"የጠመጠመ ሁሉ ቄስ አይደለም የጠመደ ሁሉ ጎበዝ አራሽ አይደለም " ይሉ ነበር ያገራችን ሽማግሌዎች። ነገሮችን በምሳሌ ሲያስተምሩ ነው። እኛ ያለንበት ዳላስ ደግሞ የቦርድ አባል ሆኖ መመረጥ የመንፈሳዊ ስልጣን እየመሰላቸው "ቄሱ ምን ያውቃል እኛ እንነዳዋለን እንቢ ካለ እናባርረዋለን" ማለት ከጀመሩ ሰነበተ። ይባስ ብለው ሰባኪ መራጮች የትምህርቱን አይነት ወሳኞች መሆን ከጀመሩ ውለው አደሩ። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂዎች ደግሞ ተመራጮቹ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዳንዳችን ነንና እንደ ደረጃው የሃላፊነት ድርሻ መቀበል ይኖርብናል። በቅዱስ ሚካኤል እየነደደ ያለው እሳት መጥፋት ባለመቻሉ ከ ሺህ በላይ የነበረውን አባል ከሁለት መቶ በታች እንዲወርድ አደረገው:: ጭቅጭቅ በመፍራት ዛሬ ኪዳን አድርሶ ከቅዳሴ በፊት ወደቤቱ የሚመለሰው ምእመን ቁጥር እየጨመረ ነው:: "አንድ በሁኔታው የተበሳጨ የቤተክርስቲያኑ አባል "ጸሎት ስፈልግ ሌላ ቤተክርስቲያን ሄጄ አስቀድሳለሁ ምን እያደረጉ ይሆን ስል ደግሞ ሚካኤል ብቅ እላለሁ" ብሎ የልቡን አጫውቶን ነበር። ታዲያ ምን እስኪሆን እንጠብቃለን ያሉት መንፈሳዊ ትግል ሲጀምሩ እኛ ምን አደረግን? ብሎ መጠየቅ የተገባ ይመስለናል ።
ቤተክርስቲያንችን የእምነት ሳይሆን የፖለቲካ መፋለሚያ ሆኖ ሲሰነብት ስንቶቻችን ነን በቃ ያልን?
በስልጣን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ካልተቃወምክ ክርስቲያን አይደለህም ሲባል ስንቶቻችን ተቃውመን የቆምን?
መንግስትን መቃወም ሌላ እምነት ደግሞ ሌላ ብለን የምናምን ስንቶቻችን ነን?
የተቃወመ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን፡ ዝም ያለ ደግሞ ሃይማኖት የሌለው ባንዳ ሲባል ስለ አቡነ አረጋዊ ተው ያልን ስንቶቻችን ነን?
በፈቃደኝነት ያገለግሉ የነበሩ ወላጆች ከኮሚቴ መባረር አለባቸው ተብሎ ሲባረሩ ተው ያልን ስንቶቻችን ነበርን?
የመንፈሳዊ አባቶች ያስተማሩት ትምህርት በቦርድ ላይ ያነጣጠረ ነው ተብለው ከቤተክርስቲያን ሲባረሩ አቁሙ ያልን ስንቶቻችን ነበርን?
ሕግ እየተጣሰ ሕግ ሲደነገግ አባላት ከቤተክርስቲያን እየተገፉ ሲባረሩ ስንቶቻችን አቁሙ አልን?
እንዴው በሚካኤል አቶ አበበ ጤፉ የትኛው የቤተክርስቲያኑ ኮሚቴ ውስጥ አገልግለው ነው ለመሪነት የደረሱት?
በወላዲቷ አቶ አበራ ፊጣ ናቸው ስለ ሃይማኖት ተቆርቋሪ ሆነው ግብረገብ እኛን ማስተማር ብቻ አይደለም ከፎቅ ላይ በመሆን የአባቶችን ሰበካ የሚቆጣጠሩት?
አቶ ሙሉአለም ናቸው የሩቅና የቅርብ እቅድ አውጥተው ምእመኑን የሚመሩት?
ገንዘብ የለኝም ያሉት ባለ እዳ ዶክተር ናቸው የቤተክርስቲያኑን ገንዘብ የሚጠብቁት?
ይህንንና ሌሎችም የችግሮቹን መንስኤዎች እያነሳን ብንጠይቅ ችግሩ ከራሳችን ላይ ሆኖ እናገኛዋለን ለማለት ነው። "ድሮ እናቴ እንቁላል ስሰርቅ ብታስቆመኝ ኖሮ ዛሬ በሬ ሰርቄ እስር ቤት አልገባም ነበር" ያለውን የድሮ ትምህርታዊ አባባል ያስታውሷል። ዳላስ ደግሞ በመንፈሳዊ ሽማግሌዎች የተራቆተች ከተማ አይደለችም። ሽማግሌዎቹም ጭቅጭቁን በመጥላት ችላ አሉ እንጂ። እኛም ዝም በሉ አልናቸው ካልሆ ም እነሱም ይሉኝታና ፍራቻ አደረባቸው።
ይህ ሁሉ አልፎ አሁን ነገሩ የገባቸው የቤተክርስቲያኑ ተቆርቌሪዎች ለፊታችን ቅዳሜ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ስብሰባ እንደጠሩ ስንሰማ ማንም ይጥራው ማን ይህ ትክክለኛ ጅምር ነው ብለን ሚካኤል ያሰባችሁትን ያሰካላችሁ ብለን ተናግረናል። ሲሆንማ ለፖለቲካ ስብሰባ ይፈቀድ የነበረው የቤተክርስቲያኑ አዳራሽ ውስጥ ነበር ስለቤተክርስቲያኑ ችግር መነጋገር የነበረብን። የተገላቢጦሽ ያልለፉበት ባለንብረቶች የገነቡት የእንጀራ ልጆች ሆኑና ተቸገርን እንጂ።
ስብሰባው ምን ያመጣል ከማለት ይልቅ በስብሰባው ተካፍሎ መፍትሄ መፈለግ ደግሞ የያንዳድዳችን ጥረትና መንፈሳዊ ግዳጅ መሆን ይኖርበታል።
የቦርድ አባላት ይህንን ስብሰባ ለማደናቀፍ በቅዳሜ እለት ሌላ ስብሰባ ከሌሎች ሽማግሌ ተቆርቌሪ አባላት ጋር ለመድረግ መወሰናቸውን ስንሰማ ደካሞች ናቸው ይልቅስ ሰውና ጊዜ ከመሻማት እኛ ብንሆን ኖሮ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ከሆነ እኛም መገኘት ይኖርብናል ብለው ወንድሞችና እህቶች ምን ሆናችሁ በማለት ስብሰባውን እነሱም መሳተፍ ነበረባቸው አልን።
ለማንኛውም መረዋ ስብሰባውን እንደሚካፈል እንደገና ቃል እየገባ የመረዋ አንባብያን የሆናችሁ ሁሉ በዚህ ስብሰባ ላይ እንድትገኙ ያበረታታል።
በዛሬው እለት ከቅዳሴ በኋላ ለአደባባይ የበቁት "ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉአለም" ተጽፎ የተሰጣቸውን ማንበብ ያቃታቸውን አዋጅ ሲያነቡ በጎደለ እየሞላን አዳምጠንላቸዋል።
በንባባቸው አዲስ የገንዘብ ማውጫ የረጅምና ያጭር ጊዜ ፕላን አንብበዋል። የገረመን ገንዘብ እያነሰ ለካህናት ደሞዝ መክፈል አቃተን ያለ አስተዳደር ቦርድ በ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ለማውጣት መነሳቱ ነው። ያውም አባላት ሳያጸድቁት።
በሪፖርተር ላይ ት/ቤት ለሕጻናት እናሰራለን
የመኪና ማቆሚያውን እንጠግናለን
ቤተ ክርስቲያኑን እናሳድሳለን
እንግሊዘኛ የሚናገር መጽሃፍ ቅዱስ አስተማሪ እንቀጥራለን
መንፈሳዊ አባቶችን ሳያማክሩ ሰባክያን እንጋብዛለን የሚል ይገኝበታል።
ወይዘሮ ሰሎሜ የተመኙትን በማግኘታቸው ዘንድሮ እንኴን ደስ ያለዎ ልንላቸው እንወዳለን። "መጽሃፍ ቅዱስ ለማስተማር ኦርቶዶክስ መሆን የለበትም"ይሉ ነበርና ነገ የሚያመጡልንን መምህር እናያለን። ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል ነው ያለችው እብዷ?
ገንዘብ ለማጥፋት ኮንትራት መፍጠር የግድ ነው። ዶክተር እንኴን ደስ ያለዎ እንበል።
የሲኖዶስ ጥያቄ ደግሞ የሚቀጥለው ስብሰባ ላይ እንደሚቀርብ አሁንም ሹክ እንበላችሁ።
ከስብሰባ በኋላ የምንነግራችሁ ይኖረናል እስከዚያው በስብሰባው ላይ እንገናኝ እያልን ይህን ስብሰባ ያስተባበሩትን ከልብ እናመስግን። መፍትሄ በውይይት እንጂ ነገሮችን በመተብተብ ይሆናል ብለን አናምንም። ሚካኤል የኮሩትን ይቅር ይበላቸው ለቤተክርስቲያን መፍረስ ታጥቀው የተነሱትን በተግሳጽ ያብርዳቸው።
እውነትን ይዞ የተነሳ በእምነት የሚጔዝ ሰው ማደሪያ አያጣም።