እንዴት ከረማችሁ አንላችሁ ነገር የሰነበታችሁበትን በከፊልም ቢሆን የምናውቅ መሰለን። የተለመደውን የቤተክርስቲያኑን ስንክሳር ማለታችን ነው። አዲሶቹ የቦርድ ተመራጮች ነን ባዬች ገና ከጅምሩ ችግር እየገጠማቸው እየመጣ ለመሆኑ ብዙም አዋጅ ነጋሪ አያስፈልገውም። በተሻረው ቦርድ ኮሚቴ በጸሃፊነት ሲያገለግሉ የከረሙት አቶ ኃይሉ አራጋው የስልጣን በለስ ለደረሳቸው ለአቶ አበበ ጤፋ የቀዱትን ቃለ ጉባኤና ወደ ኮንፒውተር የገለበጡትን ጭምር ብሎም ስልጣን ላይ እያሉ የጻፏቸውን ደብዳቤዎች ለማስረከብ ወደ ቤተክርስቲያኑ ጽ/ቤት ብቅ ብለው ኮምፒውተሩ ውስጥ ያላቸውን ዶሴ ለመመልከት ሲሞክሩ የመግቢያ ሚስጥራዊ የኮምፒውተር ቁልፋቸው ተቀይሮ መግባት እንደተከለከሉ ለመረዳት ችለናል። ይህ ለምን ሆነ? ብለው ቢጠይቁም የሳቸውን ከስልጣን መውረድ ይጠብቁ የነበሩት ዶክተር ከስልጣን ከወረድህ በኌላ እዚህ አካባቢ እንድትደርስ ስላልፈለግን ነው ብለው መመለሳቸውንም ለመስማት በቅተናል። ትላንት ካህናትን ያባርሩ የነበሩት አቶ ኃይሉ ዛሬ ተገፍትረው በመባረራቸው ደስተኞች አይደለንም። ሁለት ስህተት አንድ እውነት አይሆንምና። የልብ ልብ ተሰምቷቸው የሚንጎራደዱት ዶክተር በሕይወት ቆይታቸው ሲመኙት የነበረው እራእይ እውነት እየሆነላቸው እየመጣ ለመሆኑ እሳቸውን መጠየቅ ደግሞ አያስፈልግም። እሳቸውም ቢሆኑ ንጉሱ እኔ ነኝ ምን አባታችሁ ትሆናላችሁ ቢሉ እውነት አላቸው። በሳቸው አመራር የቤተክርስቲያኑ አባላት ቁጥር ከሺህ ወደ መቶ ወርዷልና። ነገ አባላት እያነሰ ስለሆነ ቤተክርስቲያኑን ሸጠን መለስተኛ ቤት እንግዛ እንደሚሉ ደግሞ ምንም ጥርጥር የለንም። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዝም በማለታችን ሁላችንም ተጠያቂዎች እንሆናለን። ዛሬ አባል ለመሆን እንኴን የዶክተሩ ፈቃድ ካልተገኘ እንደማይቻል ሕጋቸውን አንብቡት። ሕጉን የቀየርነው የተከሰስንበትን ክስ ለማሸነፍ እንጂ አምነንበት አይደለም የሚሉት ዛሬ ከቦርድ አባልነት የወረዱት ግለሰቦች ነገ በመሃላ ፍርድ ቤት ቀርበው ይመሰክራሉ ብለን እናምናለን። ያ ካልሆነ አሁን 11.2 ማስቀየር አለብን ማለት ግን ለዶክተሩና ለነርሱ ስድብ ስለሚሆንባቸው እንደማይቀበሉት ማወቅ ይኖርብናል።
ከአዲሶቹ ተመራጮች ጀርባ ሆነው ይህንን ሕልም እውነት ለማድረግ የሰሩት የቀድሞው ሊቀመንበር ያሰባሰቧቸው የፖለቲካ ተወካዮች ዛሬ አቶ እዩኤልን አሽቀንጥረው ከዶክተሩ ጫማ ስር መውደቃቸው የሚያስገርም አይደለም። ከዓመት በፊት የቀድሞው ጸሐፊም እንዲሁ አድርገው ነበርና። ዛሬ እጣቸው ምን እንደሆነ ያያቸሁት ነው። የፖለቲካ ተሰባሳቢዎችም ይህ እጣ እንደሚደርስባቸው የሚጠራጠር ካለ የቤተክርስቲያኑን ታሪክ ያልተከታተለ ብቻ ይሆናል።
በዛሬው ሰንበት የስልጣን ክፍፍሉን ያነበቡት አዲሱ ሊቀመንበር። የተቃወማቸውን የሂትለር የወጣት ክንፍ እያሉ ሲወነጅሉ ምን ማለት እንደሆነ እንኴን የገባቸው አይመስሉም እንል ነበርና፡ ዛሬ አንብብ የተባሉትን እየተቸገሩ ማንበባቸውን አይተናል። በንባባቸው የቀድሞው ሊቀመንበር ሃላፊነት አልወስድም በማለታቸው በተራ አባልነት ለማገልገል ወስነዋል ማለታቸው እሳቸውንም ሳይገርማቸው የቀረ አልመሰለንም። ሊቀ መንበሩ ተለምነው መቆ የታቸውን ያውቁ ነበርና።
ባዲሱ ድልድል የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ ዋሽቼ አስታርቃለሁ ካላሉ በስተቀር እውነቱ ለሳቸውም እንደሚያንገፈግፋቸው አንጠራጠርም። የእቃ ግዥ ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች ገንዘብ ጠፋ በማለታቸው ከተቆጣጣሪነት ተነስተው ወደ ማድቤት መሸኘታቸው እሳቸውንም ገንዘብ አጠፉ ብሎ ለመወንጀል እንዲያመች ስለሚመስል ይጠንቀቁ እንላለን በተጨማሪም የማድቤትና የቤተክርስቲያኑ ቁልፍ ተሸካሚ ከሆኑት ከሊቀመንበሩ ባለቤት ጋር ካልተስማሙ ሊያስወጧቸው እንደሚችሉ ካሁኑ ማወቅ አለባቸው። በሂሳብ ትምህርት ተመረቅሁ የሚሉን የታክሲ ሹፌር ስራ ባለመናቃቸው እያመሰገንን ለምን የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ላይ ሙጭጭ እንዳሉ ግን ሊገባን አልቻለም። ያውም ገንዘብ ጠፋ የተባለው ደመና ሳይገልጥ። አቶ ሙሉዓለምም ሆኑ ነርሱ ከዶክተሩ ትእዛዝ ውጭ የሆነ የራሳቸው ሃሳብም ሆነ ምኞት ስለሌላቸው ተሾሙም ተመረጡም ለውጥ ያመጣሉ ብለን አናምንም። የቤተክርስቲያኑን ማፍረስ ከማፋጠን በስተቀር። አቶ አበበ ጤፉ በመመረጣቸው ምንም ለውጥ ያመጣል ብለን አንጠብቅም የፖለቲካ ትእዛዝ ከማስፈጸም ውጭ። "ተወሰደ" ያሉትን ድንበር ሳያስመልሱ የጠፋ ገንዘብ ያስመልሳሉ ብለን አናምንም። በሳቸው መመረጥ የሚኩራሩት በፓልቶክ እንደ ንጉሥ ያመልኩባቸው የነበሩ ብቻ ይሆናሉ። በተጨማሪ ካሁን በኋላ የሂሩትም ሆነ የማሩ እንጀራ ቤተክርስቲያን ድርሽ እንደማይል መተንበይ አያስቸግርም።