አሸነፍን ብለው ለደስታ የከፈቱት የሻምፓኝ ቡሽ የወደቀበትን አቅጣጫ ባናውቅም ወደእኛ እንዳልደረሰ ግን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። "የረጠበ ዝናብ አይፈራም" እንዲሉ ቀጠሮ በተቀየረ ቁጥር የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ እንደወረሱ፣ ሕንጻውን እንደተቆጣጠሩ፤ ምእመናንን አባረው እነሱ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ የሚመስላቸው፣ ግለሰቦች ዛሬም የፖለቲካ መሪዎቻቸውን አስቀድመው፡ እየጨፈሩ መሆኑን ሰምተናል። የሚያስጨፍረው ምኑ እንደሆነ ባይገባንም መታለላቸው ግን ያሳዝነናል።
እኛ የምንጨፍረው የአባላት መብት ተከብሮ ሰው በዘሩ ሳይሆን በስብእናው፣ በፖለቲካ አቋሙ ሳይሆን በእምነቱ፣ በቡድን አባልነቱ ሳይሆን፣በክርስቲያን ወንድምነቱ፣ ሲከበር ስናይ ብቻ ነው።
የእኛ ጭፈራ አባላት ሲበረክቱ እንጂ ሲመነምኑ በማየት አይሆንም።
የእኛ ደስታ ፍቅር ሲነግስ እንጂ ጠብ ሲንሰራፋ አይሆንም።
የእኛ ደስታ ጥቂቶች ሳይሆኑ ብዙሃን መወሰን ሲችሉ ብቻ ነው።
የእኛ ምኞት የማንም አባል መብት እኩል መሆኑን ማየት ነው።
የእኛ እውነታ የሚጠብቀን መልአክ እንጂ ቦርድ አይደለም ስንል ነው።
የእኛ ፍንጠዛ ልጆቻችን ተሰብስበው ሲጫወቱ ስናይ እንጂ ልጆች በሌሉበት ሕፃናት ባልተገኙበት መምህራን ሲንጎራደዱ በማስተዋል አይሆንም። ይህንን እስክናይ ድረስ ደግሞ መታገላችንን አናቆምም። ይህ የመብት ጉዳይ ነውና።
ወደተነሳንበት ለመመለስ የዛሬው ፍርድ ቤት እንዴት ዋለ? ለሚሉ የሰማንውን እናቅርብላችሁ።
በ 9:00 ሰዓት የተጀመረው ቀጠሮ የፈጀው ጊዜ ከ30 ደቂቃ ያነሰ ነበር። በእለቱ የከሳሾች ጠበቃ የቦርድ አባላትን ለጠየቀው ጥያቄ (DISCOVERY QUESTIONS) መልስ አንሰጥም በማለታቸው፣ ይህንኑ አስመልክቶ ዳኛው ትእዛዝ እንዲፈርምለት የማዘዣ ወረቀት አስገብቶ ነበር። ይህ ሲሆን የቦርዱ ጠበቆች ሁለት የተቃውሞና የፍርድ ሃሳብ ለዳኛው በማስገባት በዚህ ላይ ውሳኔ ሳትሰጥ ትእዛዙን አትፈርም ብለው በጠየቁት መሰረት የዛሬው ቀጠሮ ተቀጥሮ እንደ ነበር ይታወሳል። በወቅቱ የቦርዱ ጠበቆች ያቀረቡት የፍርድ ሃሳብ (MOTION)
1 ክሱ የተደጋገመ ነውና ክሱን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገህ በነጻ አሰናብተን።
2 ከዚህ በፊት በቦርዱ ላይ የጣልከውን እገዳ (INJECTION) ሙሉ ለሙሉ አንሳልን።
በተጨማሪ ያቀረቡትን መረጃ የማሰባሰቢያ ጥያቄዎች ከልክልልን የሚልና ባለፈው እንደተስማማነው ጉዳዩን ከዚህ በፊት ያዩትና ለይግባኝ የተላለፈውን ክስ የወሰኑት ዳኛ ይህንንም እንዲያዩት አስተላልፍልን የሚሉ ክርክሮችና ሃሳቦች ነበሩ።
ትላንት በወጣው መረዋ ልናስረዳችሁ እንደሞከርነው ዳኛው ይህ ክስ ከፊተኛው ክስ ጋር የማይዋሃድ መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ እስካሁን የቀድሞውን ዳኛ አናግራለሁ ባሉት መሰረት ባለማናገራቸው ሁለቱንም ወገን ይቅርታ ጠይቀው፣ በነገው እለት ፋይሉ እንዲዛወር እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
የተከሳሾች ጠበቃ የጠየቀውን በሙሉ አለመስማማታቸውን በመግለጽ እገዳውን እንደማያነሱ፣ ክሱ እንደማይሰረዝ፣ ሁለቱ ክስ ሊዋሃድ እንደማይችልና ወደ ቀድሞው ዳኛ እንዲተላለፍ ሁለቱም ወገኖች የተሰማሙ ቢሆንም የቀድሞው ዳኛ ጋ ምንም ፋይል ስለሌለ ይህ እንዳዲስ የሚታይ መሆኑን አስረድተው ጉዳዩ ለቀድሞው ዳኛ ይተላለፍ ብለው ወስነዋል። የውሳኔውን ግልባጭ መረዋ ካስፈለገ ላንባብያን እንዳለ እንደሚያቀርበው እየተናገርን ሙሉውን የፍርድ ቤት ቃለ ጉባኤም እንደደረሰን ለማውጣት ቃል እንገባለን።
ቀን በመራዘሙ ብቻ የነገሩ ጭብጥ ሳይታይ ምስክር ሳይሰማ፣ መረጃ ሳይቀርብ፣ ያሸነፉ የሚመስላቸው ካሉ አንድም ሁኔታው ያልገባቸው ካልሆነም ሆን ብለው ምእመኑን ለማደናገር የተነሱ ብቻ ይሆናሉ እንላለን።
እኛ ፈሪሃ ሕግ ስላለን ዋሸተን አናሳምናችሁም። ሚስት በመደብደብ አልታሰርንም። የምንም ፖለቲካ ድርጅት መሪ ሆነን ገንዘብ አልዘረፍንም። አዲስ የመጡ ስደተኞችን የድርጅት አባሎቻችን ናችው የሚል ወረቀት ለመጻፍ የድሃ ገንዘባቸውን አልገፈፍንም። እኛ የታክሲ ማህበር መሪ ሆነን ሰንብተን ከስልጣን ሲያባርሩን ተናደን መሃበሩ የጠራውን የሥራ ማቆም አድማ ጥሰን ለብቻችን በአንድ ቀን ልንከብር አልተናሳንም። እየለፋን ልጆች የምናሳድግ እንጂ በስርቆት አልተተበተብንም። ለመብታችን ግን ትላንት እንደታገልንበት ዛሬም ነገም መታገላችንን አናቆምም።
ወድ አንባብያን ይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ የደረሰን ሌላ አሳዛኝ ዜና ቢኖር በሚካኤል ቤተክርስቲያን የማርያም ጸበል ጸዲቅ ይጠጡ የነበሩ ማሕበርተኞች ካሁን በኋላ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ መሰብሰብና ማሕበር መጠጣት መከልከላቸውን ከሊቀመንበሩ እንደተነገራቸው መስማታችን ነው።
ባንድ የአካባቢያችን የፖለቲካ ባለስልጣን ነኝ ባይ የስልክ ጥሪ መሰብሰብ የሚችል ቦርድ፣ በመሃበር ለእምነታቸው የሚሰበሰቡትን አባቶችና እናቶች ሲከለክሉ መመልከት ምን ማለት እንደሆነ የገባው ቢያስረዳን ደስ ይለን ነበር።
በአሜሪካ "ፍትሕ ዘገየ ማለት ፍትሕ ተከለከል" እንደ ማለት ነው የሚለውን አባባል በመመርኮዝ ያሁኑ የጊዜ መራዘም የሚያናድዳቸው ቢኖሩ ንዴታቸውን እንጋራለን። ነገር ግን የተረገዘ እስካልተወለደ እርግዝና ነውና ተረግዞ ይቀራል ብለን ካላመንን በስተቀር የሚወለደው ልጅ የሚያስፈነጥዘን ተወልዶ ስናየው መሆኑን በማሰብ፣ እስከዛው ለሚወለደው ልጅ እኛ መኝታና ልብስ እንገዛለን እንጂ ይሞታል ብለን የመቃብር ጉድጓድ አንቆፍርም። ለእውነት ስለቆምን ደግሞ እውነት እንደሚረታ አንጠራጠርም።
መቼም ይሁን መቼ የተገፋ ያሸንፋል
እውነት ሁልጊዜ እውነት ነው።
የሳምንት ሰው ይበለን።