Sunday, February 28, 2010

የጋቢን ጥቅም ያላወቀ በልቃቂት ይጫወታል ቁጥር ፲፭

እንዴት ከረማችሁ እድምተኞቻችን። ሰሞኑን እየተከሰተ ያለውን የድህረ ገጽ የጽሑፍ ፍልሚያ ያየ ሰው ወይ ጉድ ማለት ሳይሆን ምን ዘመን ላይ አደረሰን? ቢል የምንረዳው መሰለን። የዳላስ የቤተክርስቲያን ብጥብጥ የሃይማኖት ሳይሆን የፖለቲካና የጥቅም ከሆነ ውሎ አደረ። የሃይማኖት ቢሆን ኖሮማ እስካሁን ችግሩ ተፈቶ ነበር። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ምእመናን ይቅር ለእግዚአብሔር ለመባባል ችግር የለባቸውምና። ስዚህም ነበር መረዋ በመደጋገም ችግሩ የመብት መገፋት: የንዋይ ጥማት: የፖለቲካ ክስረትና ፍጭት ነው እንጂ የሃይማኖት አይደለም ብሎ ከደመደመ የሰነበተው። በተደጋጋሚ ሰሞኑን እየተሰራጩ ያሉት የተለያዩ Bolgs ላይ የሚጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ ጸሐፊዎቹ ከየትኛው ወገን እንደሆኑ ምን እንደሚፈልጉ ለመናገር እንደሚቻል የገመገምንበት ሰዓት ነበር። መረዋን የምናዘጋጅ ግለሰቦች ከፈጣሪ በስተቀር ማንንም እንደማንፈራ ደጋግመን ግልጽ ያደረግን ይመስለናል። ወንድምና እህትን ከማክበር ግን ወደኋላ ያልንበት ሰዓት የለም ወደፊትም አይኖርም። የሚፈራ ሰው የእምነት ክስረት ያለበት ብቻ ነው። ስለሆነም መረዋ የማንንም ስም አስመስሎ ለማታለል ብሎም የበግ ለምድ ለብሶ የሚደበቅ ተኩላ ለመሆን እቅድ የለውም። ሰሞኑን የመረዋን ስም አስመስለው በ blog ላይ ሊያወናብዱ የተነሱትን አስመሳዮች ይህ ሌላውን የሚያታልሉበት መስመር ከመሰላቸው ይግፉበት ከማለት በስተቀር አንለምናቸውም። አባላት ደግሞ ከጽሑፋችን ማ ምን እንደሚል ስለሚያውቁ ግለሰቦቹ የሚሞክሩት ሙከራ የመጨረሻ የክስረት ደረጃ መሆኑን ያሳይ እንደሁ እንጂ የትም እንደማይወስዳቸው በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።
ይህ የቤተክርስቲያን ግጭት እንደተፈጠረ በድብቅ ወረቀት መበተን የጀመሩት እነዚሁ ዛሬ "የቤተክርስቲያኑን አመራር ተረክበናል" የሚሉት ግለሰቦች እንደነበሩ ምእመናን የሚያስታውሱት ጉዳይ ነው። ለበተኑት ወረቀት ምላሽ ደወል በሚል የሚታወቀው የከሳሾችን አቌም የሚያስተጋባው መጽሔት መበተን ሲጀመር እውነቱ እየመረራቸው በመምጣቱ ወደ ቦርድ ሄደው የሙጥኝ በማለት ፋታ አሰጡን ብለው "ወረቀት በቤተክርስቲያን ግቢ መበተን ተከልክሏል" የሚል አዋጅ በቦርድ አባላት አሳወጁ። ያም ሆኖ እነሱ የማይረባውን ያሉባልታ ወረቀታቸውን መበተናቸውን ቀጠሉ።
ምን እየጻፉ እንደነበር የምታውቁት ያነበባችሁት ስልሆነ ወደኋላ ተመልሰን የናንተን ጊዜ በማይረባ ማቃጠል ስለማንወድ እንዳለ እናልፈዋለን። ቆየት ብለው ደግሞ SENBETE በሚል ስም Blog ፈጥረው የስድብ አለንጋ ሲያወርዱ ያላዋቂ ሳሚ........ የሃይማኖት ሰበካ ሲሰብኩ ከረሙ።ለናሙና ስለ ሲኖዶስ ሰሞኑን ያወጡትን ገብታችሁ አንብቡላቸው። እኛ አይተን ይቅር በላቸው እያልን እየጸለይንላቸው ነው። አለማወቅ ወንጀል አይደለም። የማያውቁትን የሃይማኖት መቀባጠር ደግሞ በመምድር መናቅን ከሰማይ ደግሞ ቅስፈትን እንደሚያመጣ ግን እናውቃለን። ይህ አካሄዳቸው ሕዝቡን ለማወናበድ በማሰብ ያቀዱት ጅምር መሆኑን የተገነዘቡ ነገሩ ያሳሰባቸው ግለሰቦች Selam-tewahedo.blogspot.com በሚል ለአወናባጆቹ መልስ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ብሎግ ብቅ ማለቱን ታስታውሳላች። ይህ ብሎግም እነዚህን ሰላም ሲፈጠር የሚያንቀጠቅጣቸውን እውነት የሚያስደንብራቸውን ግለሰቦች እጅጉን አሳሰባቸው። የስድብ ውርጅብኝ መሰነዛዛርም ተጀመረ ማለት ነው። መረዋምም እንዲሁ ለምእመናን መድረስ ያለበትን ለማዳረስ ይህንኑ የጀመሩትን የብሎግ መስመር በመጠቀም ስርጭቱን ጀመረ። በጥቂት ሳምንታት እስከ 10,000 ግለሰቦች የጎበኙት መረዋ የማይጋፉት ባላጋራ መሆኑ ታያቸው። ያነበቡት ሳይሆን ወደ ፊት ሊወጣ ይችል ይሆናል የሚሉት የማያውቁት አስፋራቸው። መቅበጥበጥ ጀመሩ። ለድሮው እምነት የሌለው ግለሰብ መሪው የወለቀ መኪና ማለት ነው ይባል ነበርና።
ውድ አንባብያን ሰሞኑን ደግሞ ትላንትና selame tewahedoን የሚመስል Bloge ፈጥረው ሊያወናብዱ የተነሱት እነዚህ ግለሰቦች ዛሬ Merewametta.blogspot.com የሚለውን ብሎግ በማስመሰል ከመሃከል ካለው ሁለት T አንዱን በማውጣት ሊያወንብዱ መነሳታቸውን በጅምላ E Mail እየላኩ ስናያቸው ገረመን። ለእውነት መቆም እንጂ ሃሰትን ከእውነት በማስጠጋት ሃሰት እውነት እንደማይሆን ግን የተረዱት አልመሰለንም። በበኩላችን መልካሙን እየተመኘንላቸው ልቦናቸውን ወደ እምነት እንዲመልስላቸው ከመጸለይ አናቌርጥም። እነዚህ ወንድሞች ደግሞ የሚታይ እውነትን እየካዱ ያላዩትን ማመን ቢከብዳቸው ምን ይገርመናል?
ወደ ሌላው እንመለስና በትላንትናው እለት ተጠርቶ በነበረው ስብሰባ የተገኘው ሕዝብ ያካሄደውን ስብሰባ ተከታትለን ነበር። ተሰብሳቢው ምእመን ቦርዱ የሚያደርገው ሁሉ ቤተክርስቲያንችንን ወደጥፋት እየመራው መሆኑን ሲያምን አሁንም እባካችሁ ብለን መነጋገር አለብንና ሄደን እናናገራቸው እነሱም እኮ ወንድሞቻችን ናቸው ብለው ሲወያዩ ለማድመጥ እድል አግኝተናል። የገረመን ስብሰባው ከቤተክርስቲያኑ ውጭ መደረጉ እንጂ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው ግለሰቦች ለመሆናቸው አነጋገራቸውና ስነስርአት መጠበቃቸውን አይተን ተደስተናል። የተናገረ ይውጣ የሚል አልነበረም ፖሊስ አልተቀጠረም ስድብና ውርጅብኝ አልነበረም። ቤቱ የተስማማበትን ስራ ላይ ለማዋል የተመረጡት ወንድሞችና እህቶች ጉዞአቸው እንዲሳካላቸው ከመመኘት በስተቀር። ውሳኔውን ማቅረቡ የተመራጮቹን ሥራ መቅደም እንዳይሆን በመስጋት መረዋ እነሱ እስኪናገሩ ድረስ ከማተም ይቆጠባል። ተመራጮቹ ይፋ በሚያደርጉበት ሰዓት የበኩላችንን እንደምናበስራችሁ ቃል እንገባለን።
ለሽምግልና ሄደው ቦርዱን ያነጋገሩት ግለሰቦች ምን እንደተባሉ ለሕዝቡ ግልጽ እንደሚያደርጉም እምነታችን ነው።
እኛ ምኞታችን ቤተክርስቲያናችን ወደነበረበት እንዲመለስ ብቻ ነው። ምእመናን እንደጥንቱ የተነጠቁትን ቤተክርስቲያን ወደነበረበት የመመለስ ሃላፊነት አለባቸው ብለን እናምናለን። የሰባራ ህልሙ ምርኩ ማግኘት ነው ይላሉና?
ልትገናኙን ለምትፈልጉ ሁሉ ብሎጉ ውስት በመግባት መጻፍ እንደምትችሉ እየጋበዝን ከብሎግ ውጭ ለምትፈልጉን የ e-mail አድራሻችን በፊት እንደገለጽነው Yetayalewnetu@gmail.com መሆኑን በድጋሜ መግለጽ እንወዳለን።

  • የከርሞ ሰው ይበለን

Sunday, February 21, 2010

ታላቅ የኦርቶዶክስ ስብሰባ በዳላስ ቁጥር ፲፬

"የጠመጠመ ሁሉ ቄስ አይደለም የጠመደ ሁሉ ጎበዝ አራሽ አይደለም " ይሉ ነበር ያገራችን ሽማግሌዎች። ነገሮችን በምሳሌ ሲያስተምሩ ነው። እኛ ያለንበት ዳላስ ደግሞ የቦርድ አባል ሆኖ መመረጥ የመንፈሳዊ ስልጣን እየመሰላቸው "ቄሱ ምን ያውቃል እኛ እንነዳዋለን እንቢ ካለ እናባርረዋለን" ማለት ከጀመሩ ሰነበተ። ይባስ ብለው ሰባኪ መራጮች የትምህርቱን አይነት ወሳኞች መሆን ከጀመሩ ውለው አደሩ። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂዎች ደግሞ ተመራጮቹ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዳንዳችን ነንና እንደ ደረጃው የሃላፊነት ድርሻ መቀበል ይኖርብናል። በቅዱስ ሚካኤል እየነደደ ያለው እሳት መጥፋት ባለመቻሉ ከ ሺህ በላይ የነበረውን አባል ከሁለት መቶ በታች እንዲወርድ አደረገው:: ጭቅጭቅ በመፍራት ዛሬ ኪዳን አድርሶ ከቅዳሴ በፊት ወደቤቱ የሚመለሰው ምእመን ቁጥር እየጨመረ ነው:: "አንድ በሁኔታው የተበሳጨ የቤተክርስቲያኑ አባል "ጸሎት ስፈልግ ሌላ ቤተክርስቲያን ሄጄ አስቀድሳለሁ ምን እያደረጉ ይሆን ስል ደግሞ ሚካኤል ብቅ እላለሁ" ብሎ የልቡን አጫውቶን ነበር። ታዲያ ምን እስኪሆን እንጠብቃለን ያሉት መንፈሳዊ ትግል ሲጀምሩ እኛ ምን አደረግን? ብሎ መጠየቅ የተገባ ይመስለናል ።
ቤተክርስቲያንችን የእምነት ሳይሆን የፖለቲካ መፋለሚያ ሆኖ ሲሰነብት ስንቶቻችን ነን በቃ ያልን?
በስልጣን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ካልተቃወምክ ክርስቲያን አይደለህም ሲባል ስንቶቻችን ተቃውመን የቆምን?
መንግስትን መቃወም ሌላ እምነት ደግሞ ሌላ ብለን የምናምን ስንቶቻችን ነን?
የተቃወመ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን፡ ዝም ያለ ደግሞ ሃይማኖት የሌለው ባንዳ ሲባል ስለ አቡነ አረጋዊ ተው ያልን ስንቶቻችን ነን?
በፈቃደኝነት ያገለግሉ የነበሩ ወላጆች ከኮሚቴ መባረር አለባቸው ተብሎ ሲባረሩ ተው ያልን ስንቶቻችን ነበርን?
የመንፈሳዊ አባቶች ያስተማሩት ትምህርት በቦርድ ላይ ያነጣጠረ ነው ተብለው ከቤተክርስቲያን ሲባረሩ አቁሙ ያልን ስንቶቻችን ነበርን?
ሕግ እየተጣሰ ሕግ ሲደነገግ አባላት ከቤተክርስቲያን እየተገፉ ሲባረሩ ስንቶቻችን አቁሙ አልን?
እንዴው በሚካኤል አቶ አበበ ጤፉ የትኛው የቤተክርስቲያኑ ኮሚቴ ውስጥ አገልግለው ነው ለመሪነት የደረሱት?
በወላዲቷ አቶ አበራ ፊጣ ናቸው ስለ ሃይማኖት ተቆርቋሪ ሆነው ግብረገብ እኛን ማስተማር ብቻ አይደለም ከፎቅ ላይ በመሆን የአባቶችን ሰበካ የሚቆጣጠሩት?
አቶ ሙሉአለም ናቸው የሩቅና የቅርብ እቅድ አውጥተው ምእመኑን የሚመሩት?
ገንዘብ የለኝም ያሉት ባለ እዳ ዶክተር ናቸው የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ የሚጠብቁት?
ይህንንና ሌሎችም የችግሮቹን መንስኤዎች እያነሳን ብንጠይቅ ችግሩ ከራሳችን ላይ ሆኖ እናገኛዋለን ለማለት ነው። "ድሮ እናቴ እንቁላል ስሰርቅ ብታስቆመኝ ኖሮ ዛሬ በሬ ሰርቄ እስር ቤት አልገባም ነበር" ያለውን የድሮ ትምህርታዊ አባባል ያስታውሷል። ዳላስ ደግሞ በመንፈሳዊ ሽማግሌዎች የተራቆተች ከተማ አይደለችም። ሽማግሌዎቹም ጭቅጭቁን በመጥላት ችላ አሉ እንጂ። እኛም ዝም በሉ አልናቸው ካልሆ ም እነሱም ይሉኝታና ፍራቻ አደረባቸው።
ይህ ሁሉ አልፎ አሁን ነገሩ የገባቸው የቤተክርስቲያኑ ተቆርቌሪዎች ለፊታችን ቅዳሜ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ስብሰባ እንደጠሩ ስንሰማ ማንም ይጥራው ማን ይህ ትክክለኛ ጅምር ነው ብለን ሚካኤል ያሰባችሁትን ያሰካላችሁ ብለን ተናግረናል። ሲሆንማ ለፖለቲካ ስብሰባ ይፈቀድ የነበረው የቤተክርስቲያኑ አዳራሽ ውስጥ ነበር ስለቤተክርስቲያኑ ችግር መነጋገር የነበረብን። የተገላቢጦሽ ያልለፉበት ባለንብረቶች የገነቡት የእንጀራ ልጆች ሆኑና ተቸገርን እንጂ።
ስብሰባው ምን ያመጣል ከማለት ይልቅ በስብሰባው ተካፍሎ መፍትሄ መፈለግ ደግሞ የያንዳድዳችን ጥረትና መንፈሳዊ ግዳጅ መሆን ይኖርበታል።
የቦርድ አባላት ይህንን ስብሰባ ለማደናቀፍ በቅዳሜ እለት ሌላ ስብሰባ ከሌሎች ሽማግሌ ተቆርቌሪ አባላት ጋር ለመድረግ መወሰናቸውን ስንሰማ ደካሞች ናቸው ይልቅስ ሰውና ጊዜ ከመሻማት እኛ ብንሆን ኖሮ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከሆነ እኛም መገኘት ይኖርብናል ብለው ወንድሞችና እህቶች ምን ሆናችሁ በማለት ስብሰባውን እነሱም መሳተፍ ነበረባቸው አልን።
ለማንኛውም መረዋ ስብሰባውን እንደሚካፈል እንደገና ቃል እየገባ የመረዋ አንባብያን የሆናችሁ ሁሉ በዚህ ስብሰባ ላይ እንድትገኙ ያበረታታል።
በዛሬው እለት ከቅዳሴ በኋላ ለአደባባይ የበቁት "ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉአለም" ተጽፎ የተሰጣቸውን ማንበብ ያቃታቸውን አዋጅ ሲያነቡ በጎደለ እየሞላን አዳምጠንላቸዋል።
በንባባቸው አዲስ የገንዘብ ማውጫ የረጅምና ያጭር ጊዜ ፕላን አንብበዋል። የገረመን ገንዘብ እያነሰ ለካህናት ደሞዝ መክፈል አቃተን ያለ አስተዳደር ቦርድ በ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ለማውጣት መነሳቱ ነው። ያውም አባላት ሳያጸድቁት።
በሪፖርተር ላይ ት/ቤት ለሕጻናት እናሰራለን
የመኪና ማቆሚያውን እንጠግናለን
ቤተ ክርስቲያኑን እናሳድሳለን
እንግሊዘኛ የሚናገር መጽሃፍ ቅዱስ አስተማሪ እንቀጥራለን
መንፈሳዊ አባቶችን ሳያማክሩ ሰባክያን እንጋብዛለን የሚል ይገኝበታል።
ወይዘሮ ሰሎሜ የተመኙትን በማግኘታቸው ዘንድሮ እንኴን ደስ ያለዎ ልንላቸው እንወዳለን። "መጽሃፍ ቅዱስ ለማስተማር ኦርቶዶክስ መሆን የለበትም"ይሉ ነበርና ነገ የሚያመጡልንን መምህር እናያለን። ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል ነው ያለችው እብዷ?
ገንዘብ ለማጥፋት ኮንትራት መፍጠር የግድ ነው። ዶክተር እንኴን ደስ ያለዎ እንበል።
የሲኖዶስ ጥያቄ ደግሞ የሚቀጥለው ስብሰባ ላይ እንደሚቀርብ አሁንም ሹክ እንበላችሁ።
ከስብሰባ በኋላ የምንነግራችሁ ይኖረናል እስከዚያው በስብሰባው ላይ እንገናኝ እያልን ይህን ስብሰባ ያስተባበሩትን ከልብ እናመስግን። መፍትሄ በውይይት እንጂ ነገሮችን በመተብተብ ይሆናል ብለን አናምንም። ሚካኤል የኮሩትን ይቅር ይበላቸው ለቤተክርስቲያን መፍረስ ታጥቀው የተነሱትን በተግሳጽ ያብርዳቸው።
እውነትን ይዞ የተነሳ በእምነት የሚጔዝ ሰው ማደሪያ አያጣም።

Tuesday, February 16, 2010

ነብር የሞተ እለት ፍየል ልጇን ትድራለች ቁጥር ፲፫

"መረዋ በተደጋጋሚ ሲናገር የነበረው ሁሉ ለምን ደረሰ? ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ መልሱ ባለፈው እንዳልነው ነብይነት ኖርን ሳይሆን ከነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መጭውን መተንተን ስለቻልን ብቻ ነው። ይህንን ለመተንተን ደግሞ በትምህርትም ሆነ ባመለካከት ከኛ የላቁ ግለሰቦች በቤተክርስቲያናችን ለመኖራቸው አንዳችም ጥርጥር የለንም። ልዩነቱ እነሱ አለመናገርን ሲመርጡ፤ ከሰው ላለመጣላት፤ በይልኙንታ ሲጠመዱ እኛ ግን በእምነታችን፤ በመብታችን አንደራደርም ብለን መነሳታችን ላይ ብቻ ነው። ነገሮች እየፈጠጡ መጥተው ዛሬ ቤተክርስቲያናችን አይወድቁ አወዳደቅ ሊወድቅ መቃረቡን በማየት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ስናይ ይህ ትላንት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ............."ፍየል ልጇን ለመዳር አትነሳም ነበር" ብለን የተናገርነው። ብዙሃኑን በዘዴ ከአባልነት አባረርን የሚሉት የቤተክርስቲያናችን ጉልበተኞች አባላቱ $30 መክፈል አቅቷቸው ሳይሆን ለእምነትና ለማተባቸው በመቆም በማላምንበትና ባላፀደኩት ሕገደንብ አልተዳደርም ማለታቸውን ሊረዱት አይችሉምና። ለምን እምነት ለነሱ ባዳ ስለሆነች። ባይሆንማ ኖሮ አባላትን ማባረር የሚለው ድርጊቱ ቀርቶ ቃሉን ባልተጠቀሙት ነበር። ክርስቲያን ክርስቲያንን ይረዳል ያበረታታል እንጂ አያባርርም ነበርና።

ሰሞኑን በተለያዩ የቤተክርስቲያንችን ተቆርቌሪ አባላት እየተደረገ ያለውን ቤተክርስቲያናችንን የማዳን እንቅስቃሴ መረዋ በድጋሜ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ እያረጋገጠ፤ በተቻለው ሁሉ ለመርዳትና ወደኋላም እንደማይል በመደጋገም ቃል ይገባል። የሰሞኑ እንቅስቃሴ መሪዎች ቆርጠው መነሳታቸውን ስንሰማ የተደሰትነውን ያክል ተመራጭ ነን ባዮቹ የቦርድ አባላት እንቅስቃሴውን ለመግታት ምን ያክል የቤተክርስቲያን ገንዘብ ሊያጠፉ እንደሚነሱ ስናስብ ግን የዛኑ ያክል አዘንን። እናንተም ልታዝኑ ይገባችኋል። ያላዋጡትን ሲያዙበት ያልሰበሰቡትን ሲበትኑት ማየትን የመሰለ ምን የሚያሳዝን ነገር ሊኖር ይችላል? እንደተገለጸው አሸነፍን ብለው ጮቤ የረገጡ ሰርግና ምላሽ የሆነላቸው ግለሰቦች ለተሿሚ ሰከንድም እድሜ ነው ካላሉ በስተቀር የሕዝቡ ድጋፍ እንደሌላቸው እየተረዱት ለመምጣታቸው ከሚወስዱት እርምጃ መገምገም ይቻላል። የከተማችን የሬዲዮ ተናጋሪ የሆኑት አቶ ዘውገ የአባልነት ክፍያ ሊከፍሉ ሲሄዱ አንቀበልህም መባላቸውን ስንሰማ አዘንን። እሳቸውም በሬዲዮ የሚነገረውንና የማይነገረውን ከፖለቲካ አመለካከታቸው አኴያ እያመዛዘኑ እገዳና እቀባ እንደሚያደርጉት ነውና እሰየው ግን አላልንም። እሳቸውም ትክክል አይደሉም፤ ቦርዱም ትክክል አይደለም ብለን እናምናለንና። የቦርዱ አቀንቃኞች ቦርዱ በሰጣቸው የቡድን ገለጻ በመነሳት በያለበት የሚያነሱት የሰሞኑ የውይይት ነጥብ ደግሞ የቤተክርሰቲያን አባላት ክፍያቸውን እያጠናቀቁ ስብሰባ ይጠራና በሲኖዶስና በስደት ሲኖዶስ ምርጫ ተደርጎ አንዱን መከተል አለብን የሚል ሆኖ አግኝተንዋል።
የሚገርመው ነገር አባላት ወደነበሩበት ለመመለስ የሚያቀርቡት ጥያቄ ያልቀየርነው መተዳደሪያ ደንባችን ወደነበረበት ይመለስ ሆኖ ሳለ ጥያቄያቸው ሳይመለስ የቦርድ አባላት ያዘጋጁትን ቅጽ በመፈረም መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቁ ለማጭበርበር መነሳታቸውን አለመግለጻቸው ነው። ያዘጋጁት ቅጽ በተለይ የእንግሊዘኛው ይህንን በመፈረም የቤተክርስቲያኑን ሕግ ሙሉ ለሙሉ መቀበሌን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ ይላልና።

በነሱ ብልጠት የጎደላቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብም ይጠቅመናል ከማለታቸው ባሻገር፤ የተባለው አባል ተመልሶ እንኴን ድምጽ ቢሰጥ እነሱ ካላመኑበት ባዘጋጁት ሕግ መሰረት ቦርዱ የአባላትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመሻር የቦርዱን አባላት ፍላጎት ተፈጻሚ ለማድረግ ማቀዳቸውን ሕዝብ አያውቅም ብለው መናቃቸው ነው። ሕዝቡን ቢንቁ ደግሞ ምንም አይገርምም ሥራ ያላስያዘ ዲግሪ በእዳ የተወጠረ ዶክተር እየመራቸው ነውና።
ትላንትና አባል የሆኑት እኮ ናቸው በሕጉ መሰረት ስብሰባ ለመጥራት የአባላት ፊርማ ቢያሰባስቡ ገደል ግቡ የተባሉት፤ የዲግሪ አቻቸው በግለሰብ ሲፈርሙና ስብሰባ ይጠራ ሲሉ ግን ስብሰባ የተጠራው።
ትላንትና አባል የሆኑ እኮ ናቸው ከፈረማቸሁ አትናገሩም የተባሉት።

ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው ስነስርአት በማለታቸው በፖሊስ ተገፍትረው የተባረሩት።

ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው መሃበርቅዱሳን መባረር አለባችው ብሎ ቦርዱ ሐሙስ እለት ወስኖ ክስ በመመስረቱ ቅዳሜ ተሰብስበው ውሳኔአቸውን በግዳጅ የቀለበሱት::

ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው ከሳሾችን አናውቃቸውም ያለዛሬ አይተናቸውም አናውቅ ብለው በመሃላ በፍርድ ቤት የተናገሩት።
ይህ ሁሉ ውሳኔ ሲወሰን በትክክልነቱ ይከራከሩና አስፈጻሚም የነበሩት የቀድሞው ሊቀመንበርና ከስልጣን የወረዱት አባላትም ዛሬ ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ቤተክርስቲያኑ ወደ ጥፋት እየተገፋ መሆኑን መናገራቸውን ስንሰማ ሚካኤል ልቦናቸውን ከፈተላቸው አልን እንጂ ትላንት የአባላትን መብት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መዳፈራቸውን ግን አልረሳንም። ትላንት ዶክተሮቹና ደጋፊዎቻቸው "መልአክ" ብዙሃን አባላት ግን "ሰይጣን" ናቸው ብለው ያምኑ ነበር ቢረሱት አልረሳነውም።
ለዚህም ነው በሚካኤል ሲባል ስላልሰሙ በሕግ አምላክ ማለት ያስፈለገው።
ዛሬ አባላት ምንም አይነት ውሳኔ ቢወስኑ ቦርዱ ካላመነበት መሻር ይችላል። በዚህ የአምባገነን ሕግ ሊያስተዳድሩን ስልጣን ላይ የወጡት አቶ አበበ ጤፉ አገርቤት ያለው መንግስት ሕግ የማይገዛው አንባገነን ድንበር የሚያስማማ ሌባ የሕዝብን ድምጽ የማይሰማ ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆን የሚረዳው ሕገ መንግስት ደንግጎ በሕዝብ ላይ ያላግጣልና መገርሰስ አለበት የሚሉን። "ወደሰማይ የተወረወረ ድንጋይ መልሶ የሚመታው ወርዋሪውን ነው"። ይሏል ይህ ነው። ቤተክርስቲያናችን ከአንባገነኖች ብቻ አይደለም የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የሚታገሉ ግለሰቦች ወደ ጎን ተብለው አማንያን እስካልተረከቡት ድረስ ፍጭቱ ይቀጥላል።
በቅርቡ ሊጠራ ታስቧል የተባለው ስብሰባ ውጤት እንዲያገኝ ከተፈለገ፦
1 ሕጉ ወደነበረበት መመለስ አለበት
2 አባላት ያለምንም ጥያቄ መክፈል የሚችሉትን እየከፈሉ መመዝገብ አለባቸው።
3 የቦርድ አባላት ነን ባይ አንባገነኖች ሕዝቡ ለመረጣቸው ጊዜአዊ ኮሚቴ አስርክበው መውረድ አለባቸው።
4 የሚደረገው ስብሰባ በገለልተኛ ምእመናን መመራት ይኖ ርበታል ብለን እናምናለን።
ስብሰባው የተቃና እንዲሆን የክርስቶስ ፈቃድ ይታከልበት።

Friday, February 12, 2010

ይሉኝታ የሚሰማው መጭውን ማየት የሚችል ብቻ ነው። ቁጥር ፲፪

ከቁልቋል ወተት ሙጫ እንጂ ቅቤ እንደማይወጣ ሁሉ ተመረጡ ከተባሉት አዲስ የቦርድ አባላት ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ብለን እናምናለን። ለመሆኑ ይህንን ሁሉ ችግር የፈጠረው ማን ሆነና?። ምእመናን መባረር አለባቸው ብለው ያባረሩ እነሱ፤ በፖሊስ መመንጠር አለባቸው ያሉት እነሱ። ሕጉን ካልቀየርን ብለው የተነሱት እነሱ። የቤተክርስቲያኑ አባላት እንደማያጸድቁት ሲያውቁ በስልጣናችን ሕጉን ቀይረናዋል ያሉት እነሱ። ሕጉ ከመቀየሩ በፊት የክፍያ ተመን የወሰኑት እነሱ። ዛሬ የቦርድ አባላት ሆነው የተመረጡት እነሱ። ብለን ለመጠቆም ያክል ነው።
አባላት $30 ብር መክፈል አቅቷቸው መክፈል ያቆሙ ከመሰላቸው በጣም ተሳሰተዋል። የቦርዱ ተመራጭ ዶክተር መክፈል ከቻሉ ማንም መክፈል ይችላል። የቦርዱ ተመራጭ ዶክተርም ሆኑ አቶ አበራ ቤተክርስቲያናችንን ከመቀላቀላቸው በፊት አባላት ምን ይከፍሉ እንደነበር ቤተክርስቲያኑ በስንት ጊዜ ተከፍሎ እንዳለቀ እጎናቸው ያሉትን አዲስ ሊቀመንበር ጔደኛ እህ ቢሉ የሚነግሯቸው ይመስለናል። ነገሩ ከዛ በላይ የእምነትና የተቃውሞ መግለጫ መሆኑን ግን የተረዱት አይመስልም። ድኩላ አይቶ ለማደን የሚዘል ነብር በመሃከል ጉድጔድ መኖሩን ቢረሳ አይገርምም እይታው ድኩላው ላይ ነውና። አንተዬ የቆየ አባባል ትዝ ይልሃል "ጔደኛህ ማን እንደሆነ ንገረኝና ማን መሆንክን እነግርሃለሁ" ይባል አልነበር። ታዲያ ማንና ማን እንደተቀናጁ አስተውለን ወዴት እየሄዱ እንደሆነ መናገር ምን ያዳግታል። አቶ አበራ የቤተክርስቲያን "ተቆርቌሪ" አቶ ምናሴ የቤተክርስቲያን "ጠላት"። የሂሳብ ከፍሉ ዶክተር ቤተክርስቲያን "ገንቢ" ዲያቆን አርአያ ቤተክርስቲያን "አፍራሽ":: ሰሎሜ "ፍጹም ክርስቲያን" ጥሩአየር "አስመሳይ አማኝ":: ከዚህ መመሳሰል ላይ ችግር የለም ካልን ሁላችንም ሃኪም ማየት ሊኖርብን ነው። "ንስሐ" የሚለው ቃል አያስፈራንም ብለን ስላመንን ነው ለመጠቀም የተቆጠብነው።
"በላበክ ቴክሳስ የፕሮቴስታንት ተከታይ ሆነው የከረሙት ዶክተር ትላንት መጥተው ቤተክርስቲያናችንን አፈራረሱት" የሚባለውን አባባል ከማይጋሩት አንዱ መረዋ ነው። ተጠያቂዎቹ የጠቆሟቸውና ለስልጣን ያበቌቸው አባላት ናቸው ብሎ ስለሚያምን። ዶክተሩን ምረጡ ይሉ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ዶክተሩ ጉድ አደረጉን ቢሉ የሚያታልሉት እራሳቸውን ብቻ ነው። የራሳችንን ድክመት ለመሸፈን ሚካኤል ታምር ያሳየናል ማለትስ የራስን እምነት ፈተና ውስጥ መጣል አይሆንምን? ሚካኤልማ ምን እያደረጉ እንደሆነ እያሳየን ነው እያየን የታወርነው እየሰማን የካድነው እኛ ነን እንጂ። አቶ እዩኤል ከስልጣን ይገፈተራሉ ብለን ስንናገር ሕልም አይተን አልነበረም፡ የሁኔታዎችን አካሄድ በማየት እንጂ። ገንዘብ አጎደሉ የተባሉት እንደገና በገንዘብ ላይ ይሾማሉ ያላልነው ግን ምንም አባላትን ቢንቁ እንዲህ አፍጥጠው ይወጣሉ ብለን ስላልጠረጠርን ነው። ይህንን ባለማየታችን እራሳችንን ልንወቅስ እንወዳለን።
በየድግሱ ሲጋበዙ የነበሩት ዶክተር ዛሬ ጋባዡ መጥፋቱ ያስጨንቃቸዋል ብለን አስበን ነበር። አሁንም ተሳስተናል። የሳቸው ሕልም ሌላ ነውና። ሲያዙአቸው የነበሩትን የቀድሞ ሊቀ መንበር አንቅሮ ለመትፋት ሰከንድ ያልፈጀባቸው ዶክተር ከአዲሱ ሊቀመንበር ጋር ለወራት ይቆያሉ ብለን አናምንም አዲሱ ሊቀ መንበር ምንም መሃይም ቢሆኑ ፈጣሪን ይፈራሉ ብለን በመገመት። የዛሬውን ሊቀመንበር ምንም ባለቤታቸው ቢቆጧቸው በመቆየት የሕዝቡ ፊት ግርፊያ ያንበረክካቸውና "ምነው ወሎ" ብለው ድንገት ይነሣሉ ብለን መተንበይ እንወዳለን።
መረዋ ሰሞኑን ከሰበሰበው መረጃ አንዳንዱን እናካፍላችሁ።
ባለፈው አጠቃላይ ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበሩና በወቅቱ የሂሳብ ተቆጣጣሪ የነበሩት ወይዘሮ ገንዘብ እንደጎደለ መጠቆ ማቸው ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ቤቱ ይህንን የሚያጣራ ኮሚቴ መሰየሙም የሚታወስ ነው። ቤቱ ከሰየማቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ አቶ ኪዳኔ ምስክር እንደነበሩ ዘጋቢዎቻችን ጠቁመው፡ ይህ ግን አቶ አበራንም ሆነ ዶክተሩን ስላስቆጣቸው በቦርድ ስብሰባ ላይ ነገሩን አንስተው አቶ ኪዳኔ ምስክር ከኮሚቴው ባስቸኴይ ተገፍትረው እንዲባረሩ በድምጽ ብልጫ አስወስነዋል። "ይህ የቤቱን ስልጣን መጋፋት ይሆናል ምክንያቱም የተመረጡት በምልአተ ጉባኤው ነው" ቢባሉም አሻፈረን መተዳዳሪያ ደንቡ ደግሞ ቦርዱ የቤቱን ውሳኔ መሻር ይችላል ስለሚል መሻር እንችላለን። በተጨማሪም የአቶ ኪዳኔ ባለቤት ቤተክርሰቲያኑን የከሰሱ ስለሆነ አቶ ኪዳኔ በሚስታቸው ወንጀለኛ ናቸው መባሉንም ልናወሳችሁ እንወዳለን። እንደተለመደው መራጩ የቤተክርስቲያን አባል አላዋቂ ነውና አቶ ሙሏለም ይወስኑለት ተብሏል ማለታችን ነው። በዚህ አጋጣሚ ለአቶ አበበ ጤፉ ኧረ ድንበር እየተጣሰ ነው ብለን "አቤቱታ" እናቀርባለን። በሌላ ዜና selam tewahedo እንዲመስል ከ H ቀጥሎ ያለችው E የሌለችበት BLOG ብቅ ብሎ መጥፋቱን ስናበስራችሁ ይህ የሚደረገው ትክክል አይደለም የሚሉትን ግለሰቦች በስም እየጠቀሰ በመሳደብ ሴራቸውን አከሸፍነው የሚለው ጽሑፍ ለምን ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደተነሳ ባይገባንም በላዩ ላይ ቁምነገር ስላልነበረበት አፍረው ሊሆን ይችላል ብለን ተቀብለነዋል። ጽሑፉን ማየት ለምትፈልጉ ሁሉ ጥያቄአችሁን E mail ብታደርልን ልንልክላችሁ ዝግጁ ነን።
በሌላ ዜና ሰሞኑን የቤተክርሰቲያኑ አካሄድ ያላማራቸው ግለሰቦች እያደረጉ ያለውን ንቅናቄ መረዋ በሙሉ ልብ እያደነቀ ከጎን ሆኖ ለመስራትም ፈቃደኛ መሆኑን ቃል መግባት ይወዳል። ወንድሞችና እህቶች የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ ስለያዙ አሸነፍን ብለው የሚኩራሩትንና ተቃዋሚ ነው የምንለውን መንጥረን እናባርራለን ብለው የተማማሉትን እነሱ እኛ ባዋጣነው ገንዘብ ይመኩ እኛ ደግሞ በእምነትና በህብረት እንቌቌማቸዋለን። ምን ግዜም በእውነት ላይ የተመሰረተ ስብስብ አለት ሆኖ ይከርማልና። ለእምነትና ለእውነት እንቁም። በክርስቶስ እርዳታ ቤተክርስቲያን ታሸንፋለች።

Sunday, February 7, 2010

ተረካከቡ ወይስ ተሰዳደቡ ቁጥር ፲፩

እንዴት ከረማችሁ አንላችሁ ነገር የሰነበታችሁበትን በከፊልም ቢሆን የምናውቅ መሰለን። የተለመደውን የቤተክርስቲያኑን ስንክሳር ማለታችን ነው። አዲሶቹ የቦርድ ተመራጮች ነን ባዬች ገና ከጅምሩ ችግር እየገጠማቸው እየመጣ ለመሆኑ ብዙም አዋጅ ነጋሪ አያስፈልገውም። በተሻረው ቦርድ ኮሚቴ በጸሃፊነት ሲያገለግሉ የከረሙት አቶ ኃይሉ አራጋው የስልጣን በለስ ለደረሳቸው ለአቶ አበበ ጤፋ የቀዱትን ቃለ ጉባኤና ወደ ኮንፒውተር የገለበጡትን ጭምር ብሎም ስልጣን ላይ እያሉ የጻፏቸውን ደብዳቤዎች ለማስረከብ ወደ ቤተክርስቲያኑ ጽ/ቤት ብቅ ብለው ኮምፒውተሩ ውስጥ ያላቸውን ዶሴ ለመመልከት ሲሞክሩ የመግቢያ ሚስጥራዊ የኮምፒውተር ቁልፋቸው ተቀይሮ መግባት እንደተከለከሉ ለመረዳት ችለናል። ይህ ለምን ሆነ? ብለው ቢጠይቁም የሳቸውን ከስልጣን መውረድ ይጠብቁ የነበሩት ዶክተር ከስልጣን ከወረድህ በኌላ እዚህ አካባቢ እንድትደርስ ስላልፈለግን ነው ብለው መመለሳቸውንም ለመስማት በቅተናል። ትላንት ካህናትን ያባርሩ የነበሩት አቶ ኃይሉ ዛሬ ተገፍትረው በመባረራቸው ደስተኞች አይደለንም። ሁለት ስህተት አንድ እውነት አይሆንምና። የልብ ልብ ተሰምቷቸው የሚንጎራደዱት ዶክተር በሕይወት ቆይታቸው ሲመኙት የነበረው እራእይ እውነት እየሆነላቸው እየመጣ ለመሆኑ እሳቸውን መጠየቅ ደግሞ አያስፈልግም። እሳቸውም ቢሆኑ ንጉሱ እኔ ነኝ ምን አባታችሁ ትሆናላችሁ ቢሉ እውነት አላቸው። በሳቸው አመራር የቤተክርስቲያኑ አባላት ቁጥር ከሺህ ወደ መቶ ወርዷልና። ነገ አባላት እያነሰ ስለሆነ ቤተክርስቲያኑን ሸጠን መለስተኛ ቤት እንግዛ እንደሚሉ ደግሞ ምንም ጥርጥር የለንም። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዝም በማለታችን ሁላችንም ተጠያቂዎች እንሆናለን። ዛሬ አባል ለመሆን እንኴን የዶክተሩ ፈቃድ ካልተገኘ እንደማይቻል ሕጋቸውን አንብቡት። ሕጉን የቀየርነው የተከሰስንበትን ክስ ለማሸነፍ እንጂ አምነንበት አይደለም የሚሉት ዛሬ ከቦርድ አባልነት የወረዱት ግለሰቦች ነገ በመሃላ ፍርድ ቤት ቀርበው ይመሰክራሉ ብለን እናምናለን። ያ ካልሆነ አሁን 11.2 ማስቀየር አለብን ማለት ግን ለዶክተሩና ለነርሱ ስድብ ስለሚሆንባቸው እንደማይቀበሉት ማወቅ ይኖርብናል።
ከአዲሶቹ ተመራጮች ጀርባ ሆነው ይህንን ሕልም እውነት ለማድረግ የሰሩት የቀድሞው ሊቀመንበር ያሰባሰቧቸው የፖለቲካ ተወካዮች ዛሬ አቶ እዩኤልን አሽቀንጥረው ከዶክተሩ ጫማ ስር መውደቃቸው የሚያስገርም አይደለም። ከዓመት በፊት የቀድሞው ጸሐፊም እንዲሁ አድርገው ነበርና። ዛሬ እጣቸው ምን እንደሆነ ያያቸሁት ነው። የፖለቲካ ተሰባሳቢዎችም ይህ እጣ እንደሚደርስባቸው የሚጠራጠር ካለ የቤተክርስቲያኑን ታሪክ ያልተከታተለ ብቻ ይሆናል።
በዛሬው ሰንበት የስልጣን ክፍፍሉን ያነበቡት አዲሱ ሊቀመንበር። የተቃወማቸውን የሂትለር የወጣት ክንፍ እያሉ ሲወነጅሉ ምን ማለት እንደሆነ እንኴን የገባቸው አይመስሉም እንል ነበርና፡ ዛሬ አንብብ የተባሉትን እየተቸገሩ ማንበባቸውን አይተናል። በንባባቸው የቀድሞው ሊቀመንበር ሃላፊነት አልወስድም በማለታቸው በተራ አባልነት ለማገልገል ወስነዋል ማለታቸው እሳቸውንም ሳይገርማቸው የቀረ አልመሰለንም። ሊቀ መንበሩ ተለምነው መቆ የታቸውን ያውቁ ነበርና።
ባዲሱ ድልድል የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ ዋሽቼ አስታርቃለሁ ካላሉ በስተቀር እውነቱ ለሳቸውም እንደሚያንገፈግፋቸው አንጠራጠርም። የእቃ ግዥ ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች ገንዘብ ጠፋ በማለታቸው ከተቆጣጣሪነት ተነስተው ወደ ማድቤት መሸኘታቸው እሳቸውንም ገንዘብ አጠፉ ብሎ ለመወንጀል እንዲያመች ስለሚመስል ይጠንቀቁ እንላለን በተጨማሪም የማድቤትና የቤተክርስቲያኑ ቁልፍ ተሸካሚ ከሆኑት ከሊቀመንበሩ ባለቤት ጋር ካልተስማሙ ሊያስወጧቸው እንደሚችሉ ካሁኑ ማወቅ አለባቸው። በሂሳብ ትምህርት ተመረቅሁ የሚሉን የታክሲ ሹፌር ስራ ባለመናቃቸው እያመሰገንን ለምን የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ላይ ሙጭጭ እንዳሉ ግን ሊገባን አልቻለም። ያውም ገንዘብ ጠፋ የተባለው ደመና ሳይገልጥ። አቶ ሙሉዓለምም ሆኑ ነርሱ ከዶክተሩ ትእዛዝ ውጭ የሆነ የራሳቸው ሃሳብም ሆነ ምኞት ስለሌላቸው ተሾሙም ተመረጡም ለውጥ ያመጣሉ ብለን አናምንም። የቤተክርስቲያኑን ማፍረስ ከማፋጠን በስተቀር። አቶ አበበ ጤፉ በመመረጣቸው ምንም ለውጥ ያመጣል ብለን አንጠብቅም የፖለቲካ ትእዛዝ ከማስፈጸም ውጭ። "ተወሰደ" ያሉትን ድንበር ሳያስመልሱ የጠፋ ገንዘብ ያስመልሳሉ ብለን አናምንም። በሳቸው መመረጥ የሚኩራሩት በፓልቶክ እንደ ንጉሥ ያመልኩባቸው የነበሩ ብቻ ይሆናሉ። በተጨማሪ ካሁን በኋላ የሂሩትም ሆነ የማሩ እንጀራ ቤተክርስቲያን ድርሽ እንደማይል መተንበይ አያስቸግርም።

Monday, February 1, 2010

ዝምታ በራሱ ተቃውሞ ነው። ቁጥር ፲

በትናንትናው ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ለአምልኮ ለመጣው ሕዝብ እንዲተዋወቁ የተደረገው አዲስ የቦርድ አባላት ለአምልኮ ለመጣው ሕዝብ እንዲተዋወቁ መደረጉን ከማስተዋላችንም በላይ፧ ሥራቸው የተቃና እንዲሆን በካህኑ መመረቃቸውን ለመታዘብ በቅተናል። ያልገረመን ነገር ቢኖር ግን ስማቸው ሲጠራም ሆነ ካህኑ በድጋሜ ተነስተው አጨብጭቡ ሲሉ እንኴን ያጨበጨበ አንድም ግለሰብ አለመኖሩ ነው። በቦርድ አባባል ቤተክርስቲያኑን መስርቶ እዚህ ያደረሰው የዳላስ አማኝ እኛ ያወጣንልህን "ሕገ መንግስት" ካልተቀበልክ ተብሎ ከአባልነት ተባሮ እያለ አሁንም በስሙ ጥቂቶች ሊቀልዱበት እንደ ደርግ ሆነው ሊያላግጡበት መነሳታቸውን ያየ ምን ዘመን ላይ ደረስን ቢል አንገረምም። መረዋም ሆነ ባካባቢ የተሰባሰቡ ግለሰቦች ይህንን እውነታ ከመድረሱ በፊት መዘገባቸው ይታወሳል እስካሁን ደግሞ ይሆናል ያልነው ሆነ እንጂ ምንም አዲስ ክስተት ተፈጥሮ አላየንም። ስማቸው ሲጠራ ለምን ምእመን አላጨበጨበም ሲባል እንደተለመደው ከመሃከላችን ያለው ቀላጅ " የሚዘረፈው ገንዘብ ብዛት ካሁኑ አስፈርቶት ነው" ማለቱን ሰምተን ዛሬም ስቀናል። አባባሉ ቅዳሜ ተደረጎ በነበረው አጠቃላይ "የቤተክርስቲያን አመታዊ ስብሰባ" ላይ የቀድሞው ሊቀ መንበር የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ በቦርድ ተመራጮች እየተዘረፈ መሆኑን በዘገባቸው ላይ ጠቅሰውት የነበረውን ለማንሳት እንደሆነም ገብቶናል።

የተራበን ከብት ቡቃያ ውስጥ አስገብቶ አትጋጥ ማለት እንደማይቻል እየታወቀ ወይንም የወተት ማሰሮ መግላሊት ከፍቶ ድመትን ወተት አትቅመሺ ማለት የዋህነት መሆኑን እንዴት ሁሉም እንዳልገባቸው እያስገረመ በነበሩበት ይቆዩ ማለት ግን ስርቆትን ማጽደቅ ነው ብለን እናምናለን። በስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩ አንድ አዛውንት የተናገሩትን በዚህ አጋጣሚ ልናካፍላችሁ እንወዳለን። እኚህ አባት ገንዘብ ተሰረቀ አልተሰረቀም የተባለውን ክርክር አዳምጠው አንዴ ልናገር በማለት ተነሱና የሚከተለውን ተረቱ። አንድ ግለሰብ ታመመና ወደ ዶክተር ዘንድ በመሄድ እራስምታት እያስቸገረው መሆኑንና መድሃኒት እንደሚፈልግ ዶክተሩን ቢጠይቀው ዶክተሩ በማዘን ወንደሜ አንተ እራስምታት ትላለህ ከዛ የባሰ ካንስር እየሰረሰረህ ነው አለው ብለው ዛሬ ተሰረቀ የተባለው $6000 ሳይሆን ከዛ የባሰ ችግር ቤተክርስቲያናችን ውስጥ እንዳለና የሚያሳስባቸው እሱ መሆኑን ተናገረዋል።

ወደ ትላንትናው ትርኢት እንመለስና አዲስ ተመራጭ ነን ባዬች የቦርድ አባላትን ያስተዋወቁት "የአስመራጭ ኮሚቴ" ተወካይ የተመራጮቹን ስም ጠርተው ካስተዋወቁ በኋላ የቤተክርስቲያናችን ችግር በዚህ እንደማይፈታ መናገራቸው ባይገርመንም ከዋለ ካደረ ሰው መማር እንደሚችል ግን እሳቸውን በማየት ለመታዘብ እድል ሰጥቶናል።

በትናንትናው እለት በተደረገው የቦርድ የውስጥ "ምርጫ" የስልጣን አሰላለፍ እንደሚከተለው ሆኖአል።

ሊቀ መንበር አቶ ዬሴፍ
ም/ሊቀምንበር አቶ ሙሉአለም
ጸሃፊ አቶ አበበ ጤፉ ሆነው ስልጣነ መንበር ሲረከቡ የቀድሞው ሊቀመንበር ከቦርድ እለቃለሁ ቢሉም በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ልመና ሃሳባቸውን እንደቀየሩ የውስጥ ምንጮቻችን ገልጸውልናል። ሂሳብ አጎደሉ የተባሉት የሂሳብ ዶክተርም ሆኑ የሳቸው ተባባሪ ነርስ መረጃዎችንና ዶሴዎችን ለማጥፋት እንዲችሉ በነበሩበት እንዲቆዩ መደረጉን ልናወሳችሁ እንወዳለን።

ባለቤታቸው ከስልጣን የተባረሩባቸው ግለስብም በቦርድ መካከል የተነሳው መበጣበጥ እንዲቆም መማጸናቸውን ስናዳምጥ ከልብ ማዘናችንን መግለጹ ተገቢ ይመስለናል። ምን አልባት የቀድሞው ሊቀመንበር ከስልጣን ከለቀቁ እንደሚወራው አቶ ብዙአየሁም እንዲሁ በቃኝ ካሉ ባለቤታቸው እንደገና ወደ ቦርድ የመግባት እድል ይኖራታል ብለው አስበው ሊሆን እንደሚችል ግን ለመተንበይ አልተቸገርንም።

መረዋ ዛሬ ለሁላችንም አንድ መልእክት ማስተላለፍ ይወዳል።

ቤተክርስቲያናችን ወደ መፍረሱ እየተቃረበ ለመሆኑ ሁሉም የተስማማበት ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት። ይህንን መጥፎ ሂደት ለመግታተ የሚቻለው የሚከተሉት ማረሚያውች ባፋጣኝ ሲደረጉ ብቻ ነው ብሎ ያምናል።

1 ቦርዱ በጊዚያዊ ኮሚቴ ሲተካ
2 የቀድሞ አባላት ወደ አባልነታቸው እንዲመለሱ ሲፈቀድ
3 ተቀየረ የተባለው የአንባገነን ሕግ ተሽሮ ወደ ድሮው ሕግ ስንመለስ
4 ቤተክርስቲያኑ የአምልኮ እንጂ የፖለቲካ ስፍራ መሆኑ ሲቆም
5 የእምነትን ጉዳይ ካህናቱ ብቻ መምራት ሲችሉ
5 የቤተክርስቲያን ገንዘብ የሰረቁ ምህረት ሲደረግላቸው ብቻ ነው ብለን እናምናለን። ይህ ካልሆነ ቀጣዩ ትግል በዝምታ መሆን አይችልምና ዝምታ በራሱ ተቃውሞ መሆኑ ቢገባንም ተሰብስበን በመነጋገር መፍትሄ መፍጠር አለብን በማለት ጥሪ ማድረግ እንወዳለን።

አላዛርን ከመቃብር ያስነሳ አምላክ የመቃብር ድንጋይ መፈንቀል አላቃተውም የሕዝብን ተሳትፎ በመፈለግ ግን"የመቃብሩን ድንጋይ ፈንቅሉ" አለ እንጂ። ስለሆነም ክርስቲያናዊ ግዳጅ አለብንና አሁንስ በዛ መበያው ወቅት ዛሬ ነው እንላለን።