ከትላንትና ወደ ዛሬ በዳኛው ጥያቄ የተዛወረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ በዛሬው እለት ከሳሾችና ደጋፊዎቻቸው፤ ሰዎስት የቦርዱ "ሹማምንት" በተገኙበት ሲሰማ ውሏል። በወቅቱ "ከሳሾቹ አባላት ባለመሆናቸው ብሎም ከዚህ በፊት በዚህ ፍርድ ቤት በከሳሽነት ቀርበው የተበየነባቸው በመሆኑ ክሱ ተደጋጋሚ ነውና ዛሬውኑ ተሰርዞ በነጻ አሰናብተን" ብለው ጉዳዩን ወደ ዳኛው ያመጡት የቦርዱ ጠበቆች ሲከራከሩ ስናይ ባለፈው እንደ ሰማነው እንጂ የተቀየረ ነገር እንዳልነበረበት ለመታዘብ ችለናል። ከዚህ በፊት የነበረውን ክስ እንደማያውቁ የተናገሩት የከሳሾች ጠበቃ ዳኛው ከዚህ በፊት የወሰኑትና ይህ እሳቸው የመሰረቱት ክስ እንደማይመሳሰል ለዳኛው አስረድተዋል። በመሆኑም ዳኛው ባለፈው የወሰኑት ቦርዱ መተዳደሪያ ደንቡን መቀየር ይችላል አይችልም በሚል ላይ መሆኑን የጠቆሙት የከሳሾች ጠበቃ አንድም ቦታ መተዳደሪያ ደንቡ ትክክል ነው ብለው ዳኛው እንዳልወሰኑ በተለይም የቦርዱ ምርጫ ሕገወጥ መሆኑን አስመልክቶ ምንም የተናገሩት እንደሌለ ጠቁመው የሳቸው ክርክር መሰረቱ የቦርድ አባላት ከሕግ ውጭ የተመረጡ በመሆኑ ይህንን በማስረጃ አስመርኩዤ ለመከራከር የሚከለክለኝ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም ብለዋል። ዳኛው በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠቴን የሚያሳይ መረጃ አላችሁ ወይ? ብለው የተከሳሾችን ጠበቆች ቢጠይቁም የቦርዱ ጠበቆች ሊያቀርቡ የቻሉት ባለፈው ክስ ላይ የድሮው ጠበቃ የተናገሩት ንግግር ብቻ ነበር። የቦርዱ ጠበቆች ያቀረቡትን ያለፈ የጠበቃ የመከራከሪያ ነጥብ ንግግር ዳኛው አንብበው ይህንን ሳይሆን እኔ የወሰንኩበትን ነው የምለው በማለት በድጋሜ ጠይቀው የተከሳሾች ጠበቆች ሊያቀርቡ አልቻሉም።
አባላት አይደሉም ለሚለው የከሳሽ ጠበቃ የቦርዱ አባላት ባወጡት የመተዳደሪያው ደንብ መሰረት የከሰሰ አባል መሆን አይችልም የሚል አንቀጽ እንዳለበት ሲናገሩ፤ ዳኛው እውነትክን ነው እሱን ነገር እኔም አስታውሳለሁ በማለት ሲስቁ ተመልክተናል።
በተጨማሪም በሚመጣው 12/20/10 በቦርድ አባላት የይግባኝ ጥያቄ መሰረት በዚሁ ፍርድ ቤት ተቀጥሮ የነበረው ቀነ ቀጠሮ አስመልክቶ ወደ እረፍት በዚያን ወቅት እንደሚሄዱ ጠቅሰው እንዲቀየርላቸው የከሳሾች ጠበቃ የጠየቁትን ዳኛው በመቀበል ወደሚመጣው ወር ማለትም 1/20/11 ሲቀይሩት በ1/10/11 የነበረውም ቀጠሮ እንዲሁ እንዲራዘም ዳኛው ተስማምተዋል። ይህም የሆነው የቦርድ አባላት የተጠየቁትን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል ብለው ዳኛው እረዳት ዳኛቸው የበየኑትን ብይን ቢያጸኑት ካጸኑት በኋላ ቢያንስ 30ቀን እንደሚያስፈልጋቸው የከሳሾቹ ጠበቃ በመጠየቃቸው ነበር።
በወቅቱ ቦርዱን በመወከል ዶክተር ግርማ አቶ ዮሴፍ ከናባለቤታቸው አቶ አበበ ሲገኙ በታዛቢነት ደግሞ የአቶ አበራ ፊጣ ባለቤትና ወይዘሮ አባይነሽ አብረዋቸው እንደነበሩ አስተውለናል። ከከሳሾቹ ወገን ከሳሾቹ በሙሉ የተገኙ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው ባንድ በኩል ተቀምጠው አስተውለናል። ከቦርድ ባለፈው ጊዜአቸውን ጨርሰው የወረዱ ግለሰብ ሳይቀር ሁኔታውን ለማዳመጥ መጥተው እንደነበርም ልንነግራችሁ እንወዳለን።
በመጨረሻም የተከበሩት ዳኛ ለሁሉም መልካም ገና በመመኘት ውሳኔአቸውን በሚመጣው ሳምንት እንደሚያስታውቁ ተናግረው የችሎቱ ፍጻሜ ሆኗል። በስፍራው የተገኙት የመብት ትግሉ ደጋፊዎች ዳኛው ምንም አይነት ውሳኔ ይስጡ ትግሉ እንደማይቆም ቃል ሲገባቡ ለመመልከትም እድል ገጥሞናል።
መረዋ የፍርድ ቤቱ ብይን እንደደረሰው ብይኑን ለአንባብያን እንደሚያቀርብ ካሁኑ ቃል እየገባ በሚመጣው 12/19/10 በድሪምስ አዳራሽ በ1:00 PM ሁላችሁም እንድትገኙ ጥሪውን እንድናሰማ በመጠየቃችን ሁላችሁም ከቅዳሴ መልስ ወደዚያ እንድታመሩ ልናሳስባችሁ እንወዳለን።
እውነት ምን ጊዜም ያሸንፋል
ቸር ወሬ ያሰማን።