"መረዋ በተደጋጋሚ ሲናገር የነበረው ሁሉ ለምን ደረሰ? ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ መልሱ ባለፈው እንዳልነው ነብይነት ኖርን ሳይሆን ከነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መጭውን መተንተን ስለቻልን ብቻ ነው። ይህንን ለመተንተን ደግሞ በትምህርትም ሆነ ባመለካከት ከኛ የላቁ ግለሰቦች በቤተክርስቲያናችን ለመኖራቸው አንዳችም ጥርጥር የለንም። ልዩነቱ እነሱ አለመናገርን ሲመርጡ፤ ከሰው ላለመጣላት፤ በይልኙንታ ሲጠመዱ እኛ ግን በእምነታችን፤ በመብታችን አንደራደርም ብለን መነሳታችን ላይ ብቻ ነው። ነገሮች እየፈጠጡ መጥተው ዛሬ ቤተክርስቲያናችን አይወድቁ አወዳደቅ ሊወድቅ መቃረቡን በማየት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ስናይ ይህ ትላንት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ............."ፍየል ልጇን ለመዳር አትነሳም ነበር" ብለን የተናገርነው። ብዙሃኑን በዘዴ ከአባልነት አባረርን የሚሉት የቤተክርስቲያናችን ጉልበተኞች አባላቱ $30 መክፈል አቅቷቸው ሳይሆን ለእምነትና ለማተባቸው በመቆም በማላምንበትና ባላፀደኩት ሕገደንብ አልተዳደርም ማለታቸውን ሊረዱት አይችሉምና። ለምን እምነት ለነሱ ባዳ ስለሆነች። ባይሆንማ ኖሮ አባላትን ማባረር የሚለው ድርጊቱ ቀርቶ ቃሉን ባልተጠቀሙት ነበር። ክርስቲያን ክርስቲያንን ይረዳል ያበረታታል እንጂ አያባርርም ነበርና።
ሰሞኑን በተለያዩ የቤተክርስቲያንችን ተቆርቌሪ አባላት እየተደረገ ያለውን ቤተክርስቲያናችንን የማዳን እንቅስቃሴ መረዋ በድጋሜ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ እያረጋገጠ፤ በተቻለው ሁሉ ለመርዳትና ወደኋላም እንደማይል በመደጋገም ቃል ይገባል። የሰሞኑ እንቅስቃሴ መሪዎች ቆርጠው መነሳታቸውን ስንሰማ የተደሰትነውን ያክል ተመራጭ ነን ባዮቹ የቦርድ አባላት እንቅስቃሴውን ለመግታት ምን ያክል የቤተክርስቲያን ገንዘብ ሊያጠፉ እንደሚነሱ ስናስብ ግን የዛኑ ያክል አዘንን። እናንተም ልታዝኑ ይገባችኋል። ያላዋጡትን ሲያዙበት ያልሰበሰቡትን ሲበትኑት ማየትን የመሰለ ምን የሚያሳዝን ነገር ሊኖር ይችላል? እንደተገለጸው አሸነፍን ብለው ጮቤ የረገጡ ሰርግና ምላሽ የሆነላቸው ግለሰቦች ለተሿሚ ሰከንድም እድሜ ነው ካላሉ በስተቀር የሕዝቡ ድጋፍ እንደሌላቸው እየተረዱት ለመምጣታቸው ከሚወስዱት እርምጃ መገምገም ይቻላል። የከተማችን የሬዲዮ ተናጋሪ የሆኑት አቶ ዘውገ የአባልነት ክፍያ ሊከፍሉ ሲሄዱ አንቀበልህም መባላቸውን ስንሰማ አዘንን። እሳቸውም በሬዲዮ የሚነገረውንና የማይነገረውን ከፖለቲካ አመለካከታቸው አኴያ እያመዛዘኑ እገዳና እቀባ እንደሚያደርጉት ነውና እሰየው ግን አላልንም። እሳቸውም ትክክል አይደሉም፤ ቦርዱም ትክክል አይደለም ብለን እናምናለንና። የቦርዱ አቀንቃኞች ቦርዱ በሰጣቸው የቡድን ገለጻ በመነሳት በያለበት የሚያነሱት የሰሞኑ የውይይት ነጥብ ደግሞ የቤተክርሰቲያን አባላት ክፍያቸውን እያጠናቀቁ ስብሰባ ይጠራና በሲኖዶስና በስደት ሲኖዶስ ምርጫ ተደርጎ አንዱን መከተል አለብን የሚል ሆኖ አግኝተንዋል።
የሚገርመው ነገር አባላት ወደነበሩበት ለመመለስ የሚያቀርቡት ጥያቄ ያልቀየርነው መተዳደሪያ ደንባችን ወደነበረበት ይመለስ ሆኖ ሳለ ጥያቄያቸው ሳይመለስ የቦርድ አባላት ያዘጋጁትን ቅጽ በመፈረም መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቁ ለማጭበርበር መነሳታቸውን አለመግለጻቸው ነው። ያዘጋጁት ቅጽ በተለይ የእንግሊዘኛው ይህንን በመፈረም የቤተክርስቲያኑን ሕግ ሙሉ ለሙሉ መቀበሌን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ ይላልና።
በነሱ ብልጠት የጎደላቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብም ይጠቅመናል ከማለታቸው ባሻገር፤ የተባለው አባል ተመልሶ እንኴን ድምጽ ቢሰጥ እነሱ ካላመኑበት ባዘጋጁት ሕግ መሰረት ቦርዱ የአባላትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመሻር የቦርዱን አባላት ፍላጎት ተፈጻሚ ለማድረግ ማቀዳቸውን ሕዝብ አያውቅም ብለው መናቃቸው ነው። ሕዝቡን ቢንቁ ደግሞ ምንም አይገርምም ሥራ ያላስያዘ ዲግሪ በእዳ የተወጠረ ዶክተር እየመራቸው ነውና።
ትላንትና አባል የሆኑት እኮ ናቸው በሕጉ መሰረት ስብሰባ ለመጥራት የአባላት ፊርማ ቢያሰባስቡ ገደል ግቡ የተባሉት፤ የዲግሪ አቻቸው በግለሰብ ሲፈርሙና ስብሰባ ይጠራ ሲሉ ግን ስብሰባ የተጠራው።
ትላንትና አባል የሆኑ እኮ ናቸው ከፈረማቸሁ አትናገሩም የተባሉት።
ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው ስነስርአት በማለታቸው በፖሊስ ተገፍትረው የተባረሩት።
ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው መሃበርቅዱሳን መባረር አለባችው ብሎ ቦርዱ ሐሙስ እለት ወስኖ ክስ በመመስረቱ ቅዳሜ ተሰብስበው ውሳኔአቸውን በግዳጅ የቀለበሱት::
ትላንትና አባል ሆነው እኮ ነው ከሳሾችን አናውቃቸውም ያለዛሬ አይተናቸውም አናውቅ ብለው በመሃላ በፍርድ ቤት የተናገሩት።
ይህ ሁሉ ውሳኔ ሲወሰን በትክክልነቱ ይከራከሩና አስፈጻሚም የነበሩት የቀድሞው ሊቀመንበርና ከስልጣን የወረዱት አባላትም ዛሬ ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ቤተክርስቲያኑ ወደ ጥፋት እየተገፋ መሆኑን መናገራቸውን ስንሰማ ሚካኤል ልቦናቸውን ከፈተላቸው አልን እንጂ ትላንት የአባላትን መብት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መዳፈራቸውን ግን አልረሳንም። ትላንት ዶክተሮቹና ደጋፊዎቻቸው "መልአክ" ብዙሃን አባላት ግን "ሰይጣን" ናቸው ብለው ያምኑ ነበር ቢረሱት አልረሳነውም።
ለዚህም ነው በሚካኤል ሲባል ስላልሰሙ በሕግ አምላክ ማለት ያስፈለገው።
ዛሬ አባላት ምንም አይነት ውሳኔ ቢወስኑ ቦርዱ ካላመነበት መሻር ይችላል። በዚህ የአምባገነን ሕግ ሊያስተዳድሩን ስልጣን ላይ የወጡት አቶ አበበ ጤፉ አገርቤት ያለው መንግስት ሕግ የማይገዛው አንባገነን ድንበር የሚያስማማ ሌባ የሕዝብን ድምጽ የማይሰማ ፈላጭ ቆራጭ እንዲሆን የሚረዳው ሕገ መንግስት ደንግጎ በሕዝብ ላይ ያላግጣልና መገርሰስ አለበት የሚሉን። "ወደሰማይ የተወረወረ ድንጋይ መልሶ የሚመታው ወርዋሪውን ነው"። ይሏል ይህ ነው። ቤተክርስቲያናችን ከአንባገነኖች ብቻ አይደለም የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የሚታገሉ ግለሰቦች ወደ ጎን ተብለው አማንያን እስካልተረከቡት ድረስ ፍጭቱ ይቀጥላል።
በቅርቡ ሊጠራ ታስቧል የተባለው ስብሰባ ውጤት እንዲያገኝ ከተፈለገ፦
1 ሕጉ ወደነበረበት መመለስ አለበት
2 አባላት ያለምንም ጥያቄ መክፈል የሚችሉትን እየከፈሉ መመዝገብ አለባቸው።
3 የቦርድ አባላት ነን ባይ አንባገነኖች ሕዝቡ ለመረጣቸው ጊዜአዊ ኮሚቴ አስርክበው መውረድ አለባቸው።
4 የሚደረገው ስብሰባ በገለልተኛ ምእመናን መመራት ይኖ ርበታል ብለን እናምናለን።
ስብሰባው የተቃና እንዲሆን የክርስቶስ ፈቃድ ይታከልበት።