ከደከምኩብህ አበራታኝ፣
ከተደናቀፍኩ ሳልወድቅ አንሳኝ።
ሰው ነኝና ድኩም ፍጥረት፣
ወድቄ እንዳልቀር እንደኩበት፤
ምርኩዝ ሁነኝ ጠባቂ፣
እረዳት ሁነኝ ጠያቂ።
ለጠሉኝ ልብ ስጣቸው፣
ብርታቱን አትንፈጋቸው።
እኔ ባሪያህ ደካማ ነኝ፣
ለመጽናናቱ ጉልበት ስጠኝ።
እንደሞትክልኝ ለሃጥያቴ፣
ይቅር እንዳልከኝ በድክመቴ፣
አበራታኝ ይቅር ልበላቸው ካንጀቴ።
እኔን እንደወደድከኝ፣
እንድወዳቸው ጽናቱን ስጠኝ።
ቸር ነህና ይቅር ባይ፣
ዳግም ምሕረትህ ይታይ።
ቢበትኑ ስብስቡን፣
በዘር በጎሳ ቢለዩን፣
በፖለቲካ ቢያበራዩን።
አምባ ገነንም ቢሆኑ፣
ምሕረቱን ስጣቸው ይዳኑ።
የእሳት አለንጋ ሳይገርፋቸው፣
ሰይጣን ሳያቀሳቸው፣
ዲያብሎስ ሳይሰርጋቸው፣
የክሕደት ማቅ ሳይወርሳቸው፣
እባክህ ፈጣሪ መልሳቸው፣
የፍቅርን መንገድ አሳያቸው፣
ግፉ በዛ አሁንስ ይብቃ በላቸው።
ለእኔም ብርታቱን አትንፈገኝ፣
ከውዳሴ ፖለቲካ አድነኝ፣
በይቅርታህ ጀቡነኝ፣
ሰይፉን ሳይሆን ፍቅሩን ስጠኝ፣
እንደ ሰብአ ሰገል የብርሃን ጮራ አሳየኝ፣
በጥንካሬዬ እንጂ በድክመቴ አትዳኘኝ፣
አምላኬ ለሱ ብርታት ለኔ ጽናቱን አከናንበኝ።