልም ለማለት ነው። ይህንን ስንል ደግሞ ለማስፈራራት ሳይሆን በመብታችን ላይ ለደረሰው በደል ተጠያቂዎች እንዲጠየቁ ለማድረግ እንደምንታገል ለመግለጽ ጭምር ነው።

ለተሳዳቢዎቹ ሰው ላንመስላቸው እንችላለን እኛ ግን ሰው መሆናችንን እያወቅን ላላወቁ ለማሳየት በሕግ እንታገላለን።

በቅርቡ ቸር ወሬ እንደምንሰማ እርግጠኞች ነን።

ለዛው ያድርሰን

ልትገናኙን ለምትፈልጉ አሁንም አድራሻችን

YETAYALEWNETU@GMAIL.COM  ነው። መልካም ሳምንት።

Monday, October 18, 2010

"ውዳሴ የደገመ ሞኝ ተማሪ ደብተራ የሆነ ይመስለዋል።" ቁጥር ፵፭

አምናና  ካች አምና  ደህና  ሰው ነበረች፤
በሽታዋ  መጣ ትተኩስ ጀመረች።
ብለው የተቀኙት አዋቂ ሽክላ መተኮስ ነውር በነበረበት ሰዓት ለመወለዳቸው ምስክር አያስፈልግም። ነገሩን እንዴት በተሸፋፈነ መንገድ እንዳቀረቡት የተረዳ ሰው ደግሞ ያነጋገር ዘይቤአቸውን የቅኔ ችሎታቸውን ማድነቁ የማይቀር ነው። አባቶች ሲያሳሰቡም ሲያስተምሩም በምሳሌና በጥበብ እንደነበረ ብዙ መረጃ መጥቀስ ይቻላል። እኛን ዛሬ የቸገረን ያካባቢያችን የኃይማኖት ጋቢ የለበሰው የተንኮል ቅኔና ዘለፋ  ነው። ባለፈው የመረዋ እትምታችን የኪዳነምሕረትን ማህበር ያባረሩትና እንዲፈርስ ያደረጉት የሚካኤል ሊቀመንበር እነሆኝ በትላንትናው እለት ደግሞ በፈቃደኝነት ለዓመታት ያገለገሉትን የቤተክርስቲያን  ሱቅ (GIFT SHOP)  ከፍተው መጻሕፍትን የመዝሙር ቅጅዎችን የተለየዩ የቤተክርስቲያን ቁሳቁሶችን ለምእመናን በመሸጥ ለቤተክርስቲያኑ ገቢ በማስገኘት ያገለገሉትን አንጋፋ የቤተክርስቲያን አባላት እናቶች "ካሁን በኋላ  ስለማንፈልጋችሁ የሱቁን ቁልፍ አስረክባችሁ እንድትሄዱ ቦርዱ በወሰነው መሰረት ባስቸኳይ ቁልፉን እንድታስረክቡ"ብለው ፈርመው እንደሰጧቸው የደረሰን ዜና  ያረጋግጣል። ደብዳቤው በማ እንደተጻፈ ባናውቅም የፈረሙት ግን ሊቀመንበሩ አቶ  ዮሴፍ እንደሆኑ  አስረክቡ የሚለው ደብዳቤ  ላይ  ባሰፈሩት ፊርማቸው ለማረጋገጥ  ችለናል።
ይህ ለምን ተደረገ?  ብላችሁ ለምትጠይቁ ግለሰቦች መልሱ "የስደት ሲኖዶስ"  የነ አባ  መልከጸዲቅ መዝሙርና  ሰበካ ሲዲና ክር በእነወይዘሮ ብኩሪ አሳላፊነት በሱቁ ውስጥ እንዲሸጥ በማቀድ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናጋገራሉ። እኛም ጥርጣሬውን ሙሉ በሙሉ እንጋራለን። ሰሞኑን  መቅደስ እንዳይገቡ የተከለከሉ ዲያቆን መኖራቸውን ስንሰማ አልተገረምንም። ትላንት ከመቅደስ የተከለከሉ ካህን አይተናልና። እስካሁንም መቅደስ ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉት ካህን  ከሽማግሌዎች  ጋር ተቀምጠው ማስቀደሳቸውን አላቋረጡም። ለነገሩማ  ካህኑ የተበተነው የአማካሪ ኮሚቴ አባል አልነበሩ ከኮሚቴው ሊቀመንበርና ከአባላቱ ጎን ሆነው ቢያስቀድሱ ምን ይገርማል።

በተለያዩ ብሎጎች ላይ ይህንን ብሎግ አስመልክቶ ብዙ የተጻፈ የስድብ ውርጅብኝ በማንበብ  ለምን መልስ እንዳልሰጠን የጠየቃችሁን ብዙዎች ናችሁ። ነገር ግን መረዋ የብዙሃኑ ንብረት እንጂ የግለሰብ ንብረት ባለመሆኑ የግለሰቦች ስም በተነሳ ቁጥር ምንም እንኳን ያለማወላወል የምንደግፋቸው ግለሰቦች ቢሆኑ አካኪ ዘራፍ ማለት አልፈለግንም። በተለየዩ ወቅቶች ሁኔታው እንደፈቀደ ስማቸው የጠፋውን ግለሰቦች በመደገፍ የተሰማንን መግለጻችን ደግሞ ለሁላችሁም ግልጽ ነው። በነገራችን ላይ ግማሾቹ የመረዋን አ ቋም የማይደግፉ ግለሰቦች መሆናቸውን እያወቅን እንኳን መሰደብ እንደሌለባቸው መናገራችንን እናስታውሳለን። በእኛ እምነት ሰውን በመስደብ መጣላት እንጂ መፋቀር ይመጣል ብለን አናምንምና። ባለፈው እንዳልነው "እዳሪና አፈር የሚለየው በሽታው ነውና። " እናንተ እየለያችሁ እንደወንፊት እንደምታበጥሩት ደግሞ ሙሉ እምነታችን ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉት እነዚህ ሰዳቢዎች በዚህ መጽደቅ ከቻሉ ደግሞ ማንም ጽድቁ ይቅርብኝ ቢል እውነት አለው እንላለን። ውዳሴ  ማርያም የደገመ ሞኝ ተማሪ ደብተራ የሆነ  ቢመስለው ሞኝነቱን አረጋገጠ እንጂ ደብተራ  አልሆነምና።
ክርስቲያን ወንድሙን ይወዳል እንጂ አይሳደብም
ክርስቲያን ለእውነት ይሞታል እንጂ አይዋሽም
ከርስቲያን ለይቅርታ  ይነሳል እንጂ ክርስቲያንን ሊያባርር አይነሳም
ክርስቲያን መንፈሳዊ አባቶችን አያቀልም
ካህንን አይዘልፍም
ክርስቲያን አይሰርቅም
ክርስቲያን ድሃ  ወንድሙን ይረዳል እንጂ በድህነቱ አያፌዝም
ለዚያውስ መጽሐፉ "ሃብታም ይጸድቃል ከማለት ይልቅ ግመል በመርፌ  ቀዳዳ መሹለክ ትችላለች ማለት ይቀላል"  አይልምን።
ለነገሩ ቢገርመን ተናገርን እንጂ ባለፈው እንዳልነው ካሜከላ ብርቱካን አንጠብቅም።
እንደ ማስፈራራታችሁ ሰሚ ብታገኙ እስካሁን ተገድለን ነበር። አልሞትንም ለመብት በመጣ ደግሞ ብንሞትም አይቆጨንም።
እናንተ አስፈራሩን እኛ አሁንም በሕግ እናስቆማችኋለን። እምነት ሊያቆመው የሚችል እኮ የሚያምንን ብቻ ነው። እናንተ  እንደምትሰብኩት እምነት ስድብና ዛቻ  ከሆነ እኛ የናንተን ሳይሆን የሕግን ከለላ  እንጠይቃለን።
ውድ አንባብያን
አንዳንድ የጠየቃችሁን መልስ ለመስጠት ለጊዜው የምንጠቅሳቸው ነገሮች አሉን። ሽማግሌ በቤተክርስቲያኑ ክስ ውስጥ ገብቷል ወይ?  ብላችሁ ለጠየቃችሁን እኛም እንደናንተ መስማታችንን ያረጋገጥን  ይመስለናል። በተለይም የሚካኤል መፍትሄ  አፈላላጊ ኮሚቴ ልሳን የሆነው WWW.MELEKET4U.BLOGSPOT.COM  የዘገበውን ሄዳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ። ዋሽተን አናውቅም ስንል ለአፋችን ሳይሆን ከልባችን ነው። ዋሽተን ያገኛችሁን እለት የመሞቻችን የመጨረሻውም የመጀመሪያውም ወቅት ሆነ  ማለት ነው።

ከደረሱን መረጃዎች ጥቂቶቹን እናካፍላችሁ።

በሚካኤል ቤተክርስቲያን የመብት መደፈርን አስመልከቶ የተከፈተው ክስ ወደ ተከበሩት ዳኛ ስሚዝ መተለለፉን መናገራችን ይታወሳል። ስለሆነም ቦርዱ ለከሳሾች አልሰጥም ያለውን ፋይልና ግልጽ መረጃ አስመልክቶ ወሳኔ ለመስጠት በፊታችን ኖቬምበር 8 በዳኛ ማክፈርላንድ ችሎት እንደሚታይ ቀጠሮ መያዙን መረዳት መቻላችንን ልንነግራችሁ እንወዳለን። መረዋ በወቅቱ በፍርድ ቤት በመገኘት ስለፍርድ ቤቱ ሂደት ለአንባብያን እንደሚያቀርብ ካሁኑ ቃል እንገባለን።

በሁለተኛ ደረጃ  በቤተክርስቲያኑ ላይ የተጫነውን የዳኛ ትእዛዝ ማለትም

ፖሊስ ወደ መቅደስ አታስገቡ
አባላትን አታባሩ
ዶሴዎችን አታጥፉ የሚለውን የለም
ፖሊስ ማስገባት አለብን፡
አባላትን ማባረር መብታችን ነው፡
ዶሲዎችን ማጥፋት ይፈቀድልን። በማለት የቦርዱ ጠበቆች ይግባኝ ማለታቸው የሚታወስ ነው። በዚህም መሰረት ሁኔታውን ለማስረዳት በተያዘው የOCTOBER 29 ላይ ሁለቱም ጠበቆች በይግባኝ  ሰሚ ፍርድ ቤት ቀርበው ገለጻ ለመድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። አሁንም  በፊት እንዳደረግነው ሁሉ ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ መረዋ የሚደርሰውን ለአንባብያን እንደሚያቀርብ ቃል እንገባለን።

በመጨረሻም በወይዘሮ ሶፍያ  የተከፈተው የመብት መደፈር፡ የአካል መጎዳትና፡  ያለወንጀል መታሰር ክስ በ DISTRICT COURT 68 በተከበሩ ዳኛ ማርቲን ሆፍማን ችሎት እንደሚዳኝ ለመረዳት ችለናል። 

ውድ አንባብያን ድጋፋችሁን እያደነቅን ለምታደርጉት ሁሉ ዋጋችሁን ሚካኤል እንዲቆጥርላችሁ እየጸለይን፡ በሚደርስብን ዛቻ ማስፈራራትና  ስም ማጥፋት ተሸማቀን ሸብረክ እንደማንል በድጋሜ  ልናረጋግጥላችሁ  እንወዳለን። እስከዛሬ ግለሰብ ሲወነጀል እንሰማ የነበረው ለምን ህግ እያለ ህግን ጥሶ  እርምጃ ወሰደ  በሚል ነበር። ዛሬ  ከሳሾች መብታቸውን ለማስከበር ወደ ሕግ በመሄዳቸው እንደዚህ የሚሰደቡ ከሆነ ተሳዳቢዎቹ አንድም የአእምሮ ጨቅላዎች ናቸው። ካልሆነ ህክምና የሚሹ ህሙማን ናቸው። ባይሆንማ  ኖሮ በተሰባበረ "የምሁር"  ብእራቸው እንዲህ ሲዛለፉ ባልታዩ  ነበር።

እድሜ  ይስጠን ገና  ብዙ እናያለን።


ሰሞኑን እስክንገናኝ
ደህና  እደሩ

Thursday, October 7, 2010

የፍርድ ቤት ውሎ ልዩ እትም

አሸነፍን ብለው ለደስታ የከፈቱት የሻምፓኝ ቡሽ የወደቀበትን አቅጣጫ ባናውቅም ወደእኛ እንዳልደረሰ ግን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። "የረጠበ ዝናብ አይፈራም" እንዲሉ ቀጠሮ በተቀየረ ቁጥር የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ እንደወረሱ፣ ሕንጻውን እንደተቆጣጠሩ፤ ምእመናንን አባረው እነሱ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ የሚመስላቸው፣ ግለሰቦች ዛሬም የፖለቲካ  መሪዎቻቸውን አስቀድመው፡ እየጨፈሩ መሆኑን ሰምተናል። የሚያስጨፍረው  ምኑ እንደሆነ ባይገባንም መታለላቸው ግን ያሳዝነናል።

እኛ የምንጨፍረው የአባላት መብት ተከብሮ ሰው በዘሩ ሳይሆን በስብእናው፣ በፖለቲካ አቋሙ ሳይሆን በእምነቱ፣ በቡድን አባልነቱ ሳይሆን፣በክርስቲያን ወንድምነቱ፣ ሲከበር ስናይ ብቻ ነው።

የእኛ ጭፈራ አባላት ሲበረክቱ እንጂ ሲመነምኑ በማየት አይሆንም።

የእኛ ደስታ ፍቅር ሲነግስ እንጂ ጠብ ሲንሰራፋ  አይሆንም።

የእኛ ደስታ ጥቂቶች ሳይሆኑ ብዙሃን መወሰን ሲችሉ ብቻ ነው።

የእኛ ምኞት የማንም አባል መብት እኩል መሆኑን ማየት ነው።

የእኛ እውነታ የሚጠብቀን መልአክ እንጂ ቦርድ አይደለም ስንል ነው።

የእኛ ፍንጠዛ ልጆቻችን ተሰብስበው ሲጫወቱ ስናይ እንጂ ልጆች በሌሉበት ሕፃናት ባልተገኙበት መምህራን ሲንጎራደዱ በማስተዋል አይሆንም። ይህንን እስክናይ ድረስ ደግሞ መታገላችንን አናቆምም። ይህ የመብት ጉዳይ ነውና።

ወደተነሳንበት ለመመለስ የዛሬው ፍርድ ቤት እንዴት ዋለ? ለሚሉ የሰማንውን እናቅርብላችሁ።

በ 9:00 ሰዓት የተጀመረው ቀጠሮ  የፈጀው ጊዜ ከ30 ደቂቃ ያነሰ ነበር። በእለቱ የከሳሾች ጠበቃ የቦርድ አባላትን ለጠየቀው ጥያቄ  (DISCOVERY QUESTIONS) መልስ አንሰጥም በማለታቸው፣ ይህንኑ አስመልክቶ ዳኛው ትእዛዝ እንዲፈርምለት የማዘዣ ወረቀት አስገብቶ ነበር። ይህ ሲሆን የቦርዱ ጠበቆች  ሁለት የተቃውሞና የፍርድ ሃሳብ ለዳኛው በማስገባት በዚህ ላይ ውሳኔ  ሳትሰጥ ትእዛዙን አትፈርም ብለው በጠየቁት መሰረት የዛሬው ቀጠሮ ተቀጥሮ እንደ ነበር ይታወሳል። በወቅቱ የቦርዱ ጠበቆች ያቀረቡት የፍርድ ሃሳብ (MOTION)

1 ክሱ የተደጋገመ  ነውና ክሱን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገህ  በነጻ አሰናብተን።

2 ከዚህ በፊት በቦርዱ ላይ የጣልከውን እገዳ (INJECTION) ሙሉ ለሙሉ አንሳልን።

በተጨማሪ ያቀረቡትን መረጃ  የማሰባሰቢያ ጥያቄዎች ከልክልልን የሚልና ባለፈው እንደተስማማነው ጉዳዩን ከዚህ በፊት ያዩትና ለይግባኝ የተላለፈውን ክስ የወሰኑት ዳኛ ይህንንም እንዲያዩት አስተላልፍልን የሚሉ ክርክሮችና  ሃሳቦች ነበሩ።
ትላንት በወጣው መረዋ ልናስረዳችሁ እንደሞከርነው ዳኛው ይህ ክስ ከፊተኛው ክስ ጋር የማይዋሃድ መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ እስካሁን የቀድሞውን ዳኛ አናግራለሁ ባሉት መሰረት ባለማናገራቸው ሁለቱንም ወገን ይቅርታ ጠይቀው፣ በነገው እለት ፋይሉ እንዲዛወር እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

የተከሳሾች ጠበቃ  የጠየቀውን በሙሉ አለመስማማታቸውን በመግለጽ እገዳውን እንደማያነሱ፣ ክሱ እንደማይሰረዝ፣ ሁለቱ ክስ ሊዋሃድ እንደማይችልና ወደ  ቀድሞው ዳኛ እንዲተላለፍ ሁለቱም ወገኖች የተሰማሙ ቢሆንም የቀድሞው ዳኛ ጋ ምንም ፋይል ስለሌለ ይህ እንዳዲስ የሚታይ መሆኑን አስረድተው ጉዳዩ ለቀድሞው ዳኛ ይተላለፍ ብለው ወስነዋል። የውሳኔውን ግልባጭ መረዋ ካስፈለገ  ላንባብያን እንዳለ  እንደሚያቀርበው እየተናገርን ሙሉውን የፍርድ ቤት ቃለ ጉባኤም እንደደረሰን ለማውጣት ቃል እንገባለን።
ቀን በመራዘሙ ብቻ የነገሩ ጭብጥ ሳይታይ ምስክር ሳይሰማ፣ መረጃ  ሳይቀርብ፣  ያሸነፉ የሚመስላቸው ካሉ አንድም ሁኔታው ያልገባቸው ካልሆነም ሆን ብለው ምእመኑን ለማደናገር የተነሱ ብቻ  ይሆናሉ እንላለን።

እኛ ፈሪሃ ሕግ ስላለን ዋሸተን አናሳምናችሁም። ሚስት በመደብደብ አልታሰርንም። የምንም ፖለቲካ ድርጅት መሪ ሆነን ገንዘብ አልዘረፍንም። አዲስ የመጡ ስደተኞችን የድርጅት አባሎቻችን ናችው የሚል ወረቀት ለመጻፍ የድሃ ገንዘባቸውን አልገፈፍንም። እኛ የታክሲ ማህበር መሪ ሆነን ሰንብተን ከስልጣን ሲያባርሩን ተናደን መሃበሩ የጠራውን የሥራ  ማቆም  አድማ ጥሰን ለብቻችን በአንድ ቀን ልንከብር አልተናሳንም። እየለፋን ልጆች የምናሳድግ እንጂ በስርቆት አልተተበተብንም። ለመብታችን ግን ትላንት እንደታገልንበት ዛሬም ነገም መታገላችንን አናቆምም።

ወድ አንባብያን ይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ የደረሰን ሌላ አሳዛኝ ዜና ቢኖር በሚካኤል ቤተክርስቲያን የማርያም ጸበል ጸዲቅ ይጠጡ የነበሩ ማሕበርተኞች ካሁን በኋላ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ መሰብሰብና ማሕበር መጠጣት መከልከላቸውን  ከሊቀመንበሩ እንደተነገራቸው መስማታችን ነው። 

ባንድ የአካባቢያችን የፖለቲካ ባለስልጣን ነኝ ባይ የስልክ ጥሪ መሰብሰብ የሚችል ቦርድ፣ በመሃበር ለእምነታቸው የሚሰበሰቡትን አባቶችና  እናቶች ሲከለክሉ መመልከት  ምን ማለት እንደሆነ  የገባው ቢያስረዳን ደስ ይለን ነበር።

በአሜሪካ  "ፍትሕ ዘገየ  ማለት ፍትሕ ተከለከል"  እንደ ማለት ነው የሚለውን አባባል በመመርኮዝ ያሁኑ የጊዜ  መራዘም የሚያናድዳቸው ቢኖሩ ንዴታቸውን እንጋራለን። ነገር ግን የተረገዘ እስካልተወለደ  እርግዝና  ነውና ተረግዞ ይቀራል ብለን ካላመንን በስተቀር የሚወለደው ልጅ የሚያስፈነጥዘን ተወልዶ ስናየው መሆኑን በማሰብ፣ እስከዛው ለሚወለደው ልጅ እኛ መኝታና  ልብስ እንገዛለን እንጂ ይሞታል ብለን  የመቃብር ጉድጓድ አንቆፍርም። ለእውነት ስለቆምን ደግሞ እውነት እንደሚረታ  አንጠራጠርም።


መቼም ይሁን መቼ የተገፋ ያሸንፋል

እውነት ሁልጊዜ እውነት ነው።

የሳምንት ሰው ይበለን። 


Wednesday, October 6, 2010

ተከሳሽ የከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ ፍርድቤት አይደርስም ነበር ቁጥር ፵፬

እንኴን አደረሳችሁ ውድ አንባቢዎቻችን።

መስቀል አለፈ፣ እኛን ገና አልሰቀሉንም።
ስም አጠፉ መሰላቸው እንጂ አልጎዱንም።
የስድብ ውርጅብኝ አወረዱብን ስንንበረከክ አላዩንም።
የከሳሾችን ጠበቃ ሳይቀር በማያውቀው ቋንቋ ተሳደቡ አዋረዱት ስሙን አጠፉ ከክሱ እራሱን ሲያገል አላስተዋልንም።
ከትላንት በስትያ በብሎጋቸው የሰደቡትን ባለፈው ሰንበት ተቀጠረ የተባለውን አስተማሪ እንዲሁ በብሎጋቸው ሲያወድሱት "ስንሰማ ባንድ አፍ ሁለት ምላስ" አልን እንጂ አልተገረምንም። {ትላንት በመረዳጃ  ማሕበሩ የተደረገውን የኢትዮጵያን ቀን አስመልክቶ የተረኩትን  መልሰው የሻርሩትን ባለፈው መረዋ አስነብበናችሁ ነበርና} የሚገርመን ምን እንደሚፈልጉ አለማወቃቸው ብቻ  ነው።
በፖሊስ ያሳሰሯትን ወጣት ለልጆቿ ምን? እንዴት እንንገራቸው?  ብሎ  እንደመጨነቅ በቁርባን ያገባችውን እናት ሃይማኖት የሌላት እያሉ ሲሳደቡ አነበብን።  ስለዘለፏት የምትሸማቀቅ ከመሰላቸው እምነታቸውን መጠየቅ ያለባቸው እነሱ መሆን አለባቸው እንላለን። ትላንት ዘሯን ቆጥረው የፖለቲካ  ሴት ናት እንዳላሉ ዛሬ ትክሰሳ የምትከሰው ኢንሹራንሱን ነው ብለው ቅራኔውን ለማስፋት ተራወጡ። ወንድሞችና እህቶች ባለፈው እንዳልነው ቤተክርስቲያን የአማንያን እንጂ የተወሰነ ዘር ንብረት ነው ማለት ወንጀል ባይሆን እንኴን ክርስቲያናዊ አይደለም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ደግሞ የሃይማኖቱ የመጀመሪያ ተቀባይ የነበረው የትኛው ክፍል ነበር?

የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ  ልሳን የሆነው ብሎግ WWW.MELEKET4U.BLOGSPOT.COM ያወጣውን ኮሚቴው ከሽማግሌዎች ጋር አድርጎት የነበረውን ውይይት ሃሰት ነው ሲሉ አነበብን። ነገ ደግሞ  እነ አቶ በተሩ እነ ዶክተር ታየ እነ አቶ ጌታቸው እነ አቶ ኪዳኔ እነ አቶ  ግርማቸው እነ ሻለቃ ተፈራ እነ ወይዘሮ በየነች እነ አቶ ደም መላሽ የሚባሉ ሰዎች በዳላስ መኖራቸውን አልሰማንም ቢሉ አትገረሙ። ከመሰላቸው ይዋሹ መዋሸት ደግሞ በሽታ  ነው የሚላቸው ጓደኛ እንደሌላቸው ስናይ ማዘናችን ግን አይቀርም። ምንም ቢሆን ወንድሞቻችን ናቸውና።

በሌላ ወገን የምንነግራችሁ ነገር ቢኖር በነገው እለት ከጠዋቱ 9:00 ሰዓት ላይ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳለ  ነው።  የተያዘው ቀጠሮ  ቦርዱ ለከሳሽ ጠበቃ ተጠይቆ አልሰጥም ያለውን መጠይቅ ዳኛው ትእዛዝ እንዲሰጥበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ባለው የመጀመሪያው ቀጠሮ ላይ የቦርዱ ጠበቃ የተነሳው ቪዲዮ በመረጃነት አይገባብኝም ምስክር አይሰማም ብሎ የተከራከሩት በዳኛው ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው።ዳኛው ይህ ክስ የመብት እንጂ የሃይማኖት ጉዳይ ምንም እንደሌለው ከመናገራቸውም በላይ ቪዲዮውም እንደመረጃ እንዲገባ  ምስክርም እንዲሰማ ማድረጉ ግልጽ ነው። የተከሳሽ ጠበቃ ተቃውሟቸው እንዳልሰራ ሲረዱ ፍርድ ቤቱን ሌላውን የፍርድ ቤት ክስ ያየው ዳኛ ይህንንም በተጨማሪ ይመልከትልን ምክንያቱም ጉዳዩን በሌላ መልኩ አይቶታልና ብለው በጠየቁት መሰረት፣ ዳኛውም የቀድሞውን ዳኛ አነጋግረው ፈቃደኛ ከሆነ ቢዛወር እንደማይቃወሙ ቃል በገቡት መሰረት ምን አልባት የቀድሞው ዳኛ ይህንን ለማየት እፈልጋለሁ ካሉ ሊተላለፍ እንደሚችል ጉዳዩን ከተከታተሉት ግለሰቦች መረዳታችንን ልናሳውቃችሁ እንፈልጋለን።  ይህ ክስ አባላትን ማባረር ከጀመሩ በኋላ የተመሰረት መብትን ለማስከበር የተመሰረት ክስ መሆኑም ለሁላችንም ግልጽ ነ ው።
ስለሆነም በነገው እለት ምንም ተፈጠረ  ምን
መተዳደሪያ ደንቡ ወደነበረበት ካልተመለሰ 
የተባረሩ አባላት ካልተመለሱ
የአባላት ክፍያ  ወደነበረበት ካልተመለሰ
አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ መሆኑ ካልቀረ
የአባላት መብት ካልተጠበቀ
ፖለቲከኞች ከቤተክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካቸውን ካላቆሙ
የምእመናንን ጥቅም አስከባሪ ቦርድ እስካልተቋቋመ
ብሎም
ባለፈው እንዳደረጉት ቦርዱ በመሰብሰቢያ አዳራሻቸው እነ አቶ ሃይሉ እጅጉን ጠርተው እየተሳደቡት ክስ ከመሰረቱት ውስጥ ነህና ካላረፍክ እንከስሃለን የክስ አጋሮችህንም አብረን ለፍርድ እናቆማለን እንዳሉት በተናጠል ማስፈራራት እስካላቆሙ ድረስ 
በቦርዱ ብሎግ መሳደባቸውን እስካልገቱ ድረስ
መታገላችንን  አናቆምም

ዳላስ ለመኖር ደግሞ  የቦርድ ደጋፊዎች ነን ባዮችን ፈቃድ አንጠይቅም።
ሚካኤል ለተገፉ እንጂ ለገፊዎች ይቆማል ብለን አስበንም አናውቅ።
የነገ ሰው ይበለን።


   





Tuesday, October 5, 2010

ለሱ ብርታት ለእኔ ጽናት

ከደከምኩብህ አበራታኝ፣
ከተደናቀፍኩ ሳልወድቅ አንሳኝ።
        ሰው ነኝና ድኩም ፍጥረት፣
        ወድቄ  እንዳልቀር እንደኩበት፤
ምርኩዝ ሁነኝ ጠባቂ፣
እረዳት ሁነኝ ጠያቂ።
       ለጠሉኝ ልብ ስጣቸው፣
      ብርታቱን አትንፈጋቸው።
እኔ ባሪያህ ደካማ ነኝ፣
ለመጽናናቱ ጉልበት ስጠኝ።
     እንደሞትክልኝ ለሃጥያቴ፣
     ይቅር እንዳልከኝ በድክመቴ፣
     አበራታኝ ይቅር ልበላቸው ካንጀቴ።
እኔን እንደወደድከኝ፣
እንድወዳቸው ጽናቱን ስጠኝ።
   ቸር ነህና  ይቅር ባይ፣
   ዳግም ምሕረትህ   ይታይ።
ቢበትኑ ስብስቡን፣
በዘር በጎሳ ቢለዩን፣
በፖለቲካ ቢያበራዩን።
    አምባ ገነንም ቢሆኑ፣
    ምሕረቱን ስጣቸው ይዳኑ።
የእሳት አለንጋ ሳይገርፋቸው፣
ሰይጣን ሳያቀሳቸው፣
ዲያብሎስ ሳይሰርጋቸው፣
የክሕደት ማቅ ሳይወርሳቸው፣
እባክህ ፈጣሪ መልሳቸው፣
የፍቅርን መንገድ አሳያቸው፣
ግፉ በዛ  አሁንስ ይብቃ በላቸው።
      ለእኔም ብርታቱን አትንፈገኝ፣
      ከውዳሴ  ፖለቲካ  አድነኝ፣
      በይቅርታህ ጀቡነኝ፣
      ሰይፉን ሳይሆን ፍቅሩን ስጠኝ፣
      እንደ ሰብአ ሰገል የብርሃን ጮራ አሳየኝ፣
      በጥንካሬዬ እንጂ በድክመቴ አትዳኘኝ፣
      አምላኬ ለሱ ብርታት ለኔ ጽናቱን አከናንበኝ።