Monday, October 18, 2010

"ውዳሴ የደገመ ሞኝ ተማሪ ደብተራ የሆነ ይመስለዋል።" ቁጥር ፵፭

አምናና  ካች አምና  ደህና  ሰው ነበረች፤
በሽታዋ  መጣ ትተኩስ ጀመረች።
ብለው የተቀኙት አዋቂ ሽክላ መተኮስ ነውር በነበረበት ሰዓት ለመወለዳቸው ምስክር አያስፈልግም። ነገሩን እንዴት በተሸፋፈነ መንገድ እንዳቀረቡት የተረዳ ሰው ደግሞ ያነጋገር ዘይቤአቸውን የቅኔ ችሎታቸውን ማድነቁ የማይቀር ነው። አባቶች ሲያሳሰቡም ሲያስተምሩም በምሳሌና በጥበብ እንደነበረ ብዙ መረጃ መጥቀስ ይቻላል። እኛን ዛሬ የቸገረን ያካባቢያችን የኃይማኖት ጋቢ የለበሰው የተንኮል ቅኔና ዘለፋ  ነው። ባለፈው የመረዋ እትምታችን የኪዳነምሕረትን ማህበር ያባረሩትና እንዲፈርስ ያደረጉት የሚካኤል ሊቀመንበር እነሆኝ በትላንትናው እለት ደግሞ በፈቃደኝነት ለዓመታት ያገለገሉትን የቤተክርስቲያን  ሱቅ (GIFT SHOP)  ከፍተው መጻሕፍትን የመዝሙር ቅጅዎችን የተለየዩ የቤተክርስቲያን ቁሳቁሶችን ለምእመናን በመሸጥ ለቤተክርስቲያኑ ገቢ በማስገኘት ያገለገሉትን አንጋፋ የቤተክርስቲያን አባላት እናቶች "ካሁን በኋላ  ስለማንፈልጋችሁ የሱቁን ቁልፍ አስረክባችሁ እንድትሄዱ ቦርዱ በወሰነው መሰረት ባስቸኳይ ቁልፉን እንድታስረክቡ"ብለው ፈርመው እንደሰጧቸው የደረሰን ዜና  ያረጋግጣል። ደብዳቤው በማ እንደተጻፈ ባናውቅም የፈረሙት ግን ሊቀመንበሩ አቶ  ዮሴፍ እንደሆኑ  አስረክቡ የሚለው ደብዳቤ  ላይ  ባሰፈሩት ፊርማቸው ለማረጋገጥ  ችለናል።
ይህ ለምን ተደረገ?  ብላችሁ ለምትጠይቁ ግለሰቦች መልሱ "የስደት ሲኖዶስ"  የነ አባ  መልከጸዲቅ መዝሙርና  ሰበካ ሲዲና ክር በእነወይዘሮ ብኩሪ አሳላፊነት በሱቁ ውስጥ እንዲሸጥ በማቀድ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናጋገራሉ። እኛም ጥርጣሬውን ሙሉ በሙሉ እንጋራለን። ሰሞኑን  መቅደስ እንዳይገቡ የተከለከሉ ዲያቆን መኖራቸውን ስንሰማ አልተገረምንም። ትላንት ከመቅደስ የተከለከሉ ካህን አይተናልና። እስካሁንም መቅደስ ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉት ካህን  ከሽማግሌዎች  ጋር ተቀምጠው ማስቀደሳቸውን አላቋረጡም። ለነገሩማ  ካህኑ የተበተነው የአማካሪ ኮሚቴ አባል አልነበሩ ከኮሚቴው ሊቀመንበርና ከአባላቱ ጎን ሆነው ቢያስቀድሱ ምን ይገርማል።

በተለያዩ ብሎጎች ላይ ይህንን ብሎግ አስመልክቶ ብዙ የተጻፈ የስድብ ውርጅብኝ በማንበብ  ለምን መልስ እንዳልሰጠን የጠየቃችሁን ብዙዎች ናችሁ። ነገር ግን መረዋ የብዙሃኑ ንብረት እንጂ የግለሰብ ንብረት ባለመሆኑ የግለሰቦች ስም በተነሳ ቁጥር ምንም እንኳን ያለማወላወል የምንደግፋቸው ግለሰቦች ቢሆኑ አካኪ ዘራፍ ማለት አልፈለግንም። በተለየዩ ወቅቶች ሁኔታው እንደፈቀደ ስማቸው የጠፋውን ግለሰቦች በመደገፍ የተሰማንን መግለጻችን ደግሞ ለሁላችሁም ግልጽ ነው። በነገራችን ላይ ግማሾቹ የመረዋን አ ቋም የማይደግፉ ግለሰቦች መሆናቸውን እያወቅን እንኳን መሰደብ እንደሌለባቸው መናገራችንን እናስታውሳለን። በእኛ እምነት ሰውን በመስደብ መጣላት እንጂ መፋቀር ይመጣል ብለን አናምንምና። ባለፈው እንዳልነው "እዳሪና አፈር የሚለየው በሽታው ነውና። " እናንተ እየለያችሁ እንደወንፊት እንደምታበጥሩት ደግሞ ሙሉ እምነታችን ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉት እነዚህ ሰዳቢዎች በዚህ መጽደቅ ከቻሉ ደግሞ ማንም ጽድቁ ይቅርብኝ ቢል እውነት አለው እንላለን። ውዳሴ  ማርያም የደገመ ሞኝ ተማሪ ደብተራ የሆነ  ቢመስለው ሞኝነቱን አረጋገጠ እንጂ ደብተራ  አልሆነምና።
ክርስቲያን ወንድሙን ይወዳል እንጂ አይሳደብም
ክርስቲያን ለእውነት ይሞታል እንጂ አይዋሽም
ከርስቲያን ለይቅርታ  ይነሳል እንጂ ክርስቲያንን ሊያባርር አይነሳም
ክርስቲያን መንፈሳዊ አባቶችን አያቀልም
ካህንን አይዘልፍም
ክርስቲያን አይሰርቅም
ክርስቲያን ድሃ  ወንድሙን ይረዳል እንጂ በድህነቱ አያፌዝም
ለዚያውስ መጽሐፉ "ሃብታም ይጸድቃል ከማለት ይልቅ ግመል በመርፌ  ቀዳዳ መሹለክ ትችላለች ማለት ይቀላል"  አይልምን።
ለነገሩ ቢገርመን ተናገርን እንጂ ባለፈው እንዳልነው ካሜከላ ብርቱካን አንጠብቅም።
እንደ ማስፈራራታችሁ ሰሚ ብታገኙ እስካሁን ተገድለን ነበር። አልሞትንም ለመብት በመጣ ደግሞ ብንሞትም አይቆጨንም።
እናንተ አስፈራሩን እኛ አሁንም በሕግ እናስቆማችኋለን። እምነት ሊያቆመው የሚችል እኮ የሚያምንን ብቻ ነው። እናንተ  እንደምትሰብኩት እምነት ስድብና ዛቻ  ከሆነ እኛ የናንተን ሳይሆን የሕግን ከለላ  እንጠይቃለን።
ውድ አንባብያን
አንዳንድ የጠየቃችሁን መልስ ለመስጠት ለጊዜው የምንጠቅሳቸው ነገሮች አሉን። ሽማግሌ በቤተክርስቲያኑ ክስ ውስጥ ገብቷል ወይ?  ብላችሁ ለጠየቃችሁን እኛም እንደናንተ መስማታችንን ያረጋገጥን  ይመስለናል። በተለይም የሚካኤል መፍትሄ  አፈላላጊ ኮሚቴ ልሳን የሆነው WWW.MELEKET4U.BLOGSPOT.COM  የዘገበውን ሄዳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ። ዋሽተን አናውቅም ስንል ለአፋችን ሳይሆን ከልባችን ነው። ዋሽተን ያገኛችሁን እለት የመሞቻችን የመጨረሻውም የመጀመሪያውም ወቅት ሆነ  ማለት ነው።

ከደረሱን መረጃዎች ጥቂቶቹን እናካፍላችሁ።

በሚካኤል ቤተክርስቲያን የመብት መደፈርን አስመልከቶ የተከፈተው ክስ ወደ ተከበሩት ዳኛ ስሚዝ መተለለፉን መናገራችን ይታወሳል። ስለሆነም ቦርዱ ለከሳሾች አልሰጥም ያለውን ፋይልና ግልጽ መረጃ አስመልክቶ ወሳኔ ለመስጠት በፊታችን ኖቬምበር 8 በዳኛ ማክፈርላንድ ችሎት እንደሚታይ ቀጠሮ መያዙን መረዳት መቻላችንን ልንነግራችሁ እንወዳለን። መረዋ በወቅቱ በፍርድ ቤት በመገኘት ስለፍርድ ቤቱ ሂደት ለአንባብያን እንደሚያቀርብ ካሁኑ ቃል እንገባለን።

በሁለተኛ ደረጃ  በቤተክርስቲያኑ ላይ የተጫነውን የዳኛ ትእዛዝ ማለትም

ፖሊስ ወደ መቅደስ አታስገቡ
አባላትን አታባሩ
ዶሴዎችን አታጥፉ የሚለውን የለም
ፖሊስ ማስገባት አለብን፡
አባላትን ማባረር መብታችን ነው፡
ዶሲዎችን ማጥፋት ይፈቀድልን። በማለት የቦርዱ ጠበቆች ይግባኝ ማለታቸው የሚታወስ ነው። በዚህም መሰረት ሁኔታውን ለማስረዳት በተያዘው የOCTOBER 29 ላይ ሁለቱም ጠበቆች በይግባኝ  ሰሚ ፍርድ ቤት ቀርበው ገለጻ ለመድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። አሁንም  በፊት እንዳደረግነው ሁሉ ከፍርድ ቤት ውሎ በኋላ መረዋ የሚደርሰውን ለአንባብያን እንደሚያቀርብ ቃል እንገባለን።

በመጨረሻም በወይዘሮ ሶፍያ  የተከፈተው የመብት መደፈር፡ የአካል መጎዳትና፡  ያለወንጀል መታሰር ክስ በ DISTRICT COURT 68 በተከበሩ ዳኛ ማርቲን ሆፍማን ችሎት እንደሚዳኝ ለመረዳት ችለናል። 

ውድ አንባብያን ድጋፋችሁን እያደነቅን ለምታደርጉት ሁሉ ዋጋችሁን ሚካኤል እንዲቆጥርላችሁ እየጸለይን፡ በሚደርስብን ዛቻ ማስፈራራትና  ስም ማጥፋት ተሸማቀን ሸብረክ እንደማንል በድጋሜ  ልናረጋግጥላችሁ  እንወዳለን። እስከዛሬ ግለሰብ ሲወነጀል እንሰማ የነበረው ለምን ህግ እያለ ህግን ጥሶ  እርምጃ ወሰደ  በሚል ነበር። ዛሬ  ከሳሾች መብታቸውን ለማስከበር ወደ ሕግ በመሄዳቸው እንደዚህ የሚሰደቡ ከሆነ ተሳዳቢዎቹ አንድም የአእምሮ ጨቅላዎች ናቸው። ካልሆነ ህክምና የሚሹ ህሙማን ናቸው። ባይሆንማ  ኖሮ በተሰባበረ "የምሁር"  ብእራቸው እንዲህ ሲዛለፉ ባልታዩ  ነበር።

እድሜ  ይስጠን ገና  ብዙ እናያለን።


ሰሞኑን እስክንገናኝ
ደህና  እደሩ